ዓለምን የሚያምሰው የኮሮና ቫይረስ በአገራችን እነሱ ጋር የማይደርስ የሚመስላቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይምሰላችሁ። በእሳት የሚቀልዱ ሰዎች ቁጥራቸው በዝቷል። ኧረ ንግድም፣ ፖለቲካም አድርገው አቦኩት እንጂ። ከሰሞኑ አንጀቴን ያራሰኝን አንድ ወሬ ልንገራችሁ።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰባሰቡት (ግሩፕ) የሚፈጥሩትና የሚሆኑት ተመሳሳይ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የሆኑ ናቸው ብዬ ባላስብም በዓላማ የሚቀራረቡ፣ ለተመሳሳይ ተልዕኮ በጋራ የሚሰሩ እና ሕብረተሰባቸውን የሚጠቅሙ ናቸው ብዬ አስብ ነበር። ነገር ግን አብረው የበሰበሱ፤ ለመበስበስ ሲሉም የሚሰበሰቡ አሉ እንድል ተገድጃለሁ። እስኪ አሁን አብሮ ለመዝቀጥ ማህበር መመስረትን ምን ይሉታል? እናም ከእነዚህ ስብስቦች ‹‹ሰዕላይ በራሂ›› በሚል መጠሪያ በፌስቡክ ሰፈር የሚፈነጨው ቡድን (ጥርቅም ልበለው ይሆን?) በሥሩ ለሚጋቱ የስብስቡ አባላት ያቀረበው ቁም ነገር እንዲህ ይል ነበር፤ ‹‹ለዚህ ግሩፕ አባላት የቀረበ ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የቅማንትንና የአገውን ማንነት ሰርቆ የራሱ በማድረግ የተቋቋመ ብሄር ማን ነው?›› በማለት በክብር ይጠይቃል። አባላቱም የባጥ የቆጡን እንደልባቸው ከስር ከስር ይዘላብዳሉ። አንዱ አልፎ ሂያጂ የእንኩቶው ስብስብ አሳዘነው መሰለኝ አንገቱን ብቅ አድርጎ ምን አላቸው መሰላችሁ ‹‹ትኩረታችን ዘር ላይ ሳይሆን ዘርዘር ብሎ መቆም ላይ ነው›› ብሏቸው እርፍ!።
አንጀቴን አራሰው ጃል። አዎ። ወቅቱ ዘርዘር ብሎ በመቆም ክፉ ቀንን ማለፍ ብቻ ሳይሆን ለራስም፣ ለሕብረተሰብም፣ ለአገርም መፍትሄ ሆኖ የተገኘበት ጊዜ ነው። ክፉ ጊዜን ክፉ ተሁኖ፣ ክፉ ታስቦ ማለፍ አይቻልም። በኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ሃያላን ተንበርክከዋል። በዓለም በስልጣኔ የናጠጡ አገራት የፈጣሪን መኖር መርሳታቸውን የኮሮና ወረርሽኝ እንዳስታወሳቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ በዓለም ላይ ሰው በሚኖርባቸው አህጉርና አገራት መከራው እኩል መረጨቱን ተገንዝቦ ትምህርት ለመቅሰም የማይነሳሳ ሕሊና ያለው ፍጡር ሰው መሆኑን መጠራጠር ያስፈልጋል። ‹‹ለምን የተላከ ለጻድቃን ይተርፋል›› እንዲሉ። እንደዚህ አይነት ቡድኖች (ግሩፖች) አሁንዓለም ፈተና ላይ በወደቀበት ጊዜ ትስስራቸውን ለበጎ ተግባር ማዋል በተገባቸው ነበር።
ሰው ሆኖ መኖርን የለመዱ ባለመሆናቸው ትምህርት ሆኖ ለሕዝብ ሊተላለፍ የሚገባው ቁም ነገር ተሰውሮባቸዋል ባይ ነኝ። ብቻ ኮሮና እናንተን አይነካችሁም አይዟችሁ! ያላቸውን አካል ብናውቀው ምን አለበት፤ ዓለምም ልታውቀው ትጓጓ ነበር። በዓለም ላይ የሚገኝ የሰው ልጅ እንደቅጠል እየረገፈ ባለበት በዚህ የጭንቅ ጊዜ የሚቀልድና ምን አገባኝ የሚልን ምን ትሉታላችሁ? ኮሮና አገራችን ውስጥ ለዘመናት እንደተፈጸሙት ሰው ሰራሽ ለቅሶዎች ዘር፣ ቀለም፣ ብሄር ለይቶ የሚያስለቅስ አይደለም። የአገራችንን የበላይ አስለቃሾችም ዘመንና ወራት ቢከዳቸው እንኳን በኮሮና ወረርሽኙ የበለጠ አልቃሽ ከቶም ሊሆኑ አይችሉም። ወረርሽኙ ለአገርና ለወገን እኩል ፈተና የደቀነ ነው። በመሆኑም ወገን ለወገኑ ስለምን አይተሳሰብም? እኛ የምንማረው ችግር ውስጥ ወድቀን አሳራችንን ስናይ ብቻ ለምን ይሆናል? ምን አገባኝ ይሉት ብሂል በሕገ ኮሮና አይሰራም። አይ የኔ ነገር! በዋል ፈሰስ ሆንኩኝ እኮ፤ተግባር አይበሉኝና አይጠይቁኝ እንጂ ደሞ ለወሬ፤ እህ የሚለኝ ካገኘሁ አሰብከው። እህ ባይሉኝም አልተወው፤ ወሬው ሞልቶ ሲፈስ በዓይኔ አላየው ምን አገባኝ። አዎ! ይሄ ምን አገባኝ ብዙ ጉድ ይዟል፤ ብዙ ጉድም ያመጣል፤ ምኑ ተነግሮ ያልቃል። ‹‹ብዙ ብዙ ነገር ልናገር አልኩና፣ ምን አገባኝ ብዬ ተውኩት እንደገና።›› ነበር ያለው ያ ገጣሚ፤ ሆሆይ! በኮሮና ዘመን ምን አገባኝ የሚሰራ አይምሰላችሁ። ለአንተና ለእኔ ፈተናዎች እኩል ቀርበው ከፊት ለፊታችን እየተመለከትናቸው አንተ በእኔ የሚሳለቅ ሕሊና እንዴት ሊኖርህ ይችላል? አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ሲሆን የምንታዘበው ይሄንን ነው። የዚህ ዓይነት አባዜ የተጠናወታቸውም ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያው ታዝባችሁ አታውቁም? ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሕብረተሰቡ ጆሮ ቀጥ ብሎ እንደሚጠብቃቸው ስለሚያውቁ ስህተት የሆኑ መረጃዎችን ለመመገብ የሚንሰፈሰፉ አካላት እንደ አሸን ፈልተዋል። ከኮሮናው ወረርሽኝ በፊት ለወገናቸው ኮሮና የሆኑ ማፈሪያ ወገኖች!። አሁን ካልጠፋ ስራ እንዲህ በአገርና በወገን ላይ ባንዣበበ ችግር ጦስ እየደረቡ ሆድ መሙላትን ምን ይሉታል? በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላዩ ያለምህረት መጠቅለል መጀመራቸውን ሹክ በሏቸው፤ እጅና ቀልባቸውን ይጠቀልሉ ይሆናል። ለነገሩ እንደዚህ ዓይነት በማህበራዊ ሚዲያዎች ውሸት ወሬዎችን በመዝራት እንጀራቸውን የሚያበስሉት የዜጋ ዝቃጮች በእኛ አገር ብቻ ለተዓምር የተፈጠሩ አይምሰላችሁ።
መጠኑ ይለያይ ይሆናል እንጂ የትም ይበቅላሉ። ከሰሞኑ እንግሊዝ ሐሰተኛ የኮሮና ወሬ አሳሬን አሳይቶኛል ስትል ገልጻ ነበር። ይሄን ተከትሎም የኮሮና ቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ማህበራዊና የጤና ጉዳት ተከትሎ የሚያርም ግብረሃይል አቋቁማ በተራዋ ውሸታሞቹን አሳራቸውን ልታሳያቸው እየጣረች ትገኛለች። ቢቢሲ የእንግሊዝን የባህል ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በአገረ እንግሊዝ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ሐሰተኛ መረጃዎች፣ አሉባልታዎች እንዲሁም መልዕክቶች የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንዳመሰቃቀለ አንስተው፤ ርምጃም መወሰድ እንዳለበት ማሳወቃቸውን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
አፍሪካዊቷ አገር ኬንያም ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሐሰተኛ መረጃ በመንዛት ዜጎችን አደናግሯል፣ አሳስቷልም ያለችውን ዜጋዋን ዘብጥያ አውርዳለች። የዚህ አይነት ተግባር ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ካልተባለ የበዛ ጦስ በዜጎችና በአገር ላይ ያስከትላል። ሌሎቻችንም ከእንዲህ አይነት ተግባር ልንቆጠብ እና በሚሰሩ ዜጎቻችንም ልናፍር ይገባል ማለቷ የሚረሳ አይደለም። በኢትዮጵያም ለዘመናት በማህበራዊ ሚዲያዎች የውሸት ወሬዎች በመቀመም ተሰማርተው በርካቶች ወፍራም እንጀራቸውን ሲያበስሉ ኖረዋል። ከዚህ በኋላ ግን የሕግ ልጓም እንደተበጀላቸው ሊነገራቸው ይገባል። አንሰማም የሚሉትንና መፈንጨታችንን እንቀጥላለን የሚሉትን ደግሞ አሳድዶና አሽትቶ ለሕግ ማቅረብ ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ ጭምር ሊሆን ይገባል። ማንኛውም አካል ከፖለቲካ፣ ከስልጣን ፍላጎት፣ ከግል ቂም እና ከሌላም ፍላጎት በመነሳት የአገርና የወገን ክብር እና ጥቅም የሚያሳጣ አንዳችም ተግባር እንዲፈጽም እድል ሊሰጥ አይገባም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ሙሐመድ ሁሴን
ከዘር ይልቅ ዘርዘር ብሎ መቆም ላይ ብናተኩር