ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰባት ጥይት ተኩሶ በመሳቱ ስለተፈረደበት ሰው ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ሰባት ጥይት ተኩሶ የሳተው 10 ዓመት ተፈረደበት የመንግስት ገንዘብ አጉድሎ ጥፋተኝነቱ ቢደረስበት ለመግደል ሞክሮ ሰባት ጥይት የተኮሰባቸውና የሳታቸው አበራ ቱምሳ በተከሰሰበት ወንጀል ተመስክሮበት ለአስር አመት እስራት ወህኒ ገባ። ተከሳሹ ሽጉጥ ተኩሶ የሳታቸው አቶ ቢጋር ዮሴፍ የተባሉትን የናዝሬት ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ባልደረባ የሆኑትን ነው። አበራ ወንጀሉን የፈጸመው ከመስሪያ ቤቱ 710 ብር መስረቁ ስለተደረሰበት ጥፋቱን ለመሰወር መሆኑን የዓቃቢ ህጉ መስረጃ አረጋጧል።
አበራ ቱምሳ የመንግስት ገንዘብ ማጉደሉ ጥር አራት ቀን 1960 ዓ.ም እንደተደረሰበት በጓሮ በር አምልጦ ሸሽቶ በማግስቱ ጥር አምስት ቀን በሰረቀው ገንዘብ ቤልጂግ መትረየስ ሽጉጥ ገዝቶ በአቶ ቢጋር ዮሴፍ ላይ የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈጽሞ ሳይሳካለት መቅረቱን የምስክሮቹ ቃል ያረጋግጣል። ወታደር ሂርጳሳና ሰቦቃ የተባሉትን የፖሊስ አባሎች አልያዝም በማለት በሽጉጥ በማስፈራራት ለማምለጥ መሞከሩ ተመስክሮበታል። የወንጀሉ አፈጻጸም በቅድሚያ ከፖሊስ ጣቢያ ቀጥሎም በአዲስ አበባ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት አማካይነት ተጣርቶ አበራ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ሐምሌ አራት ቀን በዋለው ችሎት ቅጣቱ ተወስወኖበት ወህኒ ገብቷል። ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 1963 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አጭር ቀሚስ በመልበሳቸው ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው ሴቶች ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
የአስመራ ማዘጋጃ ቤት አጭር ቀሚስ ለሚለብሱ 41 ሴቶች ማስጠንቀቂያ ሰጠ
የአስመራ ማዘጋጃ ቤት አጭር ቀሚስ ለብሰው የተገኙትን 41 ሴቶች በመገሰጽ ሁለተኛ እንዳይለብሱ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። የመዘጋጃ ቤቱ ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት በከተማው እየተዘዋወሩ እነዚህን ሴቶች የያዙት ከየቡና ቤቱ ውስጥ በመልቀም ነው። ማዘጋጃ ቤቱ ወደፊትም በየቡና ቤቱና በየመንገዱ አጭር ቀሚስ የሚለብሱትን ሴቶች እየያዘ አስፈላጊውን ቅጣት የሚሰጥ መሆኑን ሻንበል ገብረ ሚካኤል ቀላቲ የአስመራ ማዘጋጃ ቤት የወታደር አዛዣ ገልጸዋል።
ቀጥለውም የአስመራ ማዘጋጃ ቤት ይህንን ርምጃ የሚወስደው የአገር ባህልን ለማስከበር መሆኑን ገልጸዋል። የአጭር ቀሚስ አለባበስ የአገራችንን ሴቶች ብቻ ሳይሆን በአስመራ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን የውጭ አገር ተወላጅ አጭር ቀሚስ ለባሾችን ጭምር እንደሚመለከት አመልክተዋል። ሻንበሉ እንደገለጹት ለማናቸውም የአስመራ ከተማ አጭር ቀሚስ ለባሾች በመጀመሪያ ተግሳጽ ይሰጣቸዋል። በሁለተኛው ጊዜ በማዘጋጃ ቤቱ ደንብ ይቀጣሉ። በሶስተኛ ጊዜ አጭር ቀሚስ ለብሰው ከተገኙ ፍርድ ቤት ቀርበው አስፈላጊው ቅጣት እንደሚፈጸምባቸው ታውቋል። የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ በዚህ አለባበስ በኩል ባህልን ለማስከበር ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር እንደሚሆን ተገልጿል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2012
የትናየት ፈሩ