የኮሮና ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) ካስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ የሐሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎች ፍሰት አሻቅቧል። አገራችንም የዓለም ማህበረሰብ አንድ አካል በመሆኗ በዚህ ረገድ አደጋ ተደቅኖባታል። ጋዜጠኛ ሽመልስ መርሳ ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጋር ተያይዞ መገናኛ ብዙሃን ወሬ የቱን ያህል የተዛባ መሆኑን ለመግለጽ እየሰማን ያለነው “ተያዘ” እና “ሞተ” ብቻ ነው ሲል ይገልጸዋል።
ቸርና ተስፋ ያለው ወሬ አንዳንዶች ዴቭሎፕመንት ጆርናሊዝም የሚሉት እየናፈቀን መጥቷል። ሌላው ቀርቶ ከተያዙ ሰዎች አንጻር የሟቾች ቁጥር ከ4 እስከ 8 በመቶ ገደማ መሆኑን እንኳን ሚዲያዎች አለመናገራቸው በሰዎች ዘንድ ፍርሃት ገዥ እንዲሆን የራሳቸው ሚና እየተጫወቱ ነው።
ጋዜጠኛ ሽመልስ እንዲህ ይላል።”…የሰሞነኛው ኮሮና ክንዱን በከፋ መልኩ ካሳረፈባቸው አገራት ውስጥ ጣልያን ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይዛለች። ስለ ጣልያን ያላዘነ፣ ስለ ጣልያን ያልፀለየ፣ ስለ ጣልያን ያላለቀሰ፣ ያልደነገጠ የለም:: እስከ መጋቢት 19/2012 ዓ.ም – (March 28/2020) ብቻ 92 ሺ 472 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ከ10 ሺ በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል::
በአገሪቱ የክፉ ዜናው የመጀመሪያዋ አርጂ ከተማ ደግሞ ቮ ነበረች:: የመጀመርያው የዚህ በሽታ ሞት በአገሪቷ የተመዘገበውም በዚህች ትንሽዬ ከተማ ነበር:: አሁን ደግሞ ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ካናዳን ጨምሮ ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ለመሆን ባለሙያዎቿ እንደነ ሲቢሲ ባሉ የዜና አውታሮች ሲቀርቡ ስናይ እውነትም “ችግር ብልሃትን ያስተምራል” አልን::ቮ ከወረርሽኝ እና የሞት ቀጠናነት ወደ ተስፋ ምድርነት ተቀየረች “Vò has become a beacon of hope” እንድትል የሲቢሲ (CBC) ”As It Happen” ዘጋቢዋ ካሮል ኦፍ:: እኛም ከሬድዮ ሞገድ የተንቆረቆረልንን ይህንን ተስፋ ሰጪ ታሪክ ልናጋራችሁ ወደድን::
የዚህ ውጤት ግንባር ቀደምቶቹ ተዋናዮች ዶክተሮች ናቸው:: ስራቸው ደግሞ እንደ ሞዴልነት እየተወሰደ ነው:: ባለሙያዎቹ አንቶንዮ ካሶኔ እና እንድርያ ክርስታኒ ዘጋርድያን ጋዜጣ ላይ እንዳሰፈሩት ሃተታ ከሆነ አሁን በከተማዋ የተጠቁት ግለሰቦች 100% ያገግማሉ አዲስ የተያዘ ሰው ደግሞ የለም – ስርጭቱም ሙሉ በሙሉ ተገቷል::”
[“ We managed to eradicate coronavirus from Vò, achieving a 100 per cent recovery rate for those previously infected while recording no further cases of transmission,”]
ይህም ሆኖ መገናኛ ብዙሃን ከእንዲህ ዓይነቱ ተስፋ ሰጪ ወሬ ይልቅ ቀልባቸውን የሚስበው እየተፈጠረ ያለው ቀውስ ነው። ክራይሲስ ሪፖርቲንግ ከባድ ኃላፊነትና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ቢሆንም ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ትኩረት እንደተለመደው ውሻው ስውየውን ነከሰ የሚባለውን የጋዜጠኝነት ሀሁ ማስፈጸም ላይ ያተኮረ መስሏል።
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱ ከተሰማ ዕለት ጀምሮ በአገራችንም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እንዲሁ አድጓል።
ሰዎች በማወቅም ባለማወቅም የሐሰተኛ መረጃዎችና አስደንጋጭ መልዕክቶችን በማሰራጨት ቀለባቸውን ለመሸመት የሚያደርጉት ሩጫ አለመቆሙ መንግሥትንም አስቆጥቷል። ሰሞኑን ከተሰራጩት መካከል “ከአንድ ሳምንት በኋላ በኢትዮጵያ እልቂት ይፈጠራል” ከሚል ሟርት ጀምሮ “200 ሺ መቃብሮች እንዲቆፈሩ መንግሥት አዘዘ” እስከሚሉ አስደንጋጭ መልዕክት ያላቸው ዘገባዎች በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭተዋል። ይህን ተከትሎም መንግሥት ከመገሰጽ ባለፈ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነር እንዳሻው ጣሰው ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ሰሞኑን ከተናገሩ በኋላ አንጻራዊ የመረጋጋት ሁኔታ ሰፍኗል ማለት ይቻላል።
የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ማሳሰቢያ የጤናቀውስበዓለም_አቀፍ ደረጃ ሲከሰት፣ የተሳሳተ መረጃን ተቀብሎ ማሰራጨት ከቀውሱ እኩል ጎጂ ነው። ማንኛውም ሰው እንዲህ ባለ ጊዜ የሐሰት ዜናዎችን ለማስቆም የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት።
የፌዴራል መንግሥት ኮቪድ 19ን በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት፣ መረጃን የማደራጀት እና በየዕለቱ የማሠራጨት ሥራን እያከናወነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣው ኮሚቴ እና ሌሎች ዐበይት ኮሚቴዎች ያላቸውን ወቅታዊ የሥራ ክንውን እያስተባበረ እና መረጃን እያስተላለፈ መሆኑ ይታወቃል።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ፣….የኮሮና ቫይረስን ስርጭትን በተመለከተ….ለህዝብ ደህንነት እጅግ አደገኛ በሆነ መልኩ አግባብነት ባላቸው የመንግስት መዋቅሮች የሚሰጡ መመሪያዎችን እየጣሱ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም ሆን ብለው ወረርሽኙን በተመለከተ አደገኛ የሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህዝብን በሚያሸብሩ፣ እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ አላግባብ የሆነ ትርፍ ለማካበት የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ከሕገ – ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር ቁጥር 661/2002 ስለተላላፊ በሽታዎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፤ ይህ አዋጅ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ “ማንኛውም ወደ ሀገር የሚገባ ወይም ከሀገር የሚወጣ መንገደኛ ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ መስፈርቶች መሠረት….በተላላፊ በሽታ ሲጠረጠር ለምርመራ የመተባበር ግዴታ አለበት”።
እንዲሁም “..ወረርሽኝ ካለበት ቦታ የመጣ ሰው ወደ ሀገር አንዳይገባ ሊታገድ ይችላል”። ይሄው አዋጅ በተጨማሪም “አግባብ ያለው የጤና ባለሙያ በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተያዘን ወይም የተጠረጠረን ማንኛውም ሰው ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ’’ ማድረግ እንዳለበት፤ በተጨማሪም “በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለምርመራ፣ ለሕክምና…ፈቃደኛ መሆን” እንዳለበት ተደንግጓል። በአዋጁ መሰረት እነዚህን ድንጋጌዎች መጣስ እስከ ስድስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ፤ በአንቀጽ 514 ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ተላላፊ በሽታን ማስተላለፍን በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ ደንግጎዋል። ይህን አንቀጽ በመጣስ የሚፈጽም ወንጀል እስከ አስር ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል ሲሆን በተለይም ተላላፊው በሽታ በወረርሽኝ ወይም በኢፒደሚክ መልክ የተከሰተ ሲሆን፣ እንደነገሩ ክብደት ቅጣቱ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ ያሳያል።
በተጨማሪም የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 830 የህዝብ ጤና እና ጤናማነትን ለመቆጣጠር በሚል ርዕስ ባሉት ደንጋጌዎች እንደተገለጸው፣ በሽታዎችን በተለይም ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኝ ስለመከላከል፣ መኖራቸውን ስለማሳወቅ፣ ለመከላከል የሚረዱ ህክምናዎችን ስለማድረግ ወይም ስለመቆጣጠር የወጣን መመሪያ መጣስ እስከ ሶስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ነው።
ለህዝብ ጤና አስጊ የሆነ አደጋ እንደሚደርስ በማስፈራራት ሆን ብሎ ህዝብን ያሸበረ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ክብደት ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 485 ተደንግጎዋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን አስመልክቶ የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ በቅድሚያ ለራስ፣ ቀጥሎም በዙሪያችን ላሉ ቤተሰቦቻችን፣ ወገኖችን እና ብሎም ለሃገር ነው። ይህን በመገንዘብ፣ ሁላችንም ተገቢውን ጥንቃቄ አቅም በፈቀደ መጠን እንድናደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ነገር ግን ጉልህ በሆነ መልኩ የቅደመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የህዝብን ጤንነት እና የሃገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ፤ እንዲሁም የኮሮና ቫይርስ ስጋትን ሰበብ አድርገው ሆን ብሎ ህዝብ የማሸበር ወንጀል በሚፈጽሙ ላይ፣ ከላይ በተጠቀሱት የህግ ድንጋጌዎችና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ በአፋጣኝ ለመውሰድ የምንገደድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
በመደበኛ ሚዲያዎቻችን ላይ የሚታዩ ጉልህ ድክመቶችአሉታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙሃን ፈተና ነው። የቀውስ ጋዜጠኝነት አንዳንዶች የሠላም ጋዜጠኝነት ይሉታል ይበልጥ ቀውስን ከሚያባብሱ ዘገባዎች ጋዜጠኞች መራቅ እንዳለባቸው የሚመክር ነው። ጋዜጠኞች በኃላፊነት ስሜት በመስራት እየተካሄዱ ያሉ ቀውሶች ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ መቆጠብ እንዳለባቸው ያስተምራል።
በዚህ ረገድ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ ልምዱን ማጋራት ይፈልጋል። ከዓመታት በፊት በዚህች አገር በዩኒቨርሲቲዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች ነበሩ። በአንድ ወቅት በአንድ ዩኒቨርሲቲ በብሔር መካከል በተከሰተ ግጭት ጉዳት መድረሱ የዜና ጥቆማ ይደርሰዋል። በእርግጥም ጥቆማው ሲጣራ ትክክል ነበር። ነገር ግን እንደወረደ ዜናውን መስራት የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ በመሆኑ በኤዲቶሪያል ቦርድ ምክክር ተደረገ። እናም ዜናው በተማሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት ጉዳት መድረሱን ብቻ በሚያሳይ መልክ እንዲሰራ ወይንም ብሔር እንዳይጠቀስ ተወሰነ። በዚሁ መሠረት ዜናውን በመሰራቱ በጋዜጣው ምክንያት ሊከሰት ይችል የነበረ አደጋ ማስቀረት ተችሏል።
እናም ጋዜጠኞች ወሬ ማስተላለፊያ ቱቦዎች አይደሉም። ወሬው ማህበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ሊያስከትል የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ሚና አስቀድመው ማወቅና መገመት ይችላሉ። በኃላፊነት ስሜት በመስራትም ከቀውስ መራቅና ለሠላም በጎ አስተዋጽኦ ማድረግም ይችላሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ የኮሮና ወረርሽኝ አስመልክቶ የሚሰሩ ዘገባዎች መርዶ ነጋሪ ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያት ባልዳበረ ግንዛቤ እየተፈጠረ ያለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ለምሳሌ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት ውስጥ የሞቱት ብቻ ሳይሆኑ ያገገሙት በሚገባ መዘገብ መቻል አለበት። ይህ ሚዛኑን በመሳቱም በህብረተሰቡ ውስጥ ኮሮና ገዳይ በሽታ ሆኖ እንዲሳል ሆኗል። እርግጥ ኮሮና ገዳይ ነው፤ ነገር ግን ከተያዙ ሰዎች አንጻር ሲታይ የሞቱት ወገኖች ከ10 በመቶ በታች መሆናቸው ሲታይ ከዚህ የባሱ ገዳይ የሆኑ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መኖራቸውን እንድናስተውል ይረዳናል። በአገራችን ደረጃ ካየነው የትራፊክ አደጋን መጥቀስ ይቻላል።
በህብረተሰቡ ውስጥ የሰረጹ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማረም ረገድ፣
ኮሮናን አስመልክቶ አንዳንድ በሚዲዎች ጭምር በተሰራ ሐሰተኛ መረጃዎች ሳቢያ ጥቂት የማይባል የህብረተሰብ ክፍል ለተሳሳተ ግንዛቤ ተጋልጧል። ቫይረሱ ልጆችንና ወጣቶችን አይዝም፣ በብዛት የሚገድለው የእድሜ ባለጸጎችን ብቻ ነው የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ መስረጹ በርካታ የህብረሰተብ ክፍሎችን ላልተገባ ጭንቀት ዳርጓል። ሌሎች ደግሞ እንዲዘናጉ መንገድ ከፍቷል።
እውነታውን ግን እንደሚባለው አለመሆኑን በአገራችን የተያዙ ሰዎች እድሜ መመልከት ብቻ በቂ ነው። እናም ሁሉንም የህብረሰተብ ክፍሎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተከታታይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ሚዲያው ብዙ ርቀት መጓዝ ይቀረዋል።
የቃላት አጠቃቀም ግድፈትና መደበላለቅ
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚነገሩ ቃላት ትክክለኛ ፍቺ የሚፈልጉ ናቸው። “Social distance” አንዳንዶች ሲተረጉሙት ማህበራዊ ፈቀቅታ ይሉታል። ሌሎች መራራቅ፣ ርቀትን መጠበቅ ይሉታል። “Physical distance” ሲተረጉም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ይሉታል። እነዚህ ቃላት አንድነትና ልዩነት በሚገባ ከማስቀመጥ አልፎ በአማርኛ የሚኖራቸውን አቻ ትርጉም በማፈላለግ ረገድ ሚዲያው የበዛ ሚና አለው።
ሌላው በተመሳሳይ ሁኔታ “Quarantine” እና “Isolation” የሚሉት ቃላት እንደወረደ የሚነገሩበት ሁኔታ እያስተዋልን ነው። እገሌ ኳራንታይን ገባ ወይንም ተደረገ ሲባል እየሰማን ነው። ኳራንታይን ማለት ለተላላፊ በሽታው ተጋላጭ የነበረን ሰው (በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር በቅርብ ግንኙነት የነበረው)፤ ግን ምንም አይነት የህመም ምልክት ያልታየበትን ሰው ምርመራው እስኪረጋገጥ ለይቶ ማቆየት ነው።
አይዞሌሽን( Isolation ) በቫይረሱ መያዙ የታወቀና ቫይረሱን ለሌሎች የማስተላለፍ ዕድል ያለውን ሰው አግልሎ ማቆየት ወይንም ማከም ነው። ሚዲያዎቻችን እነዚህንና ሌሎች ተዛማጅ ቃላቶች በሚገባ በማወቅ በመሥራት ረገድ ውሱንነት ይታይባቸዋል።
በሶሻል ሚዲያ ተጽእኖ መውደቅ፣
መደበኛ ሚዲያዎቻችንን (ሜይንስትሪም ሚዲያ) የሶሻል ሚዲያው አጀንዳዎች አራጋቢ ከሆኑ ቆዩ። ችግሩ አጀንዳውን ማራገባቸው ሳይሆን አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎችን ጭምር እንዳለ የሚቀዱ መሆናቸው ጭምር ነው።በዚህም ምክንያት ከኮሮና ጋር ተያይዞ የባሰ የሥነልቦና ጫና በህብረተሰቡ ውስጥ እንዳይፈጠር ሚዲያዎች ወደራሳቸው ሊመለከቱ ይገባል።
ምን ይደረግ?
የሚዲያዎች አቅም ግንባታ ሶስት መልክ ቢኖረው አዋጭ ይሆናል። አንደኛው እና ዋናው ሁሉም የሚዲያ ተቋም የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ጋዜጠኞች ማወቅ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የራሱን አጭር ስልጠና ቢዘጋጅ ይመረጣል። መንግስት በበኩሉ እንደጤና ሚኒስቴር ባሉ ተቋማት በኩል በየጊዜው የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ቢችል ሚዲያውን የበለጠ እንዲሰራ ማገዝ ይሆናል። ሶስተኛው እና ጋዜጠኞች የተለየ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው በራሳቸው አቅም በንባብና ሚዲያዎችን በመከታተል አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግን አጠናክሮ የመቀጠል ጉዳይ ነው። ይህ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ብቻ ሳይሆን ሙሉዕ ጋዜጠኛ ለመሆንም ጋዜጠኞች መቼም ቢሆን ሊከተሉት የሚገባ የህይወት መመሪያቸው መሆን አለበት።
በመጨረሻም ከአጼ ኃይለስላሴ ሹማምንት አንዱ የነበሩትና የፊውዳሉን ሥርዓት አጥብቀው የታገሉት አምባሳር ብርሃኑ ድንቄ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ስለፕሬስ ጫር ያደረጉትን ቁምነገር ጠቅሼ ልሰናበት “…በአሁኑ ጊዜ የአቶሚክ ኃይል በግድየለሽ መሪዎች እጅ እንዳይገባ የምንሰጋውን ያህል ፕሬስም እንደዚሁ በግድየለሾች መዳፍ ስር እንዳይወድቅ እኩል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል…።”
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ፍሬው አበበ