ጤና ይስጥልኝ! እንዴት ይዟችኋል እናንተዬ? ሌላው የመገናኛ መንገዳችን እድሜ ለኮሮና እየጠበበ መጥቷል። እናም ብቸኛው የሃሳብ መድረካችን በሆነው የአዲስ ዘመን ገበታችን ካለሁበት ሆኜ እቺን የሃሳብ እንጎቻ ላጋራችሁ ወደድኩ። ጎበዝ ይኸ ነገር ከአጭር ጊዜ አኳያ የሚቆም እንዳይመስል ሆኖ ነው የመጣብን። መቸም አንድዬ ጥሎ አይጥለንም በሚለው የተስፋ ጎተራችን እና እየተንፏቀቀም ቢሆን ቀስበቀስ ገቢራዊ ማድረግ የጀመርነው የግል ጥንቃቄ እስከ ሆነ ርቀት እንደሚወስደን የተስፋ ጭላንጭል ባያሳጣንም።
ጉዳዩ በብዙ ዓመታት ውስጥ አንዴ የሚከሰት እና የዓለማችንን ገፅታ በመሠረታዊነት የሚቀይር እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ማህበራዊ ተግባቦታችን፣ ባህላዊ ትስስራችን እና አኗኗራችን ጭምር በአዲስ ቅኝት ሊከለስ ግድ መሆኑ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል። የጤና መቅሰፍት የሆነው ይህ በሽታ የብዙ ሺህ ሰዎችን ህይወት ከመቅጠፉም በላይ የህዝቦችን ሀገራዊ ህልውናና የመንግስታትን ምጣኔ ሀብታዊ አቅምንም ጭምር በመናድ ነው ከመኖር ወደ አለመኖር እያሸጋገረን ያለው።
ከሌሎች በሽታዎች ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ቫይረሱ ለዓለማችን አዲስ እንግዳ ከመሆኑ የተነሣ አቅም ያለውም የሌለውም በበሽታው እኩል እየተጠቃ መሆኑ ነው። በኢኮኖሚ የበለፀጉት እና የተሻለ የጤና ቴክኖሎጂ ባለቤት ናቸው የሚባሉት ምዕራባውያን ሳይቀሩ ነገሩ ዱብ እዳ ሆኖባቸው የጨለማ ጉዞን ተያይዘውታል። የነፍስ ማዳኛ መሳሪያዎች እና ሌሎች አጋዥ ቁሳቁሶች በየሆስፒታሉ ከፍተኛ እጥረት እንደሚታይባቸው ፖለቲከኞች እና የጤና ባለሙያዎች በምሬት እየተናገሩ ይገኛሉ። እንግዲህ የኛን ሀገር ጉዳይ እዚህ ጋር ባላነሳው ይሻላል። ምክንያቱም ወዲያ ማዶ ካሉት ዘመዶቻችን ጋር ይህንን ለማነፃፀር መሞከር እራሱ የአእምሮ ድህነት እንዳይሆንብኝ ስለምሰጋ ማለት ነው።
ይህ ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ በዓለማችን አንደኛው ጫፍ እንደተቀሰቀሰ ይነገር እንጂ ወደ ተቀረው ዓለም በፍጥነት እንዲሰራጭ ድልድዩም እኛው የሰው ልጆች እና እኛው የገነባናቸው የምጣኔ ሀብታዊ አቅሞች እና መሠረተ ልማቶች ናቸው። ከሩቅ ምስራቅ ተነስቶ መላው አውሮፓን ያጥለቀለቀው፤ ከዚያም አልፎ ወደ ምዕራቡ ንፍቀ ክበብ የተዛመተው በሰውና በቁስ ተፈናጥጦ በአየር፣ በየብስና በውሃ መጓጓዣ መንገዶቻችን አሳላጭነት ነው። ይህም ማለት የዓለምን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማፋጠን በሰው ልጆች የምርምርና የፈጠራ አቅም በተፈበረኩ የመገናኛ እና የትራንስፖርት አብዮት አውታሮች አማካኝነት በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ከቻይና ተነስቶ አሜሪካ፣ ከአው ሮጳ ወደ አፍሪካ ወዘተ… ይገባል፤ ይወጣል አቶ ኮሮና።
የቫይረሱ ጭራቅነት ሰውንም ኢኮኖሚንም ወዲያው ይዞ ወዲያው መግደሉ ነው። እዚህ ላይ የቀናትን ሂሳብ ሳልሰራ ቀርቼም አይደል። እንዲያውም ከሰው በላይ ኢኮኖሚን ነው እንደያዘ ወዲያው አንቀርቅቦ እየገደለ ያለው። ያቺ የቫይረሱ መራቢያ እና የሰው ማገገሚያ የተባለችው አስራ አራት ቀናት እንኳ ለሰው እንጂ ለኢኮኖሚው ህልውና የተያዘች “ዊንዶው ፔሬድ” አይደለችም። በእርግጥ ከሰው ህይወት የሚበልጥ ነገር የለም።
እኔ ዛሬ ሶስት ልጆቼን ይዤ የቫይረሱን መምጣት በፍርሃት ተውጬ የምጠባበቀው በሽታው ሲመጣ እንዴት አድርጎ እንደሚገድለኝ ወይም የትኛው ሀኪም የተሻለ ህክምና እንደሚሰጠኝ በማሰብ ሳይሆን እስከዚያውስ ልጆቼን እንዴት አኖራለሁ የሚለው የድህነት ወረርሽኝ የበለጠ እንቅልፍ ስለሚነሳኝ ነው። ያለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመነ ዓለም ኮሮናን ብቻ አይደለም ከወደ ቻይና የሚያመጣልን። ማካሮኒውም፣ ዘይቱም፣ መድኃኒቱም… ሸቀጦችና የፍጆታ እቃዎቻ ችንም ይህንኑ የሉላዊነት መርከብ ተሳፍረው ነው ደጃችን ድረስ የሚመጡልን።ይኸኛው ድልድይ ተሰበረ በተባለ ቅፅበት ማካሮኒውም ይጠፋል። ልጆች ይራባሉ። ያኔ የማላውቀውን ኮሮና ሳይሆን አብሮኝ የኖረውን እና እንደ ዜጋም እንደ ሀገርም አልፋታኝ ያለውን ጨካኙን ረሃብን ነው የምፈራው። የሌለው ደግሞ ሁሌም መራቡ አይቀርም። በድህነት አዘቅት ውስጥ ሆነህ ከባለጠጎቹ እኩል ከኮሮና ጋር የነፃ ትግል (ሪስትሊንግ) ሪንግ ውስጥ ከመተናነቅ እጅግ የከፋ መዓት ምን አለ?
የኮሮና ሰጥአገባ እንግዴ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ በሁለቱ ሃያላን መካከል እንደተጀመረ እናስታውሳለን። የመጀመሪያው እሳተ ገሞራ በሀገረ ቻይና ፈነዳ እንደተባለ በፌብሩዋሪ 2020 ጆርጂዮ አጋምቤን የተሰኘ ጣሊያናዊው ፈላስፋ የጣሊያንን የመገናኛ ብዙኃን እና መንግስትን ህዝቡ ማህበራዊ ፈቀቅታንና ኳራንታይንን ተግባራዊ እንዲያደርግ ኮቪድ -19 ከመደበኛው የኢንፍሎዌንዛ ቫይረስ እምብዛም ልዩነት ይኑረው አይኑረው በቂ ማስረጃ ሳይኖራቸው ማዘዛቸውን ሲወቅስ ነበር።
ለጆርጂዮ አጋምቤን እነዚህ እርምጃዎች እርሱ “ስቴት ኦፍ ኤክሰፕሽን” ወይም የልየታ መንግስት ብሎ በገለፀው ስራው ከመደበኛው እጅግ የገዘፈ ወታደራዊ ስምሪት ሁኔታ መፈጠር መንግሥታት በዜጎቻቸው እና በሲቪክ ነፃነታቸው ዙሪያ ያልተለመደ ስልጣን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል በሚል አስፍሯል። በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲወደቅ የመንግስት ባለስልጣናት በስመ “ደህንነት” ብቻቸውን ሰጪና ከልካይ የሚሆኑበትን ማህበራዊ ነፃነት ይገድባሉ ይለናል የአጋምቤን ስቴት ኦፍ ኤክሰፕሽን።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ሳምንታት በመላው ዓለም መንግሥታት የሚያካሂዱት ኳራንታይኖች፣ ክልከላዎች፣ እና ጥርነፋዎች ፈረንሳዊው ፈላስፋ ማይክል ፎካልት በ18ኛው መቶ ክፍለዘመን በአውሮፓ ተግባራዊ የተደረገው ፕላግ የተሰኘው መንግስታት በማህበራዊ ቀውስ ወቅት የሚፈጥሩት የስልጣን ጡንቻ አይነት መሆናቸውን ያስታውሰናል።
ፕላግ ማለት ማይክል እንደፃፈው “ህዝቦችን በመኖሪያ አካባቢያቸው አልያም በሚሰሩበት ስፍራ በንኡስ በመከፋፈል አደገኛ ተግባቦቶች፣ ዘልማዳዊ እና የዘፈቀደ ግንኙነቶች እንዲሁም የተከለከሉ ንግግሮች የሚታገዱበት አስቸጋሪ ሁኔታ ማለት ነው።”
መንግስታት የአንድን ተላላፊ በሽታ መዛመት ለመገደብ ህዝብን በኳራንታይን ቅርጫ የመከፋፈሉ ተግባራቸው የየግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ በሕዝቦቻቸው ላይ ገደብ የለሽ ሥልጣን፣ አሟጠው የሚጠቀሙበት እና ግልፅነቱም ለራሳቸው ዓላማ ብቻ የሆነ አይነደረቅነት መገለጫ ነው። ለፎካልት በወረርሽኝ ወቅት የሚደረጉ ጥርነፋዎች የመንግሥትን ጡንቻ ገሃድ በማውጣት እርቃኑን የሚያሳዩን ክስተቶች ናቸው።
ጣሊያናዊው አጋምቤን በኮቪድ-19 ቀሳፊነት ዙሪያ ከፈረንሳዊው አቻው በተቃራኒው ያዘነበለ አቋም ቢኖረውም- በተለይም በትውልድ ሀገሩ ብቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጣሊያናዊያን ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ አፍቃሪ ፎካልት እንደመሆኑ መጠን ስለ ስቴት ኦፍ ኤክሰፕሽን ያቀረበው መከራከሪያ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንድንሰጠው ያስገድደናል።
ለመሆኑም በዋናነት በኒዮሊብራል የዓለም ስርዓት መንግስታዊ ስልጣን ከግሉ ሴክተር ፍላጎት ተነጥሎ በማይታይበት ሁኔታ ውስጥ የልየታ ወይም ስቴት ኦፍ ኤክሰፕሽን ምን ማለት ነው?
መንግስታት በእንዲህ አይነት የአደጋ ጊዜ ዜጎቻቸው ከቤታቸው እንዲሆኑ ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ በመጀመሪያ ሰሞን የሚያሳዩትን ማቅማማት እንዴትስ እንረዳዋለን?
በበርካታ መንግስታት ዘንድ የህዝብን እንቅስቃሴ ለማገድም ሆነ የማስ ኳራንታይን እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚታየውን መጓተት እስቲ እናጢነው። ይህ ሀገራችንንም ይጨምራል። በዚህም ስሌት በቻይናዋ የዉሃን ከተማ ላይ የተላለፈው የእንቅስቃሴ እገታ እጅግ ጥብቅ ነበር። ነገር ግን ይህ ቁለፋ የመጣው በትኩሱ ነበር ማለት ይቻላል። ልክ የመጀመሪያው የእሳት ፍንጣሪ ልብስህ ላይ ስትወድቅ የምታሳየውን ድንጋጤ ፍንጣሬዋን ከልብስህ ላይ ለማራገፍ የምታደርገው መርበትበት ብሎ መውሰድ ይቻላል።
የእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የቻይና መንግስት የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ህመም በኖቬምበር 2019 ነበር ቀደም ብሎ ያወቀው። በዲሰምበር አጋማሽ 60 የሚሆኑ የተረጋገጡ ኬዞች ተመዝግበዋል። ይሁንና የቻይና መንግሥትም ይህ ወረርሽኝ ሊሆን ይችላል ከማለት ይልቅ የሚዲያ ዘገባዎችን ሳንሱር በማድረግ እና የመረጃ አፈትላኪዎችን በማፈን በዉሃን የተቀሰቀሰውን ኒሞንያ መሰል ቫይረስ ዜና ለመደበቅ ታተረ።
የአለም የጤና ድርጅት የቻይና ቢሮ ዲሴምበር አምስት ላይ 44 የሚሆኑ ቻይናውያን ምንጩ ባልታወቀ የኒሞኒያ ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸውን በመጥቀስ ዓለምአቀፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የመንግስት ንብረት የሆነው የቻይና ማዕከላዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ ይህንን የደብሊው ኤች ኦን መላምት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ እንደሆነ በጃንዋሪ ሰባት 2020 ባሰራጨው ዜና ማረጋገጫ ሰጠ። ይሁንና እስከ ጃንዋሪ 20, 2020 ድረስ የቻይና መንግስት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ በይፋ እውቅና አልሰጠም ነበር። እናም በመጨረሻም የዉሃንን ከተማ ሙሉ በሙሉ የመዝጋት እርምጃ በጃንዋሪ 23, 2020 ዓ.ም አንድ ብሎ ጀመረ። ይህን ዓይነቱ የቁለፋ እርምጃ ወይም ኳራንታይን ተግባራዊነት በስፋት ስራ ላይ የማዋሉ ጉዳይ የኋላ ኋላ የቻይና መንግስት በቫይረሱ ዙሪያ የወጡ ሪፖርቶችን በማፈን ለመቆጣጠር በመላው ሀገሪቱ ለመተግበር የቋመጠለት ውሳኔ ነበር። የቻይና መንግስት በቫይረሱ ዙሪያ የወጡ ሪፖርቶችን በማፈን ሊቆጣጠረው የፈለገው ነገር በአጭሩ ላለፉት ሁለት ወራት ይኸው ማህበራዊ ቁለፋ ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር “ሎክዳውን” የምንለውን ያመጣውና ታሪካዊ የሆነው የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ምርቶች እድገት ድንገተኛ የዋጋ መውረድ ነበር።
እውነታው አሁን ባለንበት የኒዮሊበራል ግሎባል ኢኮኖሚ – ምጣኔ ሀብታዊ ናሽናሊዝም፣ የስቶክ ገበያና የድንበር ዘለል ኩባንያዎች ፍፁም የበላይነት፣ እንዲሁም ብዙ ጊዜ እርስ በራሱ የሚካካድ የኢኮኖሚ መብቃቃት አልያም አንዱ በአንዱ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ በመፍጠር እዚያው የሚቻቻሉበት አሠራር ውስጥ በማንኛውም የካፒታል፣ የጉልበትና የሸቀጦች ዝውውር ላይ መጠነሰፊ እቀባ የሚጥል የእገዳ እርምጃ እንደ ፀረ እድገት ተደርጎ ስለሚወሰድ በመንግሥት እና በኩባንያዎች አይፈለግም።
በሌላ መልኩ ወረርሽኙ ባመጣው የግዞት መንግስት ውስጥ የተቸነከረችው ጣሊያንም ከዚህ አስከፊ የኢኮኖሚ ልሽቀት የምታገግምበት አቅም የላትም። ወረርሽኙን ለመቀልበስ በሚል ሰበብ ለክልልና ከዚያ በታች ላሉ የመንግስት አካላት የሰጠችው እጅግ የተለጠጠ ፍፁማዊ ስልጣንና ይኸው በቻይና የተጀመረው የቁለፋ እርምጃ በጣሊያንም አግጦ የመጣ የኢኮኖሚ ድቀት ፍራቻን ቀስቅሷል።
ጎልድማን ሳክስ የተሰኘው የኢንቨስትመንት ኩባንያ ባስቀመጠው ትንተና መሠረት እንደ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ሆቴልና የጅምላ ንግድ ያለውና 23 በመቶ የሚሆነውን የጣሊያንን አጠቃላይ የምርት መጠን የሚሸፍነው የግሉ ሴክተር በቁለፋው እጅጉን ተመትቷል።
ለብዙ ሃያሲያን የአውሮፓ ህብረት ኒዮሊብራል የኦስቴሪቲ ወይም የማገገሚያ እርምጃዎች እንዲሁም በጣሊያን ቀጥሎም በስፔን ስራ ላይ የዋሉት የቁለፋ ውሳኔዎች በእርግጥም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚውን ድክመት፣ በግሉ ሴክተር ላይ የሚደረጉ እላፊ መተማመኖች እናም ከወዲሁ የተዋጠው የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶቻቸው ሽባ መሆንን የሚያጋልጡ ፍንጮች ሆነዋል።
በማርች 16, 2020 የስፔን መንግስት ሁሉንም የግል ሆስፒታሎች ወደ ራሱ ይዞታነት ለማሸጋገር በወሰነበት ጀምበር ድፍን ዓለም አንዲት እናት በማድሪድ ከተማ አንድ ሆስፒታል ደጃፍ ሁና በምሬት ስታለቅስ የሚያሳይ ቪዲዮ ተመልክቷል። እቺ ሴት ባሏ ቀደም ብሎ በኮቪድ 19 የሞተባት ሲሆን እሷም ተመርምራ በቫይረሱ መያዟ ተነግሯት ነበር። ነገር ግን “እንደ ባልሽ ለመታከም በደምብ ስላልታመምሽ” በሚል ተልካሻ ምክንያት ከሆስፒታሉ እንዳባረሯት በርካታ የዓለማችን መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ዜናውን ተቀባብለው መዘገባቸውን እናስታውሳለን።
ከፍ ሲል አጋምቤን ያስቀመጠው ስቴት ኦፍ ኤክሰፕሽን እንግዲህ በዚህ መልኩ ነው የየትኞቹ ዜጎች ህይወት ሊታደግ እንደሚገባው እና የየትኞቹን ደግሞ ችላ እንደሚባል የሚወስነው በምፀታዊ ግራ ገብነት ስንመለከተው ይህ ውሳኔ የተላለፈበት አጋጣሚ የኒዮሊበራል መንግስታት ሁሉንም ባይባል እንኳ የአብዛኛውን ዜጎቻቸውን ህይወት ለማትረፍና ለመንከባከብ አቅም እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ እውነታ ነው።
እንዲያም ሆኖ ኮሮና ዓለምን አስተሳስሯል። ከሉላዊነት ቀጥሎም ሌላኛው ምናልባትም ጠንካራው የሉላዊነት ገመድ ሆኗል። ከዚህም በመነሳት ኮሮናላይዜሽን የሚል ስያሜ ልሰጠው ወደድኩ በግሌ። ሌላኛው ግሎባላይዜሽን እንደማለት።
የዚህን ፅሁፍ ክፍል ሁለት ሁለቱን በቀጣይ ይዤ እቀርባለሁ። መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ።
አደራ እንግዴህ እጃችሁን እየታጠባችሁ!
ፈጣሪ ይጠብቀን!
ማሳሰቢያ:- በዚህ ፅሁፍ ውስጥ አንዳንድ የተጠቀምኳቸው ቃላቶች አቻ የአማርኛ ቃላትን ለመፈለግ በማሰብ ሃሳቤን ይገልፃሉ ያልኳቸውን ተጠቅሜያለሁ። ለምሳሌ ቁለፋ (lockdown)፣ ልየታ (exception)።
በፅሁፉ ላይ ያጎደልኩትን፣ ቢጨመርበት የምትሉትን እና ቢታረም የምትሉትን አስተያየትዎን ቢሰጡኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው።
በእነዚህ አድራሻ ሊያገኙኝ ይችላሉ ከትህትና ጋር።
ስልክ: +251 964 113111
ኢሜይል : hamileekoo@gmail.com
ሐሚልተን አብዱልአዚዝ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ