አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በህግ የበላይነት ላይ ለሰኮንድ እንደማይደራደርና ከህግ ወጪ በህዝብ ላይ በጉልበት ፍላጎትን ለመጫን በሚፈልግ ማንኛውም ኃይል ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ
ገለጸ፡፡ የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ መመሪያ ማስተላለፉንም አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በክልሉም ሆነ በአገሪቱ የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላምና ዴሞክራሲ የለም፤ ስልጣን መቀባበል አይቻልም። የክልሉ መንግሥት የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ ለሰኮንድ አይደራደርም።በህዝብ ላይ ከህግ ወጪ ፍላጎትን በጉልበት ለመጫን በሚፈልግ ማንኛውም ኃይል ላይ እርምጃ ይወስዳል።
ከህግ የበላይነት በመለስ ሁሉም ፓርቲዎች ያላቸውን ሃሳብ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለህዝብ አቅርበው ህዝብ መሪውን በድምጹ እንዲመርጥ ፓርቲዎች ዕድል መስጠት እንዳለባቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ሰላምንና ጉልበትን እያጣቀሱ የሚሄዱና ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ ኃይሎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚ ወስድ አሳስበዋል።
“ፓርቲዎች ከጥፋት፣ ኋላቀር ከሆነ፣ ጊዜው ካለፈበትና ተሞክሮ ከወደቀ የጉልበትና የትጥቅ ትግል መንገድ ራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው”ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው መንገድ አንድ ነው፤ ይኸውም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ፤ የጉልበትና የትጥቅ ትግል አያዋጣም፤ያ ምዕራፍ ተዘግቷል›› ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ባለፉት 60ና 70 ዓመታት ተሞክሮ ወድቋል። በጉልበት ስልጣን የያዙትም ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ እኩልነትንና ለውጥን ማረጋገጥ አልቻሉም። ይህ የጥፋት መንገድ ማንንም አይጠቅምም።
“ሁሉም ኢትዮጵያዊና ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ያመጡትን ለውጥ እንዲቀለበስ የሚያደርግ ማንኛውም መንገድ ላይ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ይሄዳል” ሲሉ የገለጹት አቶ ሽመልስ የክልሉ መንግሥት በህግ የበላይነት ላይ ለሰከንድ አይደራደርም ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በኦሮሚያ ክልልና በአገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፋት፣ የነበሩትን የታሪክ ህጸጾች ለማስተካከል፣ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።በዚህ መሰረት በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱና በትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ ያመጣው ዕድል ባለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦበታል።
ፕሬዚዳንቱ በኦሮሚያ ክልል ራሱን ኦነግ ሼኔ ብሎ በሚጠራው የታጠቀ ቡድን በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር ጠቅሰው፤ ወለጋና ጉጂ አካባቢ የቀበሌ የወረዳ፣የዞንና የከተማ የመንግሥት መዋቅሮች እንዲፈርሱና ፍርድ ቤቶች ሥራ እንዲያቆሙ፣የፖሊሲ ጣቢያዎች ከሥራ ውጭ እንዲሆኑና ባንኮች እንዲዘረፉ ሲያደርግ እንደነበር አውስተዋል።
ቡድኑ ህዝቡ ወጥቶ እንዳይገባ ሲደረግና የሰራተኞች፣ የጸጥታ ኃይሎችና የነዋሪዎችን ህይወት ሲቀጥፍ ቆይቷል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ መንገድ ዘግቶ ሁሉንም እንቅስቃሴ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ባለሀብቶችን ገንዘብ ሲቀበል፣አርሶ አደሩን እንጀራ ጋግራችሁ አቅርቡ እያለ ሲያሰቃይ በቆየው ቡድን ላይ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት እርምጃ በመውሰድ ችግሩን መፍታቱን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ህዝቡ ሰላምና መረጋጋቱ እንዲመጣና ችግሮቹ መስመር እንዲይዙ ከአመራሩና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በሰራው ሥራ አሁን በምዕራብ ኦሮሚያ ላይ ሰላምና መረጋጋት እንደተፈጠረ አመልክተው፤በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ያለምንም ችግር ይንቀሳቀሳል፣ ወጥቶ ይገባል፤ የተወሰነ እፎይታ አግኝቷል፤ ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶች ሥራ ጀምረዋል።የተጠናቀቁም አሉ።አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ሥራ እንዲጀምሩና ተቋርጦ የቆየው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትም ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑን ጠቁመዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ፤ የአካባቢውን ህዝብ ስም የማጥፋት ሥራ የሚሰማሩ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች እጃቸውን መሰብሰብ አለባቸው ፤ ከዚህ በኋላ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚደረግ ማንኛውም የስም ማጥፋት ዘመቻ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አይታገስም፤ ይህን በሚያደርግ ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ይወሰዳል።
በተያያዘ ዜና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤የኮሮና ቫይስ ችግር ዓለም አቀፍ ወረርሽ በመሆኑ በአገራችን የቫይረሱን ስርጭቱን ለመግታት የክልሉ የመንግሥት መዋቅርና ኃላፊዎች ሌላውን ሥራ ለጊዜው ተወት አድርገው 24 ሰዓት ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥና የመንግሥትን ውሳኔዎች በማስተግበር ረገድ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ መመሪያ ተላልፏል።
በኦሮሚያ ክልል ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመግታት ረገድ ህብረተሰቡን በማስተማርና የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ረገድ የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ መንግሥት የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ሙያዊ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ክፍተት በመኖሩ በተለይ ለገጠሩ ህብረተሰብ ተደራሽ የሆኑት ሬዲዮ ጣቢያዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎች የማስተማር ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል።
ህዝቡ ራሱን ከቫይረሱ ለመከላከል መንግሥት የሚወስናቸውን ውሳኔዎችና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ሙያዊ ምክሮች መከተልና መተግበር እንዳለበት ገልጸው፤ የመንግሥት ኃላፊዎች፣የጸጥታ ኃይሎችና ወጣቶች ህዝቡን በማስተማርና በመንግሥት የተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ በትጋት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ክልሉ ለኮሮና ቫይረስ በሚያጋልጥ መንገድ ስርዓተ አምልኮ በሚፈጸሙ የሃይማኖት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ታውቋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2012
ጌትነት ምህረቴ