ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ በታሪካቸው ከፍላጎታቸው ጋር የሚስማማ የፖለቲካ ወይም የአገዛዝ ሥርዓት ኖሮአቸው አያውቅም። በፖለቲካ ምክንያት የዜጎች ሕይወት ያልተቀጠፈበት፤ ደማቸው ያልፈሰሰበት፤ አካላቸው ያልጎደለበት፤ ሰላማቸውና ደህንነታቸው በአግባቡ የተከበረበት ጊዜ አልነበረም።ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ታሪክ ባብዛኛው የጦርነትና የብጥብጥ፤ የአመፅና የትርምስ እንጂ የልማትና የዕድገት፤ የሰላምና የመረጋጋት አይደለም የሚባለው። “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መፈክርን እየፈከረ ሥልጣን የያዘው ደርግ ራሱ ኢትዮጵያን በሰላም ማስተዳደር የቻለው ለጥቂት ወራት ብቻ ነው።
በእርግጥ “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም፤ በቀና መንፈስ ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው ስንኝ የደርግን የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ምኞት የሚገልጽ ብቻ አልነበረም።በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅኝትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋደዱበት ነው ማለት ይቻላል።በሰላማዊ መንገድ መጥፎ አገዛዝን አስወግዶ በዚያው መንገድ መልካም ሥርዓት በምትኩ መፍጠርን የመሰለ ሰናይ ነገር የለም። ያለመታደል ሆኖ ግን ከመፈክር አልዘለለም። ያለምንም ደም እንከኗን አውድመን ኢትዮጵያን እናስቀ ድማለን ያለው ደርግ ኢትዮጵያን በሰላም የመራው ምናልባት ከመስከረም ወር 1967 እስከ ህዳር ወር 1967 ብቻ ነው።ከመስከረም 1967 ጀምሮ እስከ ግንቦት 1983 የነበረው የ17 ዓመታት የደርግ አገዛዝና ከግንቦት 1983 እስከ መጋቢት 2010 ድረስ የነበረው የ 27 ዓመታት የኢህአዲግ አገዛዝ ከ44 ዓመታት በፊት ከወደቀው ዓጼያዊ ስርዓት የሚለዩት በቅርጽ እንጂ በይዘት አልነበረም።ሶስቱም በሕዝብ ድምፅ የተፈጠሩ አይደሉም፤ የሀገርንና የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል አድርገው የሚገዙ አልነበሩም፤ ጨቋኝና አፋኝ ነበሩ፤ በኃይል ወይም በመሣሪያ በመታገዝ የሚገዙ ነበሩ፤ ሕዝብን ከማፈን አልፈው በተለያዩ መንገዶች በመከፋፈል ሀገርን ያዳከሙ ሥርዓቶች ነበሩ፡፡
በሶስቱም ውስጥ የነበረው ጭቆና ከአንዱ ወደ አንዱ እየከረረ መጥቶ በኢህአዲግ ዘመን በመጠንም ሆነ በዓይነት ከመጨረሻው የእድገት ደረጃ ደረሰ።ሥርዓቶችን በመቃወም ሲነሳና ሲወድቅ የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ለኢህአዲግም ፋታ የሰጠ አልነበረም።በተለይ ወደ መጨረሻ በወጣቶች የተቀጣጠለው ተቃውሞና በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው በለውጥ ፈላጊነት ራሳቸውን ያደራጁ ዜጎች ባሳዩት እምቢታ ምክንያት ኢህአዲግ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ከአመራር ተገለለ።አሁን ሥልጣን ያለው የለውጥ ኃይል ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የት ድረስ እንደሚወስድ በውል አይታወቅም።የሀገራችን የፖለቲካ መርከብ ዛሬም በፖለቲካ ቀውስ እየተንገላታች ነው።ከማዕበሉ ተርፋ መልህቋን ከማይነቃነቅ መሬት (ነገር) ላይ የምትጥለው በሕዝብ ይሁንታ የሚቋቋም የፖለቲካ ሥርዓት፤ በሀገርና በሕዝብ ፍላጎት የሚመራ መንግሥት፤ ሕዝብን የሚያምንና በሕዝብ የሚታመን አስተዳደር ሲፈጠር ነው።
አሁን የሀገራችንና የሕዝባችን ጉዞ ያለ ጥርጥር ወደዚህ ሥርዓተ-መንግሥት፤ አመራርና አስተዳደር እያመራ ነው ብለን እናስባለን።ፖለቲከኞቻችንና ሊህቃኖቻችን ባንድ በኩል፤ የለውጥ አራማጆቻችን በሌላ በኩል ሀገራችንና ሕዝባችን ከሚፈልጉት ሥርዓት ያደርሱአቸው ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ መስጠት ያስቸግራል።የሚከተለው ትንተና ለጥያቄው መልስ ለማፈላለግ ይጠቅማል።ለትንተናው የምንጠቀምባቸው መረጃዎች የተገኙት ከንባብና ከምልከታ ነው።ይህ ጽሑፍ ሁለት ክፍሎች አሉት።አንደኛው ይኸው ራሱ ነው።በጥቅሉ መሠረታዊ በሆኑ የፖለቲካ ሥርዓት አፈጣጠርና ባሕርያት ላይ ትኩረት ያደርጋል።ሁለተኛው ወደፊት የሚመጣ ነው።በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርፎችና ኪሳራዎች፤ መፍትሔዎችና ተግዳሮቶች ላይ አጠቃላይ ቅኝት ያደርጋል።
ከአፈጣጠሩና ከማህበራዊ መሠረቱ እንነሳ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበረው ማህበራዊ መሠረት ጠባብ ነው።በሆነ ምክንያት ሥልጣን መያዝ የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የዘር ግንድን በማጣቀስ ወይም ከሆነ አካባቢ ተሰባስበው በሴራ ባደራጁት ቡድን ይፈጠራል።በለስ ቀንቶአቸው ሥልጣን ሲይዙ ሰፊውንና ግዙፉን የሀገሪቱን ሕዝብ በሚፈልጉት መልክ ለመምራት ሁለት ነገር ይገጥማቸዋል።አንደኛው ሕዝቡን በራሳቸው ልክና መጠን ለመስፈር በሚያደርጉት ጥረት አቅሙንና ፍላጎቱን ለማሳነስ ይሞክራሉ።የአገዛዝ ሥርዓታቸውን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁመና ጋር ለማመጣጠን ከመጣር ይልቅ ሕዝቡን ከራሳቸው ቁመና ልክ ለማስተካከል ያሳንሱታል። ሁለተኛ የራሳቸውን የአገዛዝ ሥርዓት ከሕዝቡ መጠንና አቅም ልክ ማደራጀት ይጠበቅባቸዋል።በአቅም ውስንነት የተነሳ ደግሞ ይህን ማድረግ አይችሉም።በዚህ ምክንያት ምርጫቸው የመጀመሪያው ብቻ ይሆናል።ይህም በራሱ የማይፈለግ ውስንነት አለው።ሕዝቡ ገዢዎች በሠፈሩት ልክ ላይገባላቸው፤ ገዢዎች ያሰቡትን ከመፈፀም ላይታቀቡ ትርምስ ይፈጠራል።
በእርግጥ ከታሪክ አንጻር ፖለቲካና የመንግሥት አመሠራረት በሌሎች ሀገሮችም በዚሁ መልክ የጀመረ ሊሆን ይችላል።ነገር ግን የብዙዎቹ እንደ እኛ ሀገር ፖለቲካ በተፈጠረበት ቦታ አልቀረም።ቶሎ ብለው ራሳቸውን አሻሽለውና አዳብረው ማህበራዊ መሠረታቸውን በማስፋት ሕዝብ ወደ ሚፈልገው ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ለውጠዋል።ይህን ያደረጉት በጉልበት ወይም በስምምነት፤ በጦርነት ወይም በሰላም ሊሆን ይችላል።ሁለቱም መንገዶች የተለያዩ ነገሮችን ያካተተ አቅም የሚጠይቁ ናቸው።በኢትዮጵያ ግን ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን የነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች የቅርጽ እንጂ የይዘት ዕድገት አላሳዩም።ሁሉም አንድ ዓይነት ጫማ ነበራቸው።በወደቀው ቦታ የሚተካው ሥርዓት የአሮጌውን ሥርዓት ጫማ አንስቶ በማድረግ በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ መረማመድ ይጀምራል።ዋና ሥራቸው የፖለቲካውን ማህበራዊ መሠረት ማስፋት ሳይሆን የሕዝቡን ግዝፈት ወይም ቁመና ማሳጠር ወይም ማጥበብ ነው።
ለመሆኑ ፖለቲካ ምንድነው? ያለ ፖለቲካ መኖር አይቻልም? ለምን ተፈጠረ ወይም ተፈለገ? ለራስ መገልገያ ነው ወይስ ሌላን ማገልገያ? ፖለቲካ የሚለው ቃል ለሥልጣን መታገልን፤ ሥልጣን መያዝን፤ በሥልጣን ሀገርና ሕዝብ መግዛትን ወይም ማገልገልን፤ ሥልጣን ማቆየትን፤ በሀገርና በሕዝብ ጉዳዮች ላይ የመወሰን አቅም ማግኘትን አጠቃልሎ የሚገልጽ ነው።ፖለቲካ የሥልጣን ጉዳይ ነው።ሥልጣን አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴ ለመገደብ፤ ዳር ድንበር ለማበጀት፤ ባሕርይውንና ተግባሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ነው።በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ ተወደደም ተጠላም ሥልጣን ከሕዝብ፤ ከቡድን ወይም ከአንድ ተቋም የሚሰጥ አደራ ወይም ኃላፊነት ነው።የሥልጣን መሠረታዊ ተልዕኮ ባለሥልጣኑ ሌላውን ሰው ማገልገል እንዲችል የሚሰጥ አቅም ነው።
ሁሉም ሰው መርካት የሚገባው ወይም ማርካት የሚፈልገው ፍላጎት አለው።አንዳች ዓይነት ፍላጎት የሌለው ሰው የለም።መኖርና ማደግ የሚቻለው ፍላጎት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መሟላት ሲችል ነው።ፖለቲካ የተፈጠረው በሰው ልጅ ፍላጎት ጥሪ ምክንያት ነው። ፍላጎቶች መርካት የሚችሉት የተፈለጉ ነገሮች መገኘት ሲችሉ ነው።ሰው መኖር ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለና የተሻሻለ ሕይወት ይፈልጋል።ሰላምና ፍቅር፤ ምቾትና ደስታ ያለበት ሕይወት የምን ጊዜም ፍላጎቱ ነው።ዓለም ግን የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች አሉባት።ሰላምን የሚያደፈርሱ ጦርነቶች፤ ፍቅርን የሚያጠፉ ጥላቻዎች፤ ምቾትና ደስታን የሚነሱ እኩይ ድርጊቶችና ኀዘኖች አሉ።ከእነዚህ ጉዳትና ጥፋት ከሚያስከትሉ ነገሮች መካከል አብዛኞቹ በሰዎች የሚፈጸሙ ናቸው።በተለይ በሰው ድርጊትና ባሕርይ ምክንያት የሚፈጠሩ እኩይ ነገሮች እጅግ የሚያሳስቡ ናቸው።የራሱን ሆድ ለመሙላት የሌሎች ወገኖች ሆድ ባዶ የሚያሳድር አለ።
ሰው የሚጠቅመውንና የሚመቸውን የሚያውቀውን ያህል የሚጎዳውንና የማይመቸውንም ያውቃል።ስለዚህ ሰዎች የሚፈልጉትንና የሚጠቅማቸውን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብርላቸው አደረጃጀት፤ የማይፈልጉትንና የሚጎዳቸውን ነገር የሚያስወግድላቸውን ማህበራዊ ተቋም መፍጠር ነበረባቸው። ባንድ በኩል ሥልጣን እንዲኖር የሚፈልግና የሚፈቅድ ማህበረሰብ አለ፤ በሌላ በኩል ሥልጣን ይዘው ማህበረሰቡን መምራት የሚፈልጉ ግለሰቦች አሉ።የሁለቱ የጋራ ፍላጎትና ስምምነት ፖለቲካን ፈጠረ።ይህ ማለት ለሥልጣን የሚታገሉም ሆኑ የማይታገሉ ሰዎች የፖለቲካ ፍላጎት አላቸው።ሰላምና ፍቅር የሚያስከብርላቸውን፤ ዕድገትና ልማት የሚያፋጥንላቸውን፤ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን የሚስጠብቅላቸውን፤ የሕግ የበላይነትንና የሀገር ልዕልናን የሚያሰፍንላቸውን የፖለቲካ ሥርዓት ይፈልጋሉ።ባጭሩ ፖለቲካ የተፈጠረው የብዙኃኑን ሕዝብ ፍላጎት ለማገልገል ነው።
ይሁን እንጂ በታሪክ ሂደት ውስጥ የታየው ሀቅ በተወሰነ መልኩ የዚህ ተቃራኒ ነው።ሥልጣን በበላይነት የመገደብና የመቆጣጠር አቅም ያለው በመሆኑ እንደ ሰዎች ፍላጎት ጥቅም ላይ ይውላል።ተገልጋይን ማገልገል የሚኖርበት ሥልጣን አገልጋይን እንዲያገለግል የተደረገበት ታሪካዊ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።ባለሥልጣን አገልጋይ ነው ወይንስ ተገልጋይ ነው? በአገልግሎት ሰጭና በአገልግሎት ተቀባይ መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ወሳኙ ፍላጎት የማነው? እዚህ ጋር ሁለት ፍላጎቶች አሉ።ተገልጋይ የአገልጋይን አገልግሎት የሚፈልግበት ምክንያት አለው።በተመሳሳይ መልኩ አገልጋይ ለተገልጋይ አገልግሎት መስጠት የሚፈቅድበት ምክንያት አለው።ሁለቱም ፍላጎት አላቸው፤ ወሳኙ ፍላጎት ግን የተገልጋይ ነው።የፖለቲካና ፖለቲከኛ እውነተኛ ባሕርይ ከዚህ ይመነጫል።የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተቋማት እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለባቸው።አመኔታ ማግኘት የሚችሉት የሚታመንና የሚያስተማምን አገልግሎት በመስጠት ነው።
ይሁን እንጂ በታሪክ ሂደት ውስጥ እንደታየው ሌላውን ማገልገል የሚኖርበት አገልጋይ ራሱ በተገልጋይ የሚገለገል ሆነ።ባልታወጀና ባልተጻፈ መንገድ ሕጉ ሕገ-ወጥ፤ ሕገ-ወጡ ሕግ ሆኖ አገልጋይን ተገልጋይ፤ ተገልጋይን አገልጋይ የሚያደርግ ያልታወጀ ሥርዓት ተፈጠረ። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው የሀገራችን ተረት የሥልጣን ዋና ተልዕኮ ራስን መጥቀም እንደሆነ ያመለክታል።ሹማምንቶች በሥልጣናቸው ለሚፈጽሙአቸው ሙስና እውቅና የሚሰጥ ይመስላል። ተረቱ ኢሞራላዊና የመልካም አስተዳደር ፀር ቢሆንም ሊሆን የሚችለውንና የሆነውን እውነት የሚገልጽ ነው። በእርግጥ ቀደም ሲል ተረት ነበር።በኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ ግን በተሟላ መልኩ እውነት ሆነ።
በኢትዮጵያ “ባለሥልጣን” የሚለው ቃል ራሱ አገልግሎት ሰጭው በተገልጋዩ ላይ በሕግ አግባብ ወይም ከዚያ ውጭ ገደብ የመጣል ወይም ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን ያለው መሆኑን ይገልጻል።በሌላ ሰው ላይ የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ሰው ሥልጣኑን በአግባቡ ወይም ያለ አግባብ የመጠቀም ዕድል አለው።በመሠረቱ አንድ ፀሐፊ እንዳለው “ሥልጣን የራስ ጥቅም ወይም የበላይ አለቆች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሳይሆን የሕዝብ ፍላጎትና ዕድገት ማገልገያ ነው::” ሙስና በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ግን ከላይ የተጠቀሰው ፀሐፊ እንደሚለው “አንድ ባለሥልጣን በሌሎች ሰዎች ላይ ያለው ሥልጣን ሊሰማው የሚችለው ከበሬታ በሚያገኝበት ጊዜ ሳይሆን የሌሎችን ሰዎች መንፈስ መስበር የሚያስችለው ሆኖ ሲያገኘው ነው።በሌሎች ሰዎች ላይ ሥልጣን ማግኘት ማለት እነዚህ ሰዎች የሚኖራቸውን ምርጫዎች ማሳጣት የሚያስችል አቅም መቀዳጀት ነው፡፡”
የኢትዮጵያን ሕዝቦች የፖለቲካ ፍላጎት የሚያረካ የፖለቲካ ሥርዓት በሀገራችን ተፈጥሮ የሚያውቅ አይመስልም። የኢትዮጵያና የሕዝቦችዋ ፍላጎትና ጥቅም፤ ክብርና ልዕልና ከማናቸውም ግለሰቦችና ቡድኖች በላይ ነው።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፍላጎት የሁሉንም ዜጎች ፍላጎት የሚያካትት ነው።ወደ አንድ ቡድን፤ ማህበረሰብ ወይም ፓርቲ ፍላጎት የሚጨፈለቅ አይደለም።ሀገሪቱ እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ ፍላጎት አላት።እነዚህ አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ፓርቲዎች ቁመና የማይወሰኑ ፍላጎቶች ናቸው።የኢትዮጵያንና የሕዝቦችዋን ፍላጎት ማዕከል ያላደረገ የፖለቲካ ቡድን፤ ኃይል፤ ፓርቲ ወይም ሥርዓት ይህችን ሀገር የመምራት አቅምና ቁመና አይኖረውም፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንጂ የሕዝብን ፍላጎት ማማከልና መግዛት የሚችል የፖለቲካ አስተሳሰብ የለም።ፖለቲካ ለሥልጣን መታገልን፤ ሥልጣን መያዝን፤ በሥልጣን ሀገርና ሕዝብ ማገልገልን፤ ሥልጣን መቆየትን፤ ሥልጣን ማቆየትን፤ በሀገርና በሕዝብ ጉዳዮች ላይ መወሰንን ወዘተ ያጠቃልላል።አንጻራዊ በሆነ መልኩ እውነተኛ ፖለቲካ አለ፤ ውሸተኛ ፖለቲካም አለ።ለሀገር ጥቅምና ክብር፤ ለሕዝብ ፍቅርና ሰላም ራሱን ያስገዛ የፖለቲካ ሥርዓትና ፖለቲከኛ ከሞላ ጎደል እውነተኛ ነው።በሌላ በኩል አብዛኛው በሀገርና በሕዝብ ስም የራሱን ጉዳይ ለመስራት የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ሥርዓትና ፖለቲከኛ አለ።ይህ መሠረታዊ ከሆነው የፖለቲካ ባሕርይ ያፈነገጠ ስለሆነ ውሸተኛ ሊባል ይችላል።በሀገራችን ሰፍኖ የኖረው የፖለቲካ ሥርዓትና አመለካከት ሁለተኛው ነው።ሁሉም ወይም ቢያንስ ባብዛኛው ራሱን ለሀገርና ለሕዝብ ፍላጎት ያስገዛ ቢሆን በሀገር ችግሮች ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠር ባላስቸገረ ነበር፡፡
ከላይ በተነሱት መሠረተ-ሐሳቦች ላይ ተመስርተን ዋና ጉዳያችን ወደ ሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዝለቅ።መነሻችን የሚሆነው አንድ ጎልቶ የሚታይ ሀቅ ነው።ኢትዮጵያ የብሔር-ብሔረሰብና ሕዝቦች ሀገር ናት።ጠንካራ ሀገርና መንግሥት ለመሆን የተበታተነውን በመሰብሰብ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር የግድ ነበር።ብዙዎች ፖለቲከኞች ያልዘነጉት አንድ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ማድረግ ነው።ይህን ለማድረግ ሁለት አማራጭ መንገዶች አሉ።አንዱ መንገድ ሁሉንም ወደ አንድ ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት ማቅለጥና ልዩነቶችን ማጥፋት ነው።ሁለተኛው መንገድ ሁሉንም ብሔር-ብሔረሰብና ሕዝቦች ከነልዩነታቸው አንድ ማድረግ ነው።የብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓቶች ምርጫ የመጀመሪያው ነው – የሁሉንም ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት ወደ አንድ ብሔር-ብሄረሰባዊ ማንነት ማቅለጥ።ልዩነቶች ፀጋ ሆነው አልታዩአቸውም፤ ወይም ይህን እውነት መቀበል አልፈለጉም።በየጊዜው የነበሩት ሥርዓቶች ይህን ማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ብስለት፤ ኢኮኖሚያዊ መሠረትና ወታደራዊ አቅም ግን አልነበራቸውም።በጥቂቶች አቅም ብዙኃኑን ወደ አንድ ለማቅለጥ ተሞክሯል።ይህ ያልተሳካ ሙከራ ሀገርንና ትውልዶችን ግዙፍ መስዋዕትነት አስከፍሏል።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሀገራችን የብዝሃነት ሀገር ነች። በርካታ ብሔር-ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሏት።በእንዲህ ዓይነት ልዩነቶች የታነፀችውን ሀገር የሚመራ የፖለቲካ ሥርዓት የብዝሃነትን ፀጋዎችና ተግዳሮቶች በትክክል የሚረዳ መሆን ነበረበት።ተልዕኮው የፈለገውን ነገር በሕዝብና በሀገር ላይ መጫን ሳይሆን በመሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር በመስማማት ብዝሃነትን በአንድነት ውስጥ፤ አንድነትን በብዝሃነት ውስጥ ማየት ነው።ሆኖም የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም ሲነሱት ከቆዩ ነገሮች መካከል አንዱ በአንድነትና ልዩነት (ብዝሃነት) መካከል ያለው አለመስማማት ነው።በብዝሃነት በምትታወቀው ሀገር ውስጥ በጠባብ ፍላጎትና አግላይነት መንፈስ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከሚያመጣው ልማት ይልቅ የሚፈጥረው ጥፋት ያመዝናል።ለአንድነት የሚዘምሩ ወገኖች ባንድ በኩል ሆነው ለልዩነት የሚታገሉ ወገኖች በሌላ በኩል ሆነው ሲፋጠጡና ሲፋለሙ ኖረዋል።ከነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶችም መካከል ብዙዎቹ ልዩነትን ለማዳከም ለአንድነት አጥብቀው ሰርተዋል።ሁሉም የየራሳቸውን ልዩ ገጾች (ብሄር-ብሄረሰባዊ ማንነታቸውን) ትተው ወደ አንድ (ገዢዎች ወደ መረጡላቸው ማንነት) ማንነት እንዲቀልጡ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል።
ይቀጥላል…
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ጠና ደዎ (ፒ.ኤች.ዲ)