አለማችን ልትፋለመው አቅም ባነሳት ‹‹ኮሮና›› የተሰኘ ገዳይ ወረርሽኝ ክፉኛ መፈተኗን ቀጥላለች። ቀናት አልፈው፣ ሳምንታት ቢተኩና ወራት ቢፈራረቁም ወረርሽኙን በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ በጎና አስደሳች ዜና መስማት አልሆነላትም።
ከቻይናዋ ውሃን ግዛት የተነሳው ወረርሽኝ በአሁን ወቅት ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራት በማዳረስ የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል። ዘርና የቆዳ ቀለምን ሳይመርጥ ሁሉንም የሚያጠቃው ይህ ወረርሽኝ፣ ደሃ ሃብታም፣ አዋቂና ታዋቂ፣ መሪና ተመሪን ሳይለይ በማጥቃት ከእስያ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አህጉራችን አፍሪካ አለምን በስጋት እያራደ ይገኛል።
የኮቪድ-19 ቫይረስ እስካሁን ከ190 በላይ አገራትን ሲያዳርስ፣ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜም ከአርባ ሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ነጥቋል። በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ከስምንት መቶ ሺህ ሰባት መቶ በላይ መድረሱም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አረጋግጧል።
ቫይረሱ ከእስያና ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በአህጉራችን አፍሪካ ቀሰስተኛ ስርጭት ቢያስመለክትም፣ እስካሁን ባለው ሂደት ግን የ49 አገራትን ድንበር ዘልቋል። ከአምስት ሺ ስምንት መቶ በላይ የሚሆኑ ህዝቦች በቫይረሱ መጠቃታቸው ሲታወቅ 201 የሚሆኑትን ህይወት መንጠቁም ተረጋግጧል።
በርካታ የዓለማችን ከተሞች ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ሁለንተናዊ ጉዳቱንም ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን በመከወን ላይ ተጠምደዋል። አፍሪካውያኑን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
ሰዎች በተቻለ መጠን ቤታቸው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አሳልፈዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጂምናዚያሞች፣ ሙዚየሞች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎችም ተመሳሳይ መዝናኛና ማዘውተሪያዎችን እንዲሁም ከታላላቅ የንግድ ማዕከላት እስከ ተራ ሱቅ ሁሉንም ዝግ አድርገዋል። ድንበራቸውን ከልክለው በረራ አቋርጠዋል። አየር መንገዳቸውን ስራ አስቁመዋል።
መሰል የአገራቱ ውሳኔን ተከትሎም ለወትሮው መፈናፈኛ የማይገኝባቸው ከተሞች ሳይቀር ዝም ያለ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። በርካታ አገራት በዚህ ድባብ ውስጥ መሆናቸውን ተከትሎም የአለም ኢኮኖሚ ቀጥ ብሏል። ቫይረሱም ከጤና ችግርነት አልፎ የአለምን ኢኮኖሚ ክፉኛ እያቃወሰ ይገኛል።
የአለም ኢኮኖሚ ከሁሉ በላይ በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደመሆኑም የወረርሽኙ መንሰራፋት በተለይም በትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ከባድ ጡንቻውን አሳርፋል። የነዳጅ ገበያውን በእጅጉ ተፈታትኖታል። ከባድ ኪሳራም አውጆበታል። የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው የከፋ ቀውስ ተጋርጦበታል።
በርካታ አየር መንገዶች በረራ ማቋረጥ የአቪየሽን ኢንዱስትሪውን ከማንኮታኮት ባለፈ በተለይ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በእጅጉ አዳክሞታል። በአንዳንድ አገራትም ጨርሶ ገድሎታል። ቱሪስቶች የጉብኝትና የበአል ፕሮግራማቸውን ሰርዘዋል። ይህም ዘርፉን ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ላደረጉ አገራት ከባድ ራስ ምታትን አከፋፍሏቸዋል።
የዜጎች የእንቅስቃሴ መገደብ ብሎም በቤት ውስጥ መወሰን የምርትና አገልግሎት ፍላጎቶች እንዳይኖሩና ጠያቂ እንዲያጡ አድርጓል። ይህን ተከትሎም በርካታ አገልግሎት አቅራቢዎች አንድ ደንበኛ መመልከት ብርቅ ሆኖባቸዋል።
በአውሮፓና አሜሪካ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ በተባለ መጠን ፋብሪካዎች ተዘግተዋል። ኩባንያዎች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ምርታቸውን አቋርጠዋል። በርካታ ሰራተኞቻቸውን አሰናብተዋል። አሊያም የአመት ፈቃዳቸውን ሞልተው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
የመዝናኛው ኢንዱስትሪም የቫይረሱ ገፈት በመቋደስ ላይ ይገኛል። በተለይ የስፖርቱ አለም ክፉኛ ቆስሏል። እስታዲየሞች በተመልካች ድርቅ ተመተዋል። በርካታ ውድድሮችም ተሰርዘ ዋል፤ ተራዝመዋል። በርካታ ሰዎች ፊልም፣ ቲያትር እና ኮንሰርቶች ከመመ ልከት ርቀዋል።
ባንኮች በከፋ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ ገብተዋል። ሩቺር ሸርማ የመሳሰሉ ፀሃፍት ኒውዮርክ ታይምስ ላይ ባሰፈሩት ሰፊ ሀተታ፣ አለም ከዛሬ 12 አመታት በኋላ አይታው በማታውቀው የእዳ ጫና ውስጥ ገብታለች። ኩባንያዎች የወሰዱትን ብድር ለመመለስ በእጅጉ በመዳከር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህን ተከትሎም በአሁን ወቅት የአለም ኢኮኖሚ በእጅጉ እያሽቆለቆለ ይገኛል። የአክሲዮን ገበያው እኤአ በ2008 ከተከሰተው የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተቃውሷል። ‹‹የወቅቱና መጪው ኪሳራም ከፋይናንስ ቀውሱ የሚነጻፀር ሳይሆን በእጅጉ የሚገዝፍ ነው›› የሚሉም ቁጥራቸው በርካታ እየሆነ ይገኛል።
የወረርሽኙ ጦስ በ2020 የአለም ኢኮኖሚ ያስመዘግባል ተብሎ የተገመተውን እድገት በሁለት በመቶ እንዲንቀራፈፍ ከማድረግ በላይ ድቀትን ሊከሰት እንደሚችለም የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ ጥናትም አመላክቷል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ከሚችል ቀውስ ለማምለጥ ‹‹ለወትሮው ኃያልና በኢኮኖሚ ልእልና የሚስተካከለን የለም›› የሚሉ አገራትን ሳይቀር በማርበትበት ላይ ይገኛል። የአሜሪካ ምክር ቤት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀውን ኢኮኖሚ ለመደገፍና የእርዳታ ድርጅቶችን፣ የንግድ ተቋማትና የጤና ስርዓቱን ለመደገፍ ይውላል በሚል ከቀናት በፊት ሁለት ትሪሊየን ዶላር በጀት አፅድቋል።
ወረርሽኙ እነዚህ አገራት በዚህ መልክ ሲያርበተብት የተመለከቱም ለአህጉራችን አፍሪካ በእጅጉ ሰግተዋል። አህጉሪቱ በወረርሽኙ ቀውስ ውስጥ መሆን እያደር መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚ ድቀት እንደሚከስት የተለያዩ ምሁራንና ፀሃፍት አትተዋል።
ከእነዚህ ፀሀፍት አንዱ የሆነው ሲሞን ማርክስም፣ ቫይረሱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጠራርጎ እንደሚወስደው ሰፊ ትንታኔን ቪኦኤ ላይ አቅርቧል። አፍሪካውያን ድንበር መዝጋት፣ በረራ መሰረዝና ማቋረጥን ጨምሮ የሚወስዳቸው ጠንካራ የመከላከል ተግባር ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ያሰመረበት ፀሐፊው፣ ይሁንና በተቃራኒው በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ግን በቀላሉ የሚገለፅ አለመሆኑን አስምሮበታል።
አንዳንዶቹም ‹‹ከወዲሁ የግል ሴክተሩ ኢንቨስትመንት እየተዳከመ ይገኛል፣በርካታ ኢንቨስተሮች መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ከመሳተፍ ይልቅ መጪውን የቫይረሱን እጣ ፈንታ መጠባበቅ ላይ አተኩረዋል›› ብሏል።
የአፍሪካን የፋይናንስ አበይት ጉዳዮች በመተንተን የሚታወቀው፣ ኩርት ዳቪስ ዘ- አፍሪካን ሪፖርት ላይ ባሰፈረው ሰፊ ሀተታው፣በተለይ አንጎላን ናይጄሪያ የመሳሰሉ አገራት በቫይረሱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መውደቁን ተከትሎ ከወዲሁ የህመም ስሜት ማስተናገድ ጀምረዋል ብሏል።
የነዳጅ ሃብት ከ75 እስከ 80 በመቶ በጀቷን የሚሸፍነውና 90 በመቶ የውጭ ገበያ አቅርቦቷን የምትሸፍነው አንጎላ እንዲሁም ከነዳጅ 90 በመቶ የውጭ ገቢ የምታገኘውና 70 በመቶ የመንግስት ወጪዋን የምትሸፍነው ናይጄሪያ፣ የነዳጅ ዋጋ በወደቀበትና ሌሎች አምራች አገራት ምርታቸውን በሸጎጡበት በዚህ ወቅት ከኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም ግዴታ ነዳጅዋን ለገበያ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውና ይህም ከባድ ኪሳራን እንደሚያስታቅፋቸው አብራርቷል።
በቫይረሱ ምክንያት የተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ከአምራች የአፍሪካ አገራት ብቻ ከ65 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢን እንደሚነጠቁና በተለይ ናይጄሪያ 19 ቢሊየን ዶላር እንድምታጣ ተገምቷል። ‹‹ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከባድ መርዶ ነው›› ተብሏል።
በእርግጥ የነዳጅ ምርት ከውጭ ለምታስገባው ኢትዮጵያ፣ የዋጋው መውደቅ መልካም ዜና ሊሆን ይችላል።ይሁንና ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋሯ የሆነችው ቻይና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ መጎዳት ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ላይ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ ከባድ ጫናን እንደሚከሰት በርካቶች ተስማምተውበታል።
የአፍሪካን የፋይናንስ አበይት ጉዳዮች በመተንተን የሚታወቁት ዶክተር ዴዝኒ ማሳይ እኤአ በ2001 በአሜሪካ ከተከሰተው 9/11 የሽብር ጥቃት በኋላ በአስከፊ ቀውስ ውስጥ መግባቱን በመሰከሩለት የአፍሪካ አቭየሽን ዘርፍ ኪሳራም፣ ከአህጉር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ብራንድ ስም መፍጠር የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ክፉኛ እንደሚጎዳ ተገምቷል።
የቱሪዝም ዘርፉ ሁለተኛ በርካታ የስራ እድል የሚፈጥርላት ብሎም ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዋና 10 በመቶ ኢኮኖሚዋን የምትሸፍነው ቱኒዚያም በወረርሽ ዘርፉ በሚያስከትለው ጉዳት ክፉኛ ከሚቆስሉት አገራት ግንባር ቀደም ሆና ትጠቀሳለች።
ለጣልያን ቅርብ የሆነችውን አፍሪካዊቷ አገር ጠቅላይ ሚኒስትርም፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከተገመተው ከ2 ነጥብ 7 ወደ 1 በመቶ እንደሚቀንስ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ቫይረሱ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በሚመለከትም ምሁራኑ፣ ‹‹የንግድ ስራቸው የተቀዛቀዘባቸው ኩባንያዎች ሰራተኞች ሊቀንሱ ይችላሉ፣ ይህን ወደ አፍሪካ የሚላከው የውጭ ሀዋላ ገቢ ሊቀንስ ይችላል›› ብለዋል።
አለም አቀፍ የገበያ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቀው፣የሲ ኤን ቢሲው ፀሃፊ ኤልዮት ስሚዝ፣ ፣ወትሮም ያላማረባት የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሸጋገር አትቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣በዚህ አመት የአፍሪካ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ምጣኔ፣ ከ 3 ነጥብ 2 ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንደሚል ግምቱን አስቀምጧል።
ይህን ቀውስ ለመሻገር የትብብር መንገድ ቀዳሚ አማራጭ መሆን እንዳለበት የሚያመላክቱት በርካቶች ናቸው። ላሪ አልዮት ዘ- ጋርዲያን የኢኮኖሚ ኤዲተር ባሰፈረው ሀተታ፣አፍሪካ ብቻዋን የኮሮና ቫይረስን ጡጫ መመከት እንደማትችልና ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም የገነቡ አገራት በአለም አቀፍ ትብብር መርህ እጃቸውን ሊዘረጉ እንደሚገባ አመላክቷል።
ይህ እሳቤ ያልተዋጠላቸው አንዳንዶች በአንፃሩ ‹‹በአሁን ወቅት በርካቶቹ ምዕራባውያን አገራት በቫይረሱ በወረርሽኙ ክፉኛ በመጎዳታቸው ቀድመው ድጋፋቸውን በቀላሉ ሊለግሱ አይችሉም፣ድጋፉን ማግኘትም ቀላል አይሆንም፣ ገንዘቡ ከተገኘም መጠኑ በሚፈለገው ልክ አይሆንም››ብለዋል።
ከችግሩ ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮርን ምርጫቸው ያደረጉት በአንፃሩ፣የኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስከ ተለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና ከዚህም በኋላ ሊኖር የሚችለውን ተፅዕኖውን ለመቀነስ የሚረዱ በአለም አቀፍ ትብብርና በውስጥ አቅም ሊተገበሩ የሚችሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
‹‹በመላው ዓለም የሚገኙ መንግስታትና ማዕከላዊና አበዳሪ ባንኮች ለአገራቸው ባለሀብቶች የብድር የክፍያ ጊዜ ሽግሽግን ጨምሮ የብድር መመለሻ ጊዜ ማራዘም ብሎም ወለድን ማስቀረት ቢችሉ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ድቀት ለመሻገር ፍቱን አማራጭ ነው›› ተብሏል።
አንዳንድ ምሁራን በአንፃሩ ለወቅታዊው የኮሮና የቫይረስ ቀውስ እልባት የሚያገኝበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን በማስመዝገብ የኢኮኖሚ ድቀቱም በቶሎ እንደሚያገግም የሚያመላክት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
የአውሮፓ አገራት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንጌላ ጉሪያ ግን ይህን አስተያየት በማጣጣል፣ ‹‹በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ መልሶ ለማገገም ወራትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፣አገራት በቀላሉ ከኢኮኖሚ ኪሳራ ይወጣሉ የሚለውም አጉል ምኞት ነው›› ብለዋል።
የቫይረሱ ስርጭት የዓለም ኢኮኖሚን ዕድገት በትንሹ በግማሽ እንዲቀንስ በማድረግ 1 ነጥብ 5 በመቶ ሊያደርገው እንደሚችል የተመላከተ ሲሆን ችግሩ የሚያስከትላቸው የስራ አጥ ቁጥሮችና የኩባንያ ኪሳራዎችን አሁን መገመት ባይቻልም፣ አገራት ‹‹ለመጪዎቹ ዓመታት›› ከኢኮኖሚ ኪሳራ ለማገገም እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
አለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አይ ኤል ኦም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንዳች መላ ካልተገኘለት በስተቀር በመላው አለም 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከስራ ገበታቸው ሊያፈናቅል ይችላል የሚል ስጋቱን አጋርቷል።
የአለም ሰራተኞች ገቢም በድምሩ 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ሊቀንስ እንደሚችል ያመላከተው የተቋሙ መረጃ፣ መንግስታትና ተቋማት ቫይረሱ በሰራተኞች ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ አሉን የሚላቸውን መፍትሄዎች ይተገብሩ ዘንድም ተማፅኗል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ቬራ ሶንግዌም፣ አፍሪካ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት 100 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልጋትና የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ከድቀት መከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እስካልተከናወኑ 30 ሚሊየን ስራዎችን ሊያሳጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
መሰል የኮሚሽኑም ሆነ የሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች ስጋት በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ሰሚ ጆሮ ካላገኘ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ ከተነሳም ብሮንውን ብሩቶን ዘ- አትላንቲክ ካውንስል ላይ እንደጠቆመው፣ 85 በመቶ ህዝቦቿ በቀን 5 ዶላር ያልበለጠ ገቢ በሚያገኙባት አፍሪካ መጪው ጊዜ እጅጉን አሰቃቂና አስፈሪ ሊሆን ይችላል ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2012
ታምራት ተስፋዬ