ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ-በስደት የባከኑ ዓመታት

የዛሬ እንግዳችን አስከፊውን የሕገወጥ ስደት ገፅታ ታስቃኘናለች። ‹‹ሕይወታችንን የሚያሻሽልልን አንዳች ተዓምር እናገኛለን›› በሚል ቀቢፀ ተስፋ ባሕር ማዶን መናፈቅ ማቆም እንደሚገባን ልቦለድ ከሚመስለው የግል ተሞክሮዋ እያጣቀሰች ታወጋናለች። ውቅያኖስ ቀዝፈው ለዓሣ ነባሪና ለጥልቁ ባሕር ወለል ሲሳይ የሚሆኑ ወገኖቻችንን ሕገወጥ ጉዞ ይብቃችሁ ትላለች።

ለዓመታት በሕገወጥ ስደት በርካታ ሀገራትን ድንበር አቋርጣ ገብታለች። በተደጋጋሚ ለደላሎችና አጭበርባሪዎች ሲሳይ ሆናለች። ከአንዱ ሀገር ወደሌላኛው ድንበር ጥሳ፣ ጀልባ ተሳፍራ፣ ከእስር ቤት አምልጣ በሕገወጥ መንገድ ‹‹ሕይወቴን አሻሽልበታለሁ›› ያለችውን ሥራ ሞክራለች። በውጤቱ ግን ተስፋዋን ያጨለመ ክህደት፣ ሕይወቷን ሊቀጥፍ ከጫፍ የደረሰ አጋጣሚ ጋር አጋፍጧታል።

በመጨረሻም ከ20 ዓመታት እንክርት በኋላ ለሀገሯ መሬት በቅታ ‹‹ሕገወጥ ስደትን ዛሬም የሚያስቡ እህት ወንድሞቼ ከእኔ ይማሩ›› ስትል ትማፀናለች። ይህቺ ሴት ማርታ ዳዊት ትባላለች። የዝግጅት ክፍላችን ‹‹ለመሆኑ ለሕገወጥ ስደት የዳረጋትን ምን ይሆን? ዛሬስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች?›› ሲል የሕይወት መንገዷን እንደሚከተለው ቃኝቶታል። አብራችሁን ቆዩ!!

ሰሜን ጎንደር- ደባርቅ

ማርታ ዳዊት፣ የተወለደችው በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ በገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቿ በዝቅተኛ የግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ናቸው። እድሜዋ ባይጠናም፣ ገና በሰባት ዓመቷ የቤቱን በጎችና ፍየሎች ትጠብቅና ሥራ ታግዝ እንደነበር ታስታውሳለች። በእርግጥም በአንዳንድ የገጠር መንደር ውስጥ ታዳጊዎች ኃላፊነት መውሰድና የቤት ውስጥ ሥራ ላይ መሳተፍ የሚጀምሩት ገና በልጅነታቸው ነው። ማርታም ከእነዚህ ታዳጊዎች አንዷ ነበረች።

የእንግዳችን አባት አቶ ዳዊት፣ በሥራ ምክንያት በመኖሪያ ቤታቸው አይቆዩም ነበር። በዚህ ምክንያት ልጃቸውን በቅርበት በመከታተልና ትምህርት ቤት እንድትገባ የአማራና የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነችው አዲአርቃይ አካባቢ ወደምትገኝ እህታቸው ጋር ወሰዷት። ያን ጊዜ ማርታ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበረች። አጥንቷ በደንብ ሳይጠና፣ የሕይወትን ሀሁ በአግባቡ ሳትገነዘብ ለትዳር ታጭታም ነበር። ለትምህርት ወደ አዲአርቃይ መሄዷ ግን ካለ እድሜ ጋብቻ ከሚደርስ የሥነ ልቦና ጫና አምልጣለች። ‹‹ከአካባቢው ርቄ በመሄዴና ባለመዳሬ እናቴ ከፍተኛ ጫና ይደርስባት ነበር›› ትላለች ሁኔታውን መለስ ብላ እያስታወሰች።

ካለ እድሜዋ ወደ ትዳር ከመግባት ታምልጥ እንጂ በአክስቷ ቤት ግን ሕይወት አልጋ በአልጋ አልነበረላትም። ከፍተኛ የሥራ ጫና ነበረባት። በዚህ ምከንያት ትምህርት ቤት ሁሌም አርፍዳ ነበር የምትገባው። ‹‹መምህሩ ሁሌ ነበር የሚገርፈኝ፤ በሥራ ጫና እንደማረፍድ ብነግረውም አይረዳኝም›› ትላለች ይደርስባት የነበረውን እንግልት እየተናገረች። አክስቷ ታማሚ ልጅ ስለነበራትና የቤት ውስጥ ሥራ በሙሉ በታዳጊዋ ማርታ ላይ በመውደቁ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ይደርስባታልም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እስከ 13 ዓመቷ ቆይታለች።

ወደ ገጠር በመመላለስ እናቷን የመጠየቅ አጋጣሚ የነበራት ማርታ ዳግም ግን ሕይወቷን ከቤተሰቦቿ ጋር ለመምራት አልቻለችም ነበር። ምክንያቱም የሕይወት አቅጣጫ የመራት ከትምህርት ይልቅ ስደት፣ ከድሎት ይልቅ ችግርን ለማምለጥ የሚደረግ ግብግብ ሆነ። ትምህርቷን በአክስቷ ቤት እስከ ሰባተኛ ክፍል ብትማርም ገና በታዳጊነቷ ከሚደርስባት ጫና ለማምለጥ ቆረጠች። ኑሮዋን ለማሻሻል ስደት አማራጭ መሆኑን በቅጡ ባልዳበረው አዕምሮዋ ወስና ከጥቂት እሷን ከመሰሉ ጓደኞቿ ጋር ወደ ሱዳን ለመሻገር ተመካከሩ። የማርታ ረጅሙ የስደት ታሪክ በዚህ ጀመረ።

ስደትን እንደ አማራጭ

‹‹ዓለም በስደተኞች ነው የተሠራችው›› የሚል አባባል አለ። ቅሉ ግን በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረግ ስደት ግለሰቡን አሊያም ግለሰቧን ለበርካታ መከራዎች ይዳርጋል። ሕገ ወጥ ስደት ለደላሎች ሲሳይ፣ ለበረሀ ሀሩር፣ በአሠሪዎች ለሚደርስ እንግልት፣ በባሕር ውስጥ እስከመስጠምና የአውሬ ሲሳይ እስከመሆን ያደርሳል። እንግዳችን ማርታም ‹‹ሕይወቴን ያሻሽልልኛል›› በሚል የመረጠችው መንገድ ይህንኑ የጨለማ ጉዞ የሚያሳይ ነበር። የመጀመሪያው የስደት አቦጊዳም ገና በ13 ዓመቷ ነበር የተጀመረው።

ለመሰደድ በሚል ከእሷ በትንሹ በእድሜ ከሚበልጡ ጓደኞቿ ጋር ሙከራ ለማድረግ ሳንቲም ማጠራቀም ጀመሩ። እሷ ወደ ቤተሰቦቿ ተመልሳ እህል በቅዳሜ ገበያ በመሸጥ ትንሽ ፍራንክ ቋጠረች። አክስቷ ጠላ ትሽጥ ስለነበር ከዚያም ቀናንሳ የሚበቃትን ያዘች። በ14 ዓመቷ ሱዳን ለመግባት መተማ ከባልንጀሮቿ ጋር አቀናች። በጊዜው ለአቅመ ሄዋን ያልበቃችው ማርታ ፓስፖርት እንኳን አልነበራትም። በዚህ ምክንያት ከሕገወጥ ደላሎች ጋር ተነጋግረው ወደ ሱዳን በፒካፕ መኪና ተጭነው ተወሰዱ።

‹‹በባስና በፒካፕ መኪና እያፈራረቁ ነበር የወሰዱን፤ ልጅ ስለነበርኩ በመንገድ ላይ በማያቸው ነገር ደስተኛ ነበርኩ›› ትላለች፤ ከፊቷ የሚጠብቃትን አስከፊ ፈተና ያልተገነዘበችው እንግዳችን በመኪና ጉዞ ማድረጓ ብርቅ ሆኖባት እንደነበር እየነገረችን። ሱዳን እንደገቡ ወደ ደላላ ቤት ነበር ያመሩት። በዚያ ጓደኞቿ ቶሎ ሥራ አግኝተው ሲቀጠሩ እሷ ግን ትንሽ ልጅ በመሆኗና ሰውነቷ ቀጫጫ ስለነበር ቀጣሪ ለማግኘት ተቸገረች። በአጋጣሚ ግን አንድ ግብፃዊት ልጆቼን ትጠብቅልኛለች በሚል ቀጠረቻት። አጋጣሚው ለማርታ እፎይታ ነበር። የመጀመሪያ የስደት ሕይወት ሥራዋን የጀመረችበት ጊዜ።

የማርታ ሕይወት የተረጋጋ መሰለ። ተቀጥራ የምትሠራባት ግብፃዊት ሐቀኛ ነበረች። የምትሠራበትን ክፍያ ሳታጎደል ትሰጣታለች። በሳምንት አንድ ቀን እረፍት ነበራት። እሱን ተጠቅማ ፀጉር ቤት ሥልጠና ጀመረች። የምታገኘውን ገንዘብ ግን ምንም አታጠፋም ነበር። በዚህ ሁኔታ ከዓመት በላይ ስትሠራ ቆየች። ይሁን እንጂ ልቧ አሁንም አላረፈም ነበር። አብረው ወደ ሱዳን ከገቡ አንድ ሴት ጓደኛዋ ጋር ይገናኙ ነበር። ይህ አጋጣሚ ሌላ የስደት ሕይወትን ወለደ። ጓደኛዋ ወደ ሊቢያ ቢሄዱ የተሻለ እንደሆነ አማከረቻት። ወደዚያ የሚያሻግሯቸው ደላሎች እንዳሉም አስረድታ ለሌላ ስደት ተዘጋጁ።

ጉዞ ወደሊቢያ-

ገና 15 ዓመትን ያልተሻገረችው ማርታ ድህነትን ለማምለጥ የሚደረግ ሽሽት ጀመረች። ልቧ ሁሌም የሚነግራት ‹‹መሥራት፤ መለወጥና የተሻለ ሕይወት መኖር›› የሚለውን ነበር። በዚህ ምክንያት የጓደኛዋን ምክር ተቀብላ በሕገወጥ ስደት ዳግም ድንበር ለመሻገር ተገደደች። በደላሎች አማካኝነት ወደ ሊቢያ ጉዞ ጀመረች። የሊቢያው ጉዞ ግን እንደ ሱዳኑ ቀላል አልነበረም። በግማሽ ቀን እንደሚገቡ የሚያውቁት እነ ማርታ በሊቢያ ገጠራማ ቦታ በአንዲት ጎጆ ቤት ውስጥ በከብቶች በረት የሚፈለገው የሰው ቁጥር እስኪሞላ ለቀናት ተቀመጡ። ወደ ሊቢያ ትራቮስ ለመግባትም አሸዋማ መሰል በረሀን ማቋረጥ፣ መራብና መጠማትን መቋቋም ነበረባቸው። በደላሎቹ የሚደርስባቸው ጉሸማን ጨምሮ የቋጠሩትን ጥሪት አሟጠጡ። ማርታ ‹‹በጉዞ ላይ በፒካፕ ተጭነን ስንሄድ የአሸዋ ክምር ላይ እንወድቅ ነበር፡፡›› ትላለች በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እያስታወሰች። እንደ ዕድል ሆኖ ፆታዊ ትንኮሳ ቢገጥማትም የከፋ ጉዳት እንዳላስተናገደች ትናገራለች። ሆኖም የያዙትን ለመቀማት በሚደረግ ግብ ግብ ውስጥ የጓደኛዋን ጨምሮ የብዙ ሱማሌ ስደተኞች ገንዘብ ተቀምቷል።

‹‹ሱዳን እያለሁ ቋንቋ ለምጄ ነበር። ልጅነት ቢኖርብኝም ቀልጣፋ ነበርኩ›› የምትለው ባለታሪካችን፤ አጋጣሚውን ተጠቅማ ወደ ሊቢያ ከተማ መግባት እንደቻለች ትናገራለች። በእዚያም በአንድ ጥቁር ሊቢያዊ ቤት ተቀጥራ በመሥራት ለቀጣይ የስደት ጉዞ ገንዘብ ማጠራቀሙን ተያያዘችው።

ሕገ ወጥ ደላሎቹ ከሱዳን ሊቢያ፣ ከሊቢያ ጣሊያን ጠንካራ ሠንሠለት የዘረጉ ናቸው። ከሱማሊያ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ ተጓዦችን በመመልመል ያሻግራሉ። ማርታም ይህንን ሠንሠለት ተጠቅማ ነበር ወደ ጣሊያን ለመግባት ጥረት የምታደርገው። በወቅቱ ወደጣሊያን የሚያስገባትን የባሕር ጉዞ ለማድረግ የሚያስችላትን አንድ ሺህ 200 ዶላር በቆይታዋ አጠራቅማ ዳግም ወደ ጣሊያን ለመሻገር ወሰነች። በሊቢያ እያለች ከሀበሾች ጋር ግንኙነት ፈጥራ እንዴት ወደ ጣሊያን እንደምትጓዝ አጣርታ ነበር። ከደላሎች ጋር ግንኙነትም ፈጥራለች።

ለዳግም ስደት እየተዘጋጀች ባለችበት ጊዜ ግን በሊቢያ ፖሊስ ተይዛ ወደ እስር ቤት ገባች። እሷን ጨምሮ በርካታ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጋር ንግግር ሲጀመር ግን ድራማዊ በሆነ መንገድ ከእስር ቤት አመለጠች። ከእስር ያመለጠችውም በሁለት ጊዜ ሙከራ ነበር። የመጀመሪያው የንጽሕና መጠበቂያ ለመግዛት በጥበቃ ወደሱቅ ተወስዳ በልብስ ውስጥ ተደብቃ ለማምለጥ የሞከረችበት ነበር። ይህ ሙከራዋ አብራት በታሰረች አንድ ሌላ ሴት ጠቋሚነት ሳይሳካ ቀርቶ ተያዘች።

በሁለተኛው ተሳካ። ማምለጥ የቻለችው እሷና አንድ ሌላ ጓደኛዋ ጋር በአጥር ነበር። ወደ ዋናው ከተማ በደላሎች ተመልሳ እስክትገባ አንድ 48 ሰዓት በዛፍ ላይ አድራለች። ወደ ከተማው ሊመልሷቸው የነበሩ ሊቢያውያን የፆታ ጥቃት ሊያደርሱባቸው ሞክረው ነበር። ሁኔታውን ስታስታውስ ‹‹በአምላክ ቸርነት ተርፈናል›› ትላለች። ይህ ሁሉ ፈተናና መንከራተት ግን የማርታን ልብ አሸንፎ ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ምክንያት አልሆነም። ልጅነት እና ጊዜያዊ ስሜት አሸንፏት ወደ ጣሊያን የሚደረገውን አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከሕገወጥ ደላሎች ጋር ንግግር ጀመረች።

ከባሕር የተረፈች ነብስ

ዛሬም ልጅነቷን ሽሽት አላቆመችም። ለስደት ያነሳሳት ሕይወቷን የመቀየር ውጥን በሊቢያ ብቻ ሊገታ አልቻለም። የግድ ወደ ጣሊያን መሻገር አለባት። ጣሊያንን እንደ ገነት ስለው የነገሯት ደላሎች አሉ። ሕይወትሽ ይቀየራል በሚል አማልለዋታል። የተጠየቀችውን ብር ከፍላ ከሌሎች ስደተኞች ጋር ጉዞ ለማድረግ በሊቢያ ባሕር ዳርቻ ጀልባውን መጠባበቅ ጀመረች። በዚያ በርካታ ስደተኞች ተከማችተዋል።

በትናንሽ ጀልባዎች ላይ ተጭነው ሰፊውን ባሕር ለማቋረጥ ይጠባበቃሉ። ወይ መሞት ወይ መዳን

ነው። ደላሎቹ እነ ማርታን የሰው ቁጥር እስኪሞላ በዚያ ለቀናት አቆዩአቸው። ‹‹በመጨረሻ ሰባት ትናንሽ የፕላስቲክ ጀልባዎች መጡ። ቢያንስ ከ40 እስከ 45 ሰው የሚጭኑ ናቸው። ደላሎቹ ግን ከ70 እስከ 80 ሰው በላይ በእያንዳንዱ ላይ ጭነው ጉዞ ጀመርን›› ትላለች፤ አሰቃቂውን የጉዞ ታሪኳን ስትናገር።

በጉዞው ለአምስት ቀናት በግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ አሳለፉ። አቅጣጫ መጠቆሚያ ኮምፓስ ጠፍቶ በባሕር ላይ የሚላስ የሚቀመስ እስኪጠፋ ተንከራተቱ። ‹‹ባሕሩ ጨው ነው፣ ውሃው ሰውነት ይበጣጥሳል፤ ጀልባችን ላይ ውሀ ሲገባ እንዳንሰምጥ ተራ በተራ በሳህን እየጨለፈን እንደፋ ነበር›› ትላለች፡፡ ማርታ ቀድሞ ወደጣሊያን ገብታ ያልፍልኛል በማለት የነበራት ተስፋ በእነዚህ ቀናት ተሟጦ ሕይወቷ እንዲተርፍ ብቻ ነበር የምትፀልየው። እንደ ዕድል ሆኖ ግን አብረው ከወጡት ሰባት ጀልባዎች የእነሱን እና ሌሎች ሁለት ጀልባዎች ጨምሮ በዓሣ አጥማጆች ጠቋሚነት የነብስ አድን ሠራተኞች ደርሰው ሕይወታቸውን አተረፏቸው። በቀሪዎቹ አምስት ጀልባዎች የተጫኑ ስደተኞች ግን አስከሬናቸው እንኳን አልተገኘም።

የማርታ የስደት ሕይወት ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከተስፋ ማጣት ወደ ተስፋ ጭላንጭል ተሻገረ። ሁኔታውን ስትገልፀው ‹‹ለኔ ከሞት እንደመነሳት ነው›› ትላለች። በነብስ አድን ሠራተኞች ታግዛ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ጣሊያን ገባች። ከአምስት ቀን ጉዞ በኋላ የባሕር ዳርቻ ወደሆነችው የጣሊያን ከተማ ሲደርሱ በረሀብና በውሀ ጥም በሁለት እግሯ መቆም እንኳን አትችልም ነበር። ማርታ ሕገወጥ ስደተኛ ስለነበረች በየጊዜው ስሟን እየቀያየረች፤ ከፖሊስ እያመለጠች ነበር ሕይወቷን የገፋችው።

ጣሊያን ስትገባም እንዲሁ ኤርትራዊ እንደሆነችና የፖለቲካ ጥገኝነት እንደምትፈልግ በማስረዳት ነበር የተቀበሏት። በዚያ የኪስ ገንዘብ እየሰጡ፣ መኖሪያ አመቻችተው፣ የትምህርት ዕድል ሰጥተው ተቀበሏት። ዐሻራ ሰጥታ በጣሊያን መንግሥትና በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የስደተኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ተመዘገበች። ዳግም ስደትን ላለማሰብ ለራሷ ቃል ገብታ ጣሊያንኛ ቋንቋ እየተማረችና ሥራ እየሠራች ቆየች።

በጣሊያን ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ እንደቆየች ግን የደረሰባት ፈተና፣ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ተዘነጋት። ለሌላ ስደት እራሷን ማዘጋጀት ጀመረችም። ‹‹ዳግም አይለመደኝም ብዬ የነበርኩ ልጅ ሰዎች ከጣሊያን የተሻለው ኖርዌይ ነው ሲሉኝ ልቤ መሸፈት ጀመረ›› ትላለች። ትናንት የመታት እንቅፋት ድጋሚ እንዲያደናቅፋት የወጣትነት ስሜቷ አታለላት። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ተረጋግታ ሠርታ፣ የምትፈልገውን ጥሪት አላፈራችም ነበር። አሁንም ወደ ኖርዌይ ለማቅናት በሰዎች ርዳታና ምክር ጉዞ ጀመረች። በሻንጋይ ቪዛ በሲዊድን ትራንዚት አድርጋ ኖርዌይ አየር ማረፊያ ደረሰች።

ዳግም ስደት- ወደ ኖርዌይ

ከሰሜን ጎንደር ደባርቅ በ14 ዓመቷ ስደት የጀመረችው ማርታ የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው በጉዞ፣ በእስር ቤት፣ በሰው ቤት ሠራተኝነት፣ በድብብቆሽ ነው። ቆም ብላ ብታሰላስለው በሊቢያ እስር ቤት፣ በሱዳን፣ በረሃ፣ በዛፍ ላይ ያሳለፈቻቸውን 48 ሰዓታት፣ በባሕር ላይ ከሞት አፋፍ የተረፈችበትን አምስቱን ቀናት ብታስታውስ አይደለም ለሌላ ስደት ከእናት ሀገሯ እግሯን ንክች አድርጋ አታነሳም ነበር። ሆኖም ማርታ ጣሊያንን ተሰናብታ ዳግም ወደ ኖርዌይ አቀናች።

‹‹ሰዎች የተሳሳተ ምክር አሁንም መከሩኝ። ስምሽን ቀይሪ አሉኝ›› ትላለች ኖርዌይ ዳግም በሕገ ወጥ ስደት እንዴት እንደገባች ስትናገር። ወጣትነት እና ነገሮችን አለማስተዋል ዳግም የማርታን ሕይወት አመሰቃቀለው። ዐሻራ የሰጠች በመሆኑ ስደተኛ መሆኗ ሲረጋገጥ ቪዛውን የኖርዌይ መንግሥት ከለከላት። ሆኖም ወደ ጣሊያን መመለስ ሲገባት በዚያው በሕገወጥ መልኩ ቆየች። ኖርዌይ ሌላ ድብብቆሽ ጀመረች። ይህ ሁሉ ሲሆን ማርታ ሕይወቴን አሻሽላለሁ፣ ሠርቼ የተሻለ ኑሮ እኖራለሁ በሚል ነበር። ሆኖም የመረጠችው መንገድ ይበልጥ ሕይወቷን የሚያወሳስብ ሆነ። እንደ ዕድል ሆኖ አርዓያ የሚሆናት እና የተሳሳተውን መንገድ የሚያርማት ወዳጅም ዘመድም አልነበራትም። በዚህ ምክንያት በኖርዌይ በሕገወጥነት ቆየች።

ማርታ በኖርዌይ በስደተኞች ካምፕ አካባቢ ለወራት ቆየች። ሥራ መሥራትም ወደ ጣሊያን መመለስም አትችልም ነበር። አንድ ወር፣ ሁለት ወር፣ ሦስት ወር እያለች መፍትሔ ለማፈላለግ ብትሞክርም ሕጋዊ መንገድ መያዝ አልቻለችም። ይህ የነበራትን ተስፋ ዳግም አጨለመባት። ‹‹ያቃጠልኩትን ጊዜ ሳስበው በጣም ነው የምበሳጨው›› ትላለች ውሳኔዎቿ ትክክል እንዳልነበሩ አሁን ላይ ግን በብዙ እንዳስተማራት እየገለፀችና ሁኔታውን ዞር ብላ እያሰበች። ለወራት በጥረት የቆየችው ማርታ አማራጭ ስታጣ በዚያ በስደተኞች ካምፕ ከተዋወቀችው እና ለስድስት ዓመታት በትዳር አብራው ከቆየችው የቀድሞ ባለቤቷ ጋር ትዳር መሠረተች። ከዋናው ኦስሎ ከተማ ወጥታም ኑሮ ጀመረች።

ማርታ የትዳር ሕይወቷ ጥሩ ትዝታ ያለው አይደለም። ‹‹ለስድስት ወራት በጣም ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍን›› በማለት ከዚያ በኋላ የነበሩ ዓመታት ግን በእጅጉ እንደጎዷት ትገልፃለች። ሕገ ወጥ ስለነበረች የምትሠራው ሥራ ሁሉ ክፍያ የሚገባው በእርሱ ባንክ አካውንት ነበር። ያንን ሁሉ ዓመት በስደት ስትሽሎኮሎክና ፍዳን ስትቆጥር ቆይታ በመጨረሻ በባሏ ፈላጭ ቆራጭነት ስር ወደቀች። ከባሕር የተረፈው ነፍሷ በጭካኔ በትሮች ያርፍባት ጀመር። የስደት ሕይወቷም ትዳሯም ያልሰመረላት ማርታ ችግሩን ለመፍታት ፍቺ ለማድረግ ስትሞክር ባለቤቷ ‹‹አዕምሮ ሕመምተኛ ነች›› በማለት በሆስፒታል እንድትቆይ እስከማድረግ ደርሷል።

የፊኒሺንግ (የጂብሰምና ቀለም ሥራ)፣ በጎን ደግሞ በእንግዳ ማረፊያ ፅዳት እየሠራች የምታጠራቅመው ገንዘብ በቀጥታ በእርሱ አካውንት የሚገባ በመሆኑ በግሏ ጥሪት ማፍራት አልቻለችም። በሁኔታው ምሬት ውስጥ የገባችው ማርታ በስተመጨረሻ ከስድስት ዓመት በላይ የቆየውን ትዳር እንድትፈታ አደረጋት። ትዳራቸው የተቋጨው ለሁለት ዓመት የቆየ የፍርድ ቤት ክርክር ካደረገች በኋላ ነበር። ወዲያው ያቀናችውም ወደ ዋና ከተማዋ ኦስሎ ነበር።

ማርታ በኦስሎ ከኢትዮጵያውያን ኮሚውኒቲ ጋር ተዋወቀች። ፈጣን የመግባባት ክህሎት አላት። ስደት ካስተማራት እውቀት መካከል የቋንቋ ክህሎቷ ነው። የሀገሬውን ቋንቋ ጨምሮ ዓረብኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዘኛ ትናገራለች። በዚህ ምክንያት ለስድስት ወር በኦስሎ ኢትዮጵያውያን ኮሚውኒቲ በመስተንግዶ በበጎ ፍቃድ ስትሠራ ቆይታ በመጨረሻም በቋሚነት ቀጠሯት። በዚያ ተረጋግታ መሥራት ጀመረች። ዳግም በሕይወት ከሌላ ሰው ጋር ተዋውቃ በጥምረት መኖር ቀጠለች። ንብረትም አፈራች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ግን የቀድሞ ባለቤቷ ‹‹ከእኔ ለምን ተለየች›› በሚል የቅናት መንፈስ ለኖርዌይ መንግሥት ‹‹ኢትዮጵያዊ ሆና ሳለ በኤርትራዊ ስም በውሸት እየኖረች ነው›› በማለት ጥቆማ አደረገባት።

‹‹የስደት ሕይወቴ የተቋጨበት ለ20 ዓመታት የለፋሁበት ምንም ጥሪት ሳልይዝ ነበር›› ትላለች ሁኔታውን መለስ ብላ እያስታወሰች። በቀድሞ ባለቤቷ ጠቋሚነት በኖርዌይ መንግሥት ተይዛ ያፈራችውን ንብረት (ከአንድ ሻንጣ በቀር) ሳትይዝ ሊጠርዟት ለአንድ ወር ታሰረች። የወረቀት ሥራ ሠርተው እንዳጠናቀቁ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ዝግጅታቸውን ጨረሱ። ‹‹የኖርዌይ መንግሥት የፀጥታ አካላት ለአይ ኦ ኤም ሠራተኞች ወደ ሀገሬ እንደሚመልሱኝ ነግረውኝ አየር መንገድ ውስጥ አስቀምጠውኝ ሄዱ›› የምትለው ማርታ፤ ጥቂት ቁጭ እንዳለች ሀሳቧን ቀይራ ከኤርፖርቱ ጠፍታ እንደነበር ትናገራለች።

ይሁን እንጂ ያለፉትን የስቃይ ዓመታት ስታስባቸው በስደት ሕይወት ካተረፈችው የጎደለባት በእጅጉ እንደሚበዛ ተገንዝባ ወደ ሀገሯ ለመግባት ወሰነች። ዳግም በትዳር የተጣመረችው ባለቤቷም በሕጋዊ መንገድ እንደሚመልሳት ተነጋግረው የኖርዌይ መንግሥትን ይቅርታ ጠይቃ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) እገዛ ወደ እናት ሀገሯን ገባች። እንግዳችን ማርታ ከ20 ዓመት የስደት ውጣ ውረድ በኋላ ነበር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ወደ ሀገሯ የተመለሰችው።

ማርታ ዛሬ

ማርታ ትናንት በልጅነት አዕምሮዋ የሸሸችውን ድህነት በሀገሯ ተጋፍጣ ለማሸነፍ እየታተረች ነው። ‹‹ስደት በቃኝ ዳግመኛ አልሞክረውም›› ትላለች። ለ20 ዓመታት ከሞት መንጋጋ በተዓምር ተርፋለች፤ ባሕር ተከፍቶ ሊውጣት ጫፍ ደርሶ ነበር። የኔ ባለቻቸው እና እምነቷን በሰጠቻቸው ሰዎች ተከድታለች። ለዓመታት የለፋችበት፤ ጉልበቷን ሳትሰስት የሠራችበት ሀብት ንብረት ጥሪት ላይሆን እዚህም እዚያም ባክኖ ቀርቶባታል። ሮጣ ልታመልጣት እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገችባት ሀገር ግን ዳግም እጆቿን ዘርግታ ተቀብላታለች። አሁን ወገኖቿ መሐል ነች።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ማርታ የምታውቃቸው የቅርብ ዘመዶች በአዲስ አበባ ባለመኖራቸው በብዙ ብትፈተንም አንዴ ቆርጣ ስለመጣች ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። በመንገድ ዳር በቆሎ ጠብሳ ሸጣለች፤ ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ የሚያደርገው አይ ኦ ኤም በሰጣት ጥቂት ገንዘብ አነስተኛ ሻይ ቤት ከፍታ ሠርታለች። ፈጣን አዕምሮና የመግባባት ችሎታ አላት። በዚያ ላይ ያሳለፈችው ሕይወት ብርታትን አላብሷታል።

ዛሬ ማርታ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በብድር መኪና በመግዛት የራይድ አገልግሎት እየሠራች ነው። ብድሩ በአምስት ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ቢሆንም እሷ ግን ቀን ከሌሊት እየሠራች በሁለት ዓመት ከፍላ አጠናቅቃለች። ‹‹የራይድ ሥራ ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጡ አጋጣሚዎች ጋር ቢያጋፍጠኝም በሀገሬ እስከምሠራ ድረስ አልሸበርም›› የምትለው ማርታ፤ ከ14 ዓመት የስደት ትግል በኋላ ወደ ሀገሯ ተመልሳ የሕይወት መስመሯን እያቃናች መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይ ብዙ ሕልም አላት፡፡ የንግድ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የተሻለ ስኬትን ማግኘት ትሻለች። እቅዷን በእርግጠኝነት እንደምታሳካው በሙሉ ልብ ትናገራለች።

ዛሬም ስደትን ምርጫቸው ያደረጉ ወገኖቿ የሕይወት ራዕያቸው እንዳይጨናገፍ ከተሳሳተ መስመር እንዲመለሱ ማስተማር ትፈልጋለች። የእሷን ለ20 ዓመታት የተደረገ የሕገወጥ ስደት እና ያስከፈላትን ከባድ ዋጋ በምሳሌነት እያነሳች ‹‹በእኔና በመሰል ጓደኞቼ የደረሰው መከራና እንግልት ይበቃል›› በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረገችውን ቆይታ ትቋጫለች። እኛም በሀገሯ ሠርታ ስኬታማ፣ ለብዙዎችም ምሳሌ እንድትሆን እየተመኘን የዛሬውን የሕይወት ገፅታ ዓምድ በዚሁ እናበቃለን። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You