
በአንድ ሀገር ላይ የሕዝብን ተሳትፎ የመሰለ ጉልበታም ኃይል የለም። በሀገረ ግንባታ ሂደት ውስጥ እምርታ አምጥተው ከገነኑ ስሞች መሀል ተሳትፎ የሚለው ስም በቀዳሚነት ይነሳል። ተሳትፎ በትብብር፣ በአብሮነት እንዲሁም በጋራ መሻት የሚገለጽ የእድገት የልማት እና የአብሮ ማደግ መጠሪያ ነው።
ያለፍንባቸው የታሪክ እና የለውጥ ሰርጦች በዚህ ስም የተጠሩ ስለመሆናቸው ታሪክን መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል። እንደ ሀገር በትብብር እና በቅንጅት ከባድ የሚመስሉ ድሎችን ተወጥተናል። ለአብነት ያህል የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ብናነሳ ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ውስጥ የነበረውን የሕዝብ ተሳትፎ እና ድጋፍ ማስታወስ ይቻላል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ድሮነትን ብንቃኝ የዓድዋን ብዙሀነ ውበት ማስተዋል እንችላለን። ዓድዋ ብዙ ወርቃማ የድል ስሞች ቢኖሩትም ከነዚያ ሁሉ ወርቃማ የድል ስሞቹ መሀል ኢትዮጵያውያን አንድ የሆኑበት የክተት አዋጅ በቀዳሚነት ይነሳል።
ወደዚህኛው ወደ እኔና ወደ እናንተ አሁናዊ ዘመን ስንመጣ በሕዝብ ተሳትፎ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች እንዳሉ እሙን ነው። ለዛሬ ግን ወቅታዊ ስለሆነው እና ከትላልቅ የሕዝባዊ ተሳትፎ መሀል ቀዳሚ የሆነውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን እናንሳ። ሀገራችን በየዓመቱ የክረምት መግባትን ተከትሎ ከምትከውናቸው ሥራዎች መሀል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አንዱ ነው።
7.5 ቢሊዮን ችግኞች ይተከሉበታል ተብሎ እቅድ የተያዘለት የዘንድሮው ሰባተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረ ሲሆን እንዳለፈው ጊዜ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ትጋት፣ ውህደት እና ትብብር የሚታይበት እንደሚሆን ይገመታል። ባለፉት ስድስት የተከላ ዓመታት ውስጥ ከእቅዳችን ሳንዛነፍ በልበ ሙሉነት እቅዳችንን አሳክተን ትጋታችንን አሳይተናል። ዘንድሮም ተመሳሳይ ውጤት እንደሚመጣ ይጠበቃል።
በቀጣይ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ የተያዘለት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በስምንት ዙር የተከላ መርሀ ግብር በአጠቃላይ ሀምሳ ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ይጠበቃል። ቆላማ ቦታዎችን፣ በርሃማ ሥፍራዎችን፣ ገላጣ አካባቢዎችን፣ የወንዝ ዳር ዳርቻዎችን እንደዚሁም አስፈላጊ ሥፍራዎችን ታላሚ ባደረገ መልኩ እየተሠራ ያለው እንቅስቃሴ በእስካሁኑ በርካታ ለውጦችን እንዳመጣ ይነገራል።
ዛፍ ሕይወት ነው የሚል የልጅነት እውቀት አለን። የሰው ልጅ ከእጽዋት ጋር እንደመቆራኘቱ ከሌላ ከምንም ጋር እንዳልተቆራኘ ሳይንስ ይነግረናል። ሰው በሕይወት ለመኖር ከእጽዋት የሚያገኘው ኦክስጅን ወሳኝ እንደሆነ የልጅነት የአስኮላ አካባቢ ሳይንስ ነግሮናል። ከዚህ ሳይንሳዊ እና ባይሎጂካል እውነት በመነሳት በነዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ እንደ ሀገር ያበረከትነው አስተዋጽኦ በምንም የማይገመት እንደሆነ ይጠቀሳል።
በስምንት ዓመታት ውስጥ ሀምሳ ቢሊዮን ችግኞችን እንተክላለን። ሌላ ጥቅምና ዘላቂ ፋይዳውን ትተን እንዲሁ በሰውኛ አንድን ችግኝ ከአንድ ሰው ሕይወት ጋር ብናቆራኘው የተከልነውንና የምንተክለውን ችግኝ ለሀምሳ ቢሊዮን የሰው ልጅ የመኖር ምክንያት መሆን የሚችል ነው ማለት ነው። ለጋራ ልማት ሕዝብ የተቧደነበት ሀገራዊ ጉዳይ አንድምታው ምን መሳይ እንደሆነ በችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ለመታዘብ ችለናል።
አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ማንም እንደዜጋ ለሀገሩ ሊያውለው ከሚገባ ውለታ መሀል የሚመደብ ነው። በአሁኑ ሰዓት የዓለም ትኩስ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ አንዱና ዋነኛው ነው። የችግሩን አሳሳቢነት ቀድመን ተረድተን እያደረግነው ያለው የጥንቃቄ እና የቅድመ መከላከል ሥራ እሰየው የሚያስብል ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከመዲናችን አዲስ አበባ ቢጀምርም ተልዕኮው ሀገራዊ ተልዕኮ ነው። በአንድ ዓላማ ከገጠር እስከ ከተማ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ችግኝ በመትከል አሳሳቢውን የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት የምንገታበት ነው። መንግሥት በጀት በመመደብ ከትላልቅ መንግሥታዊ ጉዳዮች እኩል አቅጣጫ እና እቅድ አስቀምጦ የሚሠራው ግዙፍ ሥራ በመሆኑ የተልዕኮውን ያክል ፍሬ እያፈራም ይገኛል።
የሰው ልጅ ሕይወት ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ተፈጥሮን በጠበቅናት ቁጥር ልትጠብቀን እና የደህንነት ዋስትና ልትሰጠን የታመነች ናት። ሰው በባህሪው ራስ ወዳድ እና ለኔ ብቻ የሚል እንስሳ በመሆኑ በእሱ እና በተፈጥሮ መካከል የተሰመረውን የሕልውና መስመር አጥፍቶ ምድርን ለራሱ ብቻ እንድትመቸው አድርጎ በማበጃጀቱ የሕልውና አደጋ ወድቆበታል። አሁን ላይ ዛፍ የምንተክለው፣ በጀት መድበን አካባቢ እንክብካቤ ሥራ የምንሠራው፣ ሀያላኖቹ ሳይቀሩ ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተፈጥሮን ከሰው ልጅ ጋር ለማስማማት እያደረጉ ያለው ጥረት ከሰው ልጅ ራስ ወዳድነት የጥፋት አካሄድ የመነጨ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ በአረንጓዴ አሻራ ካልታከመ አደገኛ ነገር ነው። የዝናብ እጥረት በማስከተል ለድርቅና በርሃማነት በማጋለጥ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። የአፈር መሸርሸርን በማስከተል ምርት እና ምርታማነትን በመቀነስ የሕልውና አደጋን ይፈጥራል። ለም የሆኑ የሥነ ምሕዳር አካባቢዎችን በመመረዝ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ለርሀብ እና ለድህነት ይዳርጋል። ከዚህ ሁሉ በላይ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ መርዛማ ጨረሮችን ወደምድር በመልቀቅ በሰው ልጅ እና በፍጡር ሁሉ ላይ ከባድ የሕልውና አደጋ መፍጠሩ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ በጊዜ ካልተከላከሉት እየቆየ ሲመጣ አደጋውም የዛኑ ያክል አስከፊ ነው የሚሆነው። በጀት መድበን፣ ጊዜ ቆርጠን፣ ሕዝብ አስተባብረን ከአካፋና ዶማ ጋር የተሰማራነውም ስለዚህ ሲባል ነው። በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ከየትኛውም የዓለም ሀገር ቀድማ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን እየከወነች ትገኛለች። በውጤቱም በርካታ ለውጦች እየታዩ መጥተዋል። የደን ሽፋናችንን ከማሳደግ፣ ጤነኛ እና ተስማሚ አካባቢን በመፍጠር፣ ለምርት ምቹ የሆነ ሥነ ምሕዳርን በመፍጠር፣ የአፈር መሸርሸርና ድርቅና በርሃማነትን በመከላከል በምርት እና ምርታማነት ላይ እምርታ ታይቷል።
ከዚህ በተጓዳኝ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከአየር ንብረት ለውጥ ቅድመ መከላከል ባለፈ ከልማት ጋር የሚያያዝም ነው። ስንተክል የበለጠ ምርታማ እየሆንን ነው። የሚተከሉት ችግኞች አድገው ዛፍ ሲሆኑ ለም መሬትን ከመሸርሸር በመጠበቅ፣ ወቅቱን በጠበቀ የአየር ንብረት የዝናብ ምጣኔን በማስተከላከል ግብርናው ዘርፍ ላይ የራሳቸው የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አላቸው። ግብርናው ሲያድግ ኢንዱስትሪው፣ ቴክኖሎጂው ይነቃቃል። ኢንዱስትሪው እና ቴክኖሎጂው ሲነቃቃ ሀገርና ሕዝብ ድህነትን ተረት አድርገው መነሳት ይችላሉ። በመሆኑም አረንጓዴ አሻራ ከነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ጋር ተሳስሮ የሚታይ ነው።
ሁሉም ነገር ተቻችሎ እና ተከባብሮ እንዲኖር በተፈጥሮ በኩል ታዟል። ካልተቻቻልን እና ካልተከባበርን አንዱ ለአንዱ ጥቅም መስጠቱ ቀርቶ ስጋት ወደመሆን ይቀየራል። ሰው ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን የመቻቻል ድንበር አፍርሶ በራሱ ላይ አደጋን ደቅኗል። ዛፍ በመቁረጥ፣ ደኖችን በመመንጠር፣ በርሀማነትን በማስፋፋት እንደዚሁም በመሰል ድርጊቱ ከተፈጥሮ ጋር ተኳርፏል። አሁን ላይ እንደ ሀገር ችግኝ የምንተክለው ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ለማውረድ ነው።
ሰው ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ካልኖረ ከዚህም በላይ ችግር ይደርስበታል። ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሄድንበት የሰባት ዓመታት የተከላ መርሀ ግብር እንደ ሀገር ሲያኮራን እንደ ዓለም ደግሞ በኩር አድርጎናል። ለጉዳዩ ትኩረት ያልሰጡ ሀገራት በእኛ ንቃት ነቅተው ተሳታፊ ወደመሆን መጥተዋል። በአሁኑ ሰዓት የአየር ንብረት ለውጥ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሲነሳ የኢትዮጵያ ስም የማይቀርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በራስ ተነሳሽነት በሌሎች ላይ በበጎ ተጽዕኖ እንደማድረስ የበረታ ጉልበት የለም።
አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ ተከላነት ባለፈ እንደ ሀገር የተቧደንበት፣ የተሳሰርንበት እና በጋራ ጉዳይ ላይ አንድነት ያሳየንበት በመሆን ከልማት ጎን ለጎን በመልካም ማኅበራዊ መስተጋብሩም የሚጠቀስ ነው። ባለፉት ሰባት የክረምት ዓመታት ለአንድ ዓላማ በአንድ ተሰልፈን ተክለናል፣ አጽድቀናል። ችግኞቻችን ዛፍ ሆነው ዛሬ ላይ ከአየር ንብረት ለውጥ ባለፈ ለምግብ ፍጆታነት በመዋል በብዙ መልኩ ግልጋሎት እየሰጡን ይገኛሉ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሰፊ ፐሮጀክት ነው። መነሻው ችግኝ እና ዛፍ ይሁን እንጂ በውስጡ ምርትና ምርታማነትንም የያዘ ነው። ለአብነት ያክል የከተማ ግብርናን፣ የሌማት ትሩፋትን፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክትን በውስጡ ያቀፈ ሰፊ ፕሮጀክት ነው። ስንተክል የአየር ለውጥ ስጋትን ከመከላከል እኩል አምርተን እየበላን ነው። ዘርተን እየቃምን ነው።
አንድነት ኃይል በመሆን በብዙ መስኮች ላይ ውጤት ሲያመጣ አይተናል። ትስስራችን በዘር እና በብሄር እስከላላ ድረስ በአብሮነት ቋጠሯችን ተዐምር መሥራት የሚቻለን ሕዝቦች ነን። ከሁሉም የቁልምጫ ስሞቻችን በላይ ‹አብሮነት› የሚል የሚያምር ስም አለን። በዚህ ስም ድንበር አልፈን፣ አጉራትን ዘለን ፊተኛ ሆነናል። ለጋራ በጋራ እስከተቧደንን ድረስ ማንም የማያቆመው ብርቱ የፈረስ ጉልበት የታደልን ነን..እናም ጉዞ ወደፊት እላለው።
ባልተገባ አካሄዳችን ምድር አኩርፋናለች፣ ለንቦጭዋን ጥላ በሸወረኒ ካደፈጠችብን ሰነባብታለች። አረንጓዴ አሻራ ደግሞ ከብዙ ትርጓሜው በላይ ምድርን ይቅርታ የምንጠይቅበት እጅ መንሻ ካሳችን ነው። ‹ምድር ሆይ እስከዛሬ ላደረስንብሽ በደልና ጥፋት ይቅር በይን› ስንል በፊቷ የምንወድቅበት ነው። ባዲስ ትውልድ ችግኝ ማሪን ስንል ልንታረቃት ግድ ይለናል።
ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ሁሉ በአንድነት የምንቆምበት ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉን። ሰላም እና ወንድማማችነትን አጥብቀን በምንፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። እርቅና ይቅርታ በሚያስፈልገን ሰሞን ላይ ነን። ይዘነው የመጣነው የትስስር ገመድ እንዳይላላ ሆኖ የጠበቀ ቢሆንም ስለት ያገኘው ቀን ግን ከመበጠስ ወደኋላ የማይል ነው። ስለቱ ዘረኝነት ነው። ስለቱ ግለኝነትን የሚሰብክ የፈሪሳውያን ልሳን ነው።
ሀገር ሰው ከሌላት..ሰው ሀገር ከሌለው ምንድናቸው? በዓለም ታሪክ አቻ የሌላቸው ሁለት ኃይሎች ቢኖሩ ‹ሰው እና ሀገር› ናቸው። በነዚህ ሁለት ቃላት ሕግ እና ስርዐት ተሰቅለዋል። ሀገር ለሰው ታቦቱ ነው፣ ሰው ለሀገር ጽላቱ። ታቦት እና ጽላት የሌሉበት መቅደስ ምንድነው ትርጉሙ? ከሁሉ በፊት የሚበጀንን ማወቅ አለብን ባይ ነኝ። እንደ እኔ አተያይ አሁን ላይ የሚበጀንን እያወቅን አይደለም። ሀገር እና ሰው የሌሉበትን ኦና ታሪክ ለመፍጠር በእልህ እና በብቻነት እየሮጥን እንገኛለን። ሩጫችን ለድል አይደለም..ወንድማማቾች እርስ በርስ የሚሽቀዳደሙበት የድል ሩጫ የለም።
አንድነታችን ነው ሀገር የሰጠን። ሀገራችንን በአንድነታችን መጠበቅ አለብን። በጋራ እንዳጸደቅናቸው እልፍ ችግኞች በጋራ የምንፈታቸው እልፍ ችግሮች አሉብን። ችግሮቻችንን ተከፋፍለን በእኔ በአንተ ከማሸሞንሞን ወጥተን በእኛነት ስሜት ልንፈታቸው ግድ በሚለን ጊዜ ላይ ነን። በሰባት ዓመታት ውስጥ ብዙ ቢሊዮን ችግኞችን ተክለን የለ? ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት ለምን አቃተን? ችግር ተቧድነው ከሄዱበት አቅመ ቢስ ነው። ተቧድነን ችግሮቻችንን ላይ በመዝመት አዲስ ታሪክ እንጻፍ እያልኩ ላብቃ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም