‹‹በሪፎርሙ 40 ሺ 236 የሕብረት ሥራ ማኅበራት አመራሮች እንዲቀየሩ ተደርጓል›› – አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ

አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር

የሀገራችን የሕብረት ሥራ ማኅበራት ታሪክ ሲጤን በ1950ዎቹ የተጀመረ ነው። በተለያየ ጊዜ የተለያየ መዋቅሮችንና ቅርጾችን እየያዘ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። ይሁን እንጂ የሕብረት ሥራ ማኅበራት የዕድሚያቸውን ያህል ዘምነውና አድገው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወቱት ሚና የሚጠበቀውን ያህል ሊሆን አልቻለም። የዝግጀት ክፍላችን የሕብረት ሥራ ኮሚሽን ማኅበራትን ሪፎርም በማድረግ የሚጠበቅባቸው ሚና እንዲወጡ ምን እየሠራ ነው? ስለምንስ በዕድሚያቸው ልክ መለወጥ አልቻሉም?፤ የተጀመረው ሪፎርም ምን ለውጥ ያመጣል? በሚሉና መሰል ነጥቦች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ከአቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ጋር ቆይታ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ሕብረት ሥራ ማኅበራትን ሪፎርም ከማድረግ አንጻር እስካሁን ምን ሠርቷል?

አቶ ሺሰማ፡– በ2016 በጀት ዓመት ላይ ይፋ የተደረገው የሕብረት ሥራ ማኅበራት ዕድገትና ተወዳዳሪነት ማሻሻያ ሪፎርም ሥራ ሲሆን ሪፎርሙ ሁለቱንም ሥራዎች ጎን ለጎን ለማስኬድ ጥረት ተደርጓል።

ዋና ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ የነበረው የተደራጁ ማኅበራትን መስመር እንዲይዙ እና ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ሌላው ከቁጠባ፣ ከብድር ከሥርጭት ላይ ተጠቃሚ ከመሆን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

ማኅበራት ያሉበትን ሁኔታ በመፈተሽ ምን ጉድለት አላቸው? በሚል የሕግ፣ የመመሪያ ድጋፍ የሚፈልግ የነበረ ሲሆን ለአሰራር ማነቆ የሚሆኑ ነገሮች መኖራቸውን በመፈተሽ ጉድለት ሲገኝ የማስተካከል ሥራ መሥራት ነው። በዚህ አግባብ ወደ 16 ሺ መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማኅበራትንና 100 ዩኒየኖች የማሳተፍ እቅድ ነበር። በሪፎርም ሥራዎች መረጃ የማጥራት ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን የማኅበራት ቁጥር ምን ያህል ነው የሚለውን ለማጥራት የመፈተሽ ሥራ ተከናውኗል። ይህን ከሠራን በኋላ ለድጋፍ እንዲመች በደረጃ የመመደብ ሥራ ተሠርቷል።

ማኅበራትን እውቅና የመስጠትና መዋሃድ የሚፈልጉ ማኅበራት ካሉም እንዲዋሃዱ፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመፍረስ ፍላጎት ያላቸው እንዲፈርሱ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ እንደ ሀገር በርካታ ተቋማት ራሳቸውን መልሶ በማደራጀት ወደ ሥራ ገብተዋልና ኮሚሽኑ ሕብረት ሥራ ማሕበራትን ሪፎርም ከማድረግ አኳያ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በሂደቱ ኮሚሽኑን ምን ፈተና ገጠመው?

አቶ ሺሰማ፡- የኮሚሽኑ የሪፎርም ሥራ ልክ እንደ ሌሎች ተቋማት አይደለም። የሚለይበትም ምክንያት በርካታ ተቋማት የሚያካሂዱት ውስጣዊ ሪፎርም ነው። የኮሚሽኑ ግን ራሳቸው ተቋም የሆኑ ሕብረት ሥራ ማሕበራት፣ የራሳቸው ሥራ አመራር ቦርድ፣ ሥራ አስኪያጅ፣ ሠራተኛ ያላቸውን ማኅበራት ላይ የሚሠራ ነው። ስለዚህ ማኅበራቱ በለውጥ አስፈላጊነት ላይ ማመን አለባቸው። ሪፎርሙ ለምን አስፈለገ ? በሚለው ጉዳይ ላይ መላ መዋቅሩ መተማመን ላይ መድረስ አለበት። ሠራተኛው፣ ሥራ አመራና ሥራ አስኪያጁ ቀጥሎም አባላት መቀበል አለባቸው። የመንግሥት ተቋም ከሆነ ሪፎርም ውስጥ እንዲገባ ከተፈለገ ድጋፍ ስለሚደረግለት የመሥራት ግዴታ አለበት። በኮሚሽኑ ግን ሌላኛው አካል ጋር በየደረጃው መነጋገር፤ መግባባት ያስፈልጋል። ስለዚህ አንዱ ሪፎርሙ ላይ የተቀመጠው አቅጣጫ መግባባት የሚል ነው። በሌሎች ሀገሮች ያለው ተሞክሮም ይህንኑ የሚያሳይ ነው።

በየትኛውም መመዘኛ ገቢያቸው ከፍተኛ የሆኑ የሕብረት ሥራ ማኅበራት በዓመታዊ የሀገር ገቢ (ጂዲፒ) በነፍስ ወከፍ ገቢ በመገንባት ትልቅ ደረጃ ላይ በደረሱ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚው ተዋናይ ናቸው። በስካንዲቪያን ሀገራት ሲታይ 70 እና 90 በመቶ የሚሸፍኑባቸው ሁኔታ አለ። የሚሠሩት ተግባር ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ከአሜሪካ ጀምሮ እስከ ምስራቁ ድረስ በሁሉም ዘርፍ ሕብረት ሥራ ማኅበራት እንደ አንድ ተዋናይ ይታያሉ። በሀገራችን መንግሥት አንዱ የኢኮኖሚ ተዋናይ ነው። የግሉ ዘርፍ ደግሞ መሪ እንዲሆን ይጠበቃል።

ቀጥሎም የሕዝብ አቅም ነው። ሕዝቡ ጋር በተናጠል ያለው አቅም ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። ስለዚህ መደራጀት መሰብሰብ አለበት፤ ይህ በሌላ መንገድ መደመር የሚለው እሳቤ ነው።

ሰብሰብ ብለው በመሥራታቸው ለምሳሌ የኬንያ ሕብረት ሥራ ማኅበራት የጂዲፒውን 45 በመቶ በመሸፈን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ሲታይ ሕብረት ሥራ ማኅበራት መደራጀት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻው አዋጅ የሚባለው አዋጅ ቁጥር 985/2009 ነው። አዋጁ ሲወጣ የነበረ የኢኮኖሚ ሁኔታ አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ቀጣናዊ ሁኔታ፣ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ለውጦች አሉ። ማኅበራት በማምረቱ፣ በአገልግሎቱ፣ በንግዱ፣ እንቅስቃሴ ውስጥ የሁኔታ ለውጥ ካለ መለወጥ አለባቸው። የንግዱ አቅጣጫ ይቀየራል።

በዋናነት ከልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ኮሚሽኑ በየጊዜው የሰበሰባቸው ሪፖርቶች፣ ተጨባጭ ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ የሚሉ ጉዳዮች የቱ ዘንድ መሰረታዊ ጉድለት አለ የሚለው በጥናቱ የተለየ ሲሆን ለሪፎርሙ መነሻ ችግሮች ናቸው።

የሪፎርም አስፈላጊነት ስለታመነበት ሪፎርሙን የሚመራ በግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የሚመራ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ‹‹ስትሪንግ›› ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ ነው። ከሕብረት ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው አደረጃጀቶች ተፈጥረው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ውስጥ የጥናት ቡድን ዝርዝር ተገኝቶ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ላይ አባላትን፣ አመራሮችን፣ ሠራተኞችን፣ ሥራ አስኪያጆችን፣ ተጠቃሚዎችን አወያይ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚላቸው ችግሮችን ለይቷል።

ሪፎርሙ የሚያስፈልገው የትኛው ነው? ለምንድን ነው? የሪፎርም አጀንዳዎቹ ምንድን ናቸው? የሚሉት ነጥቦች ላይ ምላሽ ለመስጠት የዳሰሳ ጥናት ተሠርቷል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ላይ የሌሎች የልማት አጋሮች ዕይታ ምንድን ነው የሚለው አምስት ነገሮች ላይ ሪፎርም ማድረግ እንዳለብን ተለይቷል።

አንደኛው አደረጃጀታቸው ምን ይሁን? ሲሆን ይህም ሲባል መሰረታዊ ማኅበር አይነት አላቸው፤ የትኛው ላይ እናተኩር? ሸማች ላይ? ቁጠባ ብድር ላይ? ግብርና ነክ በሆኑት ላይ እናተኩር? የሚለው ግብርና ላይ፣ ሸማች፣ ቁጠባና ብድር ላይ ብናተኩር የሚል ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተሠራ ነው።

ሁለተኛው መሰረታዊ ሕብረት ሥራ፣ ዩኒየኖች፣ ፌደሬሽኖች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማየት ተሞክሯል። አደረጃጀት ላይ በተመሰረተ ችግሮች ናቸው። አንዳንዱ ምን የተለየ ነገር ሊሠራ ነው። እዚህ አደረጃጀቶች አንዱ ከአንዱ በምን ሥራ እንደሚለይ ማየት ነው። ሌላው ሕብረት ሥራ ማኅበራት እንዴት ይመራሉ? የሚለውን ማጥናት እና መለየት ነው።

ሶስተኛው ልክ ሌሎች የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የሙያ ማኅበር እንደሚባለው የማኅበርነት ባህሪ አላቸው። እነዚህ ማኅበራት በንግድና በአገልግሎቱ መስመርም ቢዝነስ እንዲሠሩ ይጠበቃል። ስለዚህ ሁለት አይነት ባሕሪ ያላቸውን አጣጥሞ ለማስኬድ የተለየ አመራር ይፈልጋል። አንዱ ሪፎርም የሚፈልገው ዘርፍ ከአመራር ጋር የተየያዘ ነው። አደረጃት፤ አመራር፤ የፋይናንስ ሥርዓታቸውን ሲሆን፣ ለመበደር ነው፤ ለመመለስ ብቁ ነው፤ ከአባላት መዋጮ ውጭ ታምኖ ማኅበሩ አቅም ቢኖረው ይሻላል ብለው ያላቸው ካፒታል ያሰባስባሉ ወይ ተብሎ ሲታይ ከፋይናንስ አቅም፣ አስተዳደር፣ የራሱ ችግሮች እንዳሉ ተለይቷል።

አራተኛው ለማኅበራቱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የሕግ ማሕቀፍ አለ ወይ የሚለው ሲሆን አዋጁ፣ ደንቡ፣ መመሪያው ያሉ ማንዋሎች እንዲኖሩ ያስፈልጋል። ማኅበራት የራሳቸው የሆነ ባህሪ ስላላቸው ለዚያ የሚመች ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችል ነው ወይ የሚለው መፈተሽ አለበት። ከዚህ በፊት ድጎማን መሰረት አድርጎ የተቆላለፉ የአሠራር ሥርዓቶች ከታለመለት ዓላማ ውጭ እንዳይሄድ አሳሪ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው፤ የሚሉት ተፈትሸው የማስተካከል ሥራ ከአዋጁ ጀምሮ እየተሠራበት ነው። የመጨረሻውና አምስተኛው ነጥብ የተወዳዳሪነት አስተሳሰብ አለ ወይ፤ ትናንት አብዛኛው የተደራጀው መንግሥት የሚሰጠው ነገር ለእያንዳንዱ ነገር ማድረስ ስለማይችል በተቻለ መጠን አንዲሠራጭ ተብሎ የተደራጁ ናቸው።

ማኅበራትን ለማጥራት መረጃቸው፣ ካፒታላቸውና የአባላት ቁጥራቸው ታይቶ በደረጃ ተለይተው የምስክር ወረቀት ይሰጣቸው በሚል ሀሳብ ሲፈተሹ ማን እንዳደራጃቸው የማይታወቁ ማኅበራት ተገኝተዋል።

ስለዚህ ቁጥራቸውን የማጥራት እና በሂደቱ የተገኙ ውጤቶች ምን እንደሆኑ ለመሥራት በሁለት ተከፍሎ እየተሠራ ነው። አንዱ ፈጣን ለውጥ አምጭ ሲሆን አዲሱን ስትራቴጂ ከመጀመራችን በፊት ባለው የሰው ኃይል አቅም ልንሠራቸው የምንችላቸው ወደ ለውጥ የሚያስገቡ ሥራዎችን የመለየት ሥራ ጀምረናል። በሪፎርም ሥራው መረጃ የማጥራት ሥራ ተሠርቶ 36 ሺ 292 መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማኅበራት እና ወደ 19 ዩኒየኖች ተሰርዘዋል። ስለዚህ ከዚህ በፊት ይህን ያህል ቁጥር ብሎ የሚነገረው ስም ብቻ ነበር።

የተሰረዙበት ምክያትም ለምሳሌ አምስት ሺህ 400 ያህል ሕጋዊ ሥርዓት ተከትለው የሕብረት ሥራ ማኅበራት በራሳቸው ፈርሰው የምስክር ወረቀት መልሰው ነው። ማኅበር ሲፈርስ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ተበድሮ፣ አበድሮ፣ ዱቤ ገዝቶ፣ የሰበሰበው የሕዝብ ገንዘብ በተወሰኑ ሰዎች አካውንት ውስጥ ኖሮ ሊሆን ይችላል። ባይገዛ፣ ባይሸምትና ባያበድር ቦታ ቦታ መስጠት ያስፈልጋል። እነዚህ የተጠቀሱ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ሥርዓቱን ተከትለው የፈረሱ የምስክር ወረቀታቸውን መልሰው በአግባቡ እንዲፈርሱ ተደርጓል። የቀሩት ሁለት ሺ 680 ያህሉ ደግሞ በመዋሃድ የፈረሱ ናቸው። ለምሳሌ 10 ማኅበር ሆነው አንድ ማኅበር ሲመሰርቱ ዘጠኙ ይፈርሳሉ። ወይም አራት ሆነው አንድ ማኅበር ሲመሰርቱ ሶስቱ ይፈርሳሉ ማለት ነው።

በሪፎርም ሥራው 28 ሺ 212 መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማኅበራት በሰነድም በአድራሻም አልተገኙም። ጥሪ ተደርጎ እንዲቀርቡ ቢጠየቁም አልተገኙም። ስለዚህ ይህ የሚገመተው አንድ ጊዜ ለሥራ እድል ፈጠራ ለማገዝ ተብሎ እንዲደራጁ የተደረጉ ነበሩ። አልፎ አልፎም ሪፖርት ለመቀበል የሀሰት ሪፖርቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

ነገር ግን በዋናነት ለተዘዋዋሪ ፈንድ ተብሎ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በነበረ ሂደት የመጣ ነው። ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ማኅበራት እንድንቀንስ ሪፎርሙ እድል ሰጥቶናል።

አዲስ ዘመን፡- በሪፎርሙ ተጣርቶ የትክክለኛ ማኅበራት ቁጥር ስንት ሆነ?

አቶ ሺሰማ፡- አሁን የቀሩት ማኅበራት 89 ሺህ 164 የሕብረት ሥራ ማሕበራት ናቸው። እነዚህም በዐይነት ሲጠቀሱ፤ የግብርና፣ ግብርና ነክ ያልሆኑ፣ ገንዘብና ቁጠባ፣ የሕብረት ሥራ ማሕበራት፣ የሸማቾች፣ የእደጥበብ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የማዕድን ዘርፍ እና ሌሎችም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ።

ሪፎርም ለመሥራት በተጠናው ጥናት ብዙ ታሪኮች አሉ። ለምሳሌ ትልቅ አብዮት ያደረጉት ጃፓን በ1975 ስድስት ሚሊዮን አካባቢ አርሶ አደር ነበራት። በተጨማሪም ሕንድ በ2021 ሕብረት ሥራ ማኅበራትን የሚያጠናክር በ‹‹ትብብር ወደ ብልጽግና›› በሚል መሪ ሀሳብ የሕብረት ሥራ ስትራቴጂ በመንደፍ ውጤታማ ሥራ ሠርታለች።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ሕብረት ሥራ ማኅበራት ምን ያህል ካፒታል ያንቀሳቅሳሉ? በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው? ኬንያ ከኢትዮጵያ ልምድ ወስዳ ቀድማለች ይባላልና ወደ ኋላ የቀረንበት ምንድን ነው?

አቶ ሺሰማ፡- አንዱ የሪፎርሙ መነሻ የቁጥራቸውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ሚናቸውን እየተወጡ አይደለም። ኬንያውያን ልምድ ከኢትዮጵያ ወስደዋል የሚባለው በሁለት መልኩ ማየት ያስፈልጋል። እነሱ በአራት ምዕራፍ የሕብረት ሥራ ንቅናቄ አድርገዋል። እኛን የበለጡን እና ቀድመውን የሄዱበት የሚለው ሲታይ በድህረ ነጻነታቸው መጥተው አርዳይታ ሰልጥነው ወደራሳቸው ለማላመድ ልምድ ወስደዋል። ይህም በቅኝ ግዛት ላይ ተመስርቶ የነበረው ነገር ወደ ዜጋው ለማምጣት ጠይቀው ድጋፍ ፈልገው ሰልጥነው ሄደዋል። ቀድመው ድጎማውን ሳይሆን ተወዳዳሪ አድርጎ ሕብረት ሥራ ማኅበራትን በመገንባት ረገድ ቀድመው ተለውጠዋል።

ባለፈው አዲስ አበባ በነበረው ዓለም አቀፍ መድረክ ኬንያውያን ባቀረቡት የሕብረት ሥራ ተሞክሮ ሲታይ ከኢትዮጵያ ጋር ፈጽሞ ሊነጻጸጸር አይችልም። ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በዚህ ዓመት ለብድር አቅርበዋል። ይህ ከእኛ ጋር ሲነጻጸር አይገናኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ሥራ አልተጀመረም። ያለን ቁጥር ብቻ ነው። ስለዚህ 18 ሺህ 259 ቁጠባና ብድር የሕብረት ሥራ ማሕበራት ሰብሰብ ብለው አቅም ቢፈጥሩና ታማኝና ተደራሽ ሆነው ቢሠሩ መነሳት ይቻላል።

ኬንያ ላይ ታክሲው ሁሉ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ዩኒየን (SACO) የሚል ነው። የእኛ ሀገር የሁሉም የሕብረት ሥራ ማሕበራት ካፒታል ተደምሮ 100 ቢሊዮን ብር ነው። ይህም ማለት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያልሞላ ማለት ነው። ይህ ማለት ገና ብዙ መሥራት አለብን። በተለይ ቁጠባ ላይ ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡

ማይከሮ ፋይናንስ የሚባሉት በዚህ ዓመት ስንት ሰው ብድር ሰጥተዋል ብለን ወደ ስሌት ብናመጣው ከኬንያ ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለው። በበጀት ዓመቱ 900 ሺህ ብር ተበድረዋል።

ሪፎርም የሚያስፈልገን ቁጠባ አስፈላጊ መሆኑንና አስፈላጊ የሚሆነው ስለተረፈን፤ በቂ ሀብት ስላለን ብቻ አይደለም። ከእኛ የገቢ አቅም የባሰ ያላቸው ሀገራት ቁጠባ ላይ ግን በጣም ጠንካራ ባሕል አላቸው። ቁጠባ ሲኖር ገበያ ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጥ ያደርጋል።

እኛ ካለን ሀገራዊ የልማት አቅጣጫ አንጻር አሁን ላይ ያሉት የትብብር ማሕቀፎች ለሕብረት ሥራ ማኅበራት የሚመቹ ናቸው። በሌማት ትሩፋት የሚቀርቡ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ መቅረብ አለባቸው። በሕብረት ሥራ ማሕበራትና በአባላቱ መካከል መተማመን ሊኖር ይገባል።

ከዓመት በፊት ሕብረት ሥራ ማኅበራት 28 ሚሊዮን አባላት ነበሩት። እነዚህ አባላት አንድ ሺህ ብር ቢያወጡ ስንት ነው። 28 ቢሊዮን ብር ይሆናል። በዚህ እሳቤ ድሬዳዋና አካባቢው ላይ ሙከራ ሲደረግ አንድ ሰው የገዛው ትንሹ እጣ አምስት ሺ ትልቁ 100 ሺ ነው። ይህ ተግባር በብዙ ሀገሮች ሕንድ ጨምሮ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ንቅናቄ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- የሕብረት ሥራ ዕድገትና አቅም ውስንነት ሲታይ በተማረ የሰው ኃይል አለመመራታቸው የሚል ሀሳብ ይነሳልና በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ሺሰማ፡- ይህ ጥያቄ ከአመራር፣ ከአደረጃጀት፣ ፋይናንስ፣ የሕግ ማሕቀፎች ጋር የሚመደብ ነው። ባልተማሩ ሰዎች የሚለው በጥቅሉ እንደምክንያት አይወሰድም። የሆነ ወቅት ይህ ተገቢ የሆነበት ጊዜ ነበር። አመራር የሚመረጠው በአካባቢው ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ ነው። የተመረጡት አመራሮች በወቅቱ የተማሩም ይሁኑ አይሁኑ ተገቢ ነበር።

አዲስ አበባ ላይ የሕዝብ ሱቅ የሚባለው ባለቤት የለውም ነበር። በማን እንደተቋቋመ፤ በግል ይሁን በሕብረት ሥራ ማን ምን አውጥቷል የሚለውን መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ታሪካቸው ሲታይ 1968 አካበቢ የተደራጁ ናቸው። ስለዚህ ወደሸማቾች ይዙሩ ተብሎ እየተመሩ ያሉት በማን ነው የሚለው ሲጠና የተገኘው አብዛኛዎቹ የተከበሩ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጡረታ የተገለሉ፣ ትልልቅና የተማሩ ሰዎች ጭምር ናቸው። ስለዚህ በተማሩ ሰዎች ስለማይመሩ የሚለው በሚዛኑ መታየት አለበት።

የአመራር ችግር አለ። የተማረ ሰው በአማካሪነትም በተቀጣሪነትም መኖር አለበት። ዘመኑ የውድድር ዘመን ነው። የኢንዱስትሪው ምርት ወደ አርሶአደሩ መድረስ አለበት። ነገር ግን ቢዝነስ ውስብስብ ሥራ ነው። የፋይናንስ ሥርዓቱም ቴክኖሎጂ ተኮር ነው። ይህን ከመረዳት አንጻር ችግሮች እንዳይኖሩ አንዱ የለውጥ አጀንዳ እንዲሆን ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- የሕብረት ሥራ ማኅበራት የለውጥ ፍላጎት አላቸው? ካላቸው ፍላጎታቸው ምን ይመስላል? የኦዲት ሽፋኑስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሺሰማ፡- አንድ ደረጃ የሚቀር ሥራ አለ ብለን እናምናለን። እስካሁን በሄድንበት የሪፎርም ሥራ ግን ያገኘነው ግብረ መልስ እና ያለው ፍላጎት ሲታይ ዘግይታችኋል የሚሉ የማኅበራት አመራሮች አሉ። በርካታ ትብብሮች የተፈጠሩ ቢሆንም የሕዝብን ተሳትፎ የሚጠይቁ ናቸው።

ሪፎርሙ በተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በውህደት የተፈጠሩ ዓላማ ይዘው እዚህ እንደርሳለን ያሉ በርካታ የሕብረት ሥራ ማኅበራት አሉ። ቆላማና አርብቶ አደርና አርሶ አደር ያለባቸው አካባቢዎች፤ ከተማና ሌሎች አካባቢዎች እኩል አይደለም። ነገር ግን በጣም ጠቃሚ ምላሾች አሉ።

የኦዲት ሽፋን ዝቅተኛ ነው ይባላል። የኦዲት ሽፋኑ ዝቅተኛ ቢሆንም እንኳ መመዘኛው ትከክል አልነበረም። የመሰረታዊ ማኅበራት አባላት ቁጥር ቀንሷል። የቀነሰበትም ምክንያት 36 ሺህ ማኅበር በመቀነሱ ነው። ይህ ሲባል ግን አባል አልተጨመረም ማለት አይደለም። በአዲስ መንፈስ በአዲስ ጉልበት ወደ ሥራ የገቡ አሉ።

ከዚህ በፊት ኦዲት የማድረግ ሽፋኑ 18 በመቶ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 43 በመቶ አድጓል። የኦዲት ተደራሽነት ተሻሽሏል። ኦዲት ካልተደረገ ጉድለቱ አይገኝም። እየዘረፈ ይቀጥላል ማለት ነው። ኦዲት መደረጉ እንደውጤት መታየት አለበት። ጉድለቱን ለማስመለስ ሪፎርሙ አስተዋጽኦ አለው። የኦዲት ጉድለቱ የሚመለሰው በአብዛኛው በማኅበራዊ ጫና ነው።

28 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የአባላት ቁጥር ወደ 25 ሚሊዮን 947 ሺህ 337 ዝቅ ብሏል። ይህ ቁጥር ቀንሶ ግን ካፒታል ጨምሯል። ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ እንዳለ ማሳያ ነው። ለምሳሌ በ2015 ዓ.ም የነበረው 38 ቢሊዮን 294 ሺህ 793 ከ90 ሳንቲም ነበር። በ2017 ዓ.ም መጨረሻ 55 ቢሊዮን 553 ሚሊዮን 486 ሺህ 161 ብር ሆኗል። የአባላት ቁጥር በሁለት ሚሊዮን ቢቀንስም የገቡም አሉ። በቁጠባ በ2015 ዓ.ም 35 ቢሊዮን 819 ሚሊዮን 826 ሺህ 636 ብር ከነበረበት ወደ 56 ቢሊዮን 860 ሚሊዮን 28 ሺህ 420 ብር ደርሷል። ሥራው ሲጤን ገና አቧራ ጠረጋ ላይ ነን፤ ነገር ግን የሚታየው ለውጥ ከፍተኛ ነው። የሕብረት ሥራ ማኅበራት ተሳትፎና መጠንም መሻሻል አሳይቷል። ግን ሚናቸው ገና ማደግ አለበት። ግብይት ላይ የሚሳተፉ ማኅበራት ቁጥር ወደ ስምንት ሺህ አድጓል። አሁን ላይ ሰባት ሺህ 90 ገደማ ደርሷል።

አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሕብረት ሥራ ማኅበራት ኦዲት ተደረጉ? በምን ያህሉስ ጉድለት ተገኘባቸው?

አቶ ሺሰማ፡- ሶስት ሺህ 861 ማኅበራት ኦዲት ተደርገው በተወሰኑት ላይ 609 ሚሊዮን ብር ጉድለት ተገኝቷል። ከዚህም 447 ሚሊዮን ብር ማስመለስ ተችሏል። ይህ ትልቅ ውጤት ነው። በየዓመቱ ይህንና መሰል ሪፖርት አልነበረም። በዩኒየኖች ደረጃም 144 ሚሊዮን ብር፤ በአንድ ፌዴሬሽን 28 ሚሊዮን ብር የጎደለ አለ። ፌዴሬሽኖች ላይ ገንዘብ ሊጎል የሚችልበት ምክንያት ውስን መሆን አለበት። በዩኒየኖች ላይም 269 ሚሊዮን 259 ሺህ 956 ብር ተመልሷል። ጠቅለል ሲል ግን ዘርፉ ውስብስብ ነው። የአባላት ተጠቃሚነት ጨምሯል። ለአብነት ያልተከፋፈለ 25 ሚሊዮን 154 ሺህ 717 ብር ትርፍ እንዲከፋፈል ታቅዶ 96 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ተከፋፍሏል።

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የኦዲት ሥራ የሚያከናውን ቢሆንም የገቢዎች ሚኒስቴር በቤንች ማጂ የአርሶ አደሮች የጫካ ቡና አምራች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ላይ የምርመራ ኦዲት በማድረግ የገቢ ግብር ባለመክፈሉ ቅጣት ሲጥል ከሥራ ውጭ ሆኖ ችግር ውስጥ እንደገባ ይታወቃልና እንዲህ አይነት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ሺሰማ፡- ይህ እንዳይከሰት በመጀመሪያ አመራሩን ማብቃት ነው። የሕብረት ሥራ ማኅበራት የሚጠይቀውን ውስብስብ የሆነ የአመራር ሥርዓት የተገነዘበ መሆን አለበት። በተጠቀሰው የቡና አምራች ዩኒየን የተፈጠረው ችግር የገቢዎች አይደለም። ከግብር ነጻ ነህ ማለትና ከገቢ ግብር ነጻ ነህ ማለት ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የገቢ ግብር ሕጉን አውቀው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ዩኒየኑን ችግር ውስጥ የከተቱ ሰዎች አሉ፤ ሰዎችን ትተን ተቋሙን ምን እናድርግ ወደሚለው ልንገባ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ስህተት የለውም።

አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ትልልቅ የቡና አምራች የሕብረት ሥራ ዩኒየኖች አሉና ዩኒየኖች ለቡና ላኪዎች በሚያቀርቡበት ወቅት በክፍያ ላይ መጓተትና መጉላላት እንደሚገጥማቸው ቅሬታ ይነሳል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲፈታ ለማድረግ ምን ታስቧል?

አቶ ሺሰማ፡– ይህም በልኩ መታየት አለበት። ለምሳሌ ከማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፊት የነበረው ሁኔታ ባለኝ መረዳት አንድ ትልቅ ሊወራለት የሚገባ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያመጣው ጥቅምና ለውጥ ሕገ ወጥነትን እና ኮንትሮባድን ማዳከሙ ነው። እንደፈለጉ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ መስመር እንዲይዙ ከቻሉ በሕጋዊ መንገድ እንዲነግዱ ማድረጉ ነው። በ56 ብር እና በ120 ብር የነበረው የዶላር ምንዛሬ ልዩነት ማኅበራት የራሳቸው ደካማ ጎን ቢኖራቸውም እንኳን የሕዝብ ስለሆኑ ብዙ ነገራቸው ሥርዓት ይዞ የሚሄድ ስለሆነ ምንዛሬውን የሚያጭበረብሩበት መንገድ አይኖርም።

በዚህ ሂደት ድርሻቸው ወርዶ ወርዶ ወደ ሶስት በመቶ የደረሰበት ደረጃ ነበር። ከ2016 በጀት ዓመት አንጻር ማኅበራት ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረቡት ምርት በዕጥፍ ጨምሯል። አንዳንዱ ማኅበራት ለአራት ዓመት ያህል በኪሳራ የቆየ አለ። በአንድ ወቅት አርሶ አደሩ ጭምር በደረቅ ቼክ ችግር ውስጥ የገባበት ነበር። እሱን ለመተካት ዩኒየኖች ተደራጅተው ጥሩ የሚባል ሚና ተጫውተዋል።

አዲስ ዘመን፡- ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ምን ተጨባጭ ሥራ ተሠርቷል?

አቶ ሺሰማ፡- ከሪፎርሙ ወዲህ ተጠያቂነትን በተመለከተ 662 አደራጅ ባለሙያዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል። 173 በሚሆኑት ከቦታ የማንሳት ሥራ፤ 919 አደራጅ ባሙያዎች የቃል ማስጠንቀቂያ እና 279 ላይ ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

በሪፎርሙ 40 ሺ 236 የሕብረት ሥራ አመራር እንዲቀየሩ ተደርጓል። አሁን የሚተኩ አመራሮች በተሻለ ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፤ በተለይም ስብጥር እንዲኖረው ተደርጓል። ከሁሉም በላይ የሚያስፈልገው መተማመንና ዕምነት ነው። በሕብረት ሥራ ማኅበራት የሜካናይዜሽን አገልግሎት እየጨመሩ ነው። የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ማኅበራት ሞዴል ሥራ እየሠሩበት ሲሆን፣ በዚህም ተጠቃሚ የሆኑ የሕብረት ሥራ ማኅበራት አሉ።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ በግብርና እና በሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ መናር እንዳለ ይስተዋላል፤ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ገበያውን የማረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ሺሰማ፡– ሕብረት ሥራ ማኅበራት ሚናቸው ለመወጣት አቅም ሊኖራቸው ይገባል። ሸማቾቹ ምርት የሚገዙት ከገበያ ውስጥ ነው። ብዙ ውሎች ይፈርሳሉ። አቅም ስለሌላቸው በገቡት ቃል መሰረት ምርታቸውን ተረክበው ተገቢ በሆነ መጋዘን አስቀምጠው መሸጥ አለባቸው። ተወዳዳሪ መሆን ላይ ከአቅም ጀምሮ ክፍተት አለ። ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ መድቦ በጀቱን ጭምር ሕብረት ሥራ ማኅበራት እንዲጠቀሙ እያደረጉ ያሉ አንዳንድ ክልሎች በዚህ ደረጃ የሚሠሩ አሉ።

ተገቢው አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ ለሚለው ገና ነን። ብዙ ነገሮች መሠራት አለባቸው። በሌሎች ሀገሮች የሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ምርት ሳያልቅ የሌላ ሱቅ አይሸጥም። ነገር ግን የእኛ ሀገር ሲታይ ገና ነው። ቀድሞ የነበረው የድጎማ ሸቀጥ ለማሰራጨት ነበር። አሁን ላይ ግን ድጎማው መልኩን ቀይሯል በሴፍቲኔትና በሌሎች ምርታማነትን ሊጨምር በሚችል መንገድ እየተሠራ ነው።

የትኛው ምርት የት እንዳለ በየክልሉ ያሉ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ያደራጁት አንዱ ሚና ነው። ይኼኛው ምርት በዚህ መጠን እዚህ ጋር አለ የሚለው መረጃ ከማሰራጨትና ከማስተሳሰር አንጻር ሥራውን እንሠራለን። ከሁለቱም ወገን አንጻር ችግር አለ። ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተላመድን ስንመጣ ሻጭና ገዥ በቀላሉ ተገበያይቶ ግብይት ፈጽሞ ምርት ርክክብ የሚያደርጉበት ሲስተም እየተገባ ነው። ነገር ግን ደግሞ ሕብረት ሥራ ማኅበራት የማይናቅ ሚና አላቸው።

አዲስ ዘመን፡- ሪፎርሙን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? በቀጣይስ ምን ምን ተግባራት ይቀራሉ?

አቶ ሺሰማ፡– እስካሁን የቆየነው ፈጣን ምላሽ በሚባሉ ተግባራት ላይ ነው። መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ የምንላቸው አንዱ ሕጎች መስተካከል አለባቸው። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደየስልጣናቸው ሊያዳብሯቸው ይችላሉ። የሪፎርሙ ትግበራ ውስብስብ ነው። በተቋም ውስጥ ብቻ ደረጃ አውጥቼ፣ ፈትኜ፣ ድልደላ ሰርቼ እጨርሰዋለው የሚባል ነገር አይደለም። ተቋሙ በራሱ እስከታች ባለው መዋቅር ጉድለት አለው። ያለመናበብ ችግር ስላለበት መስተካከል አለበት። ይህ ሲሆን ግን እንደየክሎች ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ማድረግ አለበት።

የአዋጅ ማሻሻያ ሰርተን በግብርና ሚኒስቴር ካቢኔ መታየትና መጽደቅ ስላለበት ታይቶና ጸድቆ ለፍትህ ሚኒስቴር ቀርቧል። በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ምክር ቤት ሂዶ ጸድቆ ወደሥራ ይገባል ብለን እንጠብቃለን። በአዋጁ በየደረጃው ያሉ የሕብረት ሥራ ተወካዮችን በአራት ክላስተር እንዲወያዩበት ተደርጓል። በፊት የነበረው አዋጅ አብዛኛው ከልካይ ነው።

ሪፎርሙ መቼ ያልቃል ለሚለው እስከ 2023 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህን የመንግሥት ጥሩ ድጋፍ ስላለ ይሳካል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡

አቶ ሺሰማ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You