መንግስት የኮረና ቫይረስ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ መግለጫዎችን እየሰጠ ነው። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሀዝም እየጨመረ መጥቶ 11 ደርሷል። ቫይረሱ ወደ ሀገራችን መግባቱ ይፋ ከተደረገ አንስቶም መንግስት በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ መግለጫዎችንና ማሳሰቢያዎችን እየሰጠ ነው።
ከአጸደ ህጻናት አንስቶ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉትን ትምህርት ቤቶች ለሁለት ሳምንታት በመዝጋት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችልበት እድል እንዳይኖር እየተሰራ ነው። ሌሎች ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው።
እርምጃው ባለፈው ሳምንት ደግሞ ወደ 30 ሀገራት በረራዎችን በማገድ ተጠናክሯል። መንግስት ትናንት በሰጠው መግለጫም የሀገሪቱ የየብስ ድንበሮች ለሰዎች ዝግ እንዲሆን አድርጓል። መከላከያ ሰራዊት በተጠንቀቅ እንዲቆም ታዟል። 5 ቢሊዮን ብር ለቫይረሱ መከላከል ስራ ተመድቧል።
ህዝቡ እጁን በሳሙና እንዲታጠብ፣ የእጅ ማጽጃ እንደ አልኮል ፣ ሳኒታይዘር የመሳሰሉትን ኬሚካሎች በመጠቀም የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የግብአት አቅርቦቶችን እያከናወነ ይገኛል።
ተቋማትና ህብረተሰቡ በተለይ በአዲስ አበባ በየጎዳናው፣ በየተቋማቱ በሮች፣ በየአደባባዩ ህዝቡ እጁን በሳሙና እንዲታጠብ እንዲሁም በአልኮልና በሳኒታይዘር እንዲያጸዳ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል። አውቶብሶችም የእጅ ማጽጃ ኬሚካሎችን በማቅረብ ተሳፋሪው እጁን እያጸዳ ወደ አውቶብስ እንዲገለገል እያደረጉ ናቸው። ህብረተሰቡና እነዚህ ተቋማት የመንግስትን ማሳሰቢያ ተከትለው በመውሰድ ላይ በሚገኙት ጠንካራ እርምጃ ሊመሰገኑ ይገባል፤ ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
ህብረተሰቡም እጁን በሳሙና በመታጠብ እና በአልኮልና በመሳሰሉት በማጽዳት የመንግስትን ማሳሰቢያ በተግባር እያረጋገጠ ነው። ይህም በየጎዳናው በየመስሪያ ቤቱ ደጃፍ በግልጽ ይታያል። ህብረተሰቡ ያለምንም መሰላቸት በተደጋጋሚ እጅ እየታጠበ እና እያጸዳ ነው። በየመኖሪያ ቤቱም ተመሳሳይ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።
ህዝቡ ቫይረሱን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት ከሚጠቀማቸው ቁሳቀስም መረዳት ይቻላል። አንዳንዶች አፍና አፍንጫቸውን በስካርፍ እና በነጠላ ሸፍነው እየተንቀሳቀሱ ናቸው። ለተለያየ ዓላማ የተሰሩ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን እና ጓንት የሚያደርጉም ይታያሉ። ይህም ጥረት ሊደነቅ ይገባል።
ተገቢዎቹን ቁሳቁስ እየተጠቀሙ የሚገኙ ሰዎችን ማበረታታት ፣ ተገቢ ቁሳቁስ እየተጠቀሙ መስሏቸው ተገቢ ያልሆኑ ቁሳቁስ የሚጠቀሙትን አሁንም ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባል። ይህ ጥረት ግን በባለሙያ ምክር ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። የጤና ባለሙያዎች በሽታውን ለመከላከል ስራ ላይ መዋል የሚገባቸው መሳሪያዎችና ግብአቶች ምን አይነት መሆን እንዳለባቸውና እንዴትና ለምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው የማስገንዘቡ ስራ መጠናከር አለበት።
መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ይህን የህዝቡን በሽታውን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት በምክርና በቁሳቁስ አቅርቦት መደገፍ ይገባል።አንዳንዶች ደግሞ በሽታውን ከሩቁ ለማስቀረት የሚያስችለውን እንደ እጅ በሳሙና መታጠብ፣ በኬሚካል ማጽዳትና የመሳሰሉትን መሳሪያዎች ለመጠቀም ፈቃደኛ ሆነው አይታዩም፤ እምነትን ተገን እያደረጉ ሁሉንም ለፈጣሪያቸው የሚሰጡም ተስተውለዋል።
ይህ ሁሉ በአስቸኳይ መታረም ይኖርበታል። በሽታውን አቅልሎ ማየት በፍጹም ሊወገዝ ይገባል። አንድም ሰው ቢሆን በሽታውን ከመከላከል መቦዘን የለበትም። በሽታው ተላላፊ እንደመሆኑ ከመንግስትና ህዝቡ ዝግጁነት እና የመተግበር ቁርጠኝነት ጋር አብሮ አለመጓዝ ህዝብንና ሀገርንም ዋጋ ያስከፍላል።
ግንዛቤ የሚጎለውን ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ አፈንጋጭ ባህሪ የሚያሳየውን የችግሩን አሳሳቢነት በማስገንዘብ ወደ መስመሩ መመለስ ያስፈልጋል። ለእዚህ ደግሞ የጤና ባለሙያው ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም ሃላፊነት አለበት።
ሀገራችን እንዳደጉት ሀገሮች ይህን መሰሉን በሽታ የምትመክትበት በቂ ሀብት እንደሌላት ይታወቃል። እልፍ ቢል ድርቅ ቢከሰት ብላ ባላት የቆየ ተሞክሮ ሳቢያ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ የምታቆየው ጥሪት ሊኖራት ይችላል። የኮሮና ቫይረስን መመከቻ የሚሆን በቂ ሀብት ግን የላትም። ሀብቷ መከላከል እና መከላከል ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በእዚህ ላይ አንድም ሰው ሳይቀር ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።
ሀገሮች ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉ ካሉት ርብርብ አኳያ ሲታይ እጅ መታጠብ ሆነ ማህበራዊ ግንኙነትን ላላ ማድረግ በጣም ውስን ስራዎች ናቸው። ከአንድም ሰው ቢሆን ብዙ ይቀራልና ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ የማያደርጉ ሰዎችን እያረመ የመከላከል ዘመቻው አካል ሊያደርጋቸው ይገባል።
የመከላከል ስራው ግዙፍ ሃላፊነት መሆኑ ታውቆ እያንዳንዱ ግለሰብ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እንስራ! አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም ርብርብ ያድርግ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 /2012