በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ግጭቶችን ለማስቆም የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ይህንን ሚናቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩና ተቀባይነታቸውም በመቀነሱ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አለመሆኑን ባሙያዎች ይናገራሉ። ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪክስ መምህር የሆኑት አቶ ኃይለየሱስ ሙሉቀን እንደሚሉት፤ የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነትን እንዲያገኙና ሚናቸውን እንዲወጡ በመጀመሪያ ደረጃ በአማኙ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው።
ነገር ግን አሁን አሁን ይህ ሚናቸው እየቀነሰ መጥቷል። አቶ ኃይለየሱስ እንደሚሉት ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፖለቲካ በእምነት ተቋማት ውስጥ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው። በዚህም የተነሳ የሃይማኖት ሰዎች እና መሪዎች የነበራቸው ቅቡልነት በእጅጉ ቀንሷል፤ ይህ ደግሞ ሚናቸውን መወጣት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በአሁን ዘመን በሃይማኖት ተቋማቸው እምነት ያጡ ምዕመናን ማየት የተለመደ ሆኗል የሚሉት አቶ ኃይለየሱስ፤ ቅቡልነታቸው መጀመሪያ ካልተረጋገጠ አሁን በአገሪቱ ውስጥ ላለው ሁኔታ ስለሰላም አስፈላጊነት መስበክ የሚያስችላቸው ቁመና ቢኖራቸውም ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ኃይለየሱስ ገለጻ፤ ቀደም ብለው የነበሩ የእምነት ተቋማት ውስጥ የሚከበሩ የሃይማኖት መሪዎች ስለነበሩ ምዕመኑ እነሱን የመቀበል ሁኔታው ከፍተኛ ነበር። የሃይማኖት ተቋማት ሥራቸው ሰውን ከመምከር እና ስለ ሰላም ከመስበክ አኳያ ከዚህ ቀደም ያሳለፉት የታሪክ አመጣጦች ተፅዕኖ አሳድሯል። አሁንም ቢሆን የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን ከመስበክ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም። ነገር ግን ስለ ሰላም ከመስበካቸው በፊት የሃይማኖት ተቋማት አደረጃጀት ለምዕመኑ ግልጽ መሆን አለበት። የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳደ ደስታ እንደሚናገሩት፤ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን ተወጥተው ቢሆን አሁን የተስማማ፣ ቅንጅት ያለው፣ የተዋሀደና ግጭት ውስጥ የሌለ ማህበረሰብ መፍጠር ይቻል ነበር።
የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን ያልተወጡት የነሱ ጥረት ማነስ ወይም ፍላጎት አለመኖር ሳይሆን ምቹ ሁኔታው በደንብ ስላልተመቻቸላቸው ነው። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ኃላፊዎች እና ማህበረሰቡ ለነሱ የሚሰጣቸው ትኩረትና ቦታ ስለሌለ ነው። ‹‹በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ጉዳይ መወጣት የሚገባቸው ሚና ምንድነው የሚለው ነው›› ያሉት አቶ ዳደ፤ በሰላም ዙሪያ ሚናቸውን ተወጥተዋል ወይስ አልተወጡም ለማለት በአገሪቱ ምን ያክል መግባባትና ሰላም አለ የሚለው አለበት ይላሉ። በአገሪቱ በአሁን ወቅት አብዛኞቹ የሚታዩት ምልክቶች የተከፋፋለ ማህበረሰብ እንዳለ ሲሆን፤ እነዚህ ነገሮች አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ ሊያሻግሩ የሚችሉ ክፍተቶችና ቅራኔዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የረጅም ጊዜ ታሪክ እንደሚያሳየው ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። እንደ አቶ ዳደ አባባል የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ይህ እውን እንዲሆን በቂ ዕድል እየተሰጣቸው አይደለም። የፖለቲካ መሪዎችና አዲሱ ትውልድ ለነሱ በቂ ቦታ እየሰጠ አይደለም። ሚናቸው ላይ በተግባር ጥረት እያሳዩ ያሉበት ቦታ አለ፡፡ በአንድ አገር ውስጥም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር ማን ይምጣ የሚለው ነገር ነው ዋና ጉዳይ መሆን ያለበት፡፡ በአገሪቱ ግጭቶች ሲነሱ የውጭ ኃይሎች እንዲገቡ ዝግጁ የመሆን ነገር ይስተዋላል፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አይታሰቡም፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በራሳቸው ጥረት ሲመጡ ደግሞ ያለመቀበል ሁኔታ አለ፡፡
የውጭ ኃይሎች አንድን ግጭት ወይም ያልተፈታ ችግር በትክክለኛ መንገድ ለመፍታት አያስቡም የሚሉት አቶ ዳደ፤ ይሄንን ሊያስብ የሚችለው በቦታው ያለ ሰው ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፤ የውጭ ኃይሎች አስታርቁ ሲባሉ ከፋፍለው እንደሚሄዱ ያስረዳሉ፡፡ በምሳሌነትም የኢትዮ ኤርትራ ችግር በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ተይዞ ቢሆን ችግር ሳይፈጠር መልክ ማስያዝ ይቻል እንደነበር ያብራራሉ፡፡ አቶ ዳደ እንደሚሉት፤ አሁን አገሪቱ ውስብስብ ነገሮች ውስጥ ነው ያለችው፡፡ አንዳንዶቹ በውይይት የሚፈቱ ቢሆኑም ለመፍታት መስማማት አልተቻለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አስቸጋሪ የሆኑት ደግሞ የአረዳድ ሁኔታዎች በተለይ በሃሳብና በግምት ደረጃ ያሉ የሚመስሉና እውነትም ሊሆኑም ላይሆኑም የሚችሉ ነገሮች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡
በእነዚህ ችግሮች የመከፋፈል ሁኔታዎች ይታያል፡፡ በዚህ ደግሞ እውቀቱ ያላቸውና ሚዛናዊ ህሊና ያላቸው የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የማሳተፍ ነገር አናሳ መሆኑን ይናራሉ፡፡ ሰላም ለማምጣት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ያልተሳሳተ ፍትህን መሰረት ያደረገ ምክርና እርቅ እንዲመጣ ዕድል መሰጠት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ የሃይማኖት አባቶች በምዕመኑ ዘንድ የነበራቸው ተሰሚነትና ተቀባይነት ከፍተኛ ነበር የሚሉት አቶ ዳደ በዚህም በወቅቱ የነበሩት መንግሥታት ሃይማኖት ተቋማት ላይ ተፅዕኖ በማሳደራቸው የሃይማኖት መሪዎች ለሞትና ለስደት ተዳርገዋል ይላሉ፡፡
በተመሳሳይ የአገር ሽማግሌዎች በማስታረቅና አገርን ወክለው ድርድር በማድረግ ውጤማነታቸውን በአክሱም ሀውልት ማስመለስ ላይ አሳይተዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው ቅቡልነታቸው ቀንሷል፡፡ በዚህም ሰላም እንዲሰፍንና እርቅ ለማምጣት ሚናቸውን መወጣት አልቻሉም፡፡
እንደ አቶ ኃይለየሱስ አባባል፤ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከዕድሜያቸውና ከበርካታ ልምዳቸው ለአገራቸው በርካታ ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ ሚናቸውን መወጣት ሲያቅታቸውና ቅቡልነታቸው ሲቀንስ በማህበረሰቡ ዘንድ አለመረጋጋት ያመጣል፡፡ ታናሽ ከታላላቆቹ ለመማር ፈቃደኛ ባልሆነ ቁጥር እና ትልቁም ያለውን ልምድ ካላካፈለ ተፈሪና ተከባሪ ስለማይሆን የማህበረሰብ ቀውስ ያመጣል፡፡
እንደ አቶ ዳደ ገለጻ፤ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን መወጣት እንዲችሉ የግድ በቂ ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የመከባበር የመደማመጥና ፍትህን መሰረት አድርጎ ትክክለኛ ቦታቸው ላይ እንዲገኙ የማድረጉ እሴትም ከትውልድ ትውልድ መቀጠል አለበት፡፡ አለበለዚያ በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ክፍተትና ጉድለት ይፈጠራል፡፡ ወጣቱ ከአባቶቹ የወረሰውን ማስተላለፍ ላይ እጥረቶች አሉ፡፡ በዚህም የሚኖረው ማህበረሰብ ትክክለኛ ወዝ የሌለውና በችግር ጊዜ የመደራረስ እሴት ይቀንሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
በመርድ ክፍሉ