የከተማም ሆነ የከተሜነት ብያኔ እንደየአገሩ ይለያያል። ከተማ የሚለውም እንደየአገሩ የህግ ብያኔ ይሰጥበታል። ከዚህም የተነሳ እርግጠኛ የሆነና ሁሉንም የሚያስማማ ብያኔ አለ ማለት ይከብዳል። ነገር ግን በግርድፉ ህዝቦች ተጠጋግተው የሚኖሩበት፣ ለኑሮ ስርዓታቸው ደግሞ ቦታም ስርዓትም የሚያበጁበት ነው፤ ብዙ ጊዜ ግን ሲወራ ከተማ የኑሮ ቦታ ብቻ ይመስላል። ነገር ግን ከተማ ማለት ቦታና የኑሮ ውቅር ወይም ስርዓት ነው።
ከተሜነትንና ኢትዮጵያ ለከተሜነት ምን ያህል ዝግጁ ናት በሚለው ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ስለከተማ ብያኔ የተናገሩትም ተመሳሳይ ሐሳብ ነው። ይኸውም፤ ከተማ ሲባል በኢትዮጵያ ህግ ስርዓት የሚወሰደው ከሁለት ሺህ ህዝብ በላይ ያለበትን እንደሆነ ነው። እነዚሁ የዘርፉ ባለሙያዎች ከተማ ሲባል አብዛኛው ህዝብ ከግብርና ውጭ ባለ የኑሮ ማሸነፊያ ስርዓት የሚኖርበትን አካባቢ ሲሆን፣ የራሱ የሆነ አስተዳደራዊ ፣ ፖለቲካም ኢኮኖሚ መዋቅር ያለው እንደሆነም ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ መምህር ዶክተር ዘገየ ቸርነት እንደሚሉት፤ የከተማ ብያኔ ሲቀመጥ ብያኔው በመላ ዓለም ሁለት ሺህ ሰው የሚኖርበት ማለት አይደለም፤ የተለያየ ቁጥር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ዓለምአቀፍ የህዝብ ብዛት ወይም የቦታ ስርዓት የወጣለት ደንብ የለም። በመሆኑም ሳይንሳዊ የሆነ ብያኔ የለውም ማለት ነው። እስካሁን ባለው አካሄድ በሳይንቲስቶችና በአጥኚዎች ብያኔ የሚሰጠው ሳይሆን በህግ ብያኔ የሚሰጠው ነው።
ከተማ ማለት የተለያዩ አይነት ሰዎች ለአብሮ መኖር የሚፈጥሩት የቦታና የአስተዳደር ቀመር ነው። ከመንደር አሊያም ከገጠር የሚለየው በይበልጥ የተለያዩ ሰዎች መሆናቸው ላይ ነው። ስለዚህ የተለያዩ ሰዎች መጥተው ሐሳብና እቃ የሚቀያየሩበት ስርዓትም ስለሆነ ከተማ ከገጠር የሚለየው በዚህም ነው። በተጨማሪ ከተማ የስልጣኔ ምንጭ ነው። ከተሜነት ሲባል ደግሞ የባህል ወርድና ስፋት አለው። ከተሜ ማለት በጥግግት ከማያውቁት ሰው ጋር በህግና በስርዓት አብሮ መኖር ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ለከተማነት ምን ያህል ተዘጋጅታለች ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶክተር ዘገየ ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ለከተማነት አልተዘጋጀችም። ›› ሲሉ ነው የማያወላውል አቋማቸውን በማስቀመጥ ምላሻቸውን የገለፁት። ‹‹ዝግጁነት ሲባል ለአብሮነት የመድረክ ቅንብር ግዑዛዊ የሆነውን የከተማ ስርዓት ማዘጋጀት፣ ግዑዛዊ ያልሆኑ ደግሞ ህግጋቱንና ስርዓቱን ማዘጋጀት፣ ለእነዚህ ዝግጅቶች የሚረዱትን የሰው ኃይል፣ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት የሚሉትን ስናይ ፈፅሞ አልተዘጋጀችም። ›› ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር ዘገየ፣ ‹‹ወደድንም ጠላንም በቀጣዮቹ ጊዜያት አገራችን ወደከተሜነት መሸጋገሯ አይቀርም ብለን ስንጮህ ነበር። ›› ማለታቸውን አስታውሰው፤ ‹‹እኤአ ከ2007 ጀምሮ ከ50በመቶ በላይ የዓለም ህዝብ የሚኖረው በከተማ ነው። ይህ ማለት የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ነው። አሁን ደግሞ ያለንበትን ደረጃ ማሰብ ይቻላል። ››በማለት አመልክተዋል።
‹‹ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ህዝብ የሚኖረው ከተማ ውስጥ ነው። ይህ አሀዝ አሁን ወደ 40 በመቶ ተጠግቷል ይባላል። ›› ያሉት ዶክተር ዘገየ፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዓመት ከ20 በመቶ በታች ነን፤ የዓለም የመጨረሻ ከሚባሉት አገሮች ተርታ ነን። ››ይላሉ።
‹‹ላለፉት ብዙ ዓመታት የኢኮኖሚው ፖሊሲያችን ገጠርን ማዕከል ያደረገ ነው፣ ማህበራዊ ጉዳዮቻችን የፖለቲካ አመለካከታችን ገጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው፤ ምነው ተብለው ፖለቲከኞች ሲጠየቁ ከ85 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠር ነው የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። አገሪቱ የምትጠቀመው በእርሻ ሆኖ ሳለ ስለምን ሌላ ወሬ እናወራለን ይላሉ። ››ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በመሰረቱ ከተሜነት ወይም የመከተም ስርዓት ከልማት መለኪያ ጋር ይያያዛል። ዝግጁነት ደግሞ ከሰው ኃይል፣ ከልማት፣ ከህግና ፖሊሲ ስርዓትና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዘ ስለሆነ በዚህ በኩል ሲታይ አገሪቱ ፈፅሞ አልተዘጋጀችም። እውነቱን ለመናገር እስከ 2009 እና 2010 ዓ.ም ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ስለከተማና ስለ ስነ ህንፃ ያስተምር የነበረ አንድ ቀጭን ቀጫጫ ዲፓርትመንት ያለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ይህ ማለት እንግዲህ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት አንድ ለእናቱ ህንፃ ኮሌጅ ብቻ ነበር። ያውም ደግሞ በዝቅተኛ ችሎታ። ምክንያቱም አብዛኛው አካል ስነ ህንፃና ስነ ከተማ የቅንጦት ትምህርት ስለሚመስለው ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር አስራ አምስት ዓመታት ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰቱ እንደ ደራሽ ጎርፍ ከመምጣቱ በፊት እባካችሁ መዘጋጀቱ፣ ሰው ማስተማሩ፣ ስርዓቶችን ማስተካከሉ የግድ ይላል በማለት ሲጮህ ነበር። ግን መልስ የለም። ስለዚህ በአጭሩ አገሪቱ በጭራሽ ለከተሜነት አልተዘጋጀችም።
‹‹በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባን አንገቷ የታነቀ ስለመሆኑ ማስተዋል ይቻላል። ሳትዘጋጅም ህዝቡ ድንገት እንደደረሰባት መረዳት አይቸግርም። በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ መኖሪያና መሰል አስፈላጊ ነገሮችንም ለህዝቧ ማቅረብ እንዳቃታትም ማስተዋል አይገድም። ከመንገዱ መጨናነቅ የተነሳ በየቀኑ የሚባክነው ጊዜ ከግምት ውስጥ ሲገባ አይታይም። አንድ ሰው ወደመስሪያ ቤቱ የሚደርሰው ሰዓታትን ፈጅቶ በጠራራ ፀሐይ ነው። ›› ሲሉ ያብራራሉ። እንደዛም ሆኖ አዲስ አበባ ከሌሎቹ በተሻለ አቅርቦቱ አላት ተብሎ ስለሚታሰብ አንድ ነገር ኮሽም ሲል ሰው የሚመጣው ወደዚህች ከተማ መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ግን ሁሉ ነገር ከአቅሟ በላይ እየሆነ ልትታነቅ የደረሰች እስኪመስል ድረስ ትዝብት ላይ መውደቋን ያስረዳሉ።
መ ፍ ት ሄ ብለው የጠቆሙት ደግሞ አሁንም ቢሆን አገሪቱ ለከተማነት መዘጋጀት ያለባት ስለመሆኑ ነው። ‹‹ምክንያቱም›› ይላሉ ‹‹የከተማ ስርዓት ኢንቫይሮሜንቱን፣ ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን ሁሉን ስለሚነካ ስለ ጉዳዩ ጥራት ያለው ትምህርት ይጠይቃል። የከተማ መሀንዲሶችን የከተማ ኢኮኖሚስቶች፣ እነዚህን የመሳሰሉ ባለሙያዎች በጥራት ሊኖሩን ይገባል፤ አለበለዚያ የምናበዛው ጥፋት ነው። ››ብለዋል።
ኢትዮጵያ የከተሜነትና የከተማ ሽፋናቸው ዝቅተኛ ከሚባሉ አገሮች መካከል ስለሆነች ጥሩ እድል እንዳላትም ይጠቁማሉ። በብዙ መከራ ማለፍ ሳይኖርባት ቀደም ሲል መከራን አይተው ካለፉ አገራት ልምድ ለመውሰድ እንደ እድል ሊቆጠር የሚችል ነው። ሌሎች አገሮች የሰሯቸውን ስህተቶች ከሌሎች በመማር የተሻለ በፍጥነት ነገሮችን ማቀናበር የሚቻልበት እድል አለ። ከኋላ መነሳት ስህተት ላለመድገም እድል እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ዘገየ አነጋገር፤ ብቁ የማንበብና የመረዳት አቅም ያላቸውን ወጣቶች መፍጠር ያለብን ለዚህ ነው። ምክንያቱም ሐተት፣ ኮሌራ፣ ውሃ ወለድ በሽታ የመሳሰሉ ኃይለኛ ወረርሽኞች የከተማ ውጤት ናቸው። ብዙዎቹ ህዝብ በተጨናነቀበት ይፈጠራሉ። አውሮፓ በአንድ ዘመን አንድ ሶስተኛ የአውሮፓ ህዝብ መሞት ነበረበት፤ ፓሪስ፣ ለንደን፣ በርሊን የሚባሉ ውብ ውብ ከተሞች የሞት ስፍራ ነበሩ። ይህ የሆነው ከከተማ ስርዓት ማጣት የተነሳ ነው። የሕዝብ ጤንነት ጉዳይ የዶክተሮች ጉዳይ ሳይሆን የዲዛይነሮችና የአርክቴክቶች ጉዳይ ነው። ስለዚህ ባለሙያዎችን በስርዓትና በጥራት ማስተማር ግድ ይላል። ያለበለዚያ ወጪው ይበዛል።
‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ አስር ገዳይ በሽታዎች ውስጥ ለዘጠኙ የዶክተሮቹ የመከላከል አቅም ዜሮ ነው። ለምሳሌ መኪና አደጋን ዶክተር በምን ይቀንሳል፡ የመኪና አደጋ የህዝብ/የማስ/ በሽታ ነው፤ መንገዳችንን ዲዛይን ያደረግንበት፣ የትራፊክ ስርዓታችን ጉዳይ ነው። ይህም የከተማችን የአወቃቀር ጉዳይ ነው፤ የህዝባችን የአኗኗር ባህል ነው። ››ሲሉ ያብራራሉ።
በዚህ ጉዳይ እንግዲህ ሐኪም ምን ያደርግልናል። መኪና አደጋ ከደረሰ በኋላ ወይ እግር ይቆርጣል ወይ ሰፍቶ ያክማል። ለአንዲት ከተማ ፓርክ መኖሩ ህዝቡ በእግር የመጓዝ እድል እንዲኖረው ያደርጋል፤ በእግሩ ሲንቀሳቀስ ደግሞ እንደ ስኳር በሽታ አይነት አይያዝም። ስለዚህ ከአስሩ ገዳይ በሽታዎች ውስጥ በዘጠኙ በሽታዎች ሐኪም ሊረዳን አይችልም። ለእዚህም ነው ስለከተማ እንዘጋጅ ስንል ብቁ ሰዎችን፣ አሳቢዎችን፣ ከተማን ማዋቀር የሚችሉና ህግና ስርዓቱን ማበጀት የሚችሉ ምሁራንን እንዲሁም ህግን በማስተካከል መፍጠር አለብን የምንለው ይላሉ።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ አማካሪ አቶ ሄኖክ ባለሟል በበኩላቸው፤ አገሪቱ ለከተሜነት ለመዘጋጀት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ያመለክታሉ። ‹‹ከዚህ አኳያ ስትራቴጂዎችን በማውጣት ላይ ነን፤ ስታንዳርድና ማንዋሎችንም እያዘጋጀን ነው። ›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ ያለፕላን የሚመሩ ከተሞች እንዳይኖሩ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ተግባራዊ የሚደረገው ፕላን ደግሞ አንድ ከተማ መያዝ የሚገባውን መስፈርት የያዘ መሆን እንዳለበትም ያመለክታሉ።
እንደ አማካሪው ገለፃ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ አንድን ከተማ ከተማ ነው የሚያሰኘው አንደኛው የህዝብ ብዛቱ ነው። ያ ማለት ከሁለት ሺህ በላይ የህዝብ ብዛት ያለው ከሆነ ከተማ ተብሎ ይመዘገባል። አንድ ከተማ ከተማ የሚለውን ስያሜ ካገኘ በኋላ ወደከተሜነት ለመቀየር ዋናው ጉዳዮቹ ህዝቡ የሚያገኛቸው እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ገበያዎች፣ ፖሊስ ጣቢዎች ያሉት መሰል አገልግሎቶች ናቸው።
‹‹የከተማ ነዋሪው እንደ ከተማነት መኖር የሚያስችለውን ልማት በእኔ አመለካከት አግኝቷል ማለት አያስደፍረኝም። ከመንገድ አኳያ እንኳ ሲታይ ለአካል ጉዳተኛውም ብዙ የማይመቹ ነገሮች አሉ። በከተማ ንፅህናም የተሰራው ዝቅተኛ ነው። እነዚህንና መሰል መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት ይገባል። ››ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ እስከዛሬ መሰረት ተደርጎ የተሰራው ህንፃን መስራትና ማሳደግ ላይ ነው። ከተማ ላይም ፍሳሽ ማስወገጃና ቆሻሻ መጣያዎች በበቂ ሁኔታ አይታዩም። በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ሲታይ ለነዋሪው ምቹ አይደለም። ስለዚህ እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ማሟላት ያስፈልጋል። የከተሜነትን ባህሪ መላበስ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፤ ይህም አብዝቶ መስራትን ይጠይቃል።
‹‹ከዚህ በኋላ ለከተሜነት ለሚሰሩ ነገሮች ዝግጅት አድርገናል። ›› ያሉት አቶ ሄኖክ፣ ከተማ ውስጥ ለሚሰሩ እያንዳንዳቸው መንገዶች፣ ቤቶች፣ ህንፃዎችና መሰል ተግባሮች ምን መደረግና መካተት እንዳለበት እንዲሁም ምን ቢደረግ ነው ከተሞች ለነዋሪው ምቹ ሊሆኑ የሚችሉት የሚለው በሰነድ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
በስትራቴጂና በማኑዋል ደረጃም ዝግጅት መደረጉን፣ የሌሎችንም አገር ተሞክሮዎችን በመውሰድ ወሳኝ የሆኑ ስታንዳርዶች ተዘጋጅተው እየተጠኑ ስለመሆናቸውም አብራርተዋል። በተለይ ከዚህም በኋላ የሚሰሩ የከተማ ፕላኖች እነዚህን መስፈርቶች ያሟሉ እንዲሆኑ ስለሚደረጉ የተሻለ ከተማ ማየት እንደሚቻል ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
አስቴር ኤልያስ