ስለ ህይወት ትርጉም ማሰላሰላችን ምን አልባትም ወጣ ያለ፣ አላዋቂ ወይም ጭንቀታም የሚል ስያሜ ሊሰጠን ይችላል። በሌላ ጎንም በዚህ ዘመን ሰዎች አንዳንዴ ሀዘን በተላበሰ ቅላፄ አንዳንዴም በቁጣ እናበምፀት ስሜት “ህይወት ትርጉም የለውም” ሲሉ ይደመጣሉ። ይባስ ብሎም አንዳንዶች ይህን ወሳኝ ጥያቄ ሳያስተናግዱት የህይወት ዘመናቸውን ይገፋሉ።
ለዚህ መከሰት ሁለት ምክንያቶች ተደጋግመው ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው ተጠቃሽ ምክንያት ሃይማኖት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍቱ እንደሚያወሱን ከዘመናት በፊት የሰው ልጅ ህይወት ከአምላክ የተሰጣት ግልጽ ትርጉም ነበራት እሱም አምላክን ማምለክ እና በትዕዛዛቶቹ መኖር ነበር። ግን እምነት በሰው ልጆች የቀን ተቀን መስተጋብር ውስጥ ያለው ሚና እየቀጨጨ ሲመጣ እና የአምላክ መረሳትን ተከትሎ ከእምነት የሚነሳው የህይወት ትርጉም አብሮ ሊዳከም ችሏል።
ሁለተኛው ለህይወት ትርጉም መዛባት ተጠያቂው ዘመናዊ ሳይንስ ነው። ሳይንቲስቶች ለህይወት መፈጠር እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት የኬሚካሎች እና ጋዞች ገጠመኛዊ ውህደት እንደ አንድ ትርጉም ልንወስደው እንችል ይሆናል። ግን ይህ ትርጉም ለብቻው ጠባብነት እና ጨለምተኝነትን የተሸከመ ነው። የሰው ልጅ ህይወት እንደ ሌላው ህይወት ያለው ነገር ሁሉ (ለምሳሌ አሜባ) የህይወት ትርጉሙ በህይወት መቆየት እና ዘረመልን አስተላልፎ ማለፍ ነው ስንል ምንም እንኳን እውነትነት ቢኖረውም በተመሳሳይ ህይወትን ዋጋቢስ እና ጭጋጋማ ያደርገዋል።
ስለዚህ በዚህ አጭር ፅሁፍ፣ ስለህይወት ትርጉም ማሰላሰል ወሳኝ እንደሆነ፣ ህይወት ሚዛን ሊደፉ የሚችሉ ትርጉሞች እንዳሏት እና ታላቅ ትርጉም ለማግኘትም ልንከተላቸው የሚገቡ ትናንሽ እርምጃዎችን ጠቅለል ባለመልኩ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
እንዲህ ብለን መጀመር ግን ይበጃል፡፡ እሱም፣ እኛ የሰው ልጆች ፈልገን ከምንቀበለው ውጪ ሌላ ትርጉም ሊመጣ አይችልም የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ ከክዋክብት ላይ የተጻፈ፣ በቅዱሳን መጽሀፍት ላይ የተከተበም ሆነ በዘረመል /DNA; Deoxyribo Nucleic Acid/ ላይ የተነቀሰ ዝርዝር የህይወት ትርጉም የለም፡፡
ሰዎች ታዲያ ስለህይወት ትርጉም ማጣት ለምን ያማርራሉ ስንል አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሱት የተለያዩ ደስታን ከሰው የሚያርቁ የህይወት ገጠመኞች ናቸው፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች እስኪ እንመልከት፡- የፍቅር ግንኙነት ውስጥነህ/ሽ ግን መጀመሪያ ላይ የነበረው የጋለ ስሜት በሮ ሄዷል። ምንም አይነት ቁም ነገር ያዘለ ነገር አትነጋገሩም፣ የሚያስፈሯችሁን ስሜቶች እና ሀሳቦች ዙሪያም እንደመነጋገር አዝላችሁ ይዛችሁታል፡፡ ስለዚህ ትርጉም አልባነት ሊከብህ/ሽ ይችላል፡፡ ወይም ምንም አይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሳትሆን እንኳ ብዙ ጓደኞች ቢኖርህ/ሽም ሁሌ ስትገናኙ ወሬው ሁሉ ውሃ የማይሞላ እና ምንም ጠብ የማይል ሊሆን ይችላል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርትህን እየተከታተልክ ነው። ኮርሶችን ለመውሰድ መረጥክ/ሽ ሆኖም ምን መሆን እንዳለብህ/ሽ ግልጽ የሆነ መስመር አይታይህም/ሽም፡፡ ምን አልባት ክፍል ቁጭ ብዬ መማሬ እና መጽሀፍ ማንበቤ ምን መሆን እንዳለብኝ ግልጽ አድርጎ ያሳየኛል ብለህ/ሽ ይሆናል። ግን ትምህርቶቹን ይባስ ደረቅ እና አሰልቺ ሆነው ልታገኛቸው/ኚያቸው ትችላለህ/ያለሽ፡፡ ትርጉም የለውም ብለህ/ሽ ልትነጫነጭ/ጪ ትችላለህ/ያለሽ፡፡
ትልቅ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረህ/ሽ እየሰራህ/ሽ ኪስ የሚሞላ ገንዘብ በወር እያገኘህ/ሽ ነው፡፡ ግን ስራውን በትልቁ መነጽር ስንመለከተው ጠቃሚነቱ የጎላ ላይሆን ይችላል፡፡ ማለትም የማንንም ህይወት ሊያሻሽል ወይም ሊለውጥ የሚችል ስራ ላይሆን ይችላል፡፡ አሊያም ስራውን ከእኛ ማንነት ጋር አዋህዶ ለመስራት ሊቸግረን ይችላል፡፡ ስራው በሮቦት በተሰራ የሚያስብል ድግግሞሽ የበዛበትም ሊሆን ይችላል፡፡
ከዚህ ተነስተህ የትርጉም ጽንሰ ሀሳብ ልናመነጭ እንችላለን። ትርጉሙም ከሶስት ተግባራት ሊነሳ ይችላል። እነዚህም ከተግባቦት /communication/፣ ከመረዳት /un¬derstanding/፣ ከአገልግሎት /service/ ናቸው፡፡
እስቲ መጀመሪያ ተግባቦትን /communication/ እንመልከት፡፡ በተፈጥሮአችን ብቸኛ ፍጡራን ነን፡፡ ሆኖም በጣም ትርጉም የምንሰጣቸው ገጠመኞች ከሌሎች ጋር ሆነን በሚኖሩን ወሳኝ ቅጽበቶች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል እነዚህን እንደምሳሌ እንይ፤ ለፍቅረኛችን ስነ ልቦናዊ እና አካላዊ ምሉእ ማንነታችንን ገልጸን ስናሳይ ወይም ለጓደኛችን ከበድ ያሉ የኛን እውነታዎች ስናጋራ፤ አሊያም ርቀን ሄደን የማናቀው ማህበረሰብ ዘንድ ተጉዘን ከእንግዳ ሰው ጋር ንግግር ጀምረን ምንም እንኳ የቋንቋ እና የባህል ልዩነት የሚገድቡ ቢሆኑም መግባባት ስንችል ግን የሚሰጠን ልዩ ስሜት፤ ወይም መጽሀፍት፣ ዘፈኖች እና ፊልሞች የት እንደነበር የማናውቀውን ስሜቶች ተጭነው ከውስጥ ወደ ውጪ የተደበቀ ስሜትን ፈንቅለው ሲያወጡ ያለው ውበት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው የትርጉም ጽንሰ ሀሳብ ከመረዳት ሊመነጭ ይችላል፡፡ ስለ ዓለማችን ወይንም ስላለንበት ሁኔታ ያልገቡንን ሀሳቦች ወይንም ሁኔታዎች ስንረዳ የሚፈጠረው የሃሴት ስሜትን ያካትታል፡፡ ሳይንቲስት ሆንን ኢኮኖሚስት፣ ገጣሚ ሆንን ለምክክር አገልግሎት የሄድን ደንበኛ በአጠቃላይ በየትኛውም የስራ መስክ እንገኝ፣ ከሥራ እና ድርጊቶቻችን የሚመነጨው የደስታ እና የእርካታ ስሜት ያልገቡንን ሀሳቦችን ወይንም ሁኔታዎችን መረዳት በመቻላችን ምክንያት የሚገኘው ነው፡፡
ሦስተኛው ደግሞ አገልግሎት ነው። ሌላኛው በህይወታችን ትልቅ ትርጉም ሊሰጠን የሚችለው ነገር ሌሎችን ማገልገል ነው። ይህም አገልግሎት የሰዎችን ህይወት ለማሻሻል፣ ወይም የሰዎችን ችግር እና ስቃይ ለመቀነስ አሊያም አዲስ የደስታ እና ሀሴት ምንጭ ለሰዎች ለመፍጠር የሚደረግ ሊሆን ይችላል። እንበል እና የህክምና ዶክተር ብንሆን የስራችን ትርጉም የሰውን ህመም በየተራ መቀነስ እና ሠላማዊ እንቅልፍ እንዲተኙ መርዳት ሊሆን ይችላል፣ ዋናው ቁምነገር ራስን ተረድቶ የአገልግሎትን መስመር መምረጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
እነዚህን ሀሳቦች ታጥቀን የህይወትን ትርጉም ፍላጋ መጓዝ እንችላለን። ስለዚህ የህይወት ትርጉም የሰውን ብልጽግና እና እድገት በተግባቦት፣ በመረዳት እና በአገልግሎት መፈለግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትርጉም ያለው ህይወት ለመኖር ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸው ነገሮች አሉ።
በሰው ልጅ ህይወት አሳዛኙ ነገር ግን ትርጉም ያለው ህይወት እንዳይኖር ብዙ ጋሬጣዎች መኖራቸው ነው። በተግባቦት ዙሪያ ካሉ መሰናክሎች ብንጀምር ለምሳሌ ለግብረ-ስጋ ግንኙነት የሚሰጥ ልዩ ትኩረት፣ ጓደኝነትን አሳንሶ ማየት የጉርብትና መድከም ወይም ለዚህ የተመቸ ባህልና አስተሳሰብ እና ማጣት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በውስጣዊ ደረጃም ያለን ስሜት ላይ መሠረት ያደረገ ችግር ሰዎችን በቀላሉ እንዳንግባባ መሰናክል ሊሆን ይችላል፡፡
በመረዳት ዙሪያ ችግር የሚሆኑት የጥሩ መረጃ እጥረት፣ ራስን መርምሮ አለመረዳት፣ በምክክር ሙያ ላይ እምነት አለማሳደር እና ከላይ ከላይ ብቻ የሆነና ከእውነታው አለም የተለየ የትምህርት ዓለም መኖሩ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ትርጉም ያለው ህይወት ለመገንባትም የሰው ልጅ ስሜቶች ላይ፣ ማህበራዊ ትስስራችን ላይ፣ ራስን የመረዳት ባህላችን ላይ እና ከዚህ የተሻለ ግልፅና የሚታመን ካፒታሊዝም ሥርዓት ላይ ትኩረት ተደርጐ ሊሰራ ይገባል። ምንም እንኳ ገና ትርጉም ያለው ሕይወት ባይኖረንም ግን ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ይቻላል የሚለው ሀሳብ ለራሳችን ጠልቆ ሊገባን ይገባል፡፡ በተጨሪም ትርጉም ያለው ሕይወት በውስጡ ተለይተው ሊነገሩ የሚችሉ ነገሮች እና ቀስ በቀስም ሊያሟሏቸው የሚችሉ ነገሮችን መያዙን መረዳት ይገባናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
አብርሃም ታረቀኝ