ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለትንሣዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለትንሣዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የትንሣዔን በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት፤ “ትንሣዔ የማሸነፍ በዓል ነው። ራሳችን እስካልተሸነፍን ድረስ ማንም ሊያሸንፈን እንደማይችል እንማርበታለን።” ብለዋል።

ሮማውያን እና አይሁድ በክርስቶስ ላይ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ነበር። ፈርደውበታል፤ ገርፈውታል፤ ጎትተውታል፤ ሰቅለውታል፤ ገድለውታል። በመጨረሻም በመቃብር ቀብረው መቃብሩን አትመውታል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ኢየሱስ ክርስቶስን በመቃብር አስረው ከትንሣዔን አላስቀሩትም። በትንሣዔ ሌሊት፣ ሞት ታሪክ መቃብርም ተረት ሆነ። ያ ሁሉ ግርግር እና ጩኸት ከንቱ ሆነ። ከሞት አጠገብ ሕይወት፣ ከመቃብር አጠገብ ትንሣዔ ተገለጠ በማለት አብራርተዋል።

እውነትን ማን ሊያሸንፋት ይችላል? ፀሐይንስ ማን ሊሸፍናት ይችላል? ሲሉ ጠይቀው፣ አውሎና ወጀቡ የሚያሸንፉት ለመሸነፍ የተዘጋጀውን ነው ብለዋል።

ጩኸትና ግርግር የሚያስደነብሩት ለመደንበር የተዘጋጀውን ነው። ወሬና ሐሜት የሚያስደነግጡት ለመደንገጥ የተዘጋጀውን ነው። ለማሸነፍ የወሰኑትን ማንም ምንም አያደርጋቸውም ሲሉም ገልጸዋል።

የረቡዕን አድማ፣ የሐሙስን ሤራ፣ የዓርብ ጠዋትን የጲላጦስ ፍርድ፣ የዓርብ እኩለ ቀንን ጨለማ፣ የቅዳም ስዑርን የከበደ ጸጥታ – ላየ፣ ሁሉም ነገር ያለቀና የተቆረጠ ይመስል እንደነበር አንስተው፤ ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ግን ሁሉም ነገር ተገለበጠ። ታሪክ ተለወጠ፤ እውነት ተገለጠ። ሐሰት ደነገጠ። ጠላት ተናወጠ። የኢትዮጵያ ትንሣዔ በኢትዮጵያ ማንሠራራት ጀምሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጩኸቱ እያለፈ እና ጨለማው እየነጋ፣ ሤራው እየተበጣጠሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉንም ወደ ኋላዋ እየተወችው ነው። የኢትዮጵያ ጸጋ ለዓለም እየተገለጠ ነው። በጲላጦስ አደባባይ በኢትዮጵያ ላይ ሲጮኹ የነበሩ ሁሉ፣ እጃቸውን በአፋቸው ይጭናሉ። ዓይናቸው እያየ ኢትዮጵያ ስትነሣ ያያሉ። ‘የወጉት ያዩታል’ እንዲል ሲሉ በድጋሚ መልካም በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የትንሣዔ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸውም፤ በዓሉን ስናከብር ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያሰብን፤ የታረዙትን እያለበስን፤ የተራቡትን እያበላን፤ የተጠሙትን እያጠጣን ፍጹም ሠብዓዊነትን በተላበሰ ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች በዓሉ በፓርቲያችን የሰው ተኮርነትና የሠብዓዊነት መርሆች ደምቆ እንዲከበር እያደረጋችሁ የምትገኙትን እንቅስቃሴ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እየጠየቅኩ በድጋሚ ፍቅር፣ ደስታንና ሰላምን በጋራ የምንቋደስበት መልካም የፋሲካ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የትንሣዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የሰው ልጆችን ከሃጢያት ለማንጻት ራሱን አሳልፎ በመስጠት ወደር የማይገኝለት ፍቅሩን በመስቀል ላይ ገልፆ በሞቱ ለሰው ልጆች ሁሉ ምህረት ያስገኘበት እና ሞትንም ድል በመንሳት ከሞት የተነሳበት በዓል እንደሆነ ተናግረዋል።

እኛም ኢየሱስ ክርስቶስን በተምሳሌትነት በመከተል እርስ በርስ በመፋቀር፣ በመተሳሰብ፣ በይቅርታና ምህረት በማድረግ ከሰው ልጆች ጋር ሁሉ በሰላም እንድንኖር እሱ ይርዳን። በዓሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የምህረት፣ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት፣ የደስታ እና አብሮነታችን የሚጠናከርበት ይሁን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ በክልሉና በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የትንሣዔ በዓልን ተመኝተዋል፡፡

የትንሣዔ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር እና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ በዓሉ የሰላም የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በዓሉ ፍቅር፣ አንድነትና መተሳሰብን የሚያስተምር በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር እርስ በእርስ በመተሳሰብና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባም አቶ አሻድሊ ሀሰን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የትንሣዔ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው “የትንሣዔ በዓልን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደም፤ ብርሃነ ትንሣዔው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ የተሻረበት፤ መርገም የተወገደበት፤ ነፃነት የተገኘበት በመሆኑ፤ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ደማቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡

በዓለ ትንሣዔውን ስናከብር ከመጓተት ይልቅ አብሮ መቆምን፤ ከመገፋፋት ይልቅ ትብብርን፤ ከመለያየት ይልቅ ህብረትና አንድነትን ይበልጥ አጠናክረን፤ ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የልማት ትልሞቻችን በጋራ በመረባረብ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጎዞ ለማፅናት በመነሣት ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሌሎችም የክልል ርእሰ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You