ሴቶች በተፈጥሯቸው ብልሆች እና ጠንካራ ሰራተኞች ናቸው። ትዕግስተኛ እና አስተዋይ ናቸው።ሀብታቸውን በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚያውሉና ቆጣቢ መሆናቸውም ይታወቃል። ይሄንን ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጥበብ ተጠቅመው የተባሉትን ለመሆን የቻሉ በርካታ ናቸው።
ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ጀግኖች መሆናቸውን በየዘመናቱና አጋጣሚዎቹ ሁሉ አረጋግጠዋል። በዚህኛውም ትውልድ ይሄንኑ ጀግንነታቸውን ለመድገም ከወንድ አጋሮቻቸው ጎን ቆመዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ብርቱዋ ሴት ማንነቷን የምታሳየው ገና ከልጅነቷ አንስቶ ቤተሰቧን እንድታግዝ ኃላፊነት ሲሰጣት ጀምሮ ነው።
ኃላፊነትን ልጅነቷ ሳይጫናት ትወጣላች:: በተለይ በገጠር ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ምግብ እና መጠጥ ከማዘጋጀት ጀምሮ እንጨት ተሸክማ እናቷን ታግዛለች። በኃላፊነት ስሜት ተኮትኩታ በማደጓ በቀጣይ የራሷን ቤተሰብ ለማስተዳደር፣ በኣካባቢዋ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት አትቸገርም፤ የአገር ዋልታና ማገር እስከመሆን ትደርሳለች። ለዚህም እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ብቻ በአብነት ማንሳት ይበቃል።
ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ሰራዊት አድዋ ላይ ድል ሲያደርጉ የእቴጌ ጣይቱ ሚና በጣም ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እቴጌ ጣይቱ የጣሊያን ጦር ለሽንፈት እንዲዳረግ ያደረጉት በቀሰሙት የዘመናዊ ትምህርት በሰለጠኑበት ወታደራዊ ጥበብ ተጠቅመው አይደለም፤ በብልሀት እና በአገር ወዳድነት ስሜት በመነሳሳት እንጂ።
መጀመሪያ ክተት ሰራዊት፣ ጎስም ነጋሪት ከመባሉ በፊት የውጫሌ ስምምነት በሁለት ቋንቋ መጻፉን የሰሙት ጣይቱ በጣሊያንኛ ቋንቋ የተፃፈው እንዲነበብላቸውና ትርጉሙ እንዲነገራቸው ነበር ያደረጉት። ጣልያን በውሉ መሰረት ኢትዮጵያን በበላይነት ለመቆጣጠርና በቀኝ ለመግዛት ያለመ መሆኑን ሲረዱ በእምቢ ባይነት የአገር ዳር ድንበርንና ሉአላዊነትን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት በቀዳሚነት በወኔ ተሰልፈዋል።
መቀሌ ላይ የመሸገው የጠላት ጦር ለምግብ ማብሰያ እና ለመጠጥ የሚጠቀምበትን ምንጭ በራሳቸው ሰራዊት አስከብበዋል። ሰራዊት ሳይበላና ሳይጠጣ መዋጋትም ሆነ ማሸነፍ አይችልምና በውሀ ጥም ሽንፈቱን እንዲከናነብ ያደረጉ ብልሀተኛ ናቸው።
ከእቴጌ ጣይቱ ጋር አብረው የዘመቱ ከ20 እስከ 30 ሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች በምግብ ዝግጅት፣ ቁስለኛ በማንሳትና በማከም፣ መረጃ በመሰለል እንዲሁም በቀረርቶና ሽለላ የኢትዮጵያን ሰራዊት በማበረታታት ለድሉ ትልቅ መሰዋዕትነት ከፍለዋል። ይህ የአገር ፍቅር ስሜታቸው፣ አስተዋይነታቸውና ጥበባዊ ብቃታቸው በእኛ ዘንድም አድሯል። ይህን ጀግንነታቸውን ዛሬ በኩራት እያወደስን እንገኛለን።
ይሁን እንጂ ታሪክ ማውራት ብቻ ጀግና አያደርግም። የዛሬዎቹ ሴቶችም የራሳችንን የታሪክ አሻራ አስቀምጠን ማለፍ ይጠበቅብናል። ዛሬ ሴቶች ይብዛም ይነስ በትምህርት ታግዘው በእውቀት ጎልብተው ከአገር ፕሬዚዳንትነት ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር በየደረጃው በአመራርነት እያገለገሉ ናቸው። በአስተዋይነት፣ በጥበብ፣ በትዕግስት እና በአገር ፍቅር አገራቸውን እየመሩ ይገኛሉ። ይህ ጥረታቸው ከአጋር ወንዶች ጋር በመተባበር አገራችንን ወደ ብልጽግናው ማማ ያወጣታል።
የዚህ ዘመን ዋናው ጠላታችን ድህነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ድህነትን ድል ለመምታት ከመንግስት ጎን በመቆም እቅዱን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡ከድህነት አረንቋ ለማውጣት በመንግስት ከተያዙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ ታሪክ የሚሆነውም ይህን ግድብ ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባት ይሆናል።
በመሆኑም ሴቶች በጥበብና በብልሀት ጭምር በአባይ ተጠቃሚነት ላይ የሚሰነዘሩ ጣልቃ ገብነቶችን በመቋቋም ግንባታውን እናጠናቅቃለን። ይሄ የዚህን ዘመን ትውልዶች በተለይም ሴቶች “አንደፈርም” የሚለውን ቃላችንን ዳግም የምናረጋገጥበት ይሆናል፡፡ ይህንንም አንዱ የጀግንነታችን ማሳያ ልናደርገው ይገባል። ግድባችን ድህነታችንን የምናሸንፍበት፣ በመብራት እራት ሳይበላ የሚያድረውን 70 በመቶ ዜጋ የብርሃን ባለቤት የምናደርግበት ፕሮጀክት ነው።
እቴጌ ጣይቱና ከጎናቸው የተሰለፉ ሴት ጀግኖች በጦርነት የሰሩትን ጀግንነት በሚስተካከል መልኩ ድህነትን ድል ነስተን ታሪካችንን በወርቅ ቀለም መጻፍና መድገም ይጠበቅበናል። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነውና አንድነታችንን እናጠናክር። ትዕግስት፣ ብልሀት፣ ጥበብ እና ጀግንነታችንን ተጠቅመን ዛሬም እንደ ጣይቱ ታሪክ እንሰራለን!
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2012