ሐሙስ ሐምሌ ሁለት ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከልክ በላይ በመጠጣታቸው በፍርድ ቤት ቅጣት ስለተላለፈባቸው ሰካራሞች ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
32 ሰካራሞች እያንዳንዳቸው
50 ብር ተቀጡ
የአዲስ አበባ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከመጠን በላይ በመጣጣት አቅማቸውን ባልመጠኑ ጠጪዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር 32 ሰዎች ተይዘው ስድስተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ እያንዳንዳቸው ከማስጠንቀቂያ ጋር 50 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው መሆኑን የጣቢያው አዛዥ ገለጹ፡፡
ከዚህም በቀር በህዝብ መተላለፊያ መንገዶች፣ በዋና አደባባይ ዙሪያ፣ በመኖሪያ ሰፈሮች አካባቢ ያለአንዳች ምክንያት በስራ ፈትነት “ይህችን ያገኘ ያን ይብላ” እያሉ በማወናበድ ህዝብን የሚያስቸግሩ 48 የካርታ ቁማርተኞች ተከሰው እያንዳንዳቸው ከብርቱ ማስጠንቀቂያ ጋር 50 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ፤ መቀጫውን ባይከፍሉ በሁለት ወር እስራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሆኑን የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል ደጀኔ መሸሻ በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
እሁድ መጋቢት አምስት ቀን 1963 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለስራ የተሰጠውን ሽጉጥ ስለሸጠ ፖሊስ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ለስራ የተሰጠውን ሽጉጥ የሸጠው ፖሊስ ወህኒ ገባ
በአዲስ አበባ ከተማ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ በስራ ላይ ተመድቦ ለጸጥታ ማስከበሪያ የተሰጠውን ኮልት ሽጉጥ ሸጦ ለግል ጥቅሙ ያዋለው ወታደር ይልማ ተናኘ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ መጋቢት ሁለት ቀን 1963 ዓ.ም ተፈረደበት፡፡ ተከሳሹ ከሁለት ዓመት እስራት በተጨማሪ ሁለት መቶ ብር መቀጫ ሲወሰንበት ገንዘቡን ባይከፍል በሶስት ዓመት እስራት እንዲቀጣ የአዲሰ አበባ አውራጃ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በይኗል፡፡
ወታደሩ የሸጠላቸውን የመንግስት ሽጉጥ ገዝተው በእጃቸው ላይ የተያዘባቸው ሁለት ሰዎች እያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ብር መቀጫ ከፍለው ሁለት ወር እንዲታሰሩ ሲፈረድባቸው ገንዘቡን ባይከፍሉ እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ በወታደር ይልማ ተናኝ ተሸጦ የነበረው ሽጉጥ በፖሊስ ምርመራ ተደርሶበት ተይዞ በኤግዝቢት ቀርቦ ስለነበር ሽጉጡ አስቀድሞ ከወጣበት የመንግስት ግምጃ ቤት ተመላሽ እንዲሆን ታዞ ተከሳሹ ወደ ወህኒ ቤት ተልኳል፡፡
ረቡዕ ሐምሌ ስምንት ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንቁራሪቶችን ከነነፍሳቸው ስለሚውጥ የውጭ አገር ዜጋ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
እንግሊዛዊው አንጀቱ እንዲሰራ እንቁራሪት ከነነፍሷ ይውጣል
አንድ የ57 ዓመት ዕድሜ ያለው የእንግሊዝ ተወላጅ ከኩሬዎችና ፈሳሽ ካለባቸው ሥፍራዎች ትንንሽ እንቁራሪቶችን እየለቀመ የሚውጥ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሰውዬው እንቁራሪቶችን እየለቀመ ለምን ከነህይወታቸው እንደሚውጣቸው በተጠየቀ ጊዜ አንጀቴ በትክክል እንዲሰራና የምግብ ፍላጎቴ ከፍ እንዲል ነው ብሏል፡፡ እንቁራሪቶቹም ሆዱ በዘለቁ ጊዜ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ወይም ቁርቋሮ እንደማይሰማው ካስታወቀ በኋላ እንዲያውም አንጀቴ በትክክለል እንዲሰራ ይረዳሉ ብሏል፡፡
ሰውዬው እንቁራሪቶችን ከነህይወታቸው መዋጥ የለመደው ከ46 ዓመታት በፊት ወንድሙ ከአሳ ጋር ያሰገራቸውን እንቁራሪቶች ሲበላ በመመልከቱና ቀስ በቀስም እሱ እንቁራሪት በመዋጥ ልምምድ በማድረጉ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
የትናየት ፈሩ