አሁንም እያስጨነቀ ነው። ለሰው ልጅ መቅሰፍት መሆኑን ተያይዞታል። ህዝብም የምድርን ሁሉ እየሞከረ ተማፅኖውን ወደ ላይኛው ካስተላለፈ ሰንብቷል። በኮሮና ምክንያት ጊዜው ለሁሉም እኩል ከፍቷል። ያላስጨነቀው፣ “እንዴት ታረገኝ ይሆን?” የማይል፣ ላለመቀደም የማይታትር የለም።
ሁሉም እኩል እየተፍጨረጨረና ከኮሮና ጋር ግብ ግብ እንደተያያዘ ነው። ጥንቃቄው ከፀጉር የቀጠነ ቢሆንም ሁሉም የሚችለውን ከማድረግ አልቦዘነም (መዘናጋቱ እንዳለ ሆኖ)። በተለይ የመከላከሉ ጥንቃቄ ከከፍተኛ የአካል ክፍሎች (እጅ፣ አፍ፣ አይን፣ አፍንጫ፣ ባጠቃላይ ፊት) ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለጥንቃቄ እየተደረገ ያለውን ተግባር እጅጉን በጭንቀት የተሞላ አድርጎታል።
ከነባሩና እድሜ ጠገቡ የማህበራዊ ኑሮ ዘይቤና መስተጋብር አኳያም ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥንቃቄና የእየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተፈለገው ፍጥነትና ደረጃ እንዳይሄድ አድርጎታል። በተለይ አካላዊ ፈቀቅታ የሚለውን የጥንቃቄ እርምጃ ተግባራዊ ለማድረግ አጠቃላይ ህዝቡ በሚባል ደረጃ ሲቸገር እየታየ ሲሆን፤ በሚመለከታቸው በኩልም የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሰዉ ቢያንስ ሁለት ሜትር ተራርቆ እንዲሄድ እየወተወቱና ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ውጤቱ ተያይዞ ማለቅ መሆኑን እየተናገሩ ይገኛሉ።
እርግጥ ነው ይህ አካላዊ ፈቀቅታ የተባለውን የጥንቃቄና መከላከል እርምጃ በተነገረበት ፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ሊከብድ ቢችል የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም ከእኛ ዘመናትን ከተሻገረ ማህበረ-ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤ አንፃር ሲታይ ይህ ተራርቆ የመኖር ዘይቤ በፍፁም የሚዋጥ፤ ከቶም የሚታሰብ አይደለም። አብሮ ሲበላና ሲጠጣ ለኖረ፣ አብሮ ሲደሰት (ሰርግ) እና አብሮ ሲያዝን (ሀዘን) ለኖረ፣ ወገብ ለወገብ ተቃቅፎ፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ ካልሄደ ለማይሆንለት ማህበረሰብ፤ ማህበር ሲደግስና ሲያበላ (እራሱም ሲታደም) ለኖረ ማህበረሰብ፣ በደቦና ጂጊ ለሚሰራ ማህበረሰብ፤ በዚህ ላይ ድህነት ሳይወድ በግድ ተፋፍጎ፣ ተጠጋግቶ፣ ተጨናንቆ እንዲኖር ለፈረደበት ማህበረሰብ አካላዊ ፈቀቅታ ባንድ ጀምበር ስራ ላይ ይውላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ቢመስልም ጉዳዩ የመኖርና ያለመኖር፤ ትውልድ የማቆምና የማስቀጠል፤ ባጠቃላይ የአገርና ህዝብ ህልውና ጉዳይ ነውና ተግባራዊ መደረግ ያለበት መሆኑ ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬም ሆነ ማመንታት ሳይኖርበት ተግባራዊ ሊደረግ የግድ ነው። በአሁኑ ሰአት የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሚዲያው እና ሌሎችም ሳይታክቱ እየወተወቱ ያሉት ይህንኑ ነው። ቫይረሱ በአገራችን እንዳይስፋፋና በሌላው ዓለም በቀን ሺዎችን እየቀጠፈ ያለው አይነት ሁኔታ በአሀገራችንም እንዳይከሰት ለማድረግ ቁልፍ ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች መካከል የእጅ ንፅህናን መጠበቅና ከመነካካት/ንክኪ መራቅ በመሆናቸው አጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ እንደሚገባን ነው እየተወተወተ ያለው።
በመሆኑም ይህንን ወሳኝ ምክርና አስተያየት ተቀብለው የሚያደርጉ የመኖራቸውን ያህል ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ መኖራቸውንም ከሚነገረውና ከምንሰማው ባለፈ የምናየው ጉዳይ ነውና እኛም ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንዳሉት “እኛ ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን ባጠቃላይ አብረን የምንበላ አብረን … ለጊዜው ይህ ችግር እስኪያልፍ እባካችሁ ተራርቀን እንንቀሳቀስ …” እንላለን። በተለይ ከባለፈው እሁድ እለት ጀምሮ ማለትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሞት ከተከሰተ ወዲህ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ያሉ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል ከነበረው የጥንቃቄ እርምጃ አወሳሰዱ ሁኔታ እየተለወጠ መጥቷል።
ባለሙያዎች እንደሚመክሩት እየተወሰደ ያለው ጥንቃቄ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ምንም አይነት መረበሽ ሊኖር የሚገባ አለመሆኑን ነው። በመንግስት በኩልም ህዝቡ ተረጋጋግቶ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች የሚሰጡ መረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው፤ መንግስትም ሁኔታዎች የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ለመግታት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ እየተናገረ ይገኛል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ህዝቡ በተለይ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተለቀቁ ካሉ የሀሰት መረጃዎችም እራሱን መጠበቅ፣ መጠንቀቅ፣ ሳያጣራ ወደ ውሳኔ መሄድ እንደሌለበትም እየተነገረ ነው። ኮሮና እዚህ ድረስ የሰውን ልጅ እያስጨነቀ ቢገኝም አሁንም፣ እስከ እዚህች ደቂቃ ድረስ ከመጠንቀቅና መከላከል ያለፈ ምንም አይነት መፍትሄ አልተገኘለትምና ከአሳሳቢና አስጊነት ደረጃው አልወረደም። እስካሁን የቃኘነው የአገራችንን አጠቃላይ ሁኔታ ሲሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታውም ያውና የባሰ ነው። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በአንፃራዊነት ኢትዮጵያም ሆነች አጠቃላይ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሆነዋል ማለት አይቻልም፤ የመንግስታት ጥረት ይሁን ወይም ብዙዎች እንደሚሉት ፈጣሪ ከልሏት እስካሁን ድረስ የሟቾች ቁጥር ቢደመር የአውሮፓ አገራትን የሩብ ቀን የሟቾች ቁጥርን አይደርስም። ይህ በዚሁ እንዲቆም የሁሉም ሃይማኖት አባቶች የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከባለፈው ሰኞ ማታ ሶስት ሰአት ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የፀሎት ሥነ-ስርዓት ተጀምሯል።
ሥነሥርዓቱም በተመረጡ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ ሲሆን ምእመናንም በየቤታቸው ሆነው የፆምና ፀሎቱ ሥነሥርዓት አካል ሆነው በመከታተል ላይ ናቸው። በፕሮግራሙ መክፈቻ እለት የሁሉም ሃይማኖት መሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ሁላችንም በንፁህ አእምሯችንና ልቦናችን ከፀለይን እግዚአብሄር እንደሚምረን፤ በመሆኑም ሁላችንም በየቤታችን ሆነና ርቀታችንን ጠብቀን ይህንን እንድናከናውን አሳስበዋል፤ ያለው ምርጫም ይሄው ነው።
እስካሁን ባሉት ኮሮና ወለድ የእልቂት ወራት ቫይረሱ (“Novel Coronavirus” ነው የተባለው) ከጥቂት ደሴት አገራትና በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ካለችው የመን በስተቀር የዓለም አገራትን በሙሉ አዳርሷል ማለት ይቻላል። በዚሁ መሰረትም በየአገራቱ በርካታ እልቂትንና በቫይረሱ መጠቃትን አስከትሏል። በቀዳሚነት ቫይረሱ የተከሰተባት ቻይና (ዉሃን ግዛት) (አሁን ተቆጣጥራው ከሌሎች አገራት ወደሷ እንዳይመጣባት እየተከላከለች ነው) እንደ ነበር ይታወሳል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ኮሮና ጥቃቱን አሜሪካን፣ ስፔንና ጣሊያንን እንደየቅደም ተከተላቸው በከፍተኛ ደረጃ እያጠቃ ይገኛል። ኮሮና ካስከተላቸው በርካታ አሳዛኝና አስተካዥ ነገሮች መካከል ስፔኖች ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት መልስ ነው። ባለፈው ሰኞ ጋዜጠኛው “ዛሬ እንዴት ነው?” ሲል ላቀረበው ጥያቄ የብዙዎች መልስ “ዛሬ በጣም ደስ ብሎናል። ጥሩ ነው፤ የሟቾች ቁጥር ወደ 660 አካባቢ ወርዷል።
ከሌሎቹ ቀናት አንፃር ሲታይ የዛሬ ሟቾች ቁጥር ቀንሷል።” ሲሉ የሰጡት ምላሽ የብዙዎችን አንጀት እንደሚያላውስ ይገመታልና ኮሮና የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል እያረገፈ ይገኛል ለሚለው ሌላ መረጃ ማምጣት አስፈላጊ አይደለም። በመሆኑም እምነትን በልብ ይዞ ማድረግ የሚገባን የጥንቃቄና መከላከል ተግባራትን መፈፀም ይገባል እንላለን። ኋላ “ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፣ እያወቁ ማለቅ መጣ በሰአቱ።” እንዳይሆን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ግርማ መንግሥቴ
የኮሮና ክራሞት