መንግስት በአዲስ አበባ ወደ ከተማ መልሶ ልማቱ የመጣበት አንዱ ምክንያት የመሬት ጥበት እየተከሰተ እንደሆነ ይነገራል:: መሬት ደግሞ ስለማይፈበረክ ያለውን በጥበብ መጠቀምን የሚጠይቅ ሆኖ አግኝቶታል:: በመሆኑም ችግሩን መፍታትና ሰውንም ኑሮው እንዲሻሻል ለማድረግ በማሰብ ወደ መልሶ ልማቱ ገብቷል::
በተለይ ቀደም ሲል በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰው ተጠጋግቶ ይኖራል በሚል ታሳቢም መሆኑ ይጠቀሳል:: ታዲያ የከተማ መልሶ ማልማቱ ያስገኘው ፋይዳ ይኖር ይሆን? ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮሌጅ መምህርና የአርክቴክት ባለሙያ የሆኑትንና እጩ ዶክተር መስከረም ዘውዴን አነጋግረናቸዋል::
አርክቴክቷ ‹‹የአዲስ አበባ የመሬት አጠቃቀም›› በሚል ርዕስ ላይ መመረቂያ ፅሁፋቸውን እያጠናቀቁ ይገኛሉ:: ካጠኗቸው አካባቢዎች ልደታ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ፈርሶ የተሰራ አካባቢ ነው:: ጎላ ሰፈር ደግሞ ገና ሊፈርስ እየተጠና ያለ አካባቢ ነውና በዚህ ሂደት ሰዎች ያላቸውን ስጋት በጥናታቸው ዳሰዋል:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሁለት አይነት ለውጥ አለ:: አንደኛው ማስፋፊያው ሲሆን፣ ለአብነትም እንደ እነ ጀሞ፣ ቦሌ አራብሳ አይነት አካባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል:: አርሶ አደሩ እየተነሳ የከተማው ሰው ራቅ ወዳለ አካባቢ የሚሰፍርበት እንደ ማለት ነው:: ሁለተኛው ለውጥ መሃል ከተማ ላይ የመጣው ነው::
በመልሶ ማልማት እየተሰራ ያለው:: ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ በእነዚህ ሁለት ለውጦች መካከል ተወጥራ ትገኛለች:: የአዲስ አበባ ከተማ እየተለጠጠች ስትሆን፣ መለጠጡ ደግሞ በመሬት አጠቃቀም ላይ ለውጥ ያመጣል:: ይህ ደግሞ በከተማዋ ዙሪያ ያለው አርሶ አደር እንዲነሳ ያደርጋል:: ሌላው ደግሞ መሃል ከተማውን መልሶ ማልማትና ማደስ በሚል እንቅስቃሴ ተጀምሮ የሚሰራው ነው::
‹‹ኢትዮጵያ ባለፈችበት አይነት መንገድ ሌሎችም አገራት አልፈዋል›› የሚሉት አርክቴክቷ፣ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የከተማ መልሶ ልማት ግን የሚያተኩረው አሮጌ ቤቶችን ማንሳት ላይ ነው፤ ነገሩ ግን ይህ አይደለም:: መልሶ ማልማት ሲባል ግን መታየት ያለበት አሮጌ ቤቶችን አፍርሶ አዲስ መገንባት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ሁኔታን ያገናዘበ መሆን አለበት:: ምክንያቱም መልሶ ማደስ ሲባል በፊት ከነበረው የተሻለ ማድረግ ማለት ነውና በማለት ያስረዳሉ::
‹‹የእኛ አገር መልሶ ልማት በብዛት የሚያተኩረው ፊዚካል (ቁስአካላዊ) ልማት ላይ ነው:: ይህም ማለት የምናተኩረው የደቀቁና የደከሙ ቤቶችን ማንሳት ላይ ብቻ ነው:: ይህ ስለሆነም ማህበራዊው፣ ኢኮኖሚያዊውና አካባቢያዊው ሁኔታ ላይ መሰራት የሚገባውን ያህል እየሰራን አይደለንም›› ይላሉ::‹‹ለአብነትም የደቀቁ ቤቶችን ከማፍረስ ጎን ለጎን ማህበራዊ ሁኔታዎችንም አብረን መፍጠር አለብን::
ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችን መስራት ሊሆን ይችላል:: ማህበራዊ ትስስሩንም መልሶ ማልማቱ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቃል›› በማለት ያመለክታሉ:: ለምሳሌ ልደታ አካባቢ ያለው ሁኔታ ሲስተዋል በርካታ የአካባቢው ሰዎች ተፈናቅለዋል:: ግማሹ ጎፋ ሰፈር ሌላው ደግሞ ጎተራ የጋራ መኖሪያ ሰፈር ሲሄድ፣ ሌሎችም በተለያየ ቦታ ሰፍረዋል:: አሁን አሁን በተወሰነ መልኩ የአንድ አካባቢን ሰው ወደ አንድ አካባቢ የማስፈሩ ነገር እየተሻለ መጣ እንጂ በፊትሲደረግ የነበረው የመበታተን ያህል ነው:: እንደ አርክቴክቷ አባባል፤ ማህበራዊ ትስስሩ ሲፈርስ ማህበራዊ ቀውስን ያመጣል:: ሰዎች ከእድራቸው፣ ከማህበራቸው፣ ከእቁባቸው ብሎም አብሮ ከማሳለፍ ሂደታቸው ሲለያዩ ብዙ ቀውሶችን ያመጣል:: በእርግጥ አሁን ለመሻሻል እየተሞከረ ነው፤ ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈምና አሁንም መታየት ይኖርበታል:: ‹‹ብዙውን ጊዜ የምናፈርሰው መሃል ከተማ ያለውን ነው፤ በእኛ አገር ደግሞ መሃል ከተማ ላይ ያለው አነስተኛ ገቢ ያለው ደሃው የህብረሰብ ክፍል ነው::
እነዚህ ሰዎች መሃል ከተማ በሚኖሩበት ጊዜ አብዛኛዎቹ የትራንስፖርት ወጪ የለባቸውም:: ገበያም ሆነ ትምህርት ቤቱና ሌላውም በቅርባቸው አለ:: ስለዚህ ሰዎቹን ከከተማ አውጥተን ዳር ላይ ስናሰፍራቸው አንደኛ የሚያስፈልጋቸውን ለማድረግ የኢኮኖሚ አቅም የላቸውም›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ለሌላ ተጨማሪ ወጪ ይዳረጋሉና ማፈናቀሉ ብዙ ነገሮችን እንደሚያቃውስ ያስረዳሉ::
ባለሙያዋ፣ ‹‹በጥናቴ የልደታ የጋራ መኖሪያ ቤትን እንዳየሁት 70 በመቶው የሚሆኑ የቤቱ ባለቤቶች ለሌላ አከራይተው ወጥተዋል:: ተከራዮቹ እነማን ናቸው ብንል የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች፣ የመርካቶ ነጋዴዎችና የመሳሰሉት ናቸው:: ስለዚህ መልሶ ልማቱ ዓላማውን መትቷል ወይ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ይከታል›› ይላሉ:: በቤቶቹም ዋጋ ደረጃ ሲታይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል::
በመጀመሪያ የጋራ መኖሪያ ቤት ሲነሳ መንግስት በካሬ ሜትር ለቤቶቹ ያስቀመጠው ዋጋ ከ800 እስከ አንድ ሺህ ብር ነበረ:: ይህ ነገር በሂደት አሁን ባለው ደረጃ ከአራት ሺህ ብር በላይ እየሆነ ነው:: በእርግጥ በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ይታወቃል፤ መንግስትም በተቻለው መጠን ለመደጎም ይሞክራል:: የመሬትና የመሰረተ ልማት ወጪንም የሚሸፍነው መንግስት ነው:: እኤአ የ2018ቱ የመሬት ዋጋ በካሬ ሜትር ከሁለት ሺህ 483 እስከ አራት ሺህ 776 ብር ሆኗል:: ቤት የሚሰራላቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸው በዝቅተኛ ሁኔታ የሚተዳደሩ ስለሆነ በካሬ ሜትር የተቀመጠውን ዋጋ አይችሉትም:: በዚህም የተነሳ አንዳንዱ የሚሸጠው ወዲያውኑ ነው::
ከዚህ አኳያ ያንን ከፍሎ ቤቱን የመውሰድ አቅም አይኖርም ማለት ነው:: አጥኚዋ እንደሚናገሩት፤ በሌላ በኩል ሲታይ መንግስት ፊት ለፊት ያሉትን ቤቶች ለንግድ በሊዝ ይሸጣል:: እነዚህ ለንግድ የተባሉ ቤቶች ስራ መፍጠር ያለሙ ሆነው አልተገኙም:: ምክንያቱም ማደሱ አሮጌ ቤት ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ነው መሆን ያለበት:: እንዲህም ሲባል ለአካባቢው ስራ መፈጠር መቻል አለበት ነው:: ያንን ማድረግ ካልተቻለ የመንግስት ዓላማ መሬት የመሸጥ ብቻ ይሆናል ማለት ነው:: በአካባቢው ሊያለማ የመጣ ባለሀብት የስራ እድል መፍጠር ሲችል ነው ለውጡ መጣ ማለት የሚቻለው::
ሌላው ደግሞ አቅርቦቱ ነው የሚሉት ባለሙያዋ፣ ‹‹ነገር ግን እኔ በጥናቴ ባየሁት የልደታ የጋራ መኖሪያ አካባቢ በአብዛኛው ያለው ሽያጭ አልፎ አልፎ ዳቦ ቤት ከመሆኑ በስተቀር የመለዋወጫ መሳሪያ ነው:: ሌላው ቀርቶ ውስጥ ድረስ እንኳ ለመጠጥ ቤቶች የተከራዩ ናቸው:: በእርግጥ ለልደታ መርካቶ ቅርቡ ሊሆን ቢችልም የበለጠስ ቅርብ ቢሆን የሚለው ነው መታሰብ አለበት:: ሱቆቹ በራሳቸው ሲከራዩ በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነጋዴው ደግሞ ያንን ለማካካስ ሲል በአካባቢው ነዋሪ ላይ ዋጋ ጨምሮ ይሸጣልና ነዋሪው የመግዛት አቅሙን ይፈታተነዋል›› ሲሉ ያብራራሉ::
ጎን ለጎን መታሰብ ያለበት ነዋሪው የዕለት ተዕለት ፍጆታውን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝበት ሁኔታ መሆን እንዳለበት ነው ያመለከቱት:: እንደ እርሳቸው አነጋገር፤ መስራት የሚችሉ ህንፃዎች በመልሶ ማልማቱ ሰበብ አብረው እየፈረሱ ነው:: መልሶ ልማቱ ሙሉ ለሙሉ አካባቢውን በዶዘር ማንሳት አይነት ነው:: ይህ በመሆኑ ቢቆይ ሊያገለግል የሚችል ህንፃ ሁሉ አንድ ላይ እየተጠረገ ነው::
ለምሳሌ ለገሀር አካባቢ የተጀመረው የማደስ ስራን በዱባይ ትልልቅ ህንፃዎችን የሰራው ሰው ነው የጀመረው፤ ነገር ግን ለገሀር ጥግ ላይ የመርከብ ድርጅት መስሪያ ቤት አለ፤ ይህ መስሪያ ቤት ከሃያ ምናምን ዓመት በፊት የተሰራ ነው:: እንዲፈርስ ተደርገጓል፤ ቡፌዳላጋርም እንዲሁ እንደቅርስ ሊታይ የሚችል ቢሆንም ፈርሷል:: ስለዚህ ወደ መልሶ ልማቱ ሲገባ እያሳጣ ያለው ማህበራዊ ትስስሩን፣ ኢኮኖሚያዊና አካባያዊ ሁኔታውን ብቻ ሳይሆን ቅርሶችን ጭምር ነው ማለት ይቻላል::
‹‹ኢትዮጵያ ድሃ አገር ናት:: እነ ዱባይና መሰል አገሮች አፍርሰው መስራት ይችላሉ:: እኛ ግን ማገልገል የሚችሉ ህንፃዎችን ስለምንድን ነው አፍርሰን ከእሱ ባነሰ ጥራት ሌላ ለመስራት የምንቻኮለው›› የሚሉት ባለሙያዋ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አንዱ የሚታሙበት በጥራት እንደሆነም ይገልጻሉ:: ‹‹ስለዚህ ያለንን ጥሩ ነገር በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ሀብትን በአግባቡ መጠቀም አለብን:: እንዲህ አይነቱ አካሄድ ኢኮኖሚውን ሊጎዳ የሚችል ነውና ትኩረት ይፈልጋል››ይላሉ::
ከአካባቢ አኳያ የሚነሳም ጉዳይ እንዳለ ይጠቅሳሉ:: የተገነባው አካባቢ ሰው በለመደው አይነት ሁኔታ ነው ወይ የሚለውን ማየትንም ይጠይቃል:: ለምሳሌ መሬት ላይ ሲኖር የነበረውን ህብረተሰብ ባለ አራትና ከዚያ በላይ በሆነ ወለል ህንፃ ላይ እንዲኖር ሲደረግ ከነበረው የአኗኗር ባህሉ ጋር እንዴት ነው የተፈጠረለት ሁኔታ የሚለው መታየት አለበት:: ሊፍት በሌለበት እስከ 14 ፎቅ ድረስ የመስራቱስ ጉዳይ፤ የውሃና የመብራቱስ ነገር አቅርቦቱ ምን ያህል ነው የሚለው ሊስተዋል ይገባዋል::
መልሶ ማልማት በመጠኑም ቢሆን ለውጥ አምጥቷል የሚባለው የተወሰኑ ሰዎች የቤት ባለቤት መሆን መቻላቸው መሆኑን አርክቴክቷ ይጠቅሳሉ:: እነሱም በመጠኑም ቢሆን አቅም ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ:: በቀድሞ አካባቢያቸው የነበራቸውን ኢ-መደበኛ ስራም ቢሆን ትተው ስለሚሄዱ በሄዱበት አካባቢ ተመሳሳዩን አሊያም የተሻለውን ማግኘት እንደማይችሉ ፣ በዚህ የተነሳም በኢኮኖሚው ሲጎዱ እንደሚታዩ ያብራራሉ::
አንዳንዶቹ ወደ ቀደመው ሰፈራቸው መጥተው የድሮ ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተው ሲሄዱ እንደሚስተዋልም ነው ባለሙያዋ የሚናገሩት:: ወደ መልሶ ማልማቱ ይገባል የተባለውን የጎላ ሰፈር ነዋሪዎች ‹‹ሰፈሩን መልቀቅ ትፈልጋላችሁ›› ተብለው ሲጠየቁ ከ70 በመቶ በላይ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል:: ምክንያታቸውን ሲጠየቁ ደግሞ ‹ምንም ባይኖረኝ ጎረቤቴ ያበላኛል:: ቀሪ ህይወቴን እዚህ ማሳለፍ እንጂ የማላውቀው ሰፈር መሄድ አልፈልግም›› ነው የሚሉት::
ይህ የሚያሳየው ወደ መልሶ ልማቱ ከመግባቱ በፊት ህብረተሰቡን በአግባቡ ማወያየት እንደሚያስፈልግ ነው ይላሉ:: መንግስት ያደርግ የነበረውና የሚያደርገውም ሰፈሩ መልሶ እንደሚለማ መረጃ መስጠትና ያለውን አማራጭ ማሳየት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ አካሄድ ተቀይሮ መንግስት ህብረተሰቡን በጉዳዩ ላይ በአግባቡ ማወያየት እንደሚጠበቅበት ይገልጻሉ:: አካባቢው ከለማ በኋላ መልሶ ማምጣት አሊያ በቅርብ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጥናቱ ግኝት ማመላከቱንም ይጠቅሳሉ::
እንደ እጩ ዶክተር መስከረም ገለፃ፤ ይህ የከተማ መልሶ ማልማት ውጤታማነቱ አጥጋቢ አይደለም:: ሰዎች የሚፈልጉትን ገዝተው እንዳይጠቀሙ የአቅም ጉዳይ አንቆ ይዟቸዋል:: ስለዚህ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁሉንም ሰው የግድ የቤት ባለቤት ማድረግ አይጠበቅም፤ አቅሙ የማይፈቅድ አካል ይኖራልና:: ሌላ አማራጭ ለምሳሌ በቤት ኪራይ የሚኖርበት ሁኔታ መንግስት ማመቻቸት ይችላል:: ያደጉ አገሮችም ይህንን ዘዴ ይጠቀማሉ:: ምክንያቱም ብዙዎቹ በመልሶ ማልማት ምትክ የተሰጣቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት መክፈልም መኖርም ባለመቻላቸው እየተጠቀመበት ያለው ሌላ ሆኗል::
ሌላው ጠቃሚ ምክር ሐሳብ ነው ተብሎ የቀረበው መልሶ ለማልማት ህብረተሰቡን ማወያየትና እነርሱን ተሳታፊ ማድረጉ ነው:: ፍላጎታቸውንም ማጤን ያስፈልጋል:: በተጨማሪ ብዙ ችግር የሚፈጥረው የዲዛይንና የጥራትም ሁኔታ ነውና ከተሞችን በችኮላ መስራት ትርፉ ኪሳራ ስለሚሆን መጠንቀቅ ይገባል:: ምክንያቱም አንዱ ማሳያው አብዛኛው ሰው የጋራ መኖሪያ ቤት ሲሰጠው አፍርሶ የሚሰራ መሆኑ ነው::
‹‹ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን እንዳናጣ ማድረጉ ላይ ነው::›› ይላሉ:: ‹‹ለምሳሌ ከማይዳሰሱ መካከል የአኗኗር ዘይቤያችንንና አብሮነታችን ሲሆን፣ እሱን ማጥፋት ብዙ ነገር እንደማጥፋት ይቆጠራልና ቢታሰብበት መልካም ነው›› ብለው፤ የሚዳሰሱት ደግሞ መቆየት ያለባቸው ቤቶች አሊያም ሌሎች ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህም ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ ስለመሆኑ መክረዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
አስቴር ኤልያስ