ጋብቻ የቤተሰብ መመስረቻ መሰረታዊና ዋናው መንገድ ሲሆን ቤተሰብ ደግሞ የህብረተሰብና የሀገር መሰረት ነው። ስለዚህ ጋብቻ የተጋቢዎቹ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡና የሀገርም ጉዳይ በመሆኑ የህብረተሰቡና የመንግሥት ጥበቃና እንክብካቤ ያስፈልገዋል። በኢትዮጵያም ጋብቻ በመንግሥትም ሆነ በማህበረሰቡ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንዲደረግለት ቢያስቀምጥም ሲተገበር ግን አይታይም። በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ጋብቻ እንዴት ሊመሰረትና እንዴት መጠበቅ እንዳለበት እንዲህ ያስቀምጣል፡፡
አንቀጽ አንድ ቁጥር አራት ላይ ሶስት አይነት የጋብቻ ማስፈጸሚያ ሥርዓቶች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን እነሱም አንደኛ በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ ሁለተኛ በሃይማኖት ሥርዓት መሰረት የሚፈጸም ጋብቻና በባህል ሥርዓት መሰረት የሚፈጸሙ ጋብቻዎች ሆነው ተቀምጠዋል። እነዚህ እንደተጠበቁ ሆነው በውጭ ሀገራት የተፈጸሙ ጋብቻዎች በዛ ሀገር ጋብቻ አፈጻጸም ህግ መሰረት የተፈጸመ ከሆነና የዚህን የኢትዮጵያን ህዝብ ሞራል እስካልተቃረነ ድረስ ከላይ ከተገለጹት የጋብቻ ዓይነቶች ጋር እኩል እውቅናና ተቀባይነት አለው። ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ሥርዓቶች ጋብቻ ቢፈጸምም ሶስቱም አይነት የጋብቻ መፈጸሚያ ሥርዓቶች በቅድሚያ ሊያሟሏቸው የሚገባ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ።
እነዚህም አንደኛ ፈቃደኝነት ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነጻና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ መሆን እንዳለበት፤ ሁለተኛ እድሜ ሲሆን ጋብቻ ራሱን የቻለ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ ወደ ጋብቻ የሚቀላቀሉት ጥንዶች ይህን ኃላፊነት መቀበል የሚችሉ መሆን ስላለባቸው ወንዱም ሆነ ሴቷ አስራ ስምንት ዓመት የሞላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። (በዚህ በኩል በልዩ ሁኔታ ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ይህ እድሜ ሳይሞላ በፍትህ ሚኒስትሩ ከመደበኛ እድሜ ሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ የሚችልበት ሁኔታም አለ።) ሶስተኛውና የመጨረሻው ዝምድና ሲሆን ከህብረተሰቡ ሞራልና ከጤና ምክንያት የተነሳ ተጋቢዎች የቅርብ ዝምድና (የስጋም ሆነ የጋብቻ) ሊኖራቸው እንደማይገባም የተቀመጠ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ በየትኛውም አግባብ ቢፈጸም በኢትዮጵያ ህግ የጸና ጋብቻ ያለው አንድ ሰው ይህ ጋብቻ ጸንቶ እስካለ ድረስ ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማይችል በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ አሥራ አንድ ክልከላ ተቀምጧል።
በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ከላይ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል። እነዚህን ጋብቻዎች ተፈጽመውም ከሆነ እንዲቋረጡ በእቅድም ካሉ እንዳይፈጸሙ ወይም ህጋዊ እርምት እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነትና አደራ የተሰጠው ደግሞ ለመንግሥትና ለህብረተሰቡ ነው። እነዚህም በዓቃቤ ህግ በኩል እና በተጋቢዎቹ ዘመዶችና በሌሎች ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ የህጻናትና ሴቶች መብት አስከባሪ ድርጅቶችና በመሳሰሉት የህብረተሰቡን ጥቆማ ጨምሮ የሚከናወኑ ናቸው። የመቃወሚያው መሰረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ከሆነ ይህንን ቀድሞ የጸና ጋብቻ ያለው ወይንም ያላት ባለትዳር ወይንም ዓቃቤ ህግ ሲሆን አቤቱታው የሚቀርበው ለፍርድ ቤት እንደሚሆን ተቀምጧል። በዚህ መልኩ በትዳር ላይ ትዳር መመስረት የተመሰረተም ከሆነ ህጋዊ ውሳኔ ማግኘት እንዳለበት በህግ የተቀመጠ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በገጠርም ሆነ በከተማ ችግሩ በስፋት ይስተዋላል። በዚህ ደግሞ የችግር ተጋላጭ የሚሆኑት ልጆችና እናቶች ናቸው። በርካቶች ደግሞ እንኳን በገጠር በከተማም ተቀምጠው በቂ የህግ እውቀትና አለሁ ባይ ዘመድ ከሌላቸው በችግር ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ። እንዲህ አይነት ችግሮች ከገጠሟቸው መካከል ወይዘሮ እቴነሽ እንዳለ አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ እቴነሽ እንዳለ የሚኖሩት እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ነው፡፡ አምስት ልጆችን ቅጠል እየነገዱ በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ። አገር ቤትም አዲስ አበባም እያሉ ትምህርት አልተማሩም፤ ዛሬ ላሉበትም ሁኔታ አለመማራቸውንና አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱ በወቅቱ ምክር የሚለግስ ዘመድ አዝማድ በአጠገባቸው አለመኖሩ መሆኑን እንደ አንድ ችግር ያነሱታል። ብማር ኖሮ አንዳንዶቹን ችግሮቼን በወቅቱ ሳይባባሱ ለመቅረፍ እችል ነበር፤ ነገር ግን ያልተማረ ሰው መንገድ አያውቅምና ዛሬ ላለሁበት ችግር ተዳረኩ ሲሉ ያሳለፉትን ጊዜና አሁን ያሉበትም ሁኔታ እንዲህ ይተርካሉ።
“ተወልጄ ያደኩት በደቡብ ክልል ዶርዜ ወቀተ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ በቤተሰባችን አምስት ልጆች ያለን ሲሆን ቤተሰቦቼ በአርሶ አደርነት የሚተዳደሩ ናቸው። እድሜዬንና ጊዜውን በትክክል ባላስታውሰውም በልጅነቴ ነበር የተሻለ ኑሮ ለመኖርና ቤተሰቦቼንም ለመርዳት አክስቴ ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት። እዚህ ከደረስኩም በኋላ አክስቴ በተደላደለ ኑሮ ላይ ስላልነበረች እሷንም መደገፍ ስለነበረብኝ ከእንጠጦ ማርያም ጫካ በየቀኑ እንጨት እየለቀምኩ ተሸክሞ በማምጣት መሸጥ ጀመርኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ዓመታትን ካሳለፍኩ በኋላ የዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት እኖርበት በነበረው አካባቢ በነበረች አንድ ጓደኛዬ አስተዋዋቂነት ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመርኩ። ብዙም ሳንቆይ በየቀኑ እንገናኝ ስለነበር ጓደኛዬ ‘ትዳር አልመሰረትኩም፤ ጓደኛም የለኝም፤ የምኖረውም በቤት ኪራይ ነው፤ ለምን አብረን አንኖርም? የሚል የትዳር ጥያቄ ያቀርብልኛል።’
በነገሩ ቁጭ ብዬ ካሰብኩበት በኋላ በየጫካው ብዙ ፈተናዎችን አልፌ የምለቅመው ቅጠል በገበያ ቢውልም ከእጅ ወደ አፍ ጥቅም አልፎ ጥሪት ለመቋጠር አላስቻለኝም፤ ስለዚህ ከአንድ ሁለት ይሻላል ብዬ በግሌ ሀሳቡን ተቀበልኩ። ከዛም በኋላ ጓደኞቼንም አክስቴንም ያለውን ነገር አስረድቼ ሳማክራቸው ሃሳቤን ተቀብለው እንዳገባ መከሩኝ። እናም እኔም መስማማቴን ነግሬ ቤተሰብ ማወቅ ዘመድ አዝማድም መስማት ስለነበረበት በወግ በማእረግ ለቤተሰብ ሽማግሌ ተልኮ እንዳቅም በተዘጋጀ ድግስ ፊርማ ተፈራርመን ወደ ትዳር ገባሁ። ባለቤቴ በሸማ ሥራ ሞያ ስለነበረው እኔ አንዳንድ ጊዜ ከጫካ እንጨትና ቅጠል ለቅሜ እየሸጥኩ እሱም የሰራውን እያመጣ ኑሯችንን መግፋት ጀመርን።
ነገር ግን በዚህ ሁኔታ የጀመርነው የሞቀ ትዳር ጥቂት ዓመታትንም ሳያሳልፍ የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሙት ጀመር። የመጀመሪያው ፈተና የዛሬ አሥራ ሰባት ዓመት እኔ የመጀመሪያ ልጄን በወለድኩበት ወቅት ባለቤቴ እንደ ወትሮው እቤት እቤት ማለቱን እየቀነሰ መጣ። በአንዳንድ ነገሮችም ከተለመደው እንቅስቃሴ የተለዩ ችላ ማለቶችን ብመለከትም ፍቅር እንደጀመሩት አይዘልቅም በሚል አንድ ቀን ይስተካከላል በማለት ከቀን ወደ ቀን እየጠበኩ ብቀመጥም ነገሮች እየባሱ እንጂ አልለወጥ አሉ። የእኔንና የባለቤቴን ግንኙነት የሚያወቁ ሰዎችም ምናልባትም እሱ ገጠር ሌላ ትዳር መስርቶ ሊሆን ስለሚችል ለምን አታጣሪም? ሲሉ ጠቆም ያደርጉኛል። እኔም ነገሩን ወደኃላ መለስ ብዬ ሳስብ በዓመት ከሶስት ጊዜ በላይ ገጠር የሚሄደውና እዛም የሚቆየው ጊዜ ረዘም ያለ በመሆኑ ጥርጣሬ ገብቶኝ ነገሩን ሳጣራ እውነት ሆኖ አገኘሁት። ለካስ ባለቤቴ በተመሳሳይ ወቅት ትዳር መስርቶ ስለነበር እኔ በወለድኩበት ተመሳሳይ ወቅት ገጠርም ሌላ ካገባት ሚስቱ ልጅ ተወልዶ ነበር። በሌላ መንገድ ያረጋገጥኩትን ሀቅ ባለቤቴ አዲስ አበባ ሲመጣ ስጠይቀው ያለ ምንም ማመንታት ነገሩ እውነት እንደሆነ በማመን፤ ነገር ግን ሁለተኛው ትዳር የተመሰረተው ከእነሱ ጋብቻ በኋላ እንደሆነ በመንገር እንዲህ ሲል አስተባበለኝ። ‘ሥራም እየሰራሁ በመሆኑ ለሁለቱም ቤተሰብ ቀለብም ሆነ አስፈላጊውን ነገር አሟላለሁ፤ ስጋት አይግባሽ በማለትና ቃል በመግባት’ የቤተሰቡ ህይወት ባለበት የሚቀጥልበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ።
አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ሳስበው እኔ እውቀት የለኝም እንጂ ግንኙነታችን መቋረጥ የነበረበት ይህን ጊዜ ነበር። ነገር ግን አላደረኩትም፡፡ ይልቁንም በባህላችን መሰረት አንድ ሰው በይፋም ሆነ በድብቅ ትዳር ከመሰረተና ልጅች ከወለደ ከሁለቱም የተወለዱትን ልጆች ማስተዋወቅ ግዴታ በመሆኑ አባትየው ይህን እንዲያደርግ ስላስገደዱት እንድሄድ ይጠይቀኛል። እኔም ጥሪውን ተቀብዬ ሀገር ቤት ድረስ በመሄድ ከሁለተኛ ሚስቱና ከልጁ ጋር ተዋውቄ ሰንብቼ መጣሁ። በዚህ ሁኔታ ከባለቤቴ ሚስት ጋር የጀመርኩት ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቶ ከዓመታት በኋላ እሷን የገጠር ኑሮ አልመች ሲላት እኔ ጋር በመምጣት ስምንት ወር እስከመቀመጥ ደርሳለች። እዚህ ቆይታ ስትሄድም በጣም ተቀራርበንና ተዋደን ስለነበር ልብስ ገዝቼ የምትፈልገውን አድርጌ ወደ አገር ቤት ላኳት።
ከባለቤቴ ጋር ያለው ግንኙነት ግን እንደዚህ በሰላም መቀጠል አልቻለም፡፡ በሸማ ሥራ ሁለት ቤተሰብ ማስተዳደር አስቸጋሪ እየሆነበት ይመስለኛል፡፡ ካለፍ አገደም ከገንዘብ ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንያቶችም ችግር እየተፈጠረ እስከ መጨቃጨቅ እንደርስ ጀመር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይብስ ብሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጠኝን የቤት ወጪ እየቀነሰ የቤት ኪራይ ብቻ ይቆርጥ ጀመር፡፡ ይህንንም አንዴ ሲሰጠኝ አንዴ ሲያቋርጡ ጭቅጭቁም ስለሰለቸኝ ጨርሼ እንደቀድሞው ወደ ቅጠል ለቀማው ገባሁ። በዚህ ሁኔታ አንዴ ስንታረቅ አንዴ ስንጣላ ዓመታትን አሳለፍን፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም እኔ ሶስት ልጆችን ወልጄያለሁ። ይህም ሆኖ በእኔ በኩል እሱ ባይረዳኝም እንደምንም ልጆቼን አስተምሬ አንድ ቦታ አደርሼ ለራሳቸውም ሆነው ለኔም ይተርፋሉ ብዬ በማሰብ እሱ ካመጣ እየተቀበልኩ ካላመጣም እራሴ እየሞላሁ ኑሮዬን መቀጠል እንዳለብኝ ወሰንኩ። በእነዚህ ዓመታትም ጫካ እየሄድኩ ቅጠልና ጭራሮ ለቅሞ ከመሸጥ ባለፈ በየሰው ቤት የልብስ አጠባና ሌሎች የጉልበት ሥራዎችን ካለእረፍት እሰራ ነበር።
በአንድ ወቅትም ቅጠል መሰብሰብም ይከለከል ስለነበር የአዲስ አበባው ኑሮ አስቸጋሪ በመሆኑ ምን አልባት ገጠር ከተሻለ ብዬ ትልቁን ልጄን አዲስ አበባ ከአባቱ ጋር በማስቀመጥ እኔ ገጠር ገብቼ ለመኖር ሞከርኩ። ነገር ግን እዛም ነገሮች እኔ በልጅነቴ እንዳስቀመጥኩት ሳይሆን ሁሉም ነገር አዲስና ውድ ሆነው ስለገኘኋቸው ከወራት ቆይታ በኋላ የወሰድኳቸውን አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆቼን ይዤ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። በዚህ ወቅት ደግሞ ሶስተኛ እርጉዝ ነበርኩ። ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ግን የጠበቀኝ ሌላ አዲስ እንግዳ ነገር ነበር። ባለቤቴ በድጋሚ ሶስተኛ ሚስት ገጠር አግብቶ ትዳር መስርቶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መኖር ጀምሮ አገኘሁት።
ለካስ ባለቤቴ እኔን ብቻ ሳይሆን እንደ እህቴ ከማያት ሁለተኛ ካገባት ሚስቱም ጋር የነበረውን ግንኙነት እያቋረጠ ነበር። እሷ ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ መጥታ ሰንብታ ሄዳ ነበር። ከዛ በኋላ ከእሱ ጋር መስመማት ስላልቻለች አንዱን ልጅ ትታ ከቤት ወጥታ ቀርታለች፡፡ የት እንዳለችም አይታወቅም፡፡ አንዱ ልጅ የነበረው ደግሞ አያቶቹ ጋር ነበር። አዲሷ ሚስትና ልጁ ግን መስማማት አልቻሉም፡፡ ልጁም ብዙ ጊዜ እየተቸገረ እንደሚኖር ይነግረኛል፡፡ እኔም ካለፍ አገደም በማየው ነገር ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮችን አስተውል ነበር። ብዙ ጊዜም ልጁ ለመጥፋት እየሞከረ ይዘው ይመልሱት ነበር ። በዚህ መካከል በዚሁ ጉዳይ የተነሳ የባለቤቴ እናትና ሶስተኛ ሚስቱ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸውና ችግር ስለተፈጠረ ልጁን ከቤት እንዳስወጡት ሰማሁ። እናት የሌለውን ልጅ እንዴት ከቤት ታስወጡታላችሁ፤ ህጻን ልጅ ነው! እናቱ የት እንዳለች እንኳን እሱ እኛም አናውቅም ብዬ በማምጣት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ትምህርት አስጀምሬው አሁን አምስተኛ ክፍል ደርሷል። ይሄ ሁላ ሲሆን ከባለቤቴ አገኝ የነበረው እሱ ሲፈልግ ለዚያውም አንዳንድ ጊዜ እየተቋረጠ የሚሰጠኝን የቤት ኪራይ ብቻ ነበር። እናም በዚህ የኑሮ ውድነት አምስት ልጅ ብቻዬን ይዤ እያስተማርኩ ማስተዳደር ስላቃተኝ በቋሚነት ቀለብ ወይንም ቤት ኪራይ እንዲሰፍርልኝ ለማድረግ ፍቺ ጠይቄ ወደ ፍርድ ቤት አመራሁ።
በፍርድ ቤትም የቀረበውን ፍቺ ካጸደቀ በኋላ ለልጆች ማሳደጊያ በየወሩ አንድ ሺ ብር ቀለብ እንዲሰፍርና አንደኛውን ከሌላ የሚወለደውን ልጅ ራሱ እንዲያሳድግ ወሰነበት። እሱ ግን አንደኛውን ልጅ እኔ ማሳደግ አልችልም አይመለከተኝም ብትፈልጊ አውጥተሽ ጎዳና ጣይ በማለት የተወሰነበትንም የልጅ ማሳደጊያ ለመቁረጥ ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል። ይህን ልጅ እስካሁን አሳድጌ እናቱ ሳትኖር የት እጥለዋለሁ ብዬ ልጁን ይዤ ተቀመጥኩ። በቀለብ በኩል ፍርድ ቤቱ የወሰነልኝንም በወረዳው ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በኩል በመከራከር እንዲከፍል አስደረኩት።
እስከ ቅርብ ጊዜ ቅጠል በመልቀም እሱም ሲከለከል ቀን ሥራ እሰራ ነበር፡፡ ሴፍቲኔትም ተመዝግቤ ስሰራ ቆይቺያለሁ፡፡ እስካሁንም የልጆች የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና ምሳ የሚጠቀሙት ከመንግሥት ነው። አሁን ደግሞ በሴቶችና ህጻናት በኩል አሥራ አንድ ሆነን ተደራጅተን በሶስት ቡድን ውሃ ቆሎ ማስቲካ ካርድ እንሸጣለን፡፡ ይህ ተራ የሚደርሰን ከአንድ ወር በኋላ በመሆኑ ቀሪውን ጊዜ ስበረታ ስበረታ ቅጠልና እንጨት እየለቀምኩ እሸጣለሁ። ከህመም ጋር በተያያዘ አሁን የጤና ችግር ስለገጠመኝ እንደ ከዚህ ቀደሙ ልብስ ማጠብና ሌሎች ከባድ ሥራዎችን ግን መስራት አልችልም።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በቅርቡ ደግሞ ሌላ ተደራቢ ችግር ገጥሞኛል በአንድ ወቅት ከእንጦጦ ተራራ በርከት ያለ ቅጠል ተሸክሜ ስመጣ ያገኙኝ አርቲስቶች ችግሬን ጠይቀው ተከራይቼ የሚኖሩበት ቤት አንዲት መአድ ቤት በቆርቆሮ ሰርተውልኝ ነበር። ያቺ መአድቤት ግን ለእኔ ሌላ ጦስ ይዛብኝ መጣች፡፡ የነበርኩበትን ቤት ያከራዩኝ ሰዎች ቤቱ የቀበሌ በመሆኑ ነገ የእኔ ነው ትላለች በሚል ቤቱን እንድለቅ አደረጉኝ። ሳላስበው ለቀሽ ውጪ ስላሉኝና ስላስገደዱኝ አሁን ያለሁት በአካባቢው አንድ በጎ አድራጊ አስጠግተውኝ እኔ ሶስት ልጆቼን ይዤ መአድ ቤት ውስጥ ስሆን ሁለቱን ልጆች የማሳድረው ያስጠጉኝ ሰዎች ቤት ነው። በዚህ መሀልም የተሰራው ቤት ለሰዎቹ ስለቀረ አፍርሼ ብወስድ እንኳን ብዬ በክርክር ላይ እገኛለሁ” ሲሉ አጫውተውናል፡፡ የወይዘሮ እቴነሽ እንዳለ ህይወት በዚህ ሁኔታ ቀጥሏል፤ ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ