ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮና ኮቪድ 19 ቫይረስ አሁንም መፍትሄ አልተገኘለትም። ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ እንጂ የመጥፋቱ የምስራች እየተሰማ አይደለም። ጊዜው ከምንም በላይ መተባበር፣ አንድነትና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ሰምቶ መተግበርን የሚጠይቅ ሆኗል።
ግለሰቦች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት፣ ባለሀብቶች እንዲሁም በጎ አድራጊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአንድነት እዚህ መቅሰፍት ላይ ለጦርነት ክንዳቸውን አንስተዋል። ነገር ግን አሁንም ከዚህ በበለጠ እንደ ሰንሰለት መያያዝና መተባበር የግድ ይላል። የአዲስ ዘመን የእሁድ ገፅ የኪነ ጥበብ አምድም በዚህ ዓለም አቀፋዊ ችግር ላይ ተጨማሪ ሊደረግ ስለሚገባው ርብርብ ለመጠቆም ወዷል።
በዋናነት የጥበብ ቤተሰቡ መሰል ችግሮችን እንደሌሎች ዘርፎች ለመጋፈጥ ምን ያህል አቅም አለው የሚለውን ጉዳይ በስፋት ይዳስሳል። ከዚህ ሌላ የጥበብ ፋይዳውንና ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ ችግሮች ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ ይዳስሳል። በተለይ ዘርፉ ላይ ያለው ባለሙያ ከራሱ አልፎ ለዜጎች ደህንነትና ዋስትና የሚሆኑ አበርክቶዎችን የመፍጠር አቅሙን በዚህ ዳሰሳ ላይ ለማሳየት ይሞክራል።
የኪነጥበብ ፋይዳ
ጥበብ መከሰቻዋ ብዙ ነው። ጥበብ ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖትና ጾታን አትመርጥም፤ አታበላልጥም። ከተቸገሩት ጋር መቸገሯ ከሚደሰቱት ጋር አብራ መደሰቷም ልዩ ያደርጋታል። ጥበብ ሁልጊዜም አንድ ቦታ ላይ አትቆምም። ከዘመኑ ጋር እየዘመነች ታድጋለች፤ ትጓዛለች። ጥበብ በጠቢባን ስቃይ አትደሰትም ይልቁንም ከስቃያቸው ተፈውሰው የደስታዋ ተካፋይ እንዲሆኑላት አጥብቃ ትሻለች። ሰዎች ሲደሰቱ ይበልጥ ትደሰታለች። ትፈካለች። ትጎመራለችም።
ምክንያቱም ጥበብ የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ ናትና። ለዚህም ነው በሰው ተፈጥራ ሰውን ለማገልገል የምትቆመው። ጥበብ ዘርፏም እጅጉን ሰፊ፣ ጥልቀትና ምጥቀትን ይጠይቃል። የስፋቷ ልክ የሚመዘነው ደግሞ ከዘርፎቿ በሚቀዳው ተለያይነትና ብዝሀነት ነው። ሰአሊው በብሩሹ፣ ደራሲው በብእሩ፣ ተዋናዩ በመድረኩ፣ ሞዛቂው በሙዚቃ መሳሪያውና በጉሮሮው ብሎም በመላ ሰውነቱ፣ ቀራፂው በጣቶቹና በመሮዎቹ፣ የፎቶግራፍ ባለሙያው በካሜራዎቹ፣ የፊልም ጥበበኞችም እንዲሁ በካሜራዎቻችው እያጫወቱ ነው የሚያወድሷትና የሚያንቆለጳጵሷት። በርካታ ንድፈ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሙያዎች በመውሰድ ራሷን ታበለጽጋለች። ያም ሆኖ ግን ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያላት ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው።
ሰብአዊነትና ጥበብ
ለመንደርደሪያ ያህል ስለ ኪነጥበብ ካወራሁ በቂ ነው። መንደርደሪያዬን አስከትዬ ወደተነሳሁበት ቁምነገር ላምራ። ቀደም ባሉት ዘመናት የኪነጥበብ ፋይዳ ብዙ መሆኑ ባይካድም የጠቢባኑ ኑሮ ግን ያን ያህል የሚያኮራና የሚወደድ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ጠቢባኑ መስጠትን እንጅ መቀበልን ከቁብ ሳይጥፉ ወደውና ፈቅደው ለመረጧት ጥበብ እጃቸውን በመስጠታቸው ከመቀበል ይልቅ መስጠትን ይመርጡ ነበርና ነው። በጥበብ ለመስጠት በጥበብ መሰጠትን የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ ሙያተኞቹም ከምንም ነገር በላይ ለሙያው ፍቅርን ነበር የሚያስቀድሙት። ለዚያም ነው ሙያተኞቹ በሰዎች አድናቆት ብቃታቸውን እየመዘኑ ከራሳቸው ኑሮ ይልቅ ለሌሎች ኖረው የሚያልፉት።
የታደሉ የሚባሉት ከሰው እጅ ላይ ሳይወድቁ እስከወዲያኛው ሲያሸልቡ ያልታደሉት ደግሞ ለመታከሚያ የሚሆን ቤሳ ቢስቲን ጥሪት እንኳ ሳይቋጥሩ አልጋ ላይ ይቀሩ እንደነበር ያለፉት ታሪኮቻቸው ይመሰክራሉ። ያኔ እንደተለመደው «እገሌ/እገሊት የሚባለው/የምትባለው የጥበብ ሰው መታከሚያ አጥቶ/አጥታ አልጋ ላይ ከዋለ/ከዋለች ይህን ያህል ጊዜ አሳልፏል/ አሳልፋለች። የቻላችሁትን ያህል አዋጡለትና/አዋጡላትና እናሳ ክመው/እናሳክማት» የሚለው የተለመደ አስተዛዛኝ ማስታወቂያ በየመገናኛ ብዙኃኑ ይተላለፋል።
የሌላው ከንፈሩን ይመጣል። ያለውም ለመር ዳት ይሯሯጣል። ሕመምተኛው የጥበብ ሰው ግን ሕመሙ ከጠናበት ወራትና ዓመታት ተቆጥረዋልና ከመዳኑ ይልቅ ሞቱ ተፋጥኖ ይችን ዓለም ላይመለስ ይሰናበታል። በፍቅር የወደቀላት የጥበብ ታሪኩም በነበር ዝግ ታሪክ የደመደማል።ይህ አሳዛኝ የጥበበኞች ታሪክ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሆኖ አልፏል። ዛሬ ዘመን ተለውጧል። ነገር ተገልብጧል። ምክንያቱም ጥበብ ከዘመኑ ጋር አብራ ዘምናለች፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ ጀምራለችና። ዛሬ የጥበብ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው እውቀታቸውንና ሙያቸውን በበጎ ተግባር ላይ ማዋል ጀምረዋል።
አሁን አሁን የጥበብ ባለሙያዎች በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በአምባሳደርነት በመሳተፍ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ይስተ ዋላሉ። የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ሥራ ከሚመሩት ባለፈ ዋናዎቹ አምባሳደሮች በስራቸው የምናውቃቸውና የምናደንቃቸው የጥበብ ሰዎች ናቸው። ሁሌም በየማእከላቱ የሚረዱትን አረጋውያን፣ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናትና ሴቶችን በሙያቸውና በገንዘባቸው ይደግፋሉ። በገቢ ማሰባሰቢያዎች ላይም ከማንም በፊት ቀድመው ከተፍ ይላሉ።
ድርጊቱ በቀላሉ የሚያመለክተን በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚገኙ የጥበብ ባለሙያዎች ያላቸውን ተቀባይነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በትክክለኛው መንገድ እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው። ዛሬ ለምናነሳው ቁልፍ ጉዳይ እንዲረዳን ብሎም ሃሳቡን በተጨባጭ ለመገንዘብ ከዚህ ቀደም ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የጥበብ ቤተሰቡ ስኬታማ ተግባራት ምን ምን ነበሩ የሚለውን በጥቂቱ ለማንሳት እንሞክር።
ለትውስታ
ዛሬ ለሚደረገው ጥረት የትናንቱ ስኬት የሞራል ስንቅ ይሆናል። በመነሻችን ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የጥበብ ባለሙያዎች ራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለህዝባቸው መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የተለያዩ አሳሳቢ ጉዳዮች በገጠሙ ቁጥር ከፊት በመሰለፍ አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። እየተደረገ ያለው ነገር ሙሉ ለሙሉ ማለት ሳይሆን ጅምሩ እጅግ አመርቂ መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነው።
ወደኋላ መለስ ብለን የጥበብ ቤተሰቡን ተሳትፎ ስናነሳ ቅድሚያ በህሊናችን ውስጥ የሚመጣው በህዳሴው ግድብ ላይ የተደረገው ተሳትፎ ነው። በርካቶች ዜጎች ከድህነት ይወጣ ዘንድ መተባበርና ግድቡን ከዳር ማድረስ አለበት ሲሉ አለኝታነታቸውን አሳይተዋል። ቀስቃሽ ኪነ ጥበባዊ፣ ስነጥበባዊና አስተማሪ መልክቶችን በጥበብ ሥራዎቻቸው በማንሳት በጎ ምግባር ላይ ተሳትፈዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ለልብ ህሙማን መርጃ ማእከላት በተናጠልና በጋራ የተለያዩ ድጋፎችን አሁንም ድረስ እያደረጉ ነው። በግል ጥሪታቸውን አውጥተው ታዳጊዎችን ከዚህ በሽታ እንዲያገግሙ ከማድረጋቸው ባሻገር ማህበረሰቡ ለህክምና ተቋማት ግንባታ እንዲተባበር ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅ መው ሲቀሰቅሱ ይስተዋላሉ። ጥቂት ቢሆንም ጥበባዊ ሥራዎቻቸውም ይህን መሰል ጉዳዮችን እንዲዳስስ በማድረግ ግንዛቤን ሲፈጥሩም አስተውለናል። የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሲመጡ የጥበብ ቤተሰቡ አስመስጋኝ ሥራዎችን ሰርቶ ከዜጎች ጎን እንደሚቆም አሳይቷል። ይህ የሚያመለክተው ማህበራዊ ግዴታን መወጣትና የሙያውን የመጨረሻ ግብ መረዳት ነው።
ዛሬስ ምን እንጠብቅ
ዓለም ሁሌም በለውጥ ላይ ነች። ለውጥ ደግሞ ጥሩውንም መጥፎውንም በአንድ ላይ ይዞ ይመጣል። ይህን ህግ ተከትሎ በምድራችን ላይ አዲስ ነገር ተከስቷል። ለጊዜው ለውጡ ጥሩውን ሳይሆን ክፉውን አጋጣሚ ነው ይዞ የመጣው። ምድር በአስጨናቂ ወረርሽኝ ተከባለች። ከሰው ወደ ሰው ተላልፎ የሞት መቅሰፍት የሚያመጣ በሽታ ገጥሟታል። ስልጣኔ፣ የጦር መሳሪያ ብዛትና የገንዘብ አቅም ሊገድበው አልቻለም። አሁን ሁሉም በአንድነት ስለ አንድ ጉዳይ ብቻ የሚያስብበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ተመራማሪውም ሆነ ተራው ዜጋ እኩል ወደየሚያምነው አምላክ አንጋጦ ምህረት የሚለምንበት ወቅት ነው። ጊዜው እጅግ ከባድ ነው።
ይህ ጊዜ ከየትኛውም ወቅት በተለየ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ በጥቅሉ አንድነትን ይፈልጋል። ለዚህ ነው የዛሬ ርእሰ ጉዳያችንን በቦጎነትና በትብብር ላይ አድርገን የጥበብ ድርሻዋን ለመስፈር የወደድነው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ይህን መሰል ማህበራዊ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ ከፊት የሚሰለፈውም ሆነ መቅደም ያለበት የጥበብ ቤተሰቡ ነው የሚል እምነት አለን። ቀደም ባሉ ጊዜያት በተግባር ያየነውም ይሄንኑ ነው። እስቲ ከወራት በፊት በዓለማችን ላይ ተከስቶ በቅርቡ ኢትዮጵያንም እየጎበኘ የሚገኘው ገዳይ ቫይረስ ‹‹ ኮቪድ 19›› ይዞት የመጣውንና የሚመጣውን ቀውስ ለመከላከል የጥበብ ቤተሰቡ ያሳየውን ወገንተኝነት እንመልከት። ይህን ካየን በኋላ ደግሞ በቀጣይ በሙሉ አቅም ችግሩን እንዴት መመከት ይኖርብናል ስለሚለው ጉዳይ እንዳስሳለን።
ፈጣን ምላሽ ከጥበበኞቹ
ይህ አደገኛ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ከታወቀ በኋላ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ግለሰቦች ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ። ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የሚያግዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከመስራት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችንም እያደረጉ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጥበብ ቤተሰቡ ይገኝበ ታል።
ለምሳሌ በብዙሃን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረ ፈውና በተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (በመድረክ ስሙ ቴዲ አፍሮ) 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መለገስ ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን ህዝብ የሚቆጠር ተከታይ ባለው ማህበራዊ ድረገፁም የበሽታውን አስከፊነት በመግለፅ ዜጎች እራሳ ቸውን እንዲጠብቁ አሳ ስቧል። በተመሳሳይ በተ ለያዩ የጥበብ ሥራዎቿ የምትታወቀው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬም ለተከ ታዮቿ የተለያዩ የምስልና የፅሁፍ መልክቶችን በማስ ተላለፍ ግንዛቤ ስትፈጥር ተስተውላለች።
ሌላኛዋ ተወዳጅ የጥበብ ቤተሰብ አርቲ ስት ሃመልማል አባተ ነች። ይህቺ ታዋቂ ግለ ሰብ ወደፊት ቫይረሱ ቢስፋፋ በሚል ለህክምና አገልግሎት እንዲውል በማሰብ መኖሪያ ቤቷን ሰጥታ የክፉ ጊዜ አጋርነቷን ማሳየት ችላለች። አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ለጌሪጊሲኖን የንጽህና መጠበቀያ በማበር ከት ለሌሎች ምሳሌ መሆን ችሏል።
እንዲሁ ጸጋየ እሸቱ የ40 ሺህ ብር ምግብ በቫይረሱ ለተጎዱ ወገኖች ለግሷል። የተለያዩ ፊልምና ቴአትር ቡድኖች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሰሩ ተስተውለዋል። የፊልም ባለሙያው እና የጉዞ አድዋ አስተባባሪው ያሬድ ሹመቴና ጓደኞቹ የበጎ ተግባር ሥራ ላይ ተሰማርተው በርካታ የቁስና የገንዘብ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ ናቸው።
ተጨማሪ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች
ከላይ እንደጠቀስነው የጥበብ ቤተሰቡ በፈጣን ምላሽ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ይህ ማለት ግን ከችግሩ አንፃር አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ነው ማለት አይቻልም። ቫይረሱ በፍጥነት ከመዛመቱና የሚያደርሰው ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ተደጋጋሚ ርብርብ የሚፈልግ ነው። በቀጣይ በኪነ ጥበብ፣ ስነ ጥበብ እና አጠቃላይ የጥበብ ቤተሰቡ ኃላፊነት ተወስዶ ሊከወን ስለሚገባው ተግባር እናንሳ።
ግንዛቤ
በተለይ ስርጭቱ በቀላሉ በሰው ንክኪ የሚተላለፍ ከመሆኑ አንፃር እያንዳንዱ ሰው የመተላለፊያ መንገዶቹን አውቆ እንዲጠነቀቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር መሰራት አለበት። ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የጥበብ ቤተሰቡ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ፈጠራ የታከለባቸውና እያዝናኑ የሚያስተምሩ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን ለዚህ ተግባር ማዋል ይቻላል። አሁን ላይ ወጥ ባልሆነ መንገድ አንዳንድ የምናያቸው በጎ ጅምሮች ቢኖሩም በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ መቀጠል ይኖርበታል።
ራስን መጠበቅ
ከዚህ ዓለም አቀፍ ተዛማጅ ቫይረስ ተወዳጅና ተፅዕኖ ፈጣሪ የጥበብ ቤተሰቦች እራሳቸውን ሊጠብቁና ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ሲሆን ዜጎች የእነርሱን ፈለግ የመከተል ልምድ አዳብረው በቀላሉ ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻል ያግዛል። በዓለማችን ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የጥበብ ቤተሰቦች በቫይረሱ እንደተያዙ አንዳንዶቹም ለህልፈተ ህይወት እንደተዳረጉ ሰምተናል። ይህ በዚህ አገር ቢከሰት ተፅእኖው ከባድ እንደሚሆን ተረድተው እራሳቸውን ሊጠብቁና አርአያ ሊሆኑ ይገባል።
ድጋፍ ማሰባሰብ
ይሄ ለዛሬ በኪነጥበብ አምዳችን በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ ላይ በጥበብ ቤተሰቡ መደረግ አለበት ብለን ያነሳነው ነጥብ ነው። በመሆኑም ከላይ እንዳነሳነው ችግሩ በተከሰተ ወቅት ድጋፋቸውን እንዳሳዩ ጥቂት ግለሰቦችና ስብስቦች በተጨማሪ በቅንጅትና በተደራጀ መልኩ ወጥ እንቅስቃሴ ሊደረግ ይገባል የሚል እምነት አለን።
በመሆኑም ለተጎጂዎች የሚሆን የህክምና መርጂያ መሳሪያ፣ ምግብ እና አልባሳትን ጨምሮ መሰል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብና ለሚመለ ከተው አካል ማስረከብ ትልቁ ድርሻቸው ይሆናል። ይህ ከተደረገ የማንወጣውና የማንደረምሰው የችግር ተራራ አይኖርም። ክፉውን ቀን ዛሬም እንደ ትናንቱ ተባብረን እንሻገረዋለን። ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2012
ዳግም ከበደ