ዓለም አንድ መንደር ሆናለች መባል ከጀመረ ሰነባብቷል:: የዓለም አንድ መሆን ለዘመናት የሚታወቀው ደግሞ በቴክኖሎጂ ትስስር ነበር:: የአሁኑ ትስስሮሽ ግን በችግር መሆኑ ግርምትንም ስጋትንም ፈጥሯል:: በኮሮና ወረርሽኝ ዓለም በአንድ በሽታ መገረፍ ይዛለች:: ይህ ደግሞ በሌላ በኩል የግሎባላይዜሽን ውጤት ነው:: ምክንያም በሽታው ከአንዱ አህጉር ወደሌላው አህጉር ለመሸጋገር ጥቂት ሰዓታት ብቻ በቂ እንዲሆኑ ያደረገው ቴክሎጂ ነውና::
ይህንን የበሽታ ግሎባላይዜሽን ከቀደመው ለየት የሚያደርገው ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ የበለፀጉና ያላደጉ በሚል ልዩነት የሚፈጥር አለመሆኑ ነው:: ሐብታም ደሃ፣ታላቅ ታናሽ፣ ስልጡን ኋላቀር፣ አማኝ ከሐዲ የሚባል ነገር ተረስቷል:: ከዚህ ማቅ እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል የሚሉ ተስፈኞችም የዓለምን ሕዝብ ያጽናኑት ይዘዋል:: በእርግጥ መከራና ክፉ ጊዜ አይለመድ ሆኖ እንጂ የዓለም ሕዝብ በወረርሽኝ ፍዳውን የከፈለባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ:: ስፓኒሽ ፍሉ ፣ ኩፍኝ፣ ፈንጣጣና ሌሎችም እየተፈራረቁ ዓለምን አጥቅተዋል፤ ዛሬም ተረኛው ዓለምን ማተራመሱን ተያይዞታል::
የዓለም አገራት ጥረት ምን ይመስላል?
አገራት እንደየጥረቶቻቸው ዋጋቸውን እያገኙ ነው:: ቻይና የኮሮናን ቫይረስ ዜና ለዓለም በይፋ ስታውጅ፣ መርጠሸ አትበይም ነበር ቻይው! ለማለት የዳዳቸው አገራት ነበሩ:: ኧረ የቻይና ቫይረስ በሽታ እስከማለትም መድረሳቸውን የዓለም ሚዲያዎች ተቀባብለውት ነበር:: ‹‹በአፍ በለፈለፉ….›› እንዳለው ያገሬ ሰው፤ ዛሬ ላይ ግን እነዚያ አገራት የወረርሽኙ ብርቱ ዶፍ ከሚወርድባቸው አገራት በመሪነት ይገኛሉ::
የ57 ዓመቷ ዊጉዣን ጉንፋን መሰል ሕመም ተሰም ቷቸዋል:: የአሳ ምርቶች ከሚሸጡባት የቻይናዋ ሁዋናን ገበያ አቅራቢያ ወደሚገኝ ክሊኒክ ደጋግመው በመሄድ ማስታገሻ ይወስዳሉ:: ነገርየው የዋዛ አልሆን ቢላቸው ወደ ትልቅ ሆስፒታል ሂደው ቁርጣቸውን ያውቃሉ::
‹‹ዎል ስትሪት›› የተሰኘው ጆርናልም ከመጀመ ሪያዎቹ ሃያ ሰባት ቻይናውያን የኮሮና ተጠቂዎች መካከል አስፍሯቸዋል:: የቻይናው መንግስት የዢንፒንግ ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ከዚህ ይጀምራል:: ወረርሽኝ መቀስቀሱን ተገንዝበው የተለያዩ እርምጃዎች ወስደዋል:: ጅምላ ምርመራ፣ ለይቶ ማቆየት፣ ንክኪን ማስቀረት፣ ቤት መቀመጥ ከወሰዷቸው ፈጣን ርምጃዎች ይጠቀሳሉ:: በዚህ የተነሳም ምዕራባውያን ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ ሲሉም ወርፈዋቸው ነበር:: ይሁን እንጂ እርምጃዎቹ የወረርሽኙን የስርጭትና የሞት መጠንን በእጅጉ መቀነስ አስችለዋል::
እንደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይና ስፔን ያሉ አገራት ወረርሽኙን ከቁብ አልቆጠሩትም ነበር:: አሜሪካም ሁኔታውን በዓይነቁራኛ እየተከታተለች ማፌዟን ቀጠለች:: ሆኖም ወረርሽኙ ባላሰቡት ፍጥነት የሁሉንም አገራት በሮች በርግዶ ምስቅልቅላቸውን አሳያቸው:: የሃያላኑ አገራት መሪዎች የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፋቸው:: ዜጎቻቸውም ቀባሪ እስኪቸግር ድረስ ተረፈረፉ፤ ሁኔታው አሁን ድረስ ቀጥሏል:: ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዓለም ላይ 212 ግዛቶች ተዳርሰዋል:: ከአንድ ሚሊዮን 418ሺ በላይ ዜጎች በወረርሽኙ ተይዘዋል:: በታማሚዎች ብዛት አሜሪካን የሚስተካከል የለም፤ ከ390 ሺ በላይ ዜጎች ኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ ከ15 ሺ በላይ ዜጎች ይችን ዓለም ተሰናብተዋል::
ጣሊያንን ከ17 ሺ ፣ ስፔን ከ 13 ሺ እና ፈረንሳይ ከ10 ሺ በላይ ዜጎቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል:: ዶናልድ ትራምፕም ሳይንቲስቶቻቸውን መላ ውለዱ ሲሉ ቢወተውቱም ከአፋቸው ለትችት እንደሚወጣው ቃል ቀላል አልሆነላቸውም::
እየዋሉ ሲያድሩ ያጣጣሉትንና የናቁትን የሺ ዢፒንግን መላ እየቃረሙ መተግበራቸውን ተያያዙት፤ ነገሩ ‹‹ጅብ ከሄደ ጮኸ›› አይነት የሆነ ይመስል ወረርሽኙን መቆጣጠር ተስኗቸዋል:: የዓለም የጤና ድርጅት እግር በእግር እየተከታተለ ወረርሽኙን እንደቀላል አትዩት ሲል ወትውቷል:: ዘር፣ ቀለም፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ሃያልነት፣ ወዘተ፤ሊመክተው የሚችል እንዳልሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት አድርጎ ነበር:: ጆሮ የሰጡት አገራት ግን ብዙም አልነበሩም::
ከረፈደ ሆነ ሩጫቸው:: በአንጻሩ ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ የኮቪድ ወረርሽኙን መቆጣጠር ያስቻላትን ርምጃ ለተሳለቁባት ጭምር ማስተማሯን ቀጠለች:: በብርሃን ፍጥነት በሚመስል ሩጫ ግዙፍ ሆስፒታሎች ሺ ከሚጠጉ አልጋዎች ጋር ገንብታ ለታማሚዎቿ አደረሰች፤ የፊት ማስኮች፣ የእጅ ጓንቶች፣ የባለሙያ አልባሳት፣ የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎች የአገሪቱ ፋብሪካዎች በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሳያባክኑ አስፈላጊ ግብዓቶችን ያመርታሉ::
የሕክምና ባለሙያዎቿ ማስክ ያጠለቀው ፊታቸው እስኪበልዝ ቀን ከሌት ለወገናቸው ተዋደቁ፤ እስከ ሕይወታቸውም ገበሩ:: ዜጎች የሐኪሞቻቸውንና የመሪዎቻቸውን ምክር ለመተግበር የሚቀድማቸው አልነበረም:: በዚህ ርብርብም ኮቪድ 19 ቫይረስ ላይ ቻይና ድል ተቀዳጀች፤ መቆጣጠር ቻለች:: ስቃዩ ለበረታባቸው አገራትም አሜሪካን ጨምሮ ከባለሙያዎቿ እስከ ገንዘቧ ድረስ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች::
ኢትዮጵያ ምን ልምድ ቀሰመች?
ሃያላኑን እያሽመደመደ ዓለምን ያዳረሰው ኮሮና ቫይረስ እልባት አልተገኘለትም:: መንፈቅ የሚጠጋ እድ ሜም እያስቆጠረ ነው:: ወረርሽኙ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ አቅም ጠንካራ በሆኑት ሃያላን አገራት በኩል የጀመረ በመሆኑ ሌሎቹ ልምድ የሚቀስሙበት እድል እንዲያገኙ የሚያስችላቸው እንደሆነ ባለሙያዎችና ሚዲያዎች በሰፊው ይተነትናሉ:: ርግጥ ነው ብልህ አገራት ሊጠቀሙበት ይችላሉ::
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲው የሕክምና ትምህርት ክፍል የውስጥ ዴዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ክንዴ ውብሸት “ወረርሽኙን በሕክምና መከላከል እንደማይቻል ከአው ሮፓውያን ልምድ ተገኝቷል:: ራስን በመቆጣጠር፣ በመግዛትና በስነምግባር ወረርሽኙን በጥንቃቄ ማለፍን ደግሞ ከኤሽያ አገራት ተምረናል” ሲሉ ያስረዳሉ:: ከበሽታው ብቸኛ የመዳኛ መንገድ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አለመነካካትና በቤት መቀመጥ እንዲሁም ንጽህናን መጠበቅ እንደሆነ ልምድ እንደተገኘበትበሚዲያዎች በኩል ገልጸዋል:: በተገቢውና ሐላፊነት በታከለበት መንገድ ዜጎች የሚመከሩትን ሊተገብሩ ይገባልም ነው ያሉት::
አገራዊ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት ምን ተሰራ?
የወረርሽኙን ኢትዮጵያ መግባት ተከትሎ በየአቅ ጣጫው ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የአንድነት መንፈስ ዜጎች እንዲኖራቸው መንግስት ጥሪ ማቅረቡ የሚያስመሰግን ቀዳሚ ተግባር ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ‹‹ይህ ጊዜ ያልፋል:: ሁላችሁም የብሔራዊ ኮሮና ዘማቾች ወታደሮች ናችሁ:: ይሄን ዘመቻ በድል ከተወጣን ለታሪክ የሚተርፍ ድንቅ ስራ እንደሰራን ይቆጠራል:: ለትውልድም በኩራት የሚማርበት ታሪክ አስቀምጠን ማለፍ እንችላለን፤ ሁላችንም አላፊዎች መሆናችንን ተገንዝበን የማያልፍ ታሪክ በጋራ ልንሰራ ይገባል›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል:: በዚህ መሰረትም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስና ብሎም የከፋ ችግር እንዳያደርስ ለማድረግ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ዜጎች ያላቸውን በማበርከት ለወገናቸው አለኝታነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ:: ብሔራዊ የኮሮና ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከኖች ድረስ ንኡሳን ኮሚቴዎች እያስተባበሩ ይገኛሉ::
የታሪካዊ አጋጣሚው አካል ለመሆን ከነጋዴ እስከ መደዴ፣ ከወዛደር እስከ ወታደር፣ ከመሪ እስከ ተመሪ፣ ከኢንቨስተር እስከ ሰርቶ አደር፣ ከከተማ እስከ ገጠር ኢትዮጵያውያን ተነቃንቀዋል:: በአጠቃላይ በአጭር ጊዜም በአይነትና በገንዘብ ከፍተኛ ገቢ መገኘት ጀምሯል:: ከሆቴሎቻቸው እስከ ኪራይ ገቢያቸው፣ ከጥሬ ገንዘባቸው እስከ ጉልበታቸው፣ ከፋብሪካ ምርቶች እስከ መመርመሪያ መሳሪያዎች ድረስ በወረርሽኙ ለሚጠቁ ወገኖችና ለአቅመ ደካማ ዜጎች ድጋፍ እየተሰባሰበ ይገኛል:: የዜጎችም ጥረት ይለምልም፤ ሃያላኑን ሃይል አልባ ያደረገውና ታዳጊዎችን ያስደገደገው ክፉ የኮሮና ደዌም ይክሰም::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ሙሐመድ ሁሴን