በርካታ ወጣቶችና ታዳጊዎች የግቢውን በር ወረውታል፤ ነገሩን ከርቀት የሚመለከቱ ሰዎቹ አንዳች ትእይንት ለማየት የተሰበሰቡ እንጂ ባለጉዳይ አይመስሉም። ቁመታቸው የተንዠረገገ፣ ሰውነታቸው ሞላ ያለ መሆኑ እንጂ እድሜያቸው ገና ለጋ መሆኑ ያስታውቃል። ቦታው ጥቁር አንበሳ አካባቢ የሚገኘው የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ነው።
ከግቢው መግቢያ በር አካባቢ የቆሙት አስተናባሪ ወደ በር ለሚጠጉና ፓስፖርት ለሚጠይቁ ባለጉዳዮች መጀመሪያ ወደ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሄድ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ። ታድያ አብዛኞቹ በተለይም ከተለያዩ ኢትዮጵያ ክልሎች የመጡት ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች አብዛኞቹ ቦታውን በሚገባ የሚያውቁት አይመስልም።ፓስፖርት ለማውጣት በስፍራው መገኘታቸውን እንጂ የቀረውንና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ልብ አላሉም።
ሕገወጥ ስደት ተበራክቶ በሚሰማበት በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ስደት በጥቅሉ አስከፊው ምስሉ ጎልቷል። አንዳንዴም ሕጋዊ በሚመስል የሚሄዱ ተጓዦች ከመንገድ በፊት ያለውን እንጂ ከሄዱ በኋላ የሚገጥማቸውን አይዘጋጁበትምና ብዙ ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ ይገደዳሉ።
ወጣት ከድጃ መሃመድ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቃለች። ከስልጤ ዞን ወደ አዲስ አበባ ከመጣች ጥቂት ወራት አልፈዋል። አዲስ አበባ የተገኘችው የኢሚግሬሽን የዜግነት ጉዳይ መምሪያ ፓስፖርት እንዲሰጣት ለመጠየቅ ነው። እዚህ ሥራ እስክታገኝ ድረስ ለማንኛውም ፓስፖርቱን ለመያዝ አስባ እንደሆነ ትናገራለች። ግን ከስጋቷ የተነሳ እንጂ ለሥራ ስምሪት ፈቃድ ከተገኘባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ወደ አንዱ ልታቀና መሆኑ ያስታውቃል።
ወደምትደርስበት አገር ሆኖላትና ሂደቱ ተጠናቆ ከሄደች በኋላስ? «እሱን እዛ ስደርስ ነው የማስበው፤ አላህ ያውቃል!» አለች። ለጉዞ የተነሳሳችው በፍላጎቷ ነው፤ በትውልድ አካባቢዋ እኩዮቿ ቀደም ብለው በሄዱባቸው አገራት በርትተው እየሠሩ መሆናቸው ተስፋ ሰጥቷታል። ለወደፊቷ ያሰበችው የለም፤ ለሁሉም ነገር መልሷ «ፈጣሪ ያውቃል» ብቻ ነው።
መሄዳቸውን እንጂ የሚሄዱበትን፤ ተስፋቸው ላይ እንጂ እውነታው ላይ ያልቆሙ እንደ ከድጃ ያሉ ብዙ ዜጎች አሁንም ፓስፖርት ለማውጣት ወደ መምሪያው ያቀናሉ። ለእነዚህ ዜጎች ከቅርብ ቤተሰብ፣ ከየአካካቢያቸው ማኅበረሰብና ከደላሎች በላይ፤ ከራሳቸው ከተጓዦችም ይልቅ ኢሚግሬሽን የላቀ ኃላፊነትን ይረከባል። ለዚህም ከሚመለከታቸው ተቋማትም ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ይጠበቃል።
አቶ የማነ ገብረመስቀል የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ናቸው። መምሪያው ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በአዲስ ለውጥና ተቋማዊ ግንባታ ሂደት ውስጥ ነው ይላሉ። በተለይም ደኅንነቱን የጠበቀ፣ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሳሉ።
በአሁኑ ሰዓት በኢሚግሬሽን በዋና ዓላማነት ተይዞ እየተሠራ ያለው ሕገወጥ ስደትን መከላከል ነው። ይህንን የጠቀሱት አቶ የማነ፤ ተጓዦች በሄዱበትም ቀና ነገር እንዲያጋጥማቸው ከኤጀንሲዎች ባለፈ በመንግሥት በኩል ከአገራቱ ጋር የሚካሄደውና እየተካሄደ ያለው የሁለትዮሽ ስምምነትና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ትልቅ ሚና አለው። በዚህም የሰዎች ከአገር አገር የመንቀሳቀስ መብታቸው የተጠበቀ ሆኗል።
ኢሚግሬሽን ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጥምረት ከሚሠራው የፓስፖርት መስጠት አገልግሎት በተጓዳኝ የክትትልና የቁጥጥር ሥራንም እያከናወነ ነው። ታድያ መምሪያው ባደረገው ጥናት በተለይም በቀበሌ ደረጃ የተለያዩ አስተዳደሮች ጥፋት እየፈጸሙ ይገኛል። ይህንንም «ዕድሜያቸው ያልደረሰ ልጆችን ከትምህርታቸው ተፈናቅለው፤ እድሜያቸው እንደደረሰ እያስመሰሉ መታወቂያ የሚሰጥባቸው አስተዳደሮች አሉ» ሲሉ አቶ የማነ ይገልጻሉ።
ከመንገድ በፊት የጉዞ ሰነድ ለማስወጣት አንድ ተጓዥ ወደ ኢሚግሬሽን ሲያቀና 8ኛ ክፍልን ማጠናቀቁ፣ እድሜው ከ21 በላይ መሆኑና በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ በኩል እውቅና ማግኘቱ ይረጋገጣል። ይሁንና ገና 13 ዓመትን ያልዘለሉ ልጆች እድሜያቸው ከ20 በላይ ተብሎ መታወቂያ እንደሚያገኙ መምሪያው ባደረገው ዳሰሳ ጥናት አረጋግጧል።
«የእነዚህ አስተዳደሮች ተግባር አስነዋሪና በሕግም የሚያስጠይቅ በመሆኑ እንዲቆጠቡ እንላለን። አንዳንድ ቤተሰብም እድሜው ለሥራ ያልደረሰ ልጁን እንደደረሰ አድርጎ መታወቂያ አስወጥቶ ይገኛል። በዚህ ቤተሰብ ልጆቹን ከትምህርት ገበታ አፈናቅሎ አደጋ ላይ እየጣላቸው መሆኑን ሊያስተውል ይገባል» በማለት ያሳስባሉ።
እንደ አቶ የማነ ገለጻ ጉዞዎችን ሁሉ ሕጋዊ እንዲሆኑ ማድረግ፤ ከአገራቱም ጋር ያለውን ትስስር መልካም በማድረግ የዜጎች ደኅንነትን መከታተል በትኩረት እየተሠራበት ነው። ይሁንና መረጃ በማድረስ በኩል አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውን አልደበቁም። ከመንገድ በፊትና ፓስፖርት ለማውጣት ምን ያስፈልጋል የሚለው፤ በተለይ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሄድ የሚነሱ ተጓዦች አለማወቃቸው ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል።
መገናኛ ብዙሀን በዚህ ላይ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አቶ የማነ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ «ትክክለኛው ፓስፖርት አዲስ አበባ የሚሰጠው ነው» በሚል የተሳሳተ መረጃ ብዙዎች ከተለያየ ቦታና ከርቀት አዲስ አበባ ይመጣሉ። ነገር ግን አገልግሎቱ በተመሳሳይ ሁኔታ በሃዋሳ፣ ጂማ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ እና ደሴ በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እየተሰጠ ይገኛል። ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በአሁኑ ሰዓት በድምሩ በቀን እስከ 10ሺህ ዜጎችን ተቀብለው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ እንደተዘጋጀ ዘገባ ከሆነ፤ በዘመናዊ የይለፍ ሰነድ የሚደረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1789 ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ450 ዓመተ ዓለም አካባቢ እንደ ፓስፖርት የሚያገለግል የወረቀት ሥራ መኖሩን በቅዱሱ መጽሐፍ፤ መጽሐፈ ነህምያ ላይ ተጠቅሷል። በተመሳሳይ በመካከለኛው የእስልምና ካሊፌት ዘመን እንደ ፓስፖርት የሚቆጠር «በረአ» የሚባል የግብር ደረሰኝ እንደነበረም ታሪክ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በሊድያ ተስፋዬ