( ክፍል አንድ )
ለውጡ ያስመለሰልኝን ያልተሸራረፈ ፣ ሀቀኛ ተፈጥሮ’ዊ ሀሳብን የመግለፅ ነጻነቴን ያለ አፍጣጭና ገልማጭ ካድሬ አርታኢ ፤ ያለቅድመ ምርመራ Censorship በቅድመም ሆነ ድህረ የምርጫ ሒደቱ ላይ ተያያዥነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይነት ያላቸውን መጣጥፎችን ማቅረብ አሀዱ ብያለሁ ። በየጣልቃው ወቅታዊ ፣ ነፋስ አመጣሽና ደራሽ ጉዳዮችን እዳስሳለሁ። በማነሳቸው ሀሳቦች ሙግት ቢነሳም በኢትዮጵያዊ ጭዋነት ለመሟገት ዝግጁ ነኝ ።
በሀገራችን የምርጫ ታሪክ የፊታችን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ ም ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ታሪካዊና ልዩ ስለመሆኑ አበክሮ መደምደም ቢቸግርም አፍን ሞልቶ መናገር ግን ይቻላል ። ቀደም ሲል የተካሄዱት አምስቱ ” መረጣዎች ” አነስተኛውን የምርጫ መስፈርት የማያሟሉና ለአቅመ ምርጫ የቀረቡ ስላልነበር መረጣ selection እንጂ ምርጫ election እንዳልነበሩ ያስታውሷል ። ነጻ ፣ ፍትሐዊ ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ፣ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ፣ ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚ ፣ እኩል መደላድል የተቀመጠለት ታዛቢ ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ሚዲያ ፣ ነጻ የዳኝነት አካል ፣ ገለልተኛ የጸጥታና የደህንነት መዋቅር ፣ ወዘተ . ያስፈልጋል። ከእነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ስንመለከታቸው የቀደሙት አምስቱም” ምርጫዎች ” ” መረጣ ” እንጂ ምርጫ አልነበሩም ። ሕዝቡ በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ተገዶ ፣ አማራጭ ተነፍጎ ትህነግ / ኢህአዴግን እንዲመርጥ ተደረገ እንጂ ሌላ አማራጭ አልቀረበለትም ።
በለውጡ ማግስት ሊካሄድ የታቀደው 6ኛው ምርጫ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ፤ ሀሳብን በነጻ የመግለፅ መብት በተረጋገጠበት ፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ እነ አርበኞች ግንቦት 7 ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉበት ፤ ሲቪል ማህበራት በነጻነት የሚሳተፉበት ፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት እነ ኢሳት እና ተዘግተው የነበሩ ከ200 በላይ ድረ ገጾችና ጦማሮች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ፤ በቀደሙት “መረጣዎች” ምርጫ አስፈጻሚዎች የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ከመሆናቸው ባሻገር አበል የሚከፈላቸው በመንግስት ነበር አሁን ግን በራሱ በምርጫ ቦርድ የሚከፈላቸውና ገለልተኛ መሆናቸው ፤ ኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችን አካቶ ከግንባርነት ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ተሸጋግሮ የሚካሄድ ፣ ፓርቲው በሰላም የኖቤል ተሸላሚና አሸናፊ በሆኑ ፕሬዚዳንት የሚመራ መሆኑ ፤ ምርጫው ነጻ እንዲሆን ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት መኖሩ ፤ በአንጻሩ የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ ባልተረጋገጠበት ፤ ብሔርተኝነትና ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚቀነቀንበት ፤ በዜጎች መካከል መጠራጠርና ጥላቻ በተጎነቆለበት ፤ የየክልሎች ልዩ ኃይሎች እስከ አፍንጫቸው በታጠቁበት ፤ ትህነግ ከውህደቱ አፈንግጦና ፖለቲካዊ ምህዳሩን ጠርቅሞ ፤ ምርጫው ከነተቃርኖው ማለትም ተስፋንና ስጋትን አዛንቆ የሚፈፅም መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በዚሁ ጋዜጣ ” ምርጫ የሞት ሽረት ጉዳይ አይደለም “በሚል ርዕስ ከወራት በፊት ባስነበብሁት መጣጥፍ ፤ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን ፤ የሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግብ የቅድመ እና ድህረ ምርጫ ሂደቱን ነፃ ፣ ግልፅ ፣ አሳታፊ ፣ ፍትሐዊና ታማኝ ማድረግ እንደሆነ ። ምዕራባውያንና የገንዘብ ተቋማትን ለማስደሰት ተብለው በሀገራችን የተካሄዱት 5ቱ የይስሙላ ” ምርጫዎች ” ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው ። የመጨረሻ ግባቸው የጊዜ ሰሌዳን ጠብቆ ” ምርጫ ” ማካሄድ እና ብድርና እርዳታን መቀላወጥ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አልነበረም ። በአጭሩ ገዥው ፓርቲ ብቻውን ተውኖ ብቻውን የታደመበት ባለአምስት ገቢር ቴአትሮች ነበሩ ማለት ይቻላል ። ወይም ፀሐፊ ተውኔት ራሱ ፣ ካስቲንግ ራሱ ፣ አዘጋጅ ራሱ ፣ ተዋንያን ራሱ ፣ ተመልካች ራሱ ፣ ቴአትር ራሱ የሆነባቸው ” ምርጫዎች ” ነበሩ ። እንደ አለመታደል ሆኖ ባለፉት አምስት ‘ ምርጫዎችም ሆነ ‘ በደርግና በአፄው በተካሄዱት ‘ ምርጫዎች ‘ ነፃ ፣ ፍትሐዊ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ዝግጁ አልነበርንም። በቀጣዩ ምርጫ ተፎካካሪዎች ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ፤ ያለምንም ስጋት ተዘዋውረው ቅስቀሳ የሚያደርጉበት አውድ ፣ ሰላም ፣ ፀጥታ ፣ ደህንነት ፣ መልክዓ እንደሚፈጠር ከቅርብ ወራት ወዲህ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ዋቢ በማድረግ አበክሮ መገመት ይቻላል።
ከምርጫ ጋር ተያይዞ ከአመታት በፊት ፍሬደረክ ኤበርት ስቲፍቱንግ ባደረገው ጥናት ከድህረ ግጭት በኋላም ሆነ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ምርጫ የማይተካ ሚና እንዳለው ያመለክትና የምርጫው ነፃነት ፣ ፍትሐዊነት ፣ ተአማኒነት ፣ ተቀባይነትና ዴሞክራሲያዊነት በመራጩ ፣ በተወዳዳሪዎችና በታዛቢዎች ካልተረጋገጠ ወደ ቀደመው አለመግባባትና ግጭት ሊመለስ ይችላል ሲል ስጋቱን ያጋራል ። በአፍጋኒስታን ፣ በሱዳን ፣ በብሩንዲ ፣ በጊኒ ቢሳው ፣ እና በጊኒ የተካሄዱ ምርጫዎችንም በአብነት ያወሳል። ምርጫ ለታይታ ብቻ ተብሎ የሚካሄድ ትዕይንተ ሰርከስ ሳይሆን ለመሪነት ፣ ለስልጣንና ለሀብት ክፍፍል ተብሎ የሚካሄድ ውድድር ስለሆነ ልዩ ጥንቃቄንና ማስተዋልን ይጠይቃል። በተለይ ድህረ ግጭትን ተከትሎ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማንበር የሚደረግን ምርጫ አንዳንድ ወገኖች በጦርነትና በሰላም እንዲሁም በመረጋጋትና በቀውስ መካከል በተወጠረ ቀጭን ገመድ ላይ በጥንቃቄ ከመራመድ ጋር የሚያነጻጽሩት ለዚህ ነው ። ሆኖም እነዚህን መሰል ምርጫዎች በሙሉ አይሳኩም ማለት አይደለም። በደቡብ አፍሪካ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ኒካራጓ ፣ ኤል ሳቫዶር ፣ ካምቦዲያ ፣ ሴራ ሊዎን ፣ ላይቤሪያ ፣ ወዘተ . የተሳኩ ምርጫዎችን ማካሄድ ተችሏል ። ይሁንና ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ timing ፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ፣ የቅሬታ መፍቻ አሰራር እና የሀገሩን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ የምርጫ ስርዓትን መከተል ለስኬታማነቱ ቅድመ ሁኔታ መሆናቸውን ልብ ይሏል ።
ከስድስት ወራት በኋላ በሀገራችን ለሚካሄድ ምርጫ ቢያግዝ በሚል ዕምነት ከ1980ዎች ጀምሮ ከተካሄዱ ምርጫዎች ከተቀመሩ ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ትምህርቶች ሁለቱን እንመልከት ።
1ኛ . ዝቅተኛ መስፈርቶች
አለማቀፍ የምርጫ ጠበብት ከቀደሙ ምርጫዎች ስኬትም ሆነ ውድቀት በመማር ከድህረ ግጭት በኋላ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚያግዙ ምርጫዎችን ለማካሄድ ቢያንስ ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል ይላሉ ።
ሀ . አስተማማኝ ደህንነት ፦ የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ ወሳኝ ከሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ቀዳሚው የደህንነትና የፀጥታ ጉዳይ ነው ። የታጠቁ ኃይሎች ካሉ ትጥቅ መፍታት አለባቸው ። ጦሩና ፖሊስም በአዲስ መልክ ሊደራጅ ይገ ባል። ከዚህ አንጻር የለውጥ ኃይሉ የደህንነትና የፀጥታ ኃይሉን ከፖለቲካ ወገንተኝነት አላቆ ገለልተኛ ሆኖ እንዲዋቀር የወሰዳቸው እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ይበል የሚያሰኙ ስለሆኑ እውቅና ሊቸር ይገባል።
ለ . የአስተዳደርና የኮሙኒኬሽን መዋቅሮችና መሰረተ ልማቶች ፦ ለመራጮች ምዝገባ ፣ ለምርጫ እንዲሁም የምርጫውን ሂደትና ውጤቱን ወደማዕከል ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን አበክሮ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሀገራችን ከዚህ አንጻር ከተወሰኑ ማስተካከያዎችና የምርጫ የመረጃ ቋቱን ከማደራጀት እና ተዛማጅ ስራዎችን ከማከናወን የዘለለ ምርጫን ለማከናወን የዛን ያህል የጎላ ችግር ይኖርባታል ተብሎ አይሰጋም።
ሐ . በምርጫ ሂደቱም ሆነ ከምርጫው በኋላ የሚከሰቱ እንደ ድምፅ ማጭበርበር እና ነፃነቱና ፍትሐዊነቱ ላይ የሚነሱ ክሶች አቤቱታዎች ካሉ በገለልተኛነት የሚመለከት ነጻ የዳኝነት አካል ሊኖር ይገባል ። የእነዚህ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ መሆን አለመሆን ለምርጫው ተአማኒነትና ተቀባይነት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል። በዚህ ረገድ የለውጥ ኃይሉ በአጠቃላይ የደህንነት ፣ የፀጥታና የዳኝነት መዋቅሩን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የሄደበት እርቀት የሚደነቅ ሆኖ ሪፎርሙን ተቋማዊና መዋቅራዊ ማድረግ ላይ የቀሩ ስራዎችን ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል ።
2ኛ . የምርጫ ጊዜ ውርክብ
ከላይ የተዘረዘሩ ዝቅተኛ መስፈርቶችን ለማሟላት ምርጫው በጥድፊያ እንዳይካሄድ አለማቀፍ የምርጫ ጠበብት ቢመክሩ ቢዘክሩም መንግስት ምርጫው እንዲካሄድ በወሰነው መሰረት አበረታች ሊባሉ የሚችሉ ዝግጅቶች በቦርዱ አማካኝነት እየተካሄዱ ነው ። ይሁንና ውድድሩ ፣ ፉክክሩ በጎሳ ፖለቲካ የታጀለ ስለሆነ አስ ፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እና ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባ ይዘከራሉ ። እዚህ ላይ በ1998 ዓ.ም በጎረ ቤታችንና ወዳጃችን ኬኒያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረውን የዜጎች ሞት መፈናቀል እና ሀገራዊ ቀውስ በዋቢነት ማንሳት ይቻላል ። ራይላ ኦዲንጋ የጎሳውን የሎው መብትና ጥቅም ለማስከበር በሚል ሽፋን ሎው እንደተገፋ የበይ ተመልካች እንደሆነ በመቀስቀሱ ፤ በተቃራኒው ኡሁሩ ኬኒያታ በተመሳሳይ ሁኔታ ለስልጣን ሳይሆን ለጎሳው ለኪኩዩ ጥቅም መብት የቆመ መስሎ ልዩነት ፍርሀትን በመስበኩ ፤ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲሆን በተፈጠረ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሁለቱም ጎሳዎች ሲሞቱ በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ደግሞ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። በሁለቱ ጎሳዎች መካከልም ዛሬ ድረስ ቂም ፣ መጠራጠር ፣ ጥላቻ ሰፍኖ ይገኛል ። በኋላ ላይ የወጡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ፖለቲካው ከፖሊሲ ከፕሮግራም ይልቅ በጎሳ ላይ የተመሰረተ መሆኑና ሚዲያዎችም ሁለቱን ጎሳዎች ተገን አድርገው የተቋቋሙ እና ልዩነትንና ጥላቻን ይለፍፉ ስለነበር ግጭቱን ቤንዚን ሆነው በፍጥነት እንዳቀጣጠሉት ተደጋግሞ ይነሳል። የፖለቲካ መሪዎች የየጎሳዎችን ድምፅ ለማግኘት እነዚሁን ሚዲያዎች መጠቀማቸው በእንቅርት ላይ እንዲሉ አድርጎታል። በመጨረሻ ፖለቲካውም ፣ ሚዲያውም ዘውጌአዊ ሆኖ አረፈውና ጎረቤታችን ኬኒያ ማጣፊያው ሲያጥራት ከአንድ ሁለት ሶስቴ በላይ ተመልክተናል። በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የጎሳ ፖለቲካ የክርክሩ ፣ የሀቲቱ ማዳወሪያ በሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራት ለመራጭነት ከተመዘገበው ሕዝብ 98 በመቶ የሚሆነው ድምፁን የሚሰጠው ጎሳውን ወክሎ ለሚወዳደር ፓርቲ ወይም ግለሰብ ነው። ችግሩ ከአንድ ማህበረሰብ የወጡ ሁለትና ከዚያ በላይ ተፎካካሪዎች ሲኖሩ የከፋ እንዳይሆን ያሰጋል። ይህ ጎሳ ፣ ዘውግ ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካ ምን ያህል ፖለቲካዊ አየሩን እንዳገለማው ጥሩ ማሳያ ነው። በሀገራችን በጎሳ ላይ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ አንጻር ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።
ሌላው የክልል እና ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን በአንድ ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ከማድረግ ይልቅ የክልል ምርጫዎችን አስቀድሞ ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን ማስከተል ውጥረትን እንደሚያረግብና በምርጫ ቦርድና አስፈፃሚዎች ላይ ጫና እንዳይበዛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጥናቶቹ ያሳስባሉ ።
በተለይ እንደኛ ባሉ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ዜጋ በገጠር ለሚኖርባቸው ሀገራት የአካባቢ ምርጫ ለሕዝቡ ይበልጥ ትርጉም ስለሚሰጥ ቅድሚያ ለአካባቢ ምርጫ ይገባል የሚለው መከራከሪያ ውሃ የሚያነሳ ይመስላል።
እንደ መውጫ
በተለይ በማንነት ላይ የተዋቀረ ፖለቲካ ስርዓትን ላነበረች ሀገር ቀና ፣ ነፃ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊ ፣ ግልፅ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ልዩ ጥንቃቄን ይጠይ ቃል። ከሁሉም በላይ ከቀውስ አገግማ በሁለት እግሯ ለመቆም በምትፍገመገም እና ሽግግር ላይ ላለች ሀገር ምርጫ መዳኛም መጥፊያም ነው ። ከሁለት አመት በላይ በጎሳ ግጭት ስትናጥ በሴራ ፖለቲካ ስትታመስ ለከረመች ሀገር ምርጫ ከኮሮጆው ፣ ከሳጥኑ ባሻገር መመልከትን ይጠይቃል። ጥላቻ ፣ ልዩነት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ሲሰበክባት ለኖረች ሀገር ምርጫ ባለሁለት ስለት ሰይፍ ነው ። ዜጎቿ ወደ ዘውግ ወደ ጎሳ ፈለፈል በተጠቃለሉበት ወቅት የሚካሄድ ምርጫ ከምርጫ በላይ ነው። ስለሆነም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የሀገሪቱ ደህንነት ፣ ፀጥታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መረጋገጥ አለበት። በመቀጠል የሕግ የበላይነት ለድርድር ሳይቀርብ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል። የቅድመ እና ድህረ ምርጫ ስርዓቶችም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ መከበር አለባቸው። የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ጸድቆ ወደስራ መገባቱ ፤ የቦርዱ ሰብሳቢዋን ጨምሮ ሌሎች አባላት ከገለልተኛ ወገን መሰየማቸው ተስፋ የሚጣልበት እርምጃ ነው ። በተለይ ነፃና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ የዳኝነት አካሉ እንዲሁም የደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩን ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ተላቆ እንዲደራጅ መደረጉ ፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ሆኑ በመዋቀር ላይ መሆኑ ፤ አፋኝ አዋጆች ሕጎች ገለልተኛ መማክርት ተቋቁሞ በመሻሻል ላይ መሆናቸው እንደ እኔ ላለ ተስፈኛ መጭው ጊዜ ከምርጫውም ባሻገር ብሩህ እንደሆነ ቀብድ የሚያሲዝ ነው ። ይሁንና ከተስፋዎቻችን ፊት የተደቀኑ ስጋቶችን በመላ ፣ በጥበብና በማስተዋል ካልተሻገርናቸው ለውጡን ከመገዳደር አልፈው የመቀልበስ አቅም እንዳላቸው ተረድተን የቀሩ የቤት ስራዎችን በጊዜ ማጠናቀቅ አለብን። ከእነዚህ ያደሩ የቤት ስራዎች ቀዳሚው ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው ። ከዚያም አስተማማኝ ሰላም የማስፈን በዜጎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት የማጥበብ ልዩነቶችን በኃይል በመንጋ ፍርድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በመነጋገር በውይይት ለመፍታት የሚያግዙ ተከታታይ መድረኮችን ማመቻቸት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል።
ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ከፓርቲያቸው ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም ቀጣዩ ምርጫ ነፃ ፣ ግልፅ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊ ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያግዙ ቁልፍ የምርጫ አላባውያንን በጋራ መለየት አለባቸው። ከወዲሁ የመራጩን ፣ የእጩውን ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሕዝቡን በራስ መተማመን መገንባት ትኩረት ይሻል። የዚህ ምርጫ ስኬትም ሆነ ውድቀት የሁላችንም ስኬትና ውድቀት እንደሆነ ተገንዝበን በጋራ ልንቆም ይገባል። የሀገራችንን መጻኢ እድል የምንወስንበትና የምንተረጉምበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ተገንዝበን በንቃት ፣ በማስተዋልና በጥበብ ስለ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንትጋ።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !
አሜን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com