
አዲስ አበባ፡- ትንሣዔ በዋናነት ከሞት ወደ ሕይወት የመሻገር በዓል መሆኑን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ቆሞስ አባ አማኑኤል ተክሉ ገለጹ።
ቆሞስ አባ አማኑኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ትንሳዔ በክርስቶስ የሚያምኑ ነብሳት ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዲሁም ከሠይጣን መንግሥት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተሸጋገሩበት በዓል ነው።
ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለሆነ ክርስቶስን በተለያዩ መንገዶች እናከብርበታለን ያሉት አባ አማኑኤል፤ የትንሣዔ በዓል የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ምሰሶ ነው። ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረ ጌታ ዳግመኛ ሰውን በትንሣዔው አዲስ ፍጥረት አድርጎታል ብለዋል።
ምዕመናን የተሰበረው መጠገኑን፤ የደከመው መበርታቱን፤ የወደቀው መነሳቱን፤ የተሸነፈው ማሸነፉን ለማሰብና ለማክበር በትንሣዔው እንደሚሰባሰቡ ጠቁመው፣ የአምልኮ ሥርዓታችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ ላይ የተመሠረተ ስለሆነም መስዋዕተ ቅዳሴ በመስቀልና በትንሣዔው አዲስ ፍጥረት መሆናችንን የምናከብርበት በዓል ነው። በመስቀሉና በትንሣዔው እግዚአብሔር እራሱን ከዓለም ጋር አስታርቋል ነው ያሉት።
ወደ መስቀሉ ስንቀርብ ወደ ትንሣዔውም እንቀርባለን። መስቀል መሸሸጊያችን ሲሆን ትንሣዔም እንዲሁ አምባችን ይሆናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በመስቀልና በትንሣዓው አማካኝነት አዲስ ኪዳንን፤ አዲስ ፍጥረትን፤ እውነተኛ እርቅን አምጥቷልና ሲሉም አክለዋል።
አባ አማኑኤል እንደተናገሩት፤ ካቶሊካውያን ትንሣዔን በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል። ቅዳሜ ዕኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ሲሆን የፋሲካ በዓል ቅዳሴያችንን እጀምራለን። እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ቅዳሴ ላይ እንቆያለን። ቅዳሴው ሲጠናቀቅ “ክርስቶስ ተንስአ እሙታን በዓቢ ኃይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን አግዓዞ ለአዳም ሰላም እም ይእዜሰ ኮነ ፍሐ ወሰላም” በማለት ሕዝቡ ሰላምታ በመለዋወጥ ወደ ቤቱ ይሄዳል። ትርጓሜውም ክርስቶስ ሰላምን ሰጥቶናል፤ ሰይጣንን አስሮታል አዳምን አግዟል የሚል ነው።
አያይዘውም ቤተክርስቲያናችን ክርስቶስ አንዱን በግ ለመፈለግ ዘጠና ዘጠኙን በርሃ ላይ ጥሎ እንደመጣ ሁሉ ከቤተክርስቲያን የጠፉ እና ከንስሃ የራቁ ሰዎችን በየቤታቸው በመሄድ በመጎብኘት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ ጥሪ ታስተላልፋለች። ባላት አቅምም ከራሷ እና ሕዝቡን በማስተባበር አቅመ ደካሞችን ትረዳለች። ጾሙን ለመፍታት የማይችሉ ማህበረሰቦችን በመጎብኘት ጾሙን የሚፈቱባቸውን ነገሮች ታድላለች። በአጠቃላይ ትንሣዔ ከሞት በኋላ በሕይወት መኖር እንደሆነ ቤተክርስቲያናችን ታስተምራለች ብለዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም