
መነሻው በቻይናዋ ዉሃን ግዛት የሆነው የኮሮና ቫይረስ የዓለም ሀገራትና መንግስታት ፈተና ሆኗል። አውሮፓዊቷ አገር ጣልያን የኮሮና ቫይረስ የሞት ድግሱን ከፍተኛ ያደረገባት ሀገር ነች። የዜጎቿን አስከሬን መቅበሪያ ቦታ እስኪሞላ ደረስና ቀባሪ ጠፍቶ በሀገሪቱ ወታደራዊ ተቋም ቀብር እየተፈጸመባት ትገኛለች። የሃያላን ሀገራት መሪዎች ሃያልነታቸውን በኮሮና ቫይረስ ተነጥቀዋል።
እስከ ትናንት ድረስ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከ14 ሺ 640 ሰዎች በላይ ሞት፣ ከ330 ሺ በላይ ተጠቂዎች ዓለም አስተናግዳለች። የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከልን ጨምሮ ማቆያ ቦታ (ኳረንቲን )የገቡትን ቤት ይቁጠራቸው። ኢትዮጵያም የተጠቂዎቿ ቁጥር 11 መድረሱን ይፋ አድርጋለች።
ከቡርኪናፋሶ ወደ አዲስ አበባ በገባ አንድ ጃፓናዊ ዜጋ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የመንግስትና ህዝብ ዋና አጀንዳ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ላይ ያተኮረ ሆኗል።
መንግስትም በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ይበልጥ ተስፋፍቶ በህዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ከመዋእለ ህፃናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአስራ አራት ቀናት እንዲዘጉ ወስኗል። ከመንግስት እውቅና ውጪ የሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎችን ከልክሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችም እንዳይካሄዱ አግዷል። የብዙሃን ትራንስፖርት የሚሰጡ የከተማ አውቶብሶችም ከልክ በላይ እንዳይጭኑ፤ ይህንንም ተከትሎ ለሚፈጠረው የትራንስፖርት እጥረት የመንግስት ተሽከርካሪዎች ለህብረተሰቡ
ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል። የኀገሪቱ ድንበሮች ከምግብና መድሃኒት ውጭ ሰዎች እንዳይዘዋወሩባቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ 30 ሀገራት እንዳይበር ማገድና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ደግሞ በራሳቸው ወጪ ለ14 ቀን በተዘጋጀላቸው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ወስኗል።
ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊት በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረ ምንም አይነት መደናገጥም ሆነ መረበሽ ባይኖርም ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ህብረተሰቡ መደናገጥ ቢታይበትም ጥንቃቄው ግን የድንጋጤውን ያክል አይደለም። አንዳንድ ግለሰቦችም ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችንና የእጅ ጓንቶችን አድርገው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። ቫይረሱ በብርቱ ያሳሰባቸው የመንግስትና የግል ተቋማት ደግሞ የእጅ መታጠቢያና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በየተቋሞቻቸው በር አድርገው ለዜጎች አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች ቫይረሱ በቀላሉ ከአንዱ ወደሌላው ሊተላለፍ አይችልም ከሚል የተሳሳተ ግምት ቸልተኛ በመሆን ራሳቸውን ለቫይረሱ እያጋለጡ ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ ‹‹ቫይረሱ እኛን አይነካንም የሚያድነንም እምነታችን ነው›› በሚል ቸል እያሉ ነው። ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ቫይረሱን መከላከል የሚቻለው በነጭ ሽንኩርት፣ ፌጦና ካቲካላ ነው እንጂ መጨባበጥ በማቆምና እጅን አሁንም አሁንም በመታጠብ አይደለም በሚል ይሞግታሉ። ይህ ስህተት ነው። መዘናጋት ነው። መዘናጋት ለጣልያን አልጠቀማቸውም። ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። እኛ ከዚህ መማር ካልቻልን አደጋው የከፋ ነው።
በርግጥ ሁሉም ሰው በእምነቱ መተማመኑ ችግር የለውም። ፈጣሪ ደግሞ ማሰቢያ አእምሮ ሰጥቶናል። ይህ የሆነው ደግሞ ችግር ሲያጋጥም መፍትሄ ለመሻት እንጂ እጅና እግራችንን አጣምረን ለመጠበቅ አይደለም። ስለሆነም እኛም ጥረት ማድረግ አለብን። ሀገር በቀል ባህላዊ መድሃኒቶችንም በሳይንሳዊ መንገድና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ችግር የለውም። ይህ ግን ብቻውን በቂ አይደለም። ስለዚህ የሰው ልጅ ሙሉ ጤንነቱን ሊረጋገጥ የሚችለው እምነቱን በማመኑ እና ባህላዊ መድሃኒቶችን በመጠቀሙ ብቻ አይደለም። የህክምና ባለሙያዎችን ምክርና ዘመናዊ ህክምናንም በመጠቀም ነው። ዘመናዊ ህክምናው ሰዎች ፈጣሪ በሰጣቸው እእምሮ የሰሩት መሆኑ ማወቅ ያስፈልጋል።
መቼም የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለቁጥር የሚታክቱ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሃን ሲቀርቡ ቆይተዋል። እነዚህ መረጃዎች የሚናቁ አይደሉም። በተለይ በጤና ባለሙያዎች ቫይረሱን በተመለከተ የሚተላለፉ መልእክቶች ለህብረተሰቡ ጠቃሚና ራሱን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚረዱ ናቸው። ታዲያ እነዚህን መልእክቶች ተቀብሎ ራስን በቫይረሱ ከመያዝ መጠበቅ ብልጠት እንጂ ሞኝነት አይደለም። ይህንኑ ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂም አያደርግም። በርግጥ አብዛኛው የማህበረሰቡ ክፍል የቫይረሱ አሳሳቢነት ገብቶት ጠቃሚ የሃኪም ምክሮችን ተቀብሎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ህዝብ ከላይ በጠቀስኩት ምክንያቶች አሁንም ቸልተኛ አቋም በመያዝ ራሱን ለቫይረሱ አጋልጧል። በመሆኑም በቫይረሱ ዙሪያ በየጊዜው የሚሰጠው መረጃ ዞሮ ዞሮ ለእርሱ ጥቅም ነውና ይህን ተረድቶ ምክሩን ሊከተል ይገባል።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አሁን አሁን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ሰዎች ትራንስፖርት በሚይዙባቸው አካባቢዎች ወጣቶች ውሃና የእጅ ማፅጃ ሳሙናዎችን በማዘጋጀት ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ በማድረግ የጀመሯቸው ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው። በቫይረሱ ቸልተኛ አቋም እያሳዩ ያሉ ወገኖችም ‹‹የጤና ባለሙያዎች ምክሮችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶች ከበሽታው አያድኑም›› ከሚል የተሳሳተ አመለካከት በመውጣት ከቫይረሱ ራሳቸውን መከላከል ይጠበቅባቸዋል።
በከተማዋ አንበሳና ሸገርን የመሰሉ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ለተሳፋሪዎቻቸው ሳኒታይዘር በማዘጋጀት የእጆቻቸውን ንፅህና እንዲጠብቁ እያደረጉ ነው። ይህም ተግባር በጎና ሊደገፍ የሚገባው ሆኖ ሳለ አንዳንድ ግለሰቦች ለዚህ ተገዢ ያለመሆን አዝማሚያዎችን እያሳዩ የሚገኙ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው የአብዛኛውን ህብረተሰብ ጤንነት ሊፈታተኑ አይገባም። ከዚህ ቸልተኝነት ተግባራቸው ተላቀው ጠቃሚ ምክሮችን በመስማት እንደሌላው የህበረተሰብ ክፍል ራሳቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
የዓለም ሀገራት የየራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም ህዝቧን ከቫይረሱ ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ላይ ትገኛለች። በዚህ ሂደት ታዲያ ህብረተሰቡ ለራሱ የጤና ደህንነት ሲል አስፈላጊውን ቀና ትብብር ሊደርግ ይገባል። ቫይረሱን መከላከል የሚቻለው ሁሉንም አይነት ትብብር ማድረግ ሲቻል ነውና የሃይማኖት አባቶች በቅርቡ ያስተላለፉትን መልክት በመከተልና በሃኪሞችና በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚተላለፉ ወቅታዊና ጠቃሚ መረጃዎችንም አዳምጦ ተግባራዊ በማድረግ ራስን ከቫይረሱ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ጤናችንን በጋራ እንጠብቅ። የጋራ ጤና ለጋራ ነውና!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/ 2012
አስናቀ ፀጋዬ