ወይዘሮ ሐረጓ ዓባይ ትባላለች፤ እዚሁ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገች፤ እንደማንኛውም ልጅ ተምራ የሙያ ባለቤት የሆነች ቢሆንም፤ ህይወት ለሁሉም ቀና አይደለችምና ያለ አባት የሚያሳድጓቸውን ሁለት ልጆች ለማሳደግ ስትልም የሴተኛ አዳሪነት ኑሮን ተቀላቀለች። ነገሮች ሲብሱም ከልጆቿ ጋር ለጎዳና ህይወት ተዳረገች። የጎዳና ህይወት ደግሞ እርሷን ለጫት፣ ሲጋራና አልኮል ሱሰኝነት ሲዳርጋት፤ ህይወቱ ከባድና እንቅልፍ አልባ ዙረት ስለነበረውም ከፖሊስ ጋር መባረሩም ሌላ ፈተና ነበረው።
በህይወት ውስጥ አንድ የቀን ጎዶሎ ማንነትን እንደሚያበላሽ ሁሉ፤ አንድ የህይወትን መልካም አጋጣሚን ይዛ የምትመጣ ቀን ትኖራለች። እናም ሐረጓና መሰል ጓደኞቿ በጎዳና ኑሮ የተጎሳቆለ ማንነታቸውን ይዘው አንድ ቀን ያገኟትን ሳንቲም ይዘው ሱሳቸውን ሊያስታግሱ ከሚችሉበት ጠጅ ቤት ይገባሉ። እዛ ሆነው ህይወት እስከመቼ በጎዳና ትቀጥላለች በሚል የሀሳብ መብሰልሰል ውስጥ እያሉ ስለ ዘ-ኢትዮጵያ ማህበር ሲነገር ይሰማሉ። ወዲያውም ወደስፍራው ለመሄድና ቢያንስ ለልጆቿ የሚበላ ነገር የምታገኝበትን እድል ለማመቻቸት ወስና ሄደች።
እዛም ተቀብለው የሚበሉትም፣ የሚለብሱትም፣ የሚያርፉበትም ተሰጣቸው። ከሳምንት ቆይታ በኋላ ሙያ እንዳላት በማሳወቋ በሙያዋ የምትሰራበት እድል ተመቻቸላት። ይሄን ስታስረዳም፤ ቀደም ሲል የሲንጀር ሙያ ያለኝ ቢሆንም በችግር ምክንያት ልሰራበት አልቻልኩም ነበር፤ አሁን ሲንጀርና ጣቃ ጨርቅ ተገዝቶ ተሰጥቶኝ እየሰራሁ ነው። እናም አሁን በማህበሩ መደገፍ በመቻሌ፣ በጎዳና የተለመዱ ሱሶች ተወግደው፤ ከጎዳና ወደ ቤት፤ ከጎዳና ትርፍራፊ ምግቦች (ቡሌ) በቤት ውስጥ ሰርቶ ወደመብላት ተሸጋግሬያለሁ፤ ከሴተኛ አዳሪነት ወደ በሙያ ሰርቶ አዳሪነት መለወጥ ችያለሁ። ለልጆቼም ቀለብ ከማህበሩ፣ ዩኒፎርምም ከመንግሥት እያገኙ መማር ችለዋል፤ ስትል ታስረዳለች።
የጎዳና ህይወት ከረሃብ፣ ከብርድ፣ ከሱስና ሌሎች አስከፊ ህይወቶቹ በተጓዳኝ ከመደፈር ጀምሮ ሌሎች የሰቆቃ ኑሮን ለመግፋት ያስገድዳል። ሆኖም አንዱ የሞቀ ቤት ሆኖ ሌላው ጎዳና ላይ በብርድና በተባይ መሰቃየቴ፤ አንዱ ጠግቦ ሲያማርጥ ሌላው ትርፍራፊ እየለቀመ መመገቡ፤ ወዘተ. ጉዳዮች በቃ ሊባሉ ይገባል። ለዚህ ደግሞ እንደ ዘ-ኢትዮጵያ ማህበር አይነቶቹ የወደቀና የተረሳውን ጎስቋላ ዜጋ የሚያነሱa አካላት ሊበራከቱና ሊታገዙ ያስፈልጋል። ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ወይዘሮ ዝናሽ ቦንሳ፣ በተመሳሳይ እዚሁ ተወልዳ ያደገች ሲሆን፤ እናትና አባቷ ስላልነበሩ በወንድሟ እጅ ነው ያደገችው። ይሁን እንጅ ከወንድሟ ሚስት ጋር መስማማት ባለመፈጠሩ ዱላና መሰል ችግሮች ሲበረቱ ህይወት መልኳን ቀየረችባት። ችግሩ ሲበረታም ከቤት ወደ ውጪ ወጣች፤ በአቻዎቿ ግፊትም እኩል ክፍያ በሚባል አሰራር ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሥራ ገባች። ሥራውም ብዙ የሴት ልጅ ፈተናዎች የሚገለጹበት፤ ዱላና በጉልበት ያለ መከላከያ መደፈር፤ በምላጭ መተልተልና ሌሎችም ችግሮች የሚያጋጥሙበት ነው። ይህ የመገደድና በጉልበት የመደፈር ሂደቱም ያልጠበቀችውን ልጅ አሳቀፋት፤ መጠጣትና መቃምን የመሳሰሉ ሱሶችንም አለማመዳት።
አንድም ራሷን ለማቆየት፣ አንድም ለእኩል ክፍያ የሚጠበቅባትን ገንዘብ መስጠት ስላለባት በወለደች በሶስተኛ ቀኗ ሥራ መጀመሯን የምትናገረው ዝናሽ፤ ይህም ሳትበላም መኖር፣ ሳትከፍልም ማደር አትችልምና ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን አንዲት ጎስቋላ ቤት በመከራየት ልጇን በሳንቲም የሚይዝላት ሰውጋ በመተው ሥራውን በግሏ መስራት ጀመረች። በዚህ የህይወት ፈተና ውስጥ ሆና ስለ ዘ-ኢትዮጵያ ትሰማለች። በስፍራው ሄዳም በአብረሃም እንግድነት ምግብ ትመገባለች፤ በማግስቱም ድጋፍ እንዲደረግላት ትጠይቃለች። ማህበሩም ያለችበትን ሁኔታ ተመልክቶ የተሻለ ቤት ተከራይታ እንድትኖር ገንዘብም የቁስም ድጋፍ ይደርግላታል። ከሱስ እንድትላቀቅም የሚያስችል ሰፊ የትምህርትና የምክር አገልግሎት ተሰጣት። በዚህም በ1ሺ500 ብር ቤት በመከራየት፣ አስቤዛ በመግዛትና የቤት ዕቃ በማሟላት እንዲሁም የእጅ ገንዘብ በመስጠት ከነበረችበት ህይወት እንድትወጣ ሆነች። ዛሬም ድረስ የቤት ኪራዩም ሆነ የምግብ አገልግሎቱን ከማህበሩ የምታገኝ ሲሆን፤ ማህበሩ ራሷን እንድትችል ተደጋጋሚ ድጋፍም እያደረገላት ይገኛል። በዚህም የጉልት ሥራንና ሌሎችም የእለት ሥራዎችን ብትሞክርን ከደንብ ማስከበር አባላትም ሆነ ሌሎች የሚደርስባቸው መሳደድ ሥራቸውን በሚፈለገው መልኩ እንዳይሰሩና ከእርዳታ እንዳይላቀቁ አድርጓቸዋል።
ሆኖም እንዲህ አይነት እንደ ውዳቂ ተቆጥረው ከሰው ጎራ የወጡ እስኪመስል የተጎሳቆሉ ወገኖችን እንዲህ ሰብስቦ የሚሰራ ማህበር ስሰራና ዜጎችን መታደግ ሲችል፤ መንግሥት ደግሞ እነዚህን አካላት ሊያግዝና ተደጋፊዎችም የተሻለ ራሳቸውን ችለው የሚሰሩበትን እድል መፍጠር ቢችል መልካም ነው። ምክንያቱም እነዚህ ማህበራት መንግሥት ሊሰራ ያልቻለውን እያደረጉ፤ ዜጎችን ቀና አድርገው እያስታወሱ ስለሆነ ለእነርሱም ድጋፍ፤ ለተነሱትም ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የሥራ አካባቢ ሊፈጥርላቸው ይገባል። ይህ ሲሆን የቀደሙት ራሳቸውን እየቻሉ ሲወጡ አዳዲስ ተነሺዎች እንዲታገዙና እንዲያገግሙ፤ ሌሎችን መደገፍ የሚችሉበት እድልም ይፈጠራል።
አያቱ የሐረርጌ አካባቢ ሰዎች እንደሆኑ የሚናገረው ወጣት መሐመድ ጁማ በበኩሉ፤ እናትና አባቱ እንደሌሉ፣ ሰባተኛ አካባቢ 17 ቀበሌ ያደገና ትምህርቱንም አንድ አባት ከጎዳና ላይ አንስተው እንዳስተማሩት ይናገራል። ከልጅነት የጀመረው የህይወት ፈተናም አድጎ እንዳልተለየውና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው እንዳደረገው ይገልጻል። ይህ የህይወት ውጣ ውረድና ራስን ያለመግዛት ችግር ደግሞ የተሳካ ኑሮና ትዳር እንዳይኖረው፤ አገርን ሊያገለግል ከወጣበት ከመከላከያ አባልነት ኮብልሎ እስከመውጣት እንዳደረሰው ይናገራል።
ይህ የህይወት ውጣ ውረድ፣ የኑሮና የትዳር አለመስመር፣ የነገሮች መደበላለቅ ህይወት እንድትፈትነው፣ ችግሮችንም መቋቋም እንዲሳነው ስላደረገው ለሱስ ተገዢ እንዲሆን፤ በተደጋጋሚ ራሱን ለማጥፋት እንዲሞክር አድርጎት እንደነበር ያስረዳል። በተለይ ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ በሆኑበት ጊዜ ራሱን ለማጥፋት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ደም ስሮቹን በምላጭ መቁረጡን በማስታወስ፤ ህይወት ያለቀኗ አታቋርጥምና በምክንያት ድኖ እስከዛሬ እንዲኖር መቻሉን ይገልጻል። ከሲጋራ፣ ጫትና መጠጥ ፍቅር በስተቀር የቤተሰብም ሆነ የሰው ፍቅር እንደማያውቅ በማውሳትም፤ የሚወደውን ሱሱን ለማስታገስ በጠጣ ቁጥርም ራሱን የማቁሰል ወይም ከሰው የመጣላት ባህሪም እንደነበረው ያስታውሳል።
በዚህ መልኩ ተስፋ ቆርጦ ተስፋን የሚሰጠው ሰው ባጣ ጊዜ ስለ ዘ-ኢትዮጵያ ማህበር ሰማ። መሰል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከነበሩ ጓደኞቹ (አንድ የሻሸመኔ፣ አንድ የትግራይ፣ ሁለት ወንድማማች የስልጤ አካባቢ ልጆች) ጋር በመሆንም ማህበሩ ወደሚገኝበት አመሩ። እዛም በትህትና ተቀብለው የጠየቋቸውን ማረፊያ ሰጥተው፤ ምግብ አብልተውና የቆሸሸ ሰውነታቸውን እንዲታጠቡና ልብስ እንዲቀይሩ አደረጓቸው። በዚህም ተባይ ሲበላቸው የነበረ ጎናቸው ከፍራሽ ማረፍ ቻለ፤ ሰው ሲተፋበት የነበረ ማንነታቸው ከሰው እኩል ከብሮ ተገኘ። በዚህ መልኩ ለሳምንት እንዲያገግሙ ከተደረገ በኋላ ምን መስራት እንደሚፈልጉ ተጠየቁ፤ እርሱም ሱቅ ለመስራት በመፈለጉ መርካቶ ላይ ሱቅ ይከፈትለታል። የቤት እቃ ተሟልቶለትም ራሱን እያሻሻለ በመምጣቱም ትዳሩን ያድሳል፤ በሂደትም ፍሊዶ አካባቢ የሥራም የመኖሪያ ቤቱን ቀይሮ ከባለቤቱ ጋር ተረጋግቶ መኖር ይጀምራል።
አሁን ላይ ከሶስት ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ዜጎችን በተለያየ መልኩ እየረዱ መሆኑን የሚናገረው ወጣት መሐመድ፤ ለዚህን ያህል ሰው ቀርቶ ለአንድና ሁለት ሰው ድጋፍ ማድረግ በሚከብድበት በዚህ ወቅት ይሄን መሰል ተግባር የሚያከናወኑ ማህበራት ሊበረታቱ እንደሚገባ ይገልጻል። ትናንት ጎዳና ላይ ተባይ ሲበላው የነበረው ማንነቱ በዚህ መልኩ ለራሱም ቢሆን በማያምነው ህይወት ውስጥ መሆኑን በማስታወስም፤ አሁን ላይ ያለበት የሥራ ሱቅ በማያውቀው ምክንያት አንድ ወር እንኳን ሳይሰራበት እንደታሸገበት ይገልጻል።
ይህ ደግሞ ከመከላከያ ይዞት የመጣውን የአራት ዓመት ልጁን ጨምሮ ነፍሰጡር ባለቤቱን ይዞ ለመኖር የሚከብድበትን ሁኔት የፈጠረ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት መልካም ሰዎች የወደቁን አንስተው መንገድ ያስጀመሯቸውን ዜጎች ከማደናቀፍ ይልቅ መደገፍ ተገቢ መሆኑን ይናገራል። ይህ ማህበር ደግሞ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያውያን ለማገዝ የተቋቋመ እንደመሆኑ፤ ሌሎች ሀብታም ሰዎችም ለራሱ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዝቅ ብሎ የወደቁትን ማሰብ ቢለመድ መልካም እንደሆነም ይመክራል። በመሆኑም በተለያየ ምክንያት ከጎዳና የወደቁ ወታደሮች፣ የልጅ እናቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች በርካታ ስለሆኑ መንግሥትም ሆነ መሰል ማህበራት ተናብበውና ተቀናጅተው በመስራት ሊታደጓቸው እንደሚገባ ይገልጻል።
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ወጣት ሚካኤል ግዛው፣ የርሱም ህይወት ከቀደሙት ባለታሪኮች እምብዛም እንደማይለይ ይናገራል። እርሱም ዘ-ኢትዮጵያ ማህበርን የተቀላቀለው በአብረሃም እንግዶች መዓድ ላይ ለምግብ ፍለጋ በሚሄዱበት ወቅት ነበር። ማህበሩ ግን ከምገባ ባለፈ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ ቢያደርግለትም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን አልቻለም። በሂደት ግን ከመረዳት ጎን ለጎን ማህበሩን በሥራ ወደማገዝ/ማገልገል ተሸጋገረ፤ በዚህም የተለያዩ ተረጂዎች ሲመጡ ወደማስተናበር (ተቀብሎ፣ ተራ አስይዞ፣ መዝግቦና በምዝገባቸው መሰረት ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ፣ ማን ምን መቼ ማግኘት እንዳለበት የመከታተልና መሰል ሥራን በማከናወን) ተሸጋግሮ ማህበሩ ማገዝ መጀመሩን ያብራራል።
ወጣት ሚካኤል እንደሚናገረው፤ ሥራውን በዚህ መልኩ በምገባ የጀመረው ማህበሩ በሂደት ሰዎችን ወደየመንደራቸውና ቤተሰቦቻቸው የመመለስ ሥራን ሲከናወን ነበር። ቤተሰብ ኖሯቸው መመለስ ያልቻሉትን ደግሞ ቤት ተከራይቶ ወደማኖርና ወደመደገፍ ተገባ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ሶስት ዙር ያክል መቀበልና በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ህይወት ላይ ያሉ ወገኖችን ከወደቁበት አንስቶ ማገዝ ተችሏል። ሆኖም ማህበሩ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው በጠባብ ቦታና በኪራይ ቤት መንደር ውስጥ እንደመሆኑ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበታል። በመሆኑም በመንደር ውስጥ ሆኖ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እየተረባበሸ ከሚሰራበት አካሄድ እንዲወጣና ሌሎችን ወገኖችንም በስፋት ማንሳት እንዲችል የተሻለ ቦታ የሚያገኝበት እድል ሊፈጠርለት ያስፈልጋል።
አቶ ጋሻው መለሰ፣ የዘ-ኢትዮጵያ ማህበር አባልና ሥራ አስኪያጅ ነው። እርሱ እንደሚለው፤ ማህበሩ በ2008 ዓ.ም ከ21 የስደት ኑሮ በኋላ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ በመጣች እህተማርያም በተባለች እህት አማካኝነት የመድኃኒዓለምና የቅድስት ድንግል ማርያም ማህበር በሚል ከሶስት ዓመታት በላይ የተለያዩ (መንፈሳዊና ማህበራዊ) የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ በበጎ አድራጎት ማህበርነት ተመዝግቦ ዘ-ኢትዮጵያ ማህበር በሚል ህጋዊ ሰውነትን አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ግን ሰባት ወራት ያክል ሆኖታል።
ይህ ማህበር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ እውነተኛ ኢትዮጵዊ በጎ አድራጊ ወንድምና እህቶች ከሚደረግለት ድጋፍ የዘለለ የተለየ የገቢ ምንጭ የሌለው ሲሆን፤ በአረብ አገራት ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የወጡ የወገን ችግር የሚያማቸው እነርሱ በችግር ውስጥ ሆነው ለወገን የሚደርሱ እህቶች ጭምር የሚሳተፉበት ማህበር ነው። እነዚህ ደግሞ በዜጎች ከውድቀት መነሳት ውስጥ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚመኙ ሲሆን፤ ማህበሩም ዛሬ ላይ ሶስት ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች በተለያየ መልኩ ለመደገፍ መብቃቱ በእነዚሁ ወገኖች መልካም ተሳትፎና እገዛ ነው።
ማህበሩ አሁን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን ከጎዳና ላይ ማንሳት ነው። ሰባት ወራትን ባስቆጠረው በዚህ በጎዳና የወደቁ ወገኖችን የማንሳት ሥራውም ለመጀመሪያ ጊዜ እንኳን ከጊዮርጊስ አካባቢ ብቻ 180 ሰው ማንሳት ችሏል። በዚህ መልኩ ከጎዳና ለሚነሱ ወገኖች ቤት ተከራይቶ ከማኖር ባለፈ የምግብ አገልግሎት፣ የአስቤዛና አልባሳት አቅርቦትም ይከናወናል። ከዚህ በተጓዳኝ ለበርካቶች የምገባ/የማዕድ የማብላት ስነስርዓት በየቀኑ የሚከናወን ሲሆን፤ መስራት የሚችሉ ሰዎችን እየለዩም የተለያዩ የንግድና ሌሎችም ረሳቸውን ማሻሻል የሚችሉበት ሥራ ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
በዚህም በሱቅ በደረቴ፣ በሱቅና ሌሎችም የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን እየለወጡ ያሉ አሉ። አንዳንዶችም በየአካባቢያቸው እንዲመለሱና ባሉበት ራሳቸውን መቀየር የሚችሉበት እድል እንዲፈጠር እየተደገፉ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ መኖሪያ ኖሯቸው የሚበሉት የሌላቸው ወገኖችን በአስቤዛ የመደገፍ፤ ቤታቸው የፈረሰና የዘመመባቸውን ቤት የመጠገን ተግባራት በማህበሩ አባላትና በጎፈቃደኞች ይከናወናል።
ዛሬ ላይ ወንድማማች እንኳን መሰለቻቸት ላይ በደረሱበት በዚህ ወቅት ይሄን አይነት ተግባር ማከናወን ከባድ መሆኑን የሚያነሳው አቶ ጋሻው፤ ከጎዳና ተነስተው ወደ ማህበሩ የሚገቡ ወገኖች ከነበሩበት የተጎሳቆለ ህይወት የተነሳ አካላቸው የቆሸሸ፣ ልብሳቸው የተቦጫጨቀ፣ በተባይ የተወረሩ፣ ተስፋ የቆረጡና ራሳቸውን በስለት እስከመተልተል የደረሱ በሚዘገንን ሁኔታ ላይ ያሉ መሆናቸውን ይገልጻል። በመደገፍ ሂደታቸው የሚያሳዩት ለውጥም እውነት ይሄ ያ ከጎዳና የተነሳው ሰው ነውን የሚል ጥያቄን በሚያጭር መልኩ የሚገለጽ ልዩነት ስለመሆኑም ያስረዳል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የሚሰራው ነገሮች አልጋ በአልጋ ስለሆነ አለመሆኑን በመጠቆምም፤ የምገባው እህል በሸመታ፣ የመደገፊያ ስፍራው በኪራይ፣ ገንዘቡም በምጽዋት የሚገኝ መሆኑን ያስረዳል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ማህበሩ በመንደር ውስጥ ያለ እንደመሆኑ ተደጋፊዎች ከጎዳና ተነስተው ወደ ማህበሩ በሚመጡበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው እንደመሆናቸውና በየቀኑም በስፍራው ለምገባ የሚመጡ ወገኖች ረጅም ሰልፍ ስለሚኖራቸው በመንደሩ ህብረተሰብ ላይ ጥሩ ስሜት እየፈጠረ አለመሆኑንና ቅሬታም እያቀረቡ መሆኑን ያብራራል። ይህ ደግሞ በሥራው ላይ ትልቅ ጫና እያሳደረ ሲሆን፤ በቀጣይም ማህበሩን ለማስፋትና በርካቶችን ለማንሳት ላስቀመጠው እቅድ እንቅፋት የሚሆንበት በመሆኑ የሚመለከተው አካል ማህበሩ ሥራውን በስፋት ሊከናውን እንዲችል ከቦታ ጋር ያለበትን ችግር እንዲመልስለትና እንዲፈታለት ጠይቋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ወንድወሰን ሽመልስ