የኢኮኖሚያችንን ቁመና የፈተሸው ኮንፈረንስ

ዜና ሀተታ

ርእሰ ጉዳዩ “የሁሉም ሰው” ከሆኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱና ምናልባትም ቀዳሚው ነው። ይህ በሁሉም ሰው እኩል የሚፈለግና ሁሉንም ሰው እኩል የሚጠቅም፤ የሁሉም ሰው እስትንፋስ የሆነ መሠረታዊ ጉዳይ የፖለቲካውን ሳይቀር ሰማንያ በመቶ ድርሻን ስለመያዙ ቅርበት ያላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ለሀገር ወደ ፊት መራመድ የፊት መሪነት ሚናው ተኪ የለውም። ለሀገራትና ሕዝቦች ደረጃ ይውጣ ቢባል በእሱ እንጂ በሌላ አይደለም። ባጭሩ፣ ነገሩ ሁሉ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” እንዲሉ ነውና የዛሬው ርእሰ ጉዳያችን ኢኮኖሚ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የመልማትና የመበልጸግ ፍላጎትም እንዳለ፤ መንግሥት የኢትዮጵያን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሊያስተካክሉ የሚችሉ ርምጃዎች እየወሰደና አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው። ኢትዮጵያ በማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው ከአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ስለመምጣቷ፤ ማሻሻያው ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን እያስገኘ ስለመሆኑ፤ የዋጋ ግሽበትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ስለመቻሉ፤ በሂደትም ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው። ይህ በእሳቸው የተከፈተው የሁለት ቀን (ሀምሌ 11 – 12/2017 ዓ•ም) 22ኛው ዓለም አቀፍና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ማእከል ያደረገ ኮንፈረንስ (22nd International Conference on the Ethiopian Economy) በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ፣ ከሀገርም አልፈው አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን የዳሰሱ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የቀረቡበትና ሞቅ ያለ የታዳሚዎች ተሳትፎ የታየበት ሆኖ ተጠናቅቋል።

ከዚሁ፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የልማት ኃይሎች፤ ሀገር፣ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች (ኤክስፐርቶች)፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙበትና ጥልቅ ውይይት ከተደረገበት ኮንፈረንስ መጠናቀቅ በኋላ ከአዲስ ዘመን ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንዳሉት፤ ኮንፈረንሱ ዓመታዊና ዓለም አቀፍ እንደ መሆኑ መጠን በርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች ተገኝተዋል፤ ከ60 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችም ቀርበዋል።

“ኮንፈረንሱ እንደፈለጋችሁት ተጠናቋል፤ ወይስ የቀረው ነገር አለ?” ላልናቸውም፣ ምንም የጎደለው ነገር የለም። በምንፈልገው ሁኔታ ነው የተጠናቀቀው። ከዚህ በፊት በመጀመሪያው ቀን ደመቅ ብሎ በሁለተኛው ቀን ብዙ ሰው አይገኝም ነበር፤ ተሳታፊዎች ያቋርጣሉ። ዘንድሮ ግን ለየት ብሎ ነው ያገኘነው። በሁለቱም ቀናት በሁሉም አዳራሾች የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ እንጂ ቀንሶ አልተገኘም ሲሉ ገልፀውልናል።

የታዳሚዎች ተሳትፎ ለየት ያለ ሆኖ መገኘቱን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ጣሰው በቀረቡት በእያንዳንዳቸው የጥናት ወረቀቶች ላይ ተገቢው ውይይትና ክርክር መደረጉን፤ የተመራማሪዎች ዝግጅትና አቀራረብ የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ፤ ከውይይቶችና ክርክሮቹም ተገቢ የሆኑ ግብዓቶች መገኘታቸውን ይገልፃሉ።

ኢኮኖሚ ባለ ድርሻ አካላቱ በርካቶች መሆናቸውን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ፤ የዚህችን ሀገር ኢኮኖሚ ወደ ፊት ለማራመድ የሚመለከታቸው ሁሉ ሌት ተቀን መሥራት እንዳለባቸው፤ የመንግሥት አካላትም ከፖሊሲዎች ጀምሮ መሻሻል ያለባቸውን በማሻሻልና ተገቢውን አመራር በመስጠት ለኢኮኖሚው እድገት የበኩላቸውን መሥራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

የቀረቡትን የጥናትና ምርምር ሥራዎች በተመለከተም ሁሉም የጥናትና ምርምር ሥራዎች በአንድ ተጠርዘው (ፕሮሲዲንግስ) ለመንግሥት ሥራ ሃላፊዎችና ለሚመለከታቸው ሁሉ እንደሚሰራጩ የተናገሩ ፕሬዚዳንቱ፤ በየተቋማት ቤተመጻሕፍትም እንዲገኙና ለምርምር ሥራዎች እንዲውሉ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል።

ሌላው ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ቆይታ ያደረጉት ከወደ አሜሪካ ሶስት አባላት ያሉትን ቡድን በመምራት የመጡት፤ ከንቁ ተሳታፊነትም በላይ ለየት ያለና በሀገራችን ብዙም ያልተሞከረ ጥናትን ያቀረቡት ከአሜሪካው ሳውዘርን ኮኔክቲከት ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ይልማ ገብረማሪያም ናቸው።

ሙሉ ወጪው በዩኒቨርሲቲው ተሸፍኖ የመጣው ቡድን መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ይልማ እንዳሉት፤ የቡድናቸው አባላት ኮንፈረንሱ ላይ በመገኘታቸው ደስተኞች ሲሆኑ፤ በኮንፈረንሱ ልዩ ባህርያትና አቀራረብም ተደምመዋል።

እዚያ እኛ ጋር (አሜሪካ ማለታቸው ነው) የጥናት ወረቀት ሲቀርብ 10 እና 20፤ ምናልባትም 30 ሰው ነው ሊገኝ የሚችለው። እኛ ስናቀርብ 10 ሰው እንኳን ከተገኘልን ደስታችን ሌላ ነው። እዚህ ይህ ሁሉ ሰው የጥናት ወረቀቶቹን ሲታደምና በሚገባ ሲከታተል፤ ሲተችና ያለ ገደብ አስተያየቱን ሲሰጥ ማየት በጣም በጣም ደስ የሚልና የሚገርምም ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ይልማ፤ እንደዚህ አይነት የአካዳሚክስ ባህል ምንም ሳይዛነፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባሉ።

የቀረቡትን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በተመለከተም በተገቢ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩና ሊተኮርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች እንደሆኑ፤ የታዳሚዎች ተሳትፎና የኮንፈረንሱ አዘጋጆች (ማህበሩ) ጥረትም ሊደነቅ እንደሚገባ አመልክተው፤ በጣም የተደሰቱባቸውና ከፍተኛ እውቀትም ያገኙባቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። የሀገራችን ኢኮኖሚ የገጠሙት ፈተናዎችም ሊቀረፉ እንደሚገቡ ይመክራሉ።

ቀጥሎ መሆን ያለበትንም “እንግዲህ የአካዳሚያዊ ተግባርና ሃላፊነት እዚህ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ ያለው የፖለቲካው መልካም ፈቃደኝነት ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው፣ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የቀረበን ነገር ወዲያውኑ ወደ መሬት ማውረድ ቀላል ላይሆን ይችላል። ያ እንዳለ ሆኖ በሂደት እነዚህ የምርምር ሥራዎች ወደ መሬት ወርደው ውጤት ማምጣት አለባቸው። ለእዚህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያም፤ እንደ አፍሪካም መንግሥታት ተነሳሽነቱንና የመፈፀምና ማስፈፀም ሃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል።” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

ሌሎች ማህበራትም ሆኑ ሙያ ተኮር ተቋማት የእዚህን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽንን አይነት እንቅስቃሴ በማድረግ ሀገርን ወደ ፊት የማስኬድ ሥራ ላይ በርትተው ይሠሩ ዘንድም አሳስበዋል። ይህ የዘንድሮው ኮንፈረንስ በሁለቱም ፆታዎች በርካታ ወጣት ተመራማሪዎች ወደ መድረክ የመጡበት በመሆኑ ከኮንፈረንሱ ታዳሚያን ለአዘጋጆቹ ምስጋና የቀረበ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ወደ ፊት ተስፋ ያላት አሀገር መሆኗም ተነግሯል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You