
ዜና ሐተታ
የሙቀት መጠን መጨመር፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የሰደድ እሳት መከሰት፣ የግግር በረዶ መቅለጥ፣ የውቅያኖሶች መጠን ማሻቀብና ማሽቆልቆል፣ ማዕበል፣ የለም አፈር መታጠብና የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን እየፈተኗት ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው። ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው የዛፎች ወይም የዕፅዋት መመናመንና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው የተፈጥሮ ሚዛን መዛነፍ እንደሆነ ዓለም አቀፍ የሥነ ምኅዳር ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች ያስረዳሉ።
የተዛባውን የተፈጥሮ ሚዛን ለማስተካከል ችግኞችን መትከል የመጀመሪያ መፍትሔ እንደሆነም እነኚሁ ተመራማሪዎች ይመክራሉ። በተፈጥሮ ሚዛን መዛነፍ ምክንያት ዓለም ከፊት ለፊቷ የተደቀነባትን አደጋ በአሸናፊነት መወጣት እንዲያስችላትም የዓለም ሀገራት ችግኞችን የመትከል ኃላፊነትን እንዲወጡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ይነገራል፤ ይዘከራል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በመተግበር ውጤታማ ሥራዎችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።
ዘንድሮም እንደሀገር በሰባተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዞ የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ሆኗል።
ይህን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ክልላዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ ቀንን እንደክልል ‹‹የትውልድ ጥላ›› በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ምዕራብ ዞን ወንጪ ወረዳ አካሂዷል።
ታዲያ በወንጪ ወረዳ ሶንቆሌ ቀበሌ በተደረገው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከአካባቢው የገጠር ቀበሌዎች የመጡ በርካታ ሰዎች ተሳትፈዋል። በተለይም በነቂስ ውጥተው ሲተክሉ ከነበሩ የሶንቆሌ ነዋሪዎች መካከል የታዳጊ ሕጻናት ተሳትፎና ትጋት ቀልብን የሚስብ ሆኖ አግኝተነዋል። ውርጭና ብርድን ተጋፍጠው ችግኞችን በእቅፋቸው ወደመትከያው ስፍራ እየወሰዱ ሲተክሉ ያየናቸው ብላቴናዎች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን አነጋግረናል። ምንም እንኳን ሃሳባቸውን በደንብ ተናግረው ለማስረዳት ቢቸገሩም ተግባራቸው ከአንደበታቸው በላይ የሚናገረው ቁምነገር ስላለ በዚያ ማንነታቸው ልንረዳቸው እንሞክራለን።
የብርቱካን ችግኝ እየተከለ ያገኘነው፤ ታዳጊ ሳሙኤል ደሾ በወንጪ ወረዳ የሶንቆሌ ቀበሌ ነዋሪና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ ለችግኝ ተከላ ማለዳ ወደ ሶንቆሌ ተራራ ሲወጣ እርሱም ቤተሰቦቹን አስፈቅዶ እንደመጣ ይናገራል።
የብርቱካን ችግኝን መትከል ሁለት ጥቅም አለው የሚለው ሳሙኤል፤ አንድም ለምግብነት፤ ሁለትም ለአፈር ጥበቃ እንደሚያገለግል ገልጾልናል። ሳሙኤል ችግኝን መትከል እንደሚያስደስተውም ነግሮናል።
ሌላው አይን አፋሩና አንደበተ ቁጥቡ ታዳጊ ገዳ ሰለሞን ነው። እርሱም የሶንቆሌ ቀበሌ ነዋሪና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ ከገለጸልን በኋላ ቤተሰቦቹ ችግኝ ለመትከል ወደ ተራራው ሲመጡ እርሱም አብሯቸው እንደመጣ ነግሮናል። ችግኝ መትከል ለምን ይጠቅማል? ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ‹‹አፈር እንዳይሸረሸር ያደርጋል፤ ዝናብ እንዲዘንብ ያደረጋል›› በሚል በአጭሩ መልሶልናል።
ይህም ልጆች ያሳዩቸውን ነገር መተግበር እና የታላላቆቻቸውን ተሞክሮ ማስቀጠል የሚችሉ መሆኑን ያየንበት ጥሩ አጋጣሚ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ወቅት የቤት ሥራ ሳይሆን በትውልዶች ቅብብል እየተሸጋገረ የሚቀጥል እና የሰው ልጅ የተደቀነበትን አደጋ ለመቀልበስ ሳይዘናጋ ሁልጊዜ የሚያከናውነው ተግባር ነው። ስለሆነም አዲሱ ትውልድ የዛፎችን ጥቅም እንዲያውቅ ማድረግ እና በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች እንዲህ እንዳየናቸው ዓይነት ታዳጊዎችን ማሳተፍ አዲሱ ትውልድ አዎንታዊ አቅም እንዲፈጥር ያደርጋል። የነገ ጉዳቶችን ለማስቀረት ከወዲሁ አካባቢውን እና ተፈጥሮን መንከባከብ እንዳለበትና በተለይም ዛፍ መትከልን የሕይወቱ አካል አድርጎ እንዲመለከት ያስችላል።
በኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም