ቶሎሳ ዳቢ ልጅነቱን ያጋመሰው ከትምህርት ገበታ ጋር ነው:: የዛኔ ወላጆቹ ለእሱ የሚሆን አቅም አላጡም:: እንደ እድሜ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ቀለም እንዲቆጠር ሲፈቅዱ ከልባቸው ነበር:: እንዲህ በሆነ ጊዜ የህጻኑ ቶሎሳ ደስታ ወደር የለሽ ሆነ:: ለእሱ ትምህርት ቤት ውሎ መምጣት ከምንም በላይ ትርጉም ነበረው::
ቶሎሳ አንደኛ ክፍልን እንደተሻገረ ቀጣዩን የትምህርት ወሰን ለማለፍ በብርታቱ ቀጠለ:: ከሌሎች ባልንጀሮቹ ጋር ‹‹ገላን›› ከተማ ውሎ ሲመለስም ውስጡ በተለየ ተስፋ ተመላ:: ሁሌም በልጅነት አዕምሮው የሚመላለሰው ታላቅ ህልም ራስን ማሸነፍ ሆነ:: በአካል ሲጎለብት ደግሞ ርቆ መሄድና በተሻለ ደረጃ መቆም እንደሚችል አመነ::
አስከአራተኛ ክፍል ብርታት ያልተለየው ታዳጊ ለአምስተኛ ክፍል መዘጋጀቱን አልዘነጋም:: ጊዜውን በጥንካሬ ካለፈው በቀጣይ የሚኒስትሪ ተፈታኝ ለመሆን ይበልጥ መትጋት ይኖርበታል:: እንዲህ ይሆን ዘንድም ቤተሰቦቹን እየረዳ ለወደፊቱ ያቅዳል ይዘጋጃል::
አንድ ቀን ግን ቶሎሳ ዘወትር ያስበው የነበረው እውነት ከንቱ ስለመቅረቱ አወቀ:: ሁሌም ስለትምህርቱ እያሰበ ብዙ ያቅድበት የነበረው ጉዳይ ከዚህ በኋላ እንደማይቀጥል በገባው ጊዜም ከልቡ አዘነ:: የቤተሰቦቹ አቅም ማጣትና እሱን ማስተማር ያለመቻል ጉዞውን ካቆመበት እንዳይቀጥል ምክንያት ሆነው::
ቶሎሳ አርቆ የሚያስበው የትምህርት መንገድ ከአምስተኛ ክፍል ሊቋረጥ ግድ ባለው ጊዜ ደጋግሞ እየተከዘ ደጋግሞ አሰበ:: አሁን የትምህርቱ ጉዳይ ተስፋ የለውም:: የእሱን እገዛ የሚሹ ወላጆቹም ከዚህ በላይ ሊረዱት አይቻላቸውም:: እናም በተራው እነሱን እያገዘ ራሱን መምራት የሚችልበትን አማራጭ መፈለግ ይኖርበታል::
ገላን ከተማን በትምህርት ምልልስ የሚያውቀው ቶሎሳ አሁን ደግሞ በእንጀራ ፍለጋ ሊውልበት ወስኗል:: ሰርቶ ለማደር የሚያስፈልገውን ገቢ በሚያገኘው የቀን ስራ ሲያሟሽም የጉልበቱን ጥንካሬ ማውቅ ችሏል:: ይህን ማድረጉ ደግሞ የቤቱን ጎዶሎ ሞልቶ የወላጆቹን ምርቃት ጭምር እንዲያገኝ አግዞታል::
አሁን ቶሎሳ የትምህርቱን ጉዳይ ረስቶ በጉልበቱ ወዝ ማደርን ለምዷል:: ቤተሰቦቹን እያገዘ ለራሱ የሚይዘው ገንዘብ በቂ ባይሆንም ድህነት ለተጫናቸው ወላጆቹ ግን መፍትሄ መሆን ችሏል:: ውሎ ሲያድር ደግሞ ከዚህ በተሻለ አማራጭ ወፈር ያለ እንጀራ የሚጎርስበትን ጊዜ ማሰቡን አልተወም::
ቶሎሳ በቀን ስራ ልምዱ መያዝ ያለበትን ሙያ እየቀሰመ ቆይቷል:: በዚህ ዕድሜው የትም ሰርቶ ማደር እንደሚችል ከገባውም ቆይቷል:: ራቅ ብሎ ቢሄድ ደግሞ ባለው ጉልበትና ሙያ የተሻለ ማግኘት እንደሚችል እርግጠኛ ሆኗል::
ኑሮ በመሀል ከተማ
ቶሎሳ ሲያስብበት በቆየው ጉዳይ ወስኖ ወደ መሀል አዲስ አበባ ተሻግሯል:: ገላን ከተማ ለአዲስ አበባ የቀረበ መሆኑና ወላጆቹን ለመጠየቅ ምቹ ሆኖሎታልና ያሰበውን ለመፈጸም ምክንያት ነበር:: በዚህ ስፍራ መገኘቱ ከትናንቱ የተሻለ ሆነለት:: ቦታ ቀይሮ ራቅ ማለቱም ለኑሮው በጎ ሆኖ ገቢውን ጨመረው::
የገላኑ ጎልማሳ ከቀዬው መራቁ ብቻ የስራ ውሎውን አልቀየረውም:: ዛሬም በጉልበቱ አዳሪ ሆኖ በቀን ስራ ሊሰማራ ግድ አለው:: አዲስ አበባ እንደስፋቱ መልካም ዕድሎች አሉት:: ስራና ቦታን አማርጠው ያሻውን ያደርጉበታል:: የዛኑ ያህልም ለቤት ኪራይ ፣ ለዕለት ወጪና ለሌላም የሚከፈለው ቀላል አይደለም:: ቶሎሳም ይህን አውቆ በዚህ መስመር መጓዝ ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል::
ቶሎሳ ከቀን ስራ መልስ ጎራ ከሚልባቸው መዝናኛዎቹ መሀል የወርቅነሽ አረቄ ቤትን ያዘወትራል:: በዚህ ስፍራ አረፍ ባለ ጊዜ ከበርካቶች ይገኛል:: ከጥቂቶች ተግባብቶም የልቡን ማውራት ልምድ አድርጓል:: ይህ ቦታ የዕድሜ ወሰን የለውም:: ከጠዋት አስከማታ በደንበኞች ተሞልቶ ጨዋታና ብሶት ይደራበታል::
ሁሌም ከወርቅነሽ እልፍኝ ጎራ እያለ አረቄውን ፉት የሚለው ቶሎሳ በዚህ ልምዱ ከድካሙ ያረፈ ይመስለዋል:: የግንባሩን ላብ ጠርጎ ጉልበቱን ሲያሳርፍም በጉሮሮው አልፎ የሚሄደው አረቄ ውስጡን አድብኖ ፈገግታውን ያበራል:: ዘወትር ከእጁ የማይለየውን የሲጋራ ጢስ እያቦነነም እንደለመደው ስለነገ ያስባል ይተክዛል::
ቶሎሳ ገንዘብ ከፍሎ የሚጠጣው የእህል አረቄ ሰውነቱን እያሞቀ የውሰጡን ሀሳብ ያስረሳዋል:: ከስፍራው ደርሶ መለኪያውን በጨበጠ ጊዜም የቀን ድካሙን ረስቶ በእፎይታ አረፍ ይላል:: ማልዶ ስራ ሲሄድና ውሎ ከመንደሩ ሲገባም በአይኑ ውል የሚልበትን የአረቄ ልማድ አያልፈውም::
ኮማሪቷ ወርቅነሽ ይህ ስራ ጥርሷን የነቀለችበት ነው:: የዘወትር እንግዶቿን በፈገግታ ተቀብላ ስታስተናግድ የሁሉን ባህሪ እንደመጣጡ ትቀበላለች:: የሚጣሉትን አስማምታና ከብሶተኞቹ አውግታ የመዋሏ ልምድ የዓመታት ደንበኞቿ ሳይጎድሉ እንዲቀጥሉ አግዟታል::
በዚህ ስፍራ ብዙ አይነት ሰዎች ይታያሉ:: በሰላም ገብተው እየተንገዳገዱ የሚወጡ፣ በዝምታ ዘልቀው ጠብ ያዋዛው ንግግር የሚያሰሙ፣ በድንገት አመለ ሸጋነታቸው ተለውጦ ‹‹ልደባደብ›› የሚሉ፣ ደርሰው ምሁርነት የሚቃጣቸው፣ ስለሁሉም ግድ የሚላቸውና ሌሎችም::
ከስራ መልስ ከአረቄ ቤቱ የማይጠፋው ቶሎሳ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ማውጋት ደስ ይለዋል:: በዚህ ስፍራ እሱን ጨምሮ ሌሎች በዕድሜ የበሰሉ ደንበኞች በጨዋታ ይግባባሉ:: አንዳቸው የሌላቸውን እየሰሙ ማውጋታቸው የማንነታታቸውን ልክ ወስኖታል:: በዚህ ልማድም ዓመታትን በአብሮነት ዘልቀዋል::
በእነ ቶሎሳ ዕድሜ የማይመደቡ ጎረምሶች ደግሞ ከእነሱ ጋር ጨዋታ ጥሟቸው አያውቅም:: ከአረቄ ቤቱ ገብተው ‹‹አንድ›› ከማለታቸው ለስድብና ጠብ ይጋበዛሉ:: አብዛኞቹ ይህን ማድረግ እንደ ልማድ ሆኖባቸውም ያለ ሰላም ይለያያሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ ስለማንም አይጨነቁም:: የተቀዳላቸውን ተጎንጭተው ከመሸታው ቤት ውልቅ ይላሉ::
ከአረቄ ቤቱ ደንበኞች አንዱ የሆነው ቦዬ ከዚህ ስፍራ ጠፍቶ አያውቅም:: በዕድሜው ገና ወጣት ቢሆንም ከስራ ይልቅ በስካሩ ይታወቃል:: ከእናት አባቱ የተቸረው ሲራክ የሚለው ስያሜው ነው:: በቅርብ የሚያውቁት ግን ‹‹ቦዬ›› በሚለው ቅጽል ይጠሩታል:: ቦዬ በአረቄ ስካር በመንገዳገድና ባልተመቸ ባህርይው ይታወቃል::
ቦዬና ቶሎሳ አልፎ አልፎ የወርቅነሽ አረቄ ያገናኛቸዋል:: ብዙ ጊዜ ቶሎሳ ከስራ መልስ ፉት ለማለት ጎራ ባለ ሰአት ቦዬ ከተለመደው ቦታ ተቀምጦ የለመደውን እየተጎነጨ በሞቅታ ሲናገር ይሰማዋል:: አንዳንዴም ከሌሎች ባለመስማማት ሲጨቃጨቅ ያስተውለዋል::
ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓም
ሰኔ ግም ማለት ከጀመረ ሰንበት ብሏል:: ወበቅ የከረመበት ጊዜ በዝናብ እየራስ በመሆኑ ብዙዎች አለባበሳቸውን ቀይረዋል:: ይህ አይነቱ ወቅት ደግሞ ለእንደነ ቶሎሳ አይነቶቹ የቀን ሰራተኞች ፈታኝ ይሆናል:: ማልደው በስራ ሲሰማሩና አምሽተው ወደቤታቸው ሲገቡ የክረምቱ ዝናብና ቅዝቃዜ አያልፋቸውም::
ቶሎሳ በዚህ ቀን እንደተለመደው ከስራው ላይ ውሏል:: የዕለት ግዴታውን አጠናቆም ወደቤቱ እየተመለሰ ነው:: ቤት ከመግባቱ በፊት ግን ወደ ወርቅነሽ አረቄ ቤት ጎራ ማለትን አልዘነጋም:: የመንገዱን አቅጣጫ ቀይሮ ከመሸታው ቤት ዘና ለማለት መንገዱን ጀምሯል::
ቶሎሳ የቀን ውሎው እንዳደከመው እርምጃው ይናገራል:: ከዝናቡ እየተጋፋ ሲከውነው የዋለው ስራ ከባድ የሚባል ነበር:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ከወርቅነሽ ቤት ጎራ እያለ ፉት የሚለው አረቄ ሁሉን ያስረሳዋል:: የቀኑን ብርድና ዝናብ አስወግዶም ለውስጡ ደስታን የሚቸር ሙቀት ይለግሰዋል::
ከመሸታው ደጃፍ ሲደርሰ ቤቱን የትኩስ አረቄ ሽታ አውዶታል:: ቀድሞ የሚያውቃቸውን ደንበኞች በጨረፍታ አያቸው:: ሁሉም ስፍራቸውን ይዘው ጎንጨት እያሉ ነው:: በቅርብ ያገኛቸውን ጨብጦ ራቅ ያሉትን የአንገት ሰላምታ ሰጣቸው:: ከገባ ቆየት ያለው ቦዬ ካለበት ሆኖ በሞቅታ ያወራል:: ገሚሶቹ እየሰሙት ነው:: ሌሎቹ ደግሞ በአግርሞት እያዩ ይስቁበታል:: ወርቅነሽ ቶሎሳ መግባቱን እንዳየች የአረቄ ጠርሙሷን ይዛ ቀረበች:: በመለኪያው እየሰፈረችም በሻይ ብርጭቆው ቀዳችለት::
ቶሎሳ የስራ ዕቃዎቹን ከእግሩ ስር አስቀምጦ አረፍ ለማለት ሞከረ:: ያለበት ስፍራ የተመቸው አይመስልም:: የተቀዳለትን አረቄ ጨብጦ በአይኖቹ የተሻለ ቦታን ማማተር ያዘ:: ብድግ ብሎም እነቦዬ ወዳሉበት ክፍት ቦታ ለመቀመጥ ተንቀሳቀሰ::
ቦዬ የቶሎሳን መምጣት እንዳየ ከተቀመጠበት ፈጥኖ ተነሳ:: ቦታው ላይ ከማረፉ በፊትም ኮቱን እየጎተተ እንዳይቀመጥ ከለከለው:: ቶሎሳ ቦዬ መስከሩ አልጠፋውም:: ድካሙን እንዲረዳለት ግን እየሞከረ ነው:: ቦዬ የቶሎሳ ድካምና ትዕግስት የገባው አይመስልም:: ደጋግሞ ኮቱን እየጎተተ እንዳይቀመጥ ማገዱን ቀጥሏል::
ቶሎሳ የተቀዳለትን አረቄ እንደጨበጠ እጅግ እንደደከመውና መቀመጥ እንደሚፈልግ መናገሩን አልተወም:: አሁንም ግን ቦዬ ገጽታ ላይ የይሁንታ ምላሽ አልተነበበም:: ኮቱን ጨምድዶ እንደያዘ ‹‹በቦታው ላይ መቀመጥ የለብህም›› ሲል ሞገተው:: ቶሎሳ ደጋግሞ እንዲተወው መለመኑን ቀጠለ:: የፈጣሪን ስም እየጠራም ከድካሙ አረፍ ማለት እንደሚሻ ነገረው::
ስካሩ ያደርገውን ያሳጣው ቦዬ የቶሎሳን ልብስ እንደጨመደደ ሙግቱን ቀጥሏል:: ትዕግስቱ ወደ ንዴት መቀየር የጀመረው ቶሎሳም ውስጡ በብሽቀት ግሞ የጀመረውን ድርጊት እንዲያቆም መቆጣት ይዟል:: በሁለቱ መሀል የተጀመረውን ግብግብ የሚያስተውሉት መሸተኞች ጉዳዩን ‹‹ነገሬ›› ያሉት አይመስልም:: አንዳንዶቹ በሁኔታው ከመገረም በላይ እየተዝናኑበት ነው::
አሁን የቀን ሰራተኛው ቶሎሳ ትዕግስት በእጅጉ እየተሟጠጠ ነው:: ልመናውን ትቶና ጠብቆ የተያዘውን ልብሱን መንጭቆ አረፍ ሲልም ፊቱ ላይ የተለየ እልህና ንዴት መነበብ ይዟል:: ይህን ንዴቱን በሲጋራው ጭስ መወጣት የፈለገው ቶሎሳ ከኪሱ አንድ ሲጋራ አውጥቶ ለማጨስ መተርኮሻውን ማዘጋጀት ጀምሯል:: ቦዬ ግን አሁንም ሊተወው አልፈለገም:: ከተቀመጠበት ተጠግቶ በእጁ የያዘውን የሲጋራ መተርኮሻ ነጠቀው:: ከዚህ በላይ መታገስ ያልቻለው ቶሎሳ መተርኮሻውን መንጭቆ ተነሳና ወደ ውጭ ተንደረደ:: ከአፍታ በኋላ ተመልሶ ሲገባ ባዶውን አልነበረም:: ትልቅ ድንጋይ የጨበጠ እጁን አጥብቆ ወደ ቦዬ ጭንቅላት ሰነዘረ::
ድንጋዩ የቦዬን የቀኝ ጭንቅላት ለሁለት ገምሶ ቤቱን በተለየ ድባብ ሲቀይረው ደቂቃ አልቆየም:: በተመቺው ግንባር ላይ የሚወርደው ትኩስ ደም ያስደነገጣቸው የአረቄ ቤቱ እድምተኞችና ኮማሪቷ ወርቅነሽ አካባቢውን በደማቅ ጩኸት አደባለቁት:: የበረቱት ጥቂቶች ደግሞ ተጎጂውን ወደ ሀኪም ቤት ለማድረስ ተጣደፉ::
ቶሎሳ በቀደመው ድርጊት ቢናደድም ከባድ የሚባል ድንጋጤ የተከተለው ወዲያውኑ ነበር:: ከስፍራው ሮጦ በወጣ ጊዜ በርቀት ያያትን የፖሊስ አባል ጠርቶ የሆነውን ሁሉ ለመናገር አልዘገየም:: ከፖሊስ ጣቢያ ደርሶ ቃሉን ሲሰጥም ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አንዳችም አልሸሸገም:: ከሁለት ቀናት በኋላ ክፉኛ የተጎዳው ቦዬ የማረፉ ዜና ተሰማ:: ይህ እውነት ካለበት ሆኖ የደረሰው ቶሎሳም በድርጊቱ ተጸጽቶ አንገቱን ደፋ::
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀሉ መፈጸም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ምርመራውን አደራጅቶ ክስ ለመመስረት ቃል መቀበሉን ጀምሯል:: በረዳት ኢንስፔክተር አበረ ትንታጉ የሚመራው ቡድንም ተጠርጣሪው የሚሰጠውን ዕምነት ክህደት በመዝገብ ቁጥር 162/11 ላይ በማስፈር ሰነዱን አደራጅቶ ለዓቃቤ ህግ በማሳለፍ ዝግጅቱን አጠናቋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
መልካምስራ አፈወርቅ