
የሰው ልጆችን ከጽንፍ እስካፅናፍ ያናወጠ፤ ምድርን ያስጨነቀ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስጨናቂው ክስተት፤ ሳይታሰብ ተከስቶ ብዙ ያሳሰበ፤ መግቻ መንገዱ ርቆ ብዙ ያናወጠ ወረርሽኝ፤ የሰውን ልጅ ሕይወት እንደ ዘበት የቀጠፈ፤ ባልታሰበ ፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ ያለ አሰቃቂ ገጠመኝ፤ መፍትሄ የተባሉ ርምጃዎች ሁሉ እየተወሰዱ፤ ይበጃል የተባሉ መላዎች እየተዘየዱም ጠብ የሚል መፍትሄ ያልተበጀለት ዓለም አቀፍ አደጋ፤
ዓለምን ግራ ያጋባ፣ ሀገራትን የሚይዙትን የሚጨብጡትን ያሳጣ መዓት፤ በዚህ ክስተት የሰው ልጅ ስጋት ውስጥ ወድቆ፤ ሁሉም ስለ መፍትሄው ምንነት ተጨንቆ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ለዓለም መጥፎ አጋጣሚ ይዞ ስጋትና እልቅቲን አስከትሎ መጥቷል። ዓለም ጥሩ ጊዜዋ አይደለም። ምድር ምጧ በዝቶ ማጥዋ በርክቶ በመዳህ ላይ ትገኛለች።
በፈጠረው ዓለምአቀፋዊ ቀውስ ሀገር ማዳን፤ ወገን መታደግ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን። በእያንዳንዷ ደቂቃ የሰዎችን ሕይወት በሚነጥቀው፤ የማህበረሰብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን በሚያመሰቃቅለው አደጋ ወቅት ማህበረሰባዊ መደጋገፍና አብሮ የመቆምን ልማድ ማጠናከር ወገንንና እራስን ከአደጋው ከሚጋርጡ ሁኔታዎች መጠበቅና መጠበቅ ዋንኛ ጉዳይ መሆን ይገባዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ግን አንዳንድ ከማህበረሰባችን ልማድ ያፈነገጠ ተግባር የሚፈፅሙ፤ ያለንን አብሮነት የሚንዱ፤ መተሳሰብን የሚያርቁ ከነበረን ማህበራዊ እሴት እና መገለጫ በተፃረረ መልኩ እራስ ወዳድ የሆኑ ነጋዴዎች መበርከታቸው ተሰምቷል። እኩይ ተግባር የፈፀሙ ነጋዴዎች መፈጠራቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሰምተናል።
በዚህ ፈተና ውስጥ የተጎዱ ሀገራት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አውጀው የሌላ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። እርግጥ እስካሁን ከሁለት ሺህ በላይ ዜጎቿ የተጠቁባት አፍሪካ ከሌሎቹ አንፃር ጉዳቷ ባይጎላም «ለሚመጣብሽ አደጋ ተዘጋጂ» ተብላለች። መጪው ጊዜዋ አስፈሪ ሆኗል። የተደራጀ የጤና ሥርዓት የሌላት፤ በቂ የሕክምና ተቋማት ያልታደለችው፤ አንድ ዶክተር ብዙ ሚሊዮኖችን የሚያክምባት አህጉረ አፍሪካ ስጋት አጥልቶባታል።
የሚመጣባትን ከባዱን ጉዳት በምን ትወጣው ይሆን? የሚለው የብዙዎቹ ጭንቀት ሆኗል። አህጉሪቱ ለበሽታው መዛመት ካላት ምቹነት ሁኔታ አንፃር ከዓለም ጤና ድርጅት እና ልዩ ልዩ አካላት በአህጉሪቲ ላይ የሰጡት የያሰጋኛል መግለጫ ሕዝቧን አስጨንቋል። የአፍሪካ ሀገራት በተናጠልና በጋራ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ልዩ ልዩ ተግባራት በመከወን ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ስጋቱ ካጠላባቸው ሀገራት አንዷ ነች። በመንግሥት በኩል ዘርፈ ብዙ የመከላከል ሥራዎች እየተሰራ ይገኛል። መንግሥት ኅብረተሰቡን ከወረርሽኙ ይጠብቃል የሚለውን ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ፤ እነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ተቀባይነት አግኝተው ካልተተገበሩ ውጤታቸው አመርቂ ሊሆን አይችልም። በተለይ ወረርሽኙን ተከትሎ በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጫና መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር እጅ ለጅ ተያይዞ ካልተጋፈጠው ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው።
አሁን ላይ ያለውን የገበያ ሁኔታ ማረጋጋትና ከቀውሱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጥንቃቄ ሊመሩ ይገባል። ታዲያ በዚህ ሀገርንና ሕዝብን የማዳን፤ ወገንን የማትረፍና ኢኮኖሚን የመታደግ ሂደት ላይ አንዳንድ ከሕዝብና ከአገር ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ያስበለጡ ነጋዴዎች በማህበረሰቡ ላይ ዋጋ በመቆለል ለእንግልት መዳረጋቸው ተደጋግሞ ተሰምቷል።
እነዚህ የግል ጥቅም አሳዳጅ ነጋዴዎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመዘንጋት የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ሕዝቡን ላልተገባ ወጪና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ውስጥ ጥለውታል። የኮሮናን ቫይረስ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፤ የሕዝቡ መሸበርና አደጋው የሚፈጥርበትን ጉዳት ለመከላከል የሚጠቅሙት ቁሳቁሶች ለመግዛት ወደ መደብርና የገበያ ቦታ በሚያመራበት ወቅት የገጠመው የዋጋ ንረት እጅግ ያልጠበቀው ሆኖበታል።
ወትሮ ገበያው ላይ በቀላሉ ያገኘው የነበረው ዕቃ የለም ተብሎ አልያም የነበረው ዕቃ ዋጋ በጥፍ ጨምሮ ጠዋት የሸመተው ከሰዓት ዋጋው ንሮ አስደንግጦታል። እነዚህ ነጋዴዎች ያለምንም ኢኮኖሚያዊም ሆነ የአቅርቦት ችግር የሕዝቡን መደናገጥና ወቅታዊ አጋጣሚውን በመጠቀም ለመክበር የሞከሩ ከሕዝቡ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመንጠቅ ሞክረዋል።
እነዚህ ስለ ሀገር ደንታ የሌላቸው፤ ስለ ወገን ቁብ የማይሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ነጋዴዎች በመንግሥት ተገቢ የሆነው ርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል። ነገር ግን ሕዝቡ በተለየ መልክ አንድ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ቢቀጣቸው ብዬ አሰብኩ። መደብርና ሱቆቹን ከማሸግ ባለፈ ከዚህ በላይ ቅጣት፤ ከዚህ በባሰ መግሪያ፤ ከፍ ያለ ማረቂያ በእርግጥም በእነዚህ ጥቅም አሳዳጆች ላይ መውሰድ ይገባዋል።
በራሳቸው ምክንያት እየፈጠሩ አሊያም አንዳች ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ሰበብ እየፈለጉ የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ ዋጋ እንዳሻቸው እየቆለሉ ሕዝብን የሚበዘብዙት ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አንድ ማህበረሰባዊ እርምጃ ቢወሰድባቸው አልኩ። እርግጥ መግሪያው መንገድ ብዙ ቢሆንም ከመንግሥት ቅጣትና ርምጃ ባለፈ ማህበረሰቡ አስተማሪ በሆነ መልኩ ቢያንፃቸው።
ፈረንጆች አንዳንድ ጥሩ ባህል አላቸው። ከማህበረሰባቸው ያፈነገጠውን የሚቀጡበት፤ ስህተቶችን የሚያርሙበት ስልት አላቸው። ቦይኮቲንግ (Boycotting) ይሉታል። አንድ በሕዝብ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባር የፈጸመ አካል አቅርቦቱን ወይም አገልግሎቱን ላለመጠቀም ማመጽና ምርቱ እንዲበላሽ በማድረግ ወይም በማግለል የሚያርቁበት ሥርዓት ነው። ምንም ያህል ግዙፍ ኩባንያ ይሁን አሊያም መለስተኛ ማህበረሰቡን ሊጎዳ የሚችል ማንኛውም ድርጊት ከፈፀመ ሁሉም ያ ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት እንዳይሰጥ ቢሰጥም ማንም ከሱ እንዳይጠቀም በማድረግ ኅብረተሰቡ ላይ የፈጠረው ጫና ገበያውን በመዝጋት አስተማሪ የሆነ ቅጣት ይቀጡታል።
ይህ ልምድ እኛም ሀገር አሁን በተከሰተው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ስለናንተ አያገባኝም የሚሉትን ነጋዴዎች ለይተን ከእርነሱ የምንሸምተውን ማናቸውም ነገር በማቆም መቅጣት ተገቢ ይመስለኛል። ይህ ማህበረሰባዊ ርምጃ እንደ ልምድ ተወስዶ ቢተገበር ያለምክንያትና ያላግባብ የተስገበገበ ግለሰብም ሆነ ተቋም በተገቢው መልኩ ተግባሩን እንዲከውን ያደርጋል።
ይህ ሲደረግ ታዲያ ጥንቃቄ በተሞላበትና ኃላፊነትን በሚጠይቅ መልክ መሆን ይገባዋል። ማህበረሰቡን የበዘበዘው ተቋም ወይም ደግሞ ግለሰብ ከእርሱ ምርትና አገልግሎት ማህበረሰቡን በማስተባበር እንዳይጠቀምና የሰራው ተግባር ልክ እንዳልሆነ በማሳየቱ ሂደት ከስሜት በፀዳና በትክክል ድርጅቱ ወይም ግለሰቡ ያደረገው መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል። ለምሳሌ፤ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ስርጭት ምክንያት በሙዝና በሎሚ፤ በነጭ ሽንኩርት ላይ ዋጋ በጨመሩ፤ መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት አድርገው በስጋ ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያደርጉ ሉካንዳ ቤቶችን ባለመግዛትና ለተወሰነ ጊዜ ስጋ ያለመብላት አድማ በማድረግ እኛም ስግብግቦቹን እንቅጣ፤
ይህን ፈረንጆች ለዘመናት እየተገበሩት ኢኮኖሚያዊ መዋዠቆችን የተቆጣጠሩበት፤ ያለአግባብ የሚበዘብዛቸውን ያረቁበት ያስተካከሉበት የሰለጠነ ተግባር እኛም ብንጠቀምበት አስተማሪ ይመስለኛል። ሀገራዊ ኃላፊነት ያልተረዳ ራስ ወዳድ ነጋዴ በዚህ መልኩ ቀጥቶ መግራቱ ስልጡንነትም ጭምር ነው።
በትውልድ ቅብብሎሽ የምትዘልቀው፤ በልጆቿ ትጋት የምትሻገረው ሀገር ፈተና ሲጋረጥባት የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትናፍቃለች። ከጠላት የሚከላከላትን፤ በችግር ጊዜ የሚደርስላትን ትሻለች። በዚህ ወሳኝ ጊዜ በጋራ ሆኖ የሚመጣውን ፈተና በፅናት የሚታገል ከምንም በላይ ሀገርና ሕዝብን የሚያድን፤ ከራሱ ይልቅ ለሌላው የሚያስብ ትውልድ ትሻለች። እናም ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ህልውና አደጋ የሆኑትን ፈተናዎችን ሁሉ ለመቋቋም ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ይገባናል። ያኔ የማንሻገረው ችግር አይኖርም። አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2012
ተገኝ ብሩ