ትንሣዔን በይቅርታና ለሰላም በመቆም ልናሳልፍ ይገባል

አዲስ አበባ ፡- የትንሣዔ በዓልን በየአካባቢያችን ያሉ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እርስ በእርሳችን ይቅር በመባባልና ለሰላም በመቆም ማሳለፍ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጅና በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የኮዬ ፈቼና ገላን ክፍለ ከተሞች ዋና ሥራ አስኪያጅ አስገነዘቡ።

ሥራ አስኪያጁ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳዔ በዓልን ሲያከብርን ዋጋ መክፈልን እያሰበ መሆን አለበት። ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የዋህና ትሁት ነኝ እንዳለው፤ የዋህነትን ቅንነትን ከእሱ መማር ከእያንዳንዱ ምእመን ይጠበቃል። ትንሳዔ መነሳት ማለት ነው፡ ይህም ለክርስቲያኖች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ሞቶ ሞታችንን የገደለበት ነው። በዚህም የሰው ልጅ ከሞት በኋላ መነሳቱንና ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኝበት መሆኑን የሚያረጋግጥበት ነው ብለዋል።

እርሱ ስለወደደን ራሱን አሳልፎ ሰጥቶናል። እኛም በአካባቢያችን በችግር ውስጥ ያሉትን በማሰብ ችግራቸውን ችግራችን አድርገን በመካፈል በዓሉን ልናሳልፍ ይገባናል ያሉት መላከ ምህረት አባ ገብረ እግዚአብሔር፤ በብቸኝነት ፣ በእስር ቤት፣ በህመምና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉትን ማስበና ለችግራቸው አብሮ መቆም ከእያንዳንዱ ሕዝበ ክርስቲያን የሚጠበቅ እንደሆነ ገልጸዋል። ወንድሙ ሲራብ ወንድሙ ሲጠማ ቆሞ ማየት ከክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት መላከ ምህርት አባ ገብረ እግዚአብሔር ፤ ለሰው ልጅ ከሰላም የቀደመ የለም፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት በቀዳሚነት የሚያስፈልገን ሰላም አንድነትና ህብረት መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደ መላከ ምህረት አባ ገብረ እግዚአብሔር አገላለጽ፤ አንዱ አንዱን ዋስትናውና ምርኩዙ እንጂ ስጋቱ ሊሆን አይገባም። ይህ ለክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አምላክ አለ ብሎ ለሚያምምን ሰላም ቀዳሚ መገለጫው ነው። ሰላም እስትንፋስ ነው፡፡ አምልኮቱ ስብከቱ ማስመለኩ ሁሉ የሚከናወነው ሰላም ሲኖር ነው። አምላክም ሀዋርያቱ በፍርሃትና በጭነቅት በነበሩበት ወቅት ሰላም ለእናንተ ይሁን ያላቸው ሰላም ቀዳሚ በመሆኑ ነው።

ባገኘነው አጋጣሚ ስለ ሰላም መስበክ ስለሰላም መሠራት የግድ የሚለን ነው ያሉት መላከ ምህርት አባ ገብረ እግዚአብሔር፤ በራሳችን ላይ የማንፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ ልናደርግ በፍጹም አይገባም። ሀገርም የምትቆመው ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል።

ወጣቶችም በበዓላት ወቅት መልካም ሥነምግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ ጠቁመው፤በተለይም በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚስተዋለው በበዓሉ ቀን ፈጣሪ በማይወዳቸው ሥራዎች መገኘት ተገቢ አይደለም። በመሆኑም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በተለይም ወጣቶች እንደ ጾም ወቅት ሁሉ የትንሳዔ በዓልንም በመልካም ሥነምግባር በሰላምና እንደየ አቅሙ በልግስና ሊያሳልፍ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You