በአንድ ወቅት ፈጣሪ በሰጠው ፀጋ አመስግኖ የማያውቅ አንድ ስስታም ነጋዴ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ለንግድ ሥራ ከሄደበት ገበያ ወደ ቤቱ ሲመለስ 100 የወርቅ ሳንቲም ይጠፋበታል። ነጋዴው “100 የወርቅ ሳንቲም ያገኘ ካለ ወረታውን ከፋይ ነኝ” እያለ ቢለፍፍም ሊያገኘው አልቻለም። በዚህ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ እቤቱ ቁጭ ብሎ እያለ አንድ ልብሱ የቆሸሸ፤ ገፅታው የተጎሳቆለ ሰውዬ አንድ ቀን የነጋዴውን ቤት አንኳኳ። በር ተከፍቶ ወደ ሳሎን ቤቱ ሲዘልቅ እንግዳው ሰውዬ የመጣበትን ጉዳይ እንዲህ ሲል አስረዳ።
“ጌታዬ 100 የወርቅ ሳንቲም መንገድ ላይ አግኝቼ ነበር። ባለቤቱም እርሶ እንደሆኑ ነው የተነገረኝ። ምንም የዕለት ጉርሻ የሌለኝ ድሀ ብሆንም የሰው ንብረት አልመኝም። ስለሆነም የወርቅ ሳንቲምዎን ይዤሎት መጥቻለሁ” አለ፤ የሚሰጠው ጉርሻ ምን ሊሆን እንደሚችል በልቡ እያሰበ። ነጋዴው ይህን ሲሰማ በአንዴ ፊቱ ተለዋወጠ። “አንተ እንዳልከው 100 የወርቅ ሳንቲም ብቻ አይደለም የጠፋብኝ። በአጠቃላይ የጠፋብኝ የወርቅ ሳንቲም መጠን 125 ነው። ስለዚህ 25 የወርቅ ሳንቲም አስቀርተኸብኛል። አሁን ሌላ ጣጣ ሳይከተልብህ 25ቱን ሳንቲም መልስልኝ” ሲል አምባረቀበት።
ምስኪኑ ሰውዬ በቅንነት ተነሳስቶ ያደረገው ነገር ያላሰበው ጣጣ ስላመጣበት እጅግ ተጨነቀ። “ጌታዬ እኔ ያገኘሁት ይሄ ብቻ ነው። ምናልባት ሌላ ቦታ ወድቆ እንዳይሆን። በእግዚአብሔር እምልሎታለሁ፤ እኔ አልወሰድኩም” በማለት ሊያስረዳው ሞከረ። ይሁን እንጂ ሀብታሙ ነጋዴ አእምሮው በጥቅም ታውሮ ስለነበር ምንም ዓይነት የርህራሄ ስሜት ሊያሳይ አልቻለም። በዚህም 25 የወርቅ ሳንቲም ወስዶብኛል በሚል ከሰሰው። ድሃው ሰውዬ ከዳኛ ፊት ቀርቦ እንዲህ ሲል ተከራከረ።
“ክቡር ዳኛ ከ100 የወርቅ ሳንቲም ውጭ ሌላ ነገር አላገኘሁም። አግኝቷል የሚል ምስክር ከተገኘ ግን የሚሰጠኝን ቅጣት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናገረ። በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ይመለከቱ የነበሩት ዳኛ ጠፋ የተባለውን የወርቅ ሳንቲም መጠን ምን ያህል እንደሆነ ቀደም ብሎ መረጃ ደርሷቸው ስለነበር የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፉ።
“ጠፋ የተባለው የወርቅ ሳንቲም 100 ብቻ እንደሆነ መረጃ አለን። እርስዎ የተከበሩ ከሳሽ ጠፋብኝ እያሉ ያሉት ደግሞ 125 ነው። ስለዚህ 100ው የወርቅ ሳንቲም የእርስዎ ሊሆን አይችልም። ምናልባት 125 የወርቅ ሳንቲም የወሰደ ሰው እስኪገኝ ድረስ ይጠብቁ። አሁን የተገኘው ሳንቲም ግን ትክክለኛ ባለቤቱ እስካልተገኘ ድረስ ላገኘው ሰው እንዲሰጥ ወስነናል”የሚል ፍርድ ሰጡ።
በመጨረሻም ድሃው ሰውዬ ሀብት በሀብት ሆኖ ሲመለስ ስግብግቡ ነጋዴ ደግሞ ባዶ እጁን ለመመለስ ተገደደ። “አትርፍ ባይ አጉዳይ” ይሉት እንዲህ ነው። የኛ ያልሆነውን ነገር መመኘት ዞሮ ዞሮ ኪሳራ እንጂ ምንም ትርፍ አይኖረውም። ይህንን ተረት ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። ሰሞኑን አልፎ አልፎ የታየውን ከልክ ያለፈ የስግብግብነት ተግባር በተመለከተ ትዝብቴን በመጠኑ ላካፍላችሁ ስለወደድኩ እንጂ።
የሰሞኑ የዓለም ዋነኛ አጀንዳ ኮሮና መሆኑ ይታወቃል። ይህ ገዳይ በሽታ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለምን ክፉኛ ያስደነገጠ ብቻ ሳይሆን የተራቀቀውን የሳይንስ እድገት ደረጃ ሁሉ የተፈታተነ ክስተት ነው። የዓለም ጤና ድርጅትም ይህንን በሽታ ወረርሽ መሆኑን በይፋ አውጆ ለመከላከል ዘርፈብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል። በሽታው በተከሰተ በአጭር ጊዜ ዓለምን ከማስጨነቁም ባሻገር መንግስታትም በሽታውን ለመከላከል በየዘርፉ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ። ይህንን በሽታ ለመከላከልም በርካታ አገራት ትምህርት ቤቶችን ዘግተዋል፤ ስብሰባዎችን አግደዋል፤ አንዳንዶቹም ዜጎቻቸው ከቤት እዳይወጡ ከልክለዋል። በአጠቃላይ የዓለም ማህበረሰብ ይህንን በሽታ ለመከላከል የየራሱን ሩጫ የተያያዘበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
በአገራችንም በሽታው መታየቱ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የመከላከል ዘመቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ህብረተሰቡም ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ መንግስት አሳስቧል። ከዚህ አንፃር በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተለይ ንፅህናን መጠበቅና አፍና አፍንጫን መሸፈን ዋነናኛመንገዶች ናቸው። በዚህ መሰረት እጅን በውሃና በሳሙና በየጊዜው መታጠብ፣ አልኮልን ወይም ሎሚን በመጠቀም እጅን ማፅዳት፣ እንዲሁም የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓትን በመከተል ራስን መጠበቅ ይመከራሉ። እነዚህን የመከላከያ መንገዶች ተከትሎ ታዲያ በአገራችን በተለይ በአዲስ አበባ የታየው የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ሁኔታ ከትዝብትም አልፎ የሚያሳዝን ነው።
መንግስት በአገራችን የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ግለሰብ መገኘቱን በገለፀ ማግስት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ ፋርማሲዎች ረጃጅም ሰልፎች ታይተዋል። ይህም የሆነው አልኮሆልና የአፍ መሸፈኛ ማስኮችን እንዲሁም ጓንቶችን ለመግዛት ነው። በሌላም በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ለአብነትም የሎሚ ዋጋ ላይ በአንድ ጊዜ ከአንድ መቶ ፐርሰንት በላይ ጭማሪ በማድረግ አጋጣሚውን ለመጠቀም የተደረጉ ጥረቶች ታይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ “አንድ የአፍ መሸፈኛ ማስክ 500 ብር እንሸጣለን” በሚል በፌስቡክ ሲያስተዋውቁ የነበሩና “የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ መድሃቶችን አግኝተናል” በሚል እና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶችን በማከማቸት የተያዙ ህገወጦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይህ በዜጎች ችግር ለዚያውም ደግሞ ህይወትን ለአደጋ በሚዳርገው የቫይረስ ወረርሽኝ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረግ ስግብግብነት በመሆኑ እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል። ከሞራል አኳያም ትክክል አይደለም። ምንም እንኳ ጥቂት የንግዱ ህብረተሰብ አባላት ኃላፊነት ተሰምቷቸው የሚሰሩ ቢኖሩም፤ በርካቶች ግን ስግብግብነት ታይቶባቸዋል። ይህ ስግብግብነት በተለይ በዚህ ወቅት መከሰት አልነበረበትም።
ሀገርና ህዝብ ፈተና በአጋጠማቸው ወቅት ለህዝብ ተቆርቋሪ መሆን ነበረባቸው። ግን አልሆነም። ስለሆነም የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉትና ደብቀው በሚያከማቹት ላይ መንግሥት ልክ እንደ ቻይና ፈጣንና አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ስርዓት እንዲይዙ ማድረግ አለበት፤ እያደረገም ይገኛል።
በሌላም በኩል በአንዳንድ ህብረተሰብ ክፍሎችም የሚደረገው ሩጫ አላስፈላጊና መታረም ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል። ለምሳሌ በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ያለበት ሰው መገኘቱን ተከትሎ አንዳንድ ሰዎች ከሱፐር ማርኬት ልዩ ልዩ ሸቀጣሸቀጦችን ገዝተው በመኪና ሲያስጭኑ እንደነበር ታውቋል። ለመሆኑ ችግር ሲመጣ እንዲህ እህል በገፍ በመግዛት ብቻ መዳን ይቻል ይሆን? ወይስ እነሱ ብቻ ለመኖር ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ራስ ወዳድነት ነው?
ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ድረገጽ በተላለፈ አንድ መልዕክት በርካቶች ሲሸበሩ መሰንበታቸውንም ታዝቤያለሁ። “ነጭ ሽንኩርት፣ ፌጦ፣ ማር፣ ጤናዳም እና ጨው ደባልቃችሁ ብትወቅጡና ብትጠቀሙ በሽታው አይዛችሁም” በሚል በተላለፈ የፌስቡክ መልዕክት በርካቶች ማር ፍለጋ በየመንደሩ ሲዞሩ ተስተውሏል። አንድ እፍኝ የማይሞላ ፌጦም አስር ብርና ከዚያ በላይ ተሸጧል። ጤናዳምም እስኪጠፋ ድረስ በየአካባቢው ከመጠን በላይ አገልግሎት ላይ ውሏል። እንዲህ አይነት ጊዜያዊ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ እና አላግባብ የሚደረግ ሩጫ ሊታረም ይገባል።
በርግጥ ችግር ሲከሰት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁሉንም አግበስብሶ ለዘላለም በአንድ ቤት ለመኖር በሚያስመስል ሁኔታ ገንዘብ ስላለ ብቻ በገፍ መግዛትና ገበያውን ማዛባት ጫፍ የወጣ ራስወዳድነት ነውና ለወደፊቱም ቢታሰብበት መልካም ነው። አንዳንድ ነጋዴዎችም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ነው ገበያውን ለማዛባት ጥረት የሚያደርጉት።
በዚህ ዙሪያ ከአንድ የስራ ባልደረባዬ ጋር ስንጫወት ከአመታት በፊት የተከሰተን ጉዳይ አስታወሰኝ። በወቅቱ በአገራችን የጨው ምርት ሊጠፋ ነው በሚል በተነዛ ወሬ ሰዎች ወጥተው ሲሰለፉና ጨው በገፍ ሲገዙ የተስተዋለበት ሁኔታ ነበር። በወቅቱ አንዳንዱ አንድ ኩንታል ጨው ገዝቶ ቤቱ ያስቀመጠበት ሁኔታ እንደነበርም ይታወሳል። ታዲያ ይህ ምን የሚሉት ራስወዳድነት ነው? ጨው ጠፋ እንኳን ቢባል አንድ ኩንታል ጨው ለአንድ ቤተሰብ ምን ያደርግለታል። እስከመቼስ ቁጭ ብሎ ለመብላት ነው? የሚለው ትልቅ ጥያቄን ያስነሳል። እንዲህ አይነት በስሜት የሚካሄዱ ግዢዎች ማንነታችንን የሚያሳዩ በመሆኑ እንደስግብግብ ነጋዴዎቹ ሁሉ ሊታረም ይገባዋል።
ይህ ድርጊት አንድም መንግስት ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል ከፍተኛ ሩጫ ላይ በሚገኝበትና ሁሉም በዚህ ተግባር እንዲረባረብ ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ የራስን ሃብት ለማከማቸት ጥረት ማድረግ ምን ያህል ህሊናን የመሸጥ አዝማሚያ እየሰፋ መምጣቱን አመላካች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቀላሉ ህብረተሰቡ ከመንግስት የሚሰጡ መረጃዎችን በመስማት ከመተግበር ይልቅ ችኩልነትና በማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች በቀላሉ የሚታለልበት ሁኔታ እንዳለ አመለካች ነው።
ይህ የኮሮና ቫይረስ በርካታ ጉዳዮችን አስተምሮናል። እና ኢትዮጵያውያን በችግሮቻችን ወቅት አንዱ ለሌላው ደራሽ እና መረዳዳት ባህላችን መሆኑን ለስንት ዘመን አምነን ስንቀበል ቆይተናል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ገና ይህ ቫይረስ መጣ ተብሎ ቫይረሱን ለመከላከል ሳይሆን በቫይረሱ ለመክበር ሩጫ የጀመሩ ሰዎች መኖራቸው ምን ያህል መልካም እሴቶቻችን እንደተሸረሸሩ ያመላክታል።
እኛ ኢትዮጵያውን ከዚህ ቀደም ጎረቤት ሲቸገር እንኳ ብቻውን የማይበላ ማህበረሰብ ነበርን፤ ነገር ግን በዚህ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ አኩሪ እሴት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረጉ ሰዎችን ተመልክተናል። በዚህ አጋጣሚም እንዲህ አይነት የራስወዳድነትና የግለኝነት ባህል እንዴት እዚህ ደረሰ የሚለው ቆም ተብሎ ሊታሰብበትና ለቀጣይም ሊታረም ይገባል።
በሌላም ቡኩል ቫይረሱ አለባችሁ ሲባሉ ወደሌላው እንዳይሰራጭ ጥንቃቄ ከማድረግ ይልቅ ሮጠው የሚያመልጡትንም ተመልከተናል። ችግሩ ቢኖር እንኳ በዚህ መልኩ ለማለፍ ከመሞከርና ለሌሎች ስጋት ከመሆን ራስን መስዋዕት አድርጎ ህክምና መውሰድ ተገቢ ነው። ነገር ግን በዚህ አይነት ሁኔታ ራስን ለችግር አጋልጦ ሌሎችንም ለማጋለጥ መሞከር አደገኛ አዝማሚያ ነው።
ይህ ሲባል ግን በዚህ ችግር ውስጥም ሆኖ ለህዝባቸው መልካም ነገርን የሚሰሩና ለህዝብ የሚያስቡ ዜጎች እንዳልጠፉ ሊሰመርበት ይገባል። አሁንም ቢሆን ከራሳቸው በላይ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ መስዋዕትነት የሚከፍሉ ዜጎች በየቦታው አልጠፉም። ቫይረሱ እንዲህ አይነትም ጀግኖችን አሳይቶን አልፏል። ለምሳሌ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ አንድ ትልቅ ተግባር ፈጽመዋል። እኒህ ሰው በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘበት ሰው ጋር መገናኘታቸውን መነሻ በማድረግ በራሳቸው ኃላፊነቱን በመውሰድ ራሳቸውን ለቀናት በአንድ ቦታ በማቀብ ቆይተዋል። ሌላውን ለማዳን የሄዱበት ርቀት ከራስ አልፎ ለቤተሰባቸውና ለሌሎች ዜጎችም ምን ያህል ትልቅ ሃላፊነት የሚሰማቸው እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ ግን በመጨረሻ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል። የፈፀሙት ተግባር ግን አርአያነት ያለው በመሆኑ እንዲህ አይነት ሰዎች ሊበራከቱ ይገባል።
ከንግድ እቅስቃሴ ጋር በተያያዘም በርካታ የንግድ ሱቆችና መድሃኒት ቤቶች በጊዜያዊ ትርፍ ታውረው በሸማቹ ላይ ትርፍ ቢጭኑም በርካቶች ደግሞ ሃቅን መሰረት ያደረገ ንግዳቸውን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። ለዚህም ሸዋ ሱፐር ማርኬትን ጨምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ አይነት ተቋማትና ግለሰቦችም በችግር ጊዜ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡ በመሆናቸው ሊመሰገኑና በርቱ ሊባሉ ይገባል።
አሁን የገጠመንን ፈተና ማለፋችን አይቀሬ ነው። ነገር ግን በዚህ የሚያልፍ ችግር የማይቀር ጠባሳና ትዝብት ጥለን ላለማለፍ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል። በክፉ ጊዜ የተሻለው መንገድ መረዳዳት፣ መተዛዘንና ችግሩን በጋራ ለማለፍ ከመንግስት ጎን ቆሞ መስራት ነው። እናም የነገ ሰው እንዲለን ከምንተዛዘብ እንተዛዘን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ወርቁ ማሩ