ከተማ ቋሚ እና ሠፊ ህዝብ የሰፈረበት አካባቢ ነው። ይህን አካባቢ ለየት ከሚያደርጉት መካከል ራሱን የቻለ አስተዳደር ያለው የሚለው ይገኝበታል፤ በህግ ይመራል። ዋና ከተማ ሲባል ደግሞ የአገር ወይም የክፍለ አገር መንግሥት የሚገኝበት ማዕከላዊ ከተማ ነው።
ብዙ ጊዜ ዋና ከተማ የአንድ ሀገር ትልቁ ከተማ ይሆናል። ለምሳሌ ሞንቴቪዴዮ የኡራጓይ ታላቁ ከተማ ከመሆኑ በተጨማሪ ዋና ከተማም ነው። ዋና ከተማ ሁል ጊዜ የአገሩ አንደኛው ትልቅ ከተማ ላይሆን ግን ይችላል። ለምሳሌ የአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ ሲሆን፣ በትልቅነት ግን ከኒው ዮርክ ከተማ ያንሳል። የሕንድ ዋና ከተማ ኒው ዴሊ ከታላቁ ከሙምባይ ከተማ በጣም ያንሳል።
ሀገሮች በዋና ከተሞች ላይ የተለያየ አተያይ አላቸው። አንዳንድ አገሮች ከአንድ በላይ ዋና ከተማ አላቸው። ለምሳሌ ቦሊቪያ ሁለትና ደቡብ አፍሪካ ሦስት ዋና ከተሞች አሏቸው። ናውሩ ምንም ይፋዊ ዋና ከተማ የሌላት የሰላማዊ ውቅያኖስ ደሴት አገር ናት። አንዳንድ አገሮች ደግሞ የዋና ከተሞቻቸውን ሥፍራ በየጊዜው ያዛውራሉ። ከተማ ሲባል ምን ማለት ነው? ምንስ ያህል ህዝብ መያዝ አለበት? ምንስ መሰረተ ልማት ማሟላት ይጠበቅበታል? በኢትዮጵያ ከተማ ሲባል ምን አይነት መስፈርት መሟላት አለበት? አሁን ያሉት ከተሞች ከተማ የተባሉት በህዝብ ብዛታቸው ወይስ በአደረጃጀታቸው? የሚሉት ጥያቄዎች ሁሌም ወደ አዕምሮዬ ይመጣሉ።
በ2005 ዓ.ም ስለ ከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን የወጣው አዋጅ ‹‹ከተማ ማለት ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመበት ወይም ሁለት ሺህ ወይም ከዚያ በላይ የህዝብ ቁጥር ያለውና ከዚያም ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው የሰው ሃይል ከግብርና ውጪ በሆነ ስራ የተሰማራ ሆኖ የሚገኝበት አካባቢ ነው›› ብሎ ይተረጉመዋል። በኢትዮጵያ ትልቅ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ከተሞች ይገኛሉ። ነገር ግን የመሰረተ ልማት ጉዳያቸው ሲነሳ ግን መልሱ ዝም ነው። በተለይ ደግሞ በክልሎች የሚገኙ የከተማነት ደረጃ የተሰጣቸው ቦታዎች አንድ ዓይነት መስፈርት ያሟሉ ሳይሆን፣ ለምን ይቅርባቸው በሚል የከተማነት ደረጃ የተሰጣቸው ይመስላሉ። ትዝብቴን ከዋና ከተማችን አዲስ አበባ ለጀምር…።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ይታወቃል። እንደ ዋና ከተማ መያዝ ያለባትን ይዛለች ወይ ተብሎ ቢፈተሸ ግን ከ20 በመቶ የዘለለ ነገር አይገኝም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምንድነው ብትሉ አዲስ አበባ መንገድ፣ ዘመናዊ ህንፃ፣ መዝናኛና መናፈሻዎች፣ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ፖሊስ ጣቢያ፣ ሆስፒታልና የመሳሰሉት ተቋማት በበቂና በተሟላ ሁኔታ የሌሏት መሆኑ ነው። ምን ይላል? በአዲስ አበባ ውስጥ ፖሊስ ጣቢያ፣ ሆስፒታል እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት በብዛት አሉ አይደለም እንዴ የሚል ሊኖር ይችላል። አሁን በከተማዋ ያሉት መሰረተ ልማቶችም ሆኑ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለዋና ከተማነት የሚመጥኑ አይደለም ነው መልሴ። የአዲስ አበባን ፖሊስ ጣቢዎች በአብነት ወስዶ መመልከት ይቻላል።
ፖሊስ ጣቢያዎች ለብዙ ዓመታት ውስን ሆነው የቆዩት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ጣቢያነት የሚያገለግሉ ቤቶችን በየአቅራቢያው እየገነባ ስለሰጠ ብዙ ፖሊስ ጣቢያዎች ይታያሉ። ይሁንና እነዚህም ቢሆኑ ቤቶቹ ብቻ ናቸው የሚታዩት፤ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ስለአለመሆናቸው ይነገራል፤ አብዛኞቹ ዝግ ናቸው። ሌሎች አደረጃጀቶች ካልተሻሻሉ ህንጻ ብቻውን ትርጉም እንደሌለው ከዚህ መረዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ ወንጀል መከላል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳደር ጥርጥር አይኖረውም።
ሆስፒታሎችም ቢሆኑ አዳዲስ ጤና ጣቢያዎችና የግል የጤና ተቋማት ወደ ስራ ከመግባታቸው ውጪ ፣ በቀደሙት ላይ ማስፋፊያ ከማድረግ በዘለለ ከከተማው መስፋፋት ጋር የሚራመድ የሆስፒታል አገልግሎት በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ማግኘት አይቻልም። ከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ ብትስፋፋም ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ ግዙፍ ሆስፒታሎች የሚገኙት አሁንም በከተማዋ እምብርት ላይ ብቻ ነው። አብዛኞቹ የክልል ከተሞችም ተመሳሳይ ገፅታ ነው ያላቸው። ሁሉም የከተማነት ደረጃ የተሰጣቸው የህዝብ ብዛታቸው ታሳቢ ተደርጎ ነው..።
መሰረተ ልማቱ ግን አይነሳ፤ አብዛኛዎቹ ከተሞች በውሃ፣ በመብራትና በትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ውስጥ ነው የሚገኙት። የከተማ ደረጃ ያገኙት የዞን፣ የወረዳ ዋና ከተሞች ከተማ መሆናቸው በተወሰነ ደረጃ የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ቢያደርግም እንደ ከተማ ከፍተኛ ለውጥ አላመጣላቸውም። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ ያለው በመሆኑ በቱሪስት የመጎብኘት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ይሁንና ከተሞቹን የቱሪስት መዳረሻነት ለማሳደግ ብዙም አልተሰራም፤ ለዚህም ጅማ፣ ላልይበላ፣ አክሱምን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፤ የአድዋ ድል የተገኘበትን የሶሎዳ ተራራ የሚዘክር ምንም አይነት ማስታወሻ በአድዋ ከተማ ላይ አይስተዋልም። እነዚህ ሁሉ በመርህ ደረጃ ከተሞቹ መያዝ ያለባቸውን የህዝብ ቁጥርና የከተማ ደረጃ ቢይዙም በአደረጃጀት ግን አሁንም ኋላቀር መሆናቸውን ያመለክታሉ። በአጠቃላይ የከተሞች መሰረተ ልማትን ዘመናዊ እና ተገቢ ለማድረግ ቅድሚያ ግንዛቤ ያስፈልጋል።
ምክንያቱም በከተሞች የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በሙስናና ረጅም ጊዜ አገልግሎት በማይሰጡ እቃዎች የሚሰሩ በመሆናቸው የተፈለገውን ያህል ሳያገለግሉ ሲወድሙ ይስተዋላል። ለዚህም ከተማዋ የገነባቻቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶችና መንገዶችን ማየቱ ይበቃል። ከተሞችን ውብና ለሚኖርባቸው ህብረተሰብ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የሌሎች አገራት ተሞክሮ መታየት አለበት። በአሁኑ ወቅት በከተሞች ላይ የተሰሩና እየተሰሩ የሚገኙ ህንፃዎች በቀለምና በአሰራር ተያያዥነት እንዲኖራቸው ማድረግም ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
መርድ ክፍሉ