ጉስቁልና ተጭኗታል፤ፊቷም ይህንኑ በሚገባ ይመሰክራል።ጠይምነቷን ክፉኛ ያደበዘዘው መሆኑ ያስታውቃል። ወገቧ ላይ አስራ እስከ እግሯ የለቀቀችው ወፍራም ላስቲክ ልብስ ስታጥብ የሚረጨው ውሃ ልብሷን እንዳይነካው ቢከላከልላትም፤ የተጫማችው ኮንጎ ጫማ ግን ከእጣቢው አላስጣላትም። ልብስ አጣቢዋ ወሰኔ ኤርገኖ ሁሌም ቀኑን ሙሉ ልብስ ታጥባለች።
ሥራው ከወገቧ ቀና እንዳትል እያረጋት አጎንብሳ እስከ መሄድ ቢያደርሳትም በማግስቱ ተመልሳ ወደ ልብስ አጠባ ትገባለች፤ ኑሮዋ በሰው ቤት ልብስ አጠባ ላይ የተመሰረተ ነውና። በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጌጃ አካባቢ የተወለደችው ወሰኔ ትምህርት ቤት አታውቅም። ይልቁኑ ባልጠና ዕድሜዋ ለጋብቻ ትታጫለች። የመጀመሪያ ልጇን በጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሰላም ብትገላገልም፣ ልጁ ሙቀት ክፍል መግባት እንዳለበት ይነገራታል፤ ከሦስት ቀን በኋላ ለማጥባት እንድትመለስ ይነገራትናም ልጁን ሙቀት ክፍል ትታ ወደ ቤቷ ትሄዳለች።
በሦስተኛው ቀን ሆስፒታል ስትመለስ ግን ያልጠበቀችው ነገር ያጋጥማል፣ የልጇን ዓይን ልታይ እና ልታጠባ የተመለሰችው እናት የልጇን ሞት ትረዳለች። ይህን ክፉ ስብራት ይዛ ወደ አካባቢዋ ተመልሳ ኑሮን ትያያዛለች። አግብታም ታረግዛለች፤ ባለቤቷ ግን የቤት ወጪ እየሰጠ የሚያኖር ሊሆንላት አልቻለም። ውሎ እና አዳሩ፤ ሃሳብና ህልሙ ከእርሷ ጋር ሳይሆን ከመጀመሪያ ሚስቱ እና ከልጆቹ እናት ጋር ነበር።
ይህ ያበሳጫት ወሰኔ ጨርቋን ጠቅልላ ወደ አዲስ አበባ ታቀናለች። በቤት ሠራተኝነትም ትቀጠራለች፤ ይህ በመሆኑም የመጠለያ፣ የምግብና መጠጥ ጉዳይ አላሳሰባትም። የሆዷ እየገፋ መምጣት ግን በእጅጉ እያሳሰባት ይመጣል። ቀጣሪዎቿም የሆዷን መግፋት ሲረዱ ያሰናብቷታል። ተቀጥራ ያጠራቀመቻትን ይዛ በሦስት መቶ ብር ቤት ተከራይታ መኖር ትጀምራለች፤ወንድ ልጅም በሰላም ተገላገለች።
ይሁንና የቤት ኪራይ መክፈል እያዳገታት ይመጣል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከሁለት ወር በላይ መዝለቅ ተቸገረች። ቤት ማፈላለግ ውስጥ ትገባለች። ወንዝ ዳር ላይ የፈራረሰች ብትሆንም፣ ለማደሪያ ብላ በመቶ ሰባ ብር ትከራያታለች። ልጇን አዝላ በየሰዉ ቤት ልብስ አጠባ ጀመረች። የቤት ኪራይ ዋጋ እየጨመረ መምጣት ጉልበቷን ያፈሰሰችበትን ገንዘብ እየበላባት ሦስት ዓመታትን አሳለፈች።
ልጇ ዘርይሁን ከወገቧ መውረድ መጀመሩ ደስ ሲላት፣ ሌላ መከራ መጣባት። ከወንዝ አካባቢ የመጣ ትልቅ አውሬ መሰል ውሻ ዓይኗ እያየ ዘርይሁንን ጎተተባት፤እግሩንም ክፉኛ ዘለዘለው። ይህን ያየችው እናት በድንጋጤ ደንዝዛ በመቅረቷ ልታስጥለው አልቻለችም፤ ሰዎች ተጯጩኸው አስጣሉት። ዘርይሁን ግን በውሻው ንክሻ ክፉኛ ተጎዳ። የወሰኔ ሕይወትም የባሰ ከድጡ ወደ ማጡ አሽቆለቆለ።
ውሻው ‹‹ዕብድ ሊሆን ይችላል›› በሚል ጨቅላው ዘርይሁን በሦስት ዓመቱ ለ21 ቀናት የዕብድ ውሻ መርፌ በእንብርቱ መውሰድ የግድ ሆነበት፤ ጤናው ግን ሊመለስ አልቻለም። ዳዴ ሲል እንዳይቆሽሽ ብላ ልብስ ስታጥብ አዝላ ያሳደገችው ዘርይሁን፤ ጤና አጣ። ዕድሜው እየጨመረ ሲመጣ ጭራሽ ዓይኑን እያርገበገበ መውደቅ ጀመረ። ‹‹ውሻው ሲነክሰው ተለክፎ ነው›› ተባለናም እናት እና ልጅ በየፀበሉ ተንከራተቱ፤ አሁንም ፈውስ ጠፋ። መላ ያጣችው ወሰኔ ሃኪም ቤት ተመለሰች፤ የሚጥል በሽታ እንደያዘው እና የማያቋርጥ ሕክምና እና መድኃኒት እንደሚያስፈልገው ተነገራት። የደረሰባት ፈተና የአከራዮቿን ልብ አራራላት፤ ሌሊት እንጀራ እየጋገረች ቀን እየሸጠች፤ በቀራት ጊዜ ልብስ እያጠበች የቤት ኪራይ እና የምግብ ወጪዋን መሸፈን ጀመረች፤ ይህም ቢሆን የዘርይሁንን የሕክምና ወጪ እና ለመድኃኒቱ የሚያስፈልገውን ምግብ መሸፈን አላስቻላት ይላል።
አከራዮቿ የሚተዳደሩት በቤት ኪራይ በሚያገኙት ገንዘብ በመሆኑ ኑሮው የኪራይ ዋጋ እንዲጨምሩ አስገደዳቸው፤ በ170 ብር ያከራዩዋት ቤት ኪራይ እየጨመረ መጥቶ 900 ብር ደረሰ። ወሰኔ በሰዎች እርዳታ የሕክምና እና የመድኃኒት ወጪዋ ቢሸፈንላትም፣ ከተወሰነ ጊዜ በላይ ኪራዩን መክፈል አልሆነላትም። አከራይዋ ‹‹ኑሮዬን ታውቂያለሽ፤ መክፈል ካቃተሽ ቤት ፈልገሽ ውጪ›› ይሏታል።
ልጇ 9 ዓመት ቢሆነውም፣አሁንም የሕክምና ክትትል እና መድኃኒት ያስፈልገዋል። አንዳንድ ልብስ አሳጣቢዎቿ እና ሌሎችም ችግሯን አይተው እየረዷት መድኃኒቱ ቢቀጥልም ቤት ልቀቂ መባሏ ኑሮዋን ይበልጥ አወሳሰበባት።በአቅሟ ልክ የምትከፍለው ቤት ማግኘትም አዳገታት። ጠሮ ስላሴ ቤተክርስቲያን ‹‹የቆርቆሮ ሱቅ አለ፤ ኪራዩ 500 ብር ብቻ ነው›› የሚል ወሬ ትሰማለች፤ ‹‹ገንዘብ ይዤ ባልነግድም ልኑርበት›› ብላም ትከራያለች። ቤቱ እንደነገሩ ነው፤ በሩ ጥብቅ አይደለም፤ ዙሪያ ገባው ቀዳዳ ይበዛዋል። በካርቶንና በማዳበሪያ ቀዳዳውን ወታትፋ ዕርዳታዎችን እየተቀበለች እና ልብስም እያጠበች ኑሮዋን መግፋት ቀጠለች።
በሴፍትኔት ፕሮግራም ትታቀፋለች፤ በዚህም ከቆሻሻ መጥረግ እስከ ድንጋይ መሸከም የደረሰ ሥራ እየሰራች ገቢ ማግኘት ቻለች፤ ከሴፍትኔት መልስም ልብስ ማጠቧን ቀጠለች፤ ይሁንና ኑሮ አሁንም ሊቀልላት አልቻለም። በሌሊት ልጇን ትታ ለሴፍትኒት ሥራ ትወጣለች፤ ልጇ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊት መድኃኒት እንዲውጥ ለማድረግ ትመለሳለች፤ ትምህርት ቤት ታደርሰዋለች፤ተመልሳ ወደ ሥራ ትሄዳለች።
የልጇን የመድኃኒት ሰዓት ጠብቃ በዘጠኝ ሰዓት ደግሞ ልብስ አጠባዋን እያቆመች ከትምህርት ቤተ መልሳው መድኃኒት ትሰጠዋለች። በየጊዜው ከአንድ ሺህ ብር ያላነሰ ወጪ የሚያስወጣውን የዘርይሁንን መድኃኒት በዕርዳታ መግዛት ብትችልም፤ መድኃኒቱ ከባድ በመሆኑ ልጁ መጠጣት አለበት የተባለውን ወተት እና መመገብ አለበት የተባለውን ምግብ ማብላት አልቻለችም።
የልጇ ጤና ችግር እየተወሳሰበ የተቸገረችው ወሰኔ፣ ጥረቷ የእርሷን እና የልጇን የዕለት ጉርስ ከመሸፈን እና የቤት ኪራይ ከመክፈል የዘለለ ሊሆን አልቻለም። የምትኖርበት ቤት ዋጋ እየጨመረ ቤተክርስቲያኗ ልዩነት ላለመፍጠር በሚል የምታከራየው በካሬ ሜትር ነው ተብላ አንድ አልጋ እና የተወሰኑ ዕቃዎችን ለያዘው፣ መጸዳጃ ቤት እና ውሃ ለሌለው የቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት አንድ ሺህ አራት መቶ ብር ክፈይ ተባለች።
የወሰኔን ነፍስ ያደከመው የልጇ በሽታ እና ቀለባቸው አይደለም፤ የመኖሪያ ቤት እጦት ነው። ስለመኖሪያ ቤት ስትጠየቅ እንባዋ ይፈሳል። ዛሬም የወሰኔ ልብስ አጠባ እና እረፍት አልባ ድካም አላበቃም፤ የቤት ኪራይ ለመክፈል ስትል፤ በሽታው በርትቷል፤ ወረርሽኝ መጥቷል ቢባልም ልብስ ማጠቧን አላቋረጠችም። የቤት ኪራይ ከፊት ለፊቷ አለና።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
ምህረት ሞገስ