ዶክተር ሰናይት ማሪዮ በጣልያኗ ከተማ ሚላን ነዋሪ ሲሆኑ የዋን ፋሽን ጄኔራል ማኔጀር ናቸው። እሳቸው በሚኖሩበት አገር ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። ዶክተር ሰናይትም በሚኖሩበት አገር እየጋጠመ ያለውን ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ መነሻ በማድረግ እኛም ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚያሳስብ ጽሁፍ አጋርተውናል።
የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) የሚያጠቃው በዋናነት የመተንፈሻ አካላትን ነው። በመሆኑም ቢቻል ማስክ ማድረግ፣ ካልተቻለ ደግሞ ከሰው ጋር ያለንን ማህበራዊ ርቀት (Social Distance) መጠበቅ ተገቢ ነው። በተለይ ሙቀት ከፍ ያለ እንዲሁም የሚያስል ወይም የመተንፈስ እክል ካጋጠመው ሰው ራስን ማራቅ ተገቢ ነው። እጅ መታጠብ አንዱ መከላከያ መንገድ እንጂ ብቸኛ አይደለም።
በጣሊያን በሽታው ያልደረሰባቸው ከተሞች ስብሰባዎችን ለጊዜው በመግታት ትኩረታቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ አድርገዋል። እነዚህም በቂ የውሃ አቅርቦት፣ የሕክምና ማዕከል እና ባለሙያዎችን ማዘጋጀት ስራ ላይ ናቸው። እንዲሁም በቂ ማስክ በማዘጋጀት (በቂ ማስክ ባለመኖሩ ቻይና ጣሊያንን መርዳቷ አይዘነጋም)፤ ሳኒታይዘር-ፋርማሲ በመሸጥ ብቻ ሳይሆን ህጋዊ ተመን ወጥቶለት በሁሉም መደብሮች ማከፋፈል የመሳሰሉ ዝግጅቶችም ቫይረሱ ባልተስፋፋባቸው ከተሞች ጭምር ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።
በሀገራችን ሕብረተሰቡ የየዕለት ማህበራዊ ግንኙነቱን እንዲቀንስ የሚያነቃ መልእክት መተላለፍ አለበት። ቫይረሱ በመነካካት ብቻ ሳይሆን በትንፋሽም ጭምር ስለሚተላለፍ መተቃቀፍ እስኪቀረን ተጠባብቀን የምንሰለፍባቸውን ሰልፍና ግፊያ በርቀት ማድረግ እንዳለበት ማስተማርና ሌሎች ነገሮችን የማዘጋጀት ሥራ መሥራት አለባቸው። ቫይረሱ ከመስፋፋቱ በፊት በሁሉም አካባቢዎች ላይ የመከላከል ቅድመ ዝግጅቶች በስፋት መሰራት አለበት። በዚህም ሁሉም ህብረተሰብ በተለይ ወጣቱ በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
መላው የሀገራችን ህዝብ መዘናጋት ሳይኖርበት ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ከማዘን በፊት አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈልና ይህንን ወረርሽኝ መቆጣጠር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። ነገሩ ቀላል ነው፤ ትንሽ እየሰፋና እየተስፋፋ ከመጣ ግን ሁላችንም እራሳችንን ለማዳን ስንሯሯጥ መተሳሰብ ይጠፋና አደጋው ይብሳል። ስለዚህ ካሁኑ መዘናጋታችንን ትተን ወረርሽኙ በመነካካት ብቻ ሳይሆን በጣም ከተቀራረብን በትንፋሽም የሚተላለፍ በመሆኑ፤ የትራንስፖርት ተሽከሪካሪ ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች ትርፍ ባለመጫንና በየቢያጆው አልኮል በመርጨት ለመከላከል ጥረት ቢደረግ መልካም ነው።
የህንፃ ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች በየሊፍቱ ውስጥ ሳኒታይዘር በማስቀመጥና በየኮሪደሩ (ፍሎሩ) መፀዳጃ ከነሳሙና እና አልኮል በማስቀመጥ ጥበቃዎች እያስተባበሩ ገቢና ወጪ እንዲቆጣጠሩ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል።
የሆቴል ባለቤቶች በምንም አይነት ሁኔታ ከደንበኞቻቸው ጋር መነካካት የለባቸውም፤ ወንበሮቻቸውና መመገቢያ ጠረጴዛዎቻቸው በየደቂቃው በአልኮል መጽዳት አለበት። የመኝታ ክፍሎችን በልዩ ሁኔታ መጽዳት ይጠበቅባቸዋል። ሰራተኞቻቸውም ክፍል ሲያፀዱ ጋዋንና ጓንት እንዲጠቀሙ፤ ሲጨርሱ በሳኒታይዘር እራሳቸውን እንዲያፀዱ መምከርና መከታተል ተገቢ ነው። ባለሬስቶራንቶች የመመገቢያ ወንበሮችና የምግብ ማቅረቢያ እቃዎቻቸውን በተለይ ማንኪያዎችና ሹካ በየደቂቃው በሳሙና ማጽዳት፤ ገንዘብ ሲቀበሉና መልስ ሲመልሱም እጃቸውን በሳኒታይዘር ማጽዳት እንዳለባቸው ፈጽሞ መዘንጋት የለበትም።
የሃይማኖት አባቶችና ተቋማትም በየእምነታችሁ ፀሎታችሁን አታቋርጡ፤ ለምዕመኖቻችሁም ግንዛቤን በመፍጠር በየግላቸው እራሳቸውንም ሌላውንም ህብረተሰብ እንዲጠብቁ ብታደርጉ በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ ነው።
መላው የሀገራችን ወጣቶች ይሄ የኛ የታሪክ ዘመን ነውና አገራችንን መጠበቅና ማቆየት በእኛ ላይ የወደቀ ሀላፊነት በመሆኑ ዘር ቀለም ፆታ ሳንለይ አጠራጣሪ ነገር ካየን መረጃ በመለዋወጥና ለሚመለከተው አካል ካለይሉኝታ በመጠቆምና እንዲረጋገጥ በማሳመንና በማስተባበር እንዲሁም አጠራጣሪ ከመሰለን የኢትዮጵያ ዜጋም ይሁን የውጭ ዜጋ በጥንቃቄ እርዳታና ድጋፍ ማድረግ እንጂ ፈፅሞ የማግለል ሁኔታ እንዳይኖር ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል።
የፋብሪካ ባለቤቶች፤ የሰራተኞቻችሁን ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነትና ሀገራዊ ግዴታ ስላለባችሁ ግንዛቤ መስጠትና የመፀዳጃ እቃ በማቅረብ ተጠርጣሪ ሰራተኛ ቢገኝ ለይቶ ማቆያ ስፍራ በማዘጋጀት አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባችሁ ፈጽሞ አትዘንጉ። የመኖሪያ ቤት አከራዮች ወላጆችና ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ቤታችሁ ውስጥ የሚገኙትን የቤተሰብ አባላት በንቃት በመከታተልና ወጥተው ሲገቡ እንዲታጠቡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አጠራጣሪ ነገር ካያችሁ እንዲመረመሩ በማበረታታት ወይም ጥቆማ በመስጠት ሀላፊነታችሁን ብትወጡ በሽታውን ለመግታት ጠቃሚ ነውና አትዘናጉ።
ባለመድሀኒት ቤቶች የወረርሽኝ መከላከያን እና የንፅህና መጠበቂያዎችን ብትችሉ በነፃ ካልሆነ በዋናው ያም ካልተቻለ በመጠነኛ ትርፍ ለህብረተሰቡ በስፋት እንዲደርስ ብትሰሩ ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን ተወጥታችኋል ማለት ነው። ነጋዴዎች አስፈላጊ ቁሳቁስ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱና ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እራሱን እንዲጠብቅ ብትተባበሩም በተመሳሳይ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ትድናላችሁ። የፀጥታ አካላት የሀገራችሁ ህዝቦችና ሀገራችሁ በዚህ ሰዓት በጣም ስለምትፈልጋችሁ ዘር ቀለም ሳትለዩ ከምንም በፊት የመንግስትንና የሀኪሞችን መመሪያ በመከተል እራሳችሁን እንድትጠብቁና ህዝብና ሀገር የሚጎዱና ወረርሽኙን የሚያስፋፉ አላስፈላጊ ድርጊቶችንና አስቸጋሪ ግለሰብና ድርጅቶችን በመቆጣጠር አደራችሁንና ቃላችሁን ጠብቁ። ከላይ የተጠቀሱትን ሁላችንም እንደየሀላፊነታችን በመወጣት የሀገራችን ህዝቦች በአንድነት በመሆን ወረርሽኙን በአስቸኳይ ተቆጣጥረን ታሪክ ማድረግ እንችላለን።
የሚታየው ነገር መዝናኛ አይደለምና አንዘናጋ! ብልጥ ከሌሎች ይማራል። እናቶች ለመውለድ እንኳን በቂ የማዋለጃ ሆስፒታሎች በማይኖሩባት አገር ቫይረሱ ከደረሰና ስር ከሰደደ በኋላ “ሠርገኛ መጣ…” እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ያሻል!! ምንም እንኳን ኢኮኖሚያችንን ቢጎዳም ቅድሚያ ለሰብአዊነት ነውና ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሰድ ቫይረሱ በጣም ወደ ተዛመተባቸው አገራት ለጊዜው በረራዎችን መቀነስና መሰረዝ አስፈላጊ ውሳኔ ነው። ጣሊያን ያላት የህክምና ጥበብ እንኳን መፍትሄ ሳያስገኝላት 60 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎቿን ከወራት በላይ በቤት ውስጥ ካሸገች ምክንያቱን ማወቅና መማር ይቀለናልና “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ይሻላል እላለሁ። ህዝባችንን እንታደግ፤ “ፈጣሪ ሁላችንንም ይጠብቀን”!!!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ዶክተር ሰናይት ማሪዮ ( ከሚላን – ጣሊያን)