በትንሣዔው ተስፋን እንዳየን ሁሉ ምዕመኑም ለአቅመ ደካሞች ተስፋ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ክርስቶስ ከሞት በኋላ በትንሣዔው ተስፋ እንዳሳየን ሁሉ እኛም በመተሳሰብና በመደጋገፍ ለሌሎች ተስፋ መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉ የሃይማኖት መሪው ተናገሩ፡፡

የክራይስት ፎር ዩ ኢንተርናሽናል ጎስፕል ሚኒስትሪ መስራች እና ባለ ራእይ አፖስትል አለማየሁ ግርማይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት ፤ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከመነሳቱ በፊት የነበረው ህመሙንና መከራውን በማሰብ እንዲሁም ከሞት በኋላ ያለውን ትንሣዔ በተስፋ በመዘከር እኛም የትንሣዔን በዓል በመተሳሰብና በፍቅር ልናከብረው ይገባል ፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ለዘመናት ያቆየነውን የአንድነት የማህበራዊ ሕይወት ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም በትንሣዔ በዓልም አቅመ ደካሞችን በማሰብና በመደገፍ ልናከብረው ይገባል ብለዋል፡፡

አፖስትል አለማየሁ ፤በዕለተ ዓርብ በጌታ መሰቀል ምክንያት በርካታ ክርስቲያኖች ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ እንደነበር ገልጸው ፤እሁድ ከሞት ሲነሳ ግን ተስፋ ይዞልን ተነሳ፤ ስለሆነም ክርስቲያኖች በትንሣዔ ልናከብረው የሚገባ ስጋዊ ደስታችን ብቻ ሳይሆን በትንሣዔ ያገኘነውን ብርሃን ለሌሎች ብርሃን በመሆን፣ በመተሳሰብና በአንድነት መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሰው ልጅ ተስፋ የሚቆርጥበት እና ተስፋው የሚታደስበት ጊዜ መኖሩን ጠቁመው፤ ክርስቶስ ሞቶ እንዳልቀረ ሁሉ የሰው ልጅም በማህበራዊ ህይወቱ፣ በሥራው ፣ በትምህርትና በቤተሰባዊ ጉዳይ የሚያጋጥሙትን ተስፋ አስቆራጭ ጉዳዮች በጽናት በማለፍ ዳግም ተስፋ የሚታደስበት ጊዜ እንደሚመጣ ከትንሣዔ እንማራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የትንሣዔ በዓል ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያ በመደጋገፍ፣ በመረዳዳትና በአዲስ ተስፋ እንዲያከብረውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You