ሻምበል ባሻ ዘውዴ መታፈሪያ ገና በሁለት ዓመታቸው እናታቸውን በማጣታቸው አጎታቸው ናቸው በእንክብካቤ ያሳደጓቸው፤ በልጅነት ዕድሜያቸው ለወታደር የሚሰጠው ካፖርትና ጫማ አማልሏቸው ከሚኖሩበት ሸዋ ክፍለ አገር ካራ ቆሬ ከተማ ተመልምለው ከ500 ወጣቶች ጋር በ1948 ዓ.ም አዲስ አበባ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ገቡ።
ስልጠናውን አጠናቀው ስራ ሲጀምሩ የ23 ብር ደመወዝተኛ ሆኑ። ከ23 ብር ደመወዛቸው 12 ብር ለምግብ ተቀንሶ 11 ብር ሲከፈላቸው ትዳር ለመመስረት አላነሳቸውም። እንደ ብዙዎቹ የዘመናቸው ወታደሮች ትዳራቸውን በወታደር ካምፕ ሆነው መሰረቱ።
የትዳር ህይወትን ለሶስት ዓመት ካጣጣሙ በኋላ ግን አስደንጋጭ አደጋ ተከሰተ። ከ18 ወታደሮች ጋር በመኪና ሲሄዱ የተሽከርካሪ አደጋ ደረሰባቸው። አደጋው የመኖር ተስፋቸውን ለማጨለም ጫፍ ቢያደርሳቸውም ተርፈው በ1952 ዓ.ም አስር አለቃ መሆን ቻሉ።
በጊዜው ብሩ ብዙም በቂ ስላልነበር ቤት ለመስራት አላቀዱም። በ1953 መንግስቱ ነዋይ እና ግርማሜ ነዋይ ጃንሆይን ለመገልበጥ በሞከሩበት ጊዜ ደመወዛቸው 40 ብር ደረሰ። በሂደት በውትድርና ውስጥ የተሻለ ወደሚባለው የህክምና ዘርፍ በመግባታቸው 10 ብር፤ ልጅ ያላቸው በመሆኑ ደግሞ ሌላ የልጅ አበል 3 ብር ታክሎ ዕድገቱም ተጨማምሮ ደመወዛቸው 78 ብር ደረሰ። አራት ልጆች በአናት በአናቱ ተወለዱ።
በ1966 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ተቀይረው ስለነበር ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ኤርትራ ገቡ። አስመራ ካምፕ ሆነው አብዮቱ ሲፈነዳ ለሁለት ዓመት ወደ አሰብ ተዘዋወሩ። ይህ ወዲህ ወዲያ ማለት አንድ ቦታ ተረጋግተው እንዳይቀመጡ አረጋቸው፤ የመኖሪያ ቤት እንዳይሰሩም አገዳቸው።
ከአሰብ እንደገና ወደ አስመራ ሲመለሱ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ አበበች ደግሞ ብቻቸውን አዲስ አበባ ገቡ። ወታደር ሳይሆኑ የወታደር ሚስት በመሆናቸው ወይዘሮ አበበች አራት ልጆቻቸውን ይዘው ካምፕ መግባት አልቻሉም። ቤት ለመከራየትም አከራዮችን ፈሩ፤ መከራየታቸው አልቀረም እዛው ካምፕ አካባቢ በ5 ብር ተከራዩ። ተፈሪዎቹ አከራዮቻቸው ወይዘሮ አበበች ላይ አልከፉም፤ እንዳያውም በፍቅር ምርጥ የተባለ ጊዜ አሳለፉ።
ከካምፑ ሰው፣ ከአከራዮቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ፍቅር ቢሆኑም፣ የባለቤታቸው በቅርብ አለመኖር ያስጨንቃቸው ወይዘሮ አበበች፤ ሻምበልባሻ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ አዛዦቻቸው ዘንድ ተመላልሰው መጠየቁን ተያያዙት። ደጋግመው በመጠየቃቸው አዲስ አበባ ያሉት አዛዦች ለስድስት ዓመታት በአስመራ የቆዩትን ሻምበልባሻ ዘውዴ አዲስ አበባ እንዲገቡ ቢፈቀዱም፤ አስመራ የነበረው አዛዥ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም፤ ይህም የወይዘሮ አበበችን ጭንቅ አባሰው፤ የአስመራው አዛዥ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ሻምበል ባሻን አዛወሯቸው፤ ሻምበል ባሻም ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ።
ሻምበልባሻ በወቅቱ የከተማ አስተዳደር ለነበሩት ኮሎኔል ማሞ ‹‹መሬት በምሪት ይሰጠኝ›› የሚል ጥያቄ በማቅረብ ለአንድ ዓመት ከተመላለሱ በኋላ ሰላሳ ብር ከፍለው መሬት ተሰጣቸው። የእነርሱ መሬት ማግኘት በቅርብ ወዳጆቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው ላይ ጭምር ትልቅ ደስታ ፈጠረ።
ቤቱን ለመገንባት ቅየሳ ተካሄደ፤ ሁሉም ወዳጆቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው ተባብረው በጋራ በአንድ ቀን ቤቱን አቆሙላቸው። በቀጣይ ቀን አሁንም ድረስ የሚጠቀሙበትን የቤቱን ውሃ ልክ በደቦ ገነቡት። ድምድማቱንም በፍቅር በጋራ የሰሩት ጎረቤቶቻቸው እና ወዳጆቻቸው ናቸው። በሙያተኛ የሚሰራውን ጭቃ ልጠፋ፣ ትምታሞ እና የቆርቆሮ መምታት ሥራውን ለማሰራት ደግሞ ገንዘብ በመስጠት ተረባረቡላቸው።
ምንም እንኳን በደቦ በህብረት የተሰራው ቤት ተጠናቆ ባለሙያ የግድ የሚላቸው ሥራዎች ብቻ በባለሙያ እንዲሰራ ቢደረግም፣ ቤት ሰሪ ደም የለውም እንደሚባለው ነገሮች ፈታኝ ሆነውባቸው ነበር። ቤቱ ቤት ለመሆን የበቃው መላ ቤተሰቡ ዘይት ዞር ያላለበት ወጥ እየበላ፣ ወይዘሮ አበበችም ሆኑ ሻምበልባሻ ዘውዴ ጠዋት የወጡ ምግብ ሳይቀምሱ ደርቀው እየዋሉ ነው።
እነርሱ እየራባቸው ሰራተኞችን እየመገቡ፤ ለጭቃ አቡኪዎቹ ቆሎና ጠላ እያቀረቡ፤ የበላዩም ሆነ የበታቹ ሰው ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን አንዳንዴም በአይነት ጭድን ጨምሮ ሌሎች ስጦታዎችን ቢለግሳቸውም ባለሙያዎቹ ያልሰሩበትን ገንዘብ አስቀድሞ እየጠየቁ፣ ሲሰጣቸው እየጠፉ ቢያሰቃዩዋቸውም የተንጣለለ ትልቅ የሚባል ቤት ባለቤት ለመሆን በቁ።
በ1974 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ የተጀምረው ቤት በርና መስኮት ባይሟላለትም በቆርቆሮ ሸፍነው በሚያዚያ የኮልፌ ሰፈር ጎረቤቶቻቸውን በእንባ ተሰናብተው ብዙ ሰው ወደማይኖርበት ጠሮ ወደ ተባለው ሰፈር በመግባት ሰፈሩን ከሚቆረቁሩት ጋር ተቀላቀሉ። ከቆይታ በኋላ ወይዘሮ አበበች የወርቅ ሀብላቸውን ሽጠው በር አሰሩ፤ እንጀራ እየሸጡ ልጅ ከማስተማር አልፈው ቤቱን አፀዱ፤ ጣራ ቀይሩ፤ ወለሉን አስተካከሉ። አሁን ሰፈሩ ለምቶ ቤት በቤት ቢሆንም፣ በፊት ሙሉ ለሙሉ ጫካ እንደነበር ያስታውሳሉ። ልጆቻቸውን ጅብ እንዳይበላባቸው ሌላም አውሬ እንዳይተናኮልባቸው ይሰጉም ነበር። መብራት ባለመኖሩ፤ በኩራዝ ቢከርሙም ቆይቶ መሰረተ ልማቱ መሟላት ሲችል ኑሮ ተመቻቸው።
አሁንም እነሻምበልባሻን ውለታ አሥሯቸዋል። ከ38 ዓመት በፊት የዋሉላቸውን የወዳጆቻቸውን ለቅሶ አይበሉም። ምንም እንኳ ብዙዎቹ ቢሞቱም አሁንም ድረስ በህይወት ካሉት ጋር ይገናኛሉ። ያ የፀና የቀደመ ፍቅር፤ በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት አልጋ ተዘርግቶ እና ግራ እና ቀኝ ሁለት የእንጀራ መሶብ ተቀምጦ በደባልነት ሁለት ቤተሰብ በደስታ ይኖር የነበረበት ዘመን ቢያልፍም ለነሻምበል ባሻ ትልቅ ቅርስ አትርፎላቸዋል።
ዛሬ ያ ቤት የተንጣለለ የሀብታም ጊቢ ሆኗል። ከዋናው ቤት ሌላ ማድቤትን አካቶ አስር ክፍሎች ተሰርተውበታል። እነሻምበልባሻ የኑሮ ውድነት አሻቅቦ የጡረታው ገንዘብ አፍ ባይሞላም፤ እንደበፊቱ አቅም ኖሮ ታዋቂ የእንጀራ ነጋዴ ሆነው ሽጠው አትርፈው ያሻቸውን መግዛት ባይችሉም በደህና ጊዜ የሰሩት ቤት ይጦራቸዋል። ተንደላቀው ከመኖር አልፈው ለልጆቻቸው መትረፍ ችለዋል። ጎረቤቶቻቸው ያደረጉላቸው በጎ ተግባር እስከ ዕድሜ መጨረሻቸው ቅርስ አስይዟቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
ምህረት ሞገስ