የማይጨው ጦርነት
በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከ40 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በቅኝ የመግዛት ውጥኗ በአድዋ ጦርነት የከሸፈባት ጣሊያን ዳግም ካዘመተችው ጦር ጋር ማይጨው ላይ ጦርነት የገጠመው ከ84 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር።
ጣሊያን የአድዋ ጦርነት ከተካሄደ ከ40 ዓመታት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ ተነሳች። በምፅዋ ባህር ወደብ በኤርትራ በኩል ወሰን ላይ ዘመናዊ የጦር ሃይሏን አደራጀች። በህዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ሆነ ብላ የወልወል ግጭትን በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ለመውጋት ተንደረደረች። ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት” በተሰኘው መጽሐፉ ኢትዮጵያና ጣሊያንን ለጦርነት ስላበቃው የወልወል ግጭት እንደፃፈው ወልወል በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሃገር በኦጋዴን ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው።
የጸቡ መነሻም የፋሽስት ጦር ወሰን አልፎ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወልወል በመገኘቱ ነው። የጣሊያን ትንኮሳ ቀጥሎ ከሮም “ማንኛውም የኢጣልያ ወታደር የረገጠው መሬት ሁሉ የኢጣልያ ቅኝ ግዛት መሆን አለበት። የምኒልክ ጊዜ በ1898 ዓ.ም እና ግንቦት 16 ቀን 1908 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የወሰን ስምምነት መፍረሱን የኢጣሊያ ሹማምንት ሁሉ እንዲያውቁት” የሚል ትእዛዝ በመተላለፉ ጸቡ ከረረ። ወልወል ላይ የሰፈረው የጣሊያን ጦርና የኢትዮጵያ ሠራዊት ተፋጠጡ።
ጳውሎስ ኞኞ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል “ህዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ረቡዕ ልክ ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ሲሆን በድንገት ባንዳዎቹ በኢትዮጵያ ወታደር ላይ አደጋ ጣሉ። ወዲያው በሰማይ አውሮፕላኖች፤ በምድር ታንኮች ደርሰው በጣሊያኖቹ መድፍና ቦምብ መሬቷ ተርገበገበች። ኢትዮጵያውያኑም ያሉበትን ስፍራ ሳይለቁ ባላቸው አሮጌ መሳሪያ እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ድረስ በጀግንነት ተዋጉ። በዚያም ጦርነት 94 ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ሲወድቁ 45 ቆሰሉ።”
ከግጭቱ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ብላቴን ጌታ ሕሩይ የጣሊያንን ድርጊት ተቃውመው አዲስ አበባ ከተማ ላለው የኢጣሊያ መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ ደብዳቤ ላኩ። ጣሊያኖች ግን “… ጥፋቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ወታደሮቻችሁ 30 ኢጣሊያውያን ወታደሮች ገድለውብናል። የኢጣሊያ መንግስትም ከኢትዮጵያ መንግስት ካሳ ይጠይቃል። ካሳውን ብቻ ሳይሆንም ይቅርታ እንድትጠይቁን እንፈልጋለን።” አሉ። የጦርነቱ መነሻ የወልወል ግጭት ይሁን እንጂ ዋነኛው ምክንያት ጣሊያኖች ከአርባ ዓመታት በፊት የደረሰባቸውን አሳፋሪ ሽንፈት የቋጠሩትን ቂም ለመወጣት መፈለጋቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የጣሊያንን ክስ ስላልተቀበለ ጦርነት ግድ ሆነ።
መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም የጣሊያን ጦር የመረብ ወንዝን ተሻግሮ በሦስት መስመር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከፍተ። የጥቃቱ አንዱ ዒላማ ጣሊያኖች የሃፍረት ማቅ የተከናነቡባት አድዋ ነበረች። የተቀሩት ሁለቱ የጥቃቱ ዓላማዎች እንጢቾ እና አዲግራት ነበሩ። ጣሊያን ጥቃቷን ቀጥላ በጥቅምት ወር መቐሌን ያዘች። ከወራሪው የጣሊያን ሃይል ጋር ሲወዳዳር ኋላ ቀርና አነስተኛ መሣሪያ የያዘው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሰራዊት የተላለፈለትን የክተት አዋጅ ተከትሎ ጭብጦ ስንቁን ይዞ ጦርና ጋሻውን አንግቦ ወደ ዘመቻው ተሰማራ። ጣሊያን በሶማሊያ በኩል ባደራጀችው ዘመናዊ የጦር ሃይል በምሥራቅ በዑጋዴንና በደቡብ በዶሎ በኩል፣ ጦርነት ጀመረች። ኢትዮጵያም ባላት ሃይል ለመከላከል ሰራዊቷን ወደ ሁለቱም የጦር ግንባር በእግር አጓጓዘች።
ከማይጨው ጦርነት በፊት በርካታ ውጊያዎች ተደርገው ብዙው ሰራዊትና አዛዦች ሞተዋል። የጎጃምና የጎንደር ጦር በምዕራብ ትግራይ ተዋግቶ እያሸነፉም እየተሸነፉም በመጨረሻ በአይሮፕላን መርዝ ተጠቅቶ ተበትኗል። በጦር ሚኒስትሩ የሚመራው ከ50 ሺ በላይ ይሆናል ተብሎ የተገመተው ጦርና ከወለጋ የተንቀሣቀሰ ጦር በአምባአራዶምና በሌሎች ቦታዎች ተዋግቶ ጊዚያዊ ድል አግኝቶ ነበር። ነገር ግን በአውሮፕላን መርዝና በጣሊያን ዘመናዊና ከባድ መሣሪያ ጉዳት ስለደረሰበት አዛዦችም ጭምር በጦር ሜዳ ተሰዉ። በተምቤን በኩል የዘመተው የሰላሌ፣ የደቡብ ጎንደር፣ የከምባታና የላስታ ጦርም ከታዘዘበት ቦታ ሳይደርስ በጣሊያኖች ተቆረጠ። ኢትዮጵያውያኖች በጀግንነት ተዋጋተው ብዙ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰራዊቱ ተዳከመ። በተለያዩ ውጊያዎች ለወራት ከተደረገው ውጊያ የተረፈው ወታደር ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩት ጦርነት ለመዋጋት ማይጨው ላይ ተሰበሰበ።
መጋቢት 22 1928 በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በተለያዩ ግንባሮች ተሰለፈ። አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃ›› በተባለው አንደኛ መጽሐፋቸው እንደገለጹት ጦሩ ወደ ውጊያ የገባው በአራት ክፍል ተመድቦ ነው። የመጀመሪያው ምድብ መሪ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ። በእሳቸው ሥር ቀኛዝማች መኩሪያ ባንትይርጉ፣ ግራዝማች ክፍሌ እርገቱ፣ ግራዝማች አበራ ግዛውና ሌሎችም የሚገኙ ሲሆን ደጃዝማች አደፍርሰው በደጀንነት ተሠልፈዋል።
በግራ ክንፍ የዘመተው ጦር መሪ ራስ ጌታቸው ሆነው በእሳቸው ሥር ደግሞ የከምባታ፣ የዕቃ ቤትና የገንዘብ ሚኒስቴር ጦር ተሠለፈ። በቀኛዝማች ተክለ ማርቆስ ወልደ ገብርኤል የሚታዘዘው ጦር በዚሁ ምድብ ውስጥ ይገኝ ነበር።
ጦሩ የሚንቀሳቀስባቸውን መስመሮች የሚያመለክቱና የሚመሩት ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ነበሩ። በቀኝ የጦሩ መሪ ራስ ሥዩም መንገሻ ሲሆኑ በእሳቸው ዕዝ ውስጥም ሰናድር ያዥ፣ የወለጋ ጦር፣ የሊቀ መኳስ ወልደ ገብርኤል ጭፍራና በቀኛዝማች ወልደ ዮሐንስ የሚመራ የመድፈኛ ጦር ተመድቧል። የጦሩ መንገድ መሪነት ፊታውራሪ ተድላ አበራ ላይ ተጥሏል። ራስ ካሳ ኃይሉ የመሀሉ የጦር መሪ የነበሩ ሲሆን በእሳቸው ሥርም ራስ ከበደ መንገሻ፣ በሊጋባ ዋለሉ የሚመራው የመሀል ሰፋሪ ጦርና ሌሎችም የተመደቡ ተካተዋል። የጦሩ መንገድ መሪ ደግሞ የማይጨው አገረ ገዥ ደጃዝማች አበራ ተድላ ነበሩ። በጄኔራል ባዶሊዩ የሚመራው የጣሊያን ሰራዊትም በዘመናዊ መድፎችና ከ70 በላይ በሚደርሱ የጦር አይሮፕላኖች እየታገዘ ተሰለፈ።
ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጦርነቱ ተጀመረ። ውጊያው እንደተጀመረ ኢትዮጵያኖች ኢጣሊያኖች ካምፕ ድረስ ዘልቀው በሚያስደንቅ ጀግንነት ተዋጉ። ጄኔራል ባዶሊዩ ገና በጠዋቱ ፣ የጦር አይሮፕላኖቹ በሙሉ ሃይላቸው በቦምብና በመርዝ ጋዝ ኢትዮጵያውያኖቹን እንዲደበድቡ አዘዘ። ከፍተኛ እልቂትም ሆነ። ምንም መከላከያ የሌላቸው ኢትዮጵያውያኖች ከውጊያ ውጭ ሆኑ።
ጣሊያን የበላይነቱን ብትይዝም ኢትዮጵያውያኖች ግን ከውጊያ ቀጠናቸው ሳያፈገፍጉ ቆዩ። ሠራዊቱ ምሽት ድረስ ከተዋጋ በኋላ ወደኋላው አፈገፈገ። ጣሊያኖችም የሚሸሸውን ሠራዊት እየተከታተሉ የመርዝ ጋዝ እየረጩ አስቀሩት። በአሸንጌ ሃይቅም መርዝ ረጭተው በጥም የተጎዳው ሁሉ ሲጠጣ አለቀ።
ንጉሡ ጦርነቱ ከመካሄዱ በፊት ሠራዊቱ በውጊያ ጊዜ ምን ማድርግ እንዳለበት በመዘርዘር መመሪያ ሰጥተው ነበር። አደጋ የሚያስከትል ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ ምርኮኛን አለመግደል፤ ቁስለኛ አነሳለሁ ወይም ግዳይ እጥላለሁ ብሎ ወደ ኋላ መመለስ ውጊያ ላይ ያለውን የወገን ጦር ለጥቃት የሚዳርግ በመሆኑ ፊትን አለማዞር፤ በጦርነቱ ላይ የተገኘን ንብረት ለመዝረፍ አለመጣደፍ፤ ጠላት የሸሸ መስሎ ሲያፈገፍግ ግራና ቀኝ በተጠመደ መትረየስ ውስጥ ሊያስገባ ስለሚችል መጠንቀቅ የሚሉት ከተሰጡት መመርያዎች ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን በጦርነቱ ወቅት ወታደሩ ፉከራውን እየሰማ ምርኮውን ለማሳየትና በንጉሡ ፊት ለመፎከር ወደ ኋላ ይመለስ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል። የማይጨው ጦርነት በጣሊያኖች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ።
የማይጨው ሽንፈት ለጣሊያን አንገብርም ያሉ ጀግኖች በየጫካውና ሸንተረሩ የአርበኝነት ሥራ እንዲነሳሱ አደረጋቸው። አጼ ኃይለስላሴም ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ። ጣሊያን ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ገባ። ጣሊያን በአምስት ዓመታት ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰችው ጥፋት ከፍተኛ ነው። ከአምስት ዓመት በኋላ ንጉሡ የእንግሊዝን ዕርዳታ አግኝተው አርበኞችም ጠላታቸውን አስጨንቀው ድል አደረገው ነጻነት ሆነ። ፋሽስት ጣሊያን ተነቅሎ መሪዎቹ ተገደሉ፤ ቀሪዎቹም ታሰሩ።
ጣሊያን ላደረሰችው ጥፋት ፓሪስ ላይ በተደረገ ስምምነት ስድሰት ሚሊዮን 250 ሺ ፓውንድ ስተርሊንግ ወይም 16 ሚሊዮን 300 ሺ ዶላር እንድትከፍል ተደርጓል። ይህ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 30 ሚሊዮን ገደማ ነበር። በወቅቱ ጣሊያኖች የደም ካሳ ብለው በከፈሉት 30 ሚሊዮን ብር 43 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የቆቃ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በ1952 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ በ80 ኪ.ሜ ርቀት በአዋሽ ወንዝ ላይ ተገነባ። ግድቡ በ1949 ዓ.ም ተጀምሮ በ1952 ዓ.ም ተጠናቋል።
ከድል በኋላ በ1942 ዓ.ም አፄ ኃይለ ሥላሴ በማይጨው ከተማ በጦርነቱ የወደቁ ወገኖች አፅም እንዲሰባሰብ አድርገው የመታሰቢያ ሐውልት አቆሙላቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
የትናየት ፈሩ