
አዲስ አበባ፡- ትንሣዔው ከእሥራኤል ለዓለም እንደተገለጠው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ለዓለም ትገለጣለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመላው ክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት ፤ ትንሣዔ የመሥዋዕትነት፣ የጽናት እና የተስፋ በዓል ነው። የበደለው ዓለም ነው። የተሠዋው ግን ክርስቶስ ነው። ያጠፋው የሰው ልጅ ነው፣ የካሠው ግን ክርስቶስ ነው። ባለ ዕዳው ሰው ነው። ከፋዩ ግን ክርስቶስ ነው። የክርስቶስ ሞት አንድም ለማዳን ነው፤ አንድም ለትምህርት ነው ብለዋል።
ስለ ብዙዎች ሲባል መሥዋዕትነት ካልተከፈለ ብዙዎችን ማዳን አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገርን፣ ሕዝብን፣ ወገንን ማዳን ከተፈለገ መሥዋዕትነት መክፈል ይገባል። ቃል ክርስቶስ በቃሉ ብቻ አልተናገረም። በመስቀል ላይ ውሎ ፍቅሩን በተግባር ገለጠው እንጂ። ራሱ አስታራቂ፣ ራሱ ታራቂ፣ ራሱም መሥዋዕት ሆነ። ዛሬ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ መሥዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ መሆን አለበት ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ፤ በሌሎች መሥዋዕትነት መጓዝ የኦሪት ሰዎችም አድርገውታል። ሺህ በጎችንና ሺህ ፍየሎችን ሠውተው ነበረ። አልሆነም እንጂ። ሀገርን ማዳን የሚቻለው ሌሎችን በመሠዋት አይደለም። ራስን በመሠዋት እንጂ። የራስን ጉልበት፣ ጊዜ እና ዕውቀት በመሠዋት እንጂ። የራስን ክብርና ኢጎ በመሠዋት እንጂ።
ሀገርን ለማዳን ወደ ትህትና፣ ወደ ዕርቅ እና ወደ ምክክር መስቀል አውርዶ ራስን መሠዋት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ መስቀል መከራ ነው፤ ስድብ ነው፤ ግርፋት ነው፤ ውርደት ነው። ራሳችንን ለሰላምና ለዕርቅ መንገድ ስናዘጋጅ ከብዙዎች ዘንድ ስድብ፣ ርግማን፣ መከራ፣ ይጠብቀናል። የሚያዋጣን ግን ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ የኢትዮጵያን መስቀል መሸከም ነው። ለኢትዮጵያ ትንሣዔ ስንል መስቀሏን መሸከም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ትንሣዔ ከጽናት በኋላ የሚገኝ ድል ነው። ከፊቱ የጅምላ ፍርድ አለው፤ ከፊቱ ውግዘት አለው፤ ከፊቱ ግርፋት አለው፤
መራቆት አለው፤ ከፊቱ መከዳት አለው፤ ከፊቱ የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መልበስ፣ የከዋክብትም መርገፍ አለው። በዚህ ሁሉ ግን በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ ክርስቶስ በጽናት ቆመ። ስለ ዓላማ ሲባል መከራን ታገሠ። ስለ ሰው ልጅ ሲባል ሁሉን እየቻለ በጽናት ተጓዘ ።
ሀገር ጽናት ትፈልጋለች። በመከራዎች እና በውግዘቶች ፊት በጽናት መቆም። በስድብና በንቀት ፊት በጽናት መቆም። እንደ ፀሐይ የሚታዩት ልሂቃን ሲጠፉ፣ እንደ ከዋክብት የሚታዩት ክቡራን ሲረግፉ በጽናት መቆም። አብረው የነበሩ ፈርተውና ተሽጠው ሲከዱ በጽናት መቆም – ሀገር ትፈልጋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በሚጸኑት ዘንድ የኢትዮጵያ ትንሣዔ እጅግ ቅርብ ብቻ አይደለም። የሚታይም እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ትንሣዔ ተስፋ ነው። ፈተናው እንደሚያልፍ ተስፋ ይሰጣል። ዓርብን ላየ እሑድ የሚመጣ አይመስልም ነበር። የመቃብሩን ድንጋይ ላየ የሚነሣ አይመስልም ነበር። ማኅተሙን ላየ የሚፈታ አይመስልም ነበር። ጨለማውን ላየ ብርሃን ሩቅ ይመስል ነበር። ሁሉም ግን ተገለበጠ። ታሪክን የታሪኩ ጌታ ለወጠው።
ተስፋችን በደጅ ነው። ዓርብ ላይ እሑድን እናየዋለን። ከሞት ባሻገር ሕይወትን፣ ከመቃብር አልፈንም ትንሣዔን የምንመለከት ነን። የሚጨበጥ ሕልም የጠራ ምናብ አለን። ስለዚህም ወጀብና አውሎ ነፋስ አያስደንቀንም። ዛሬ ለነገ፣ ሞት ለትንሣዔ ቦታ እንደሚለቁ የምናውቅም፣ የምናምንም ነን።
ለኢትዮጵያ ትንሣዔ የሚተጉ ብዙዎች ናቸው። የሕማማቱ ጊዜ እያለፈ ነው። አሁን ዓርብ ወደ ማታ ላይ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከጸጥታው ቀን በኋላ የኢትዮጵያ ትንሣዔ ይመጣል። ከሄዱት ብዙዎች ይመለሳሉ። ከተሳሳቱት ብዙዎች ያስተውላሉ። ዓርብ ዕለት በከንቱ የጮኹት ብዙዎች ያፍራሉ። ፈራጆች ይፀፀታሉ። ተገዳዳሪዎች ይበታተናሉ። የመቃብር ጠባቂዎች ይደነግጣሉ። ኢትዮጵያ ግን አይቀሬ በሆነው ትንሣዔ ትነሣለች ሲሉ ገልጸዋል።
ትንሣዔው ከእሥራኤል ለዓለም እንደተገለጠው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ለዓለም ትገለጣለች። የትንሣዔ በዓል የሚያስተምረንም ይሄንኑ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም