ዓለምን እያሳሰበ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሳቢያ መካሄድ አለመካሄዱ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ አምስት ወራት የቀሩት ቢሆንም በርካታ የዓለማችን አገራት በተለያዩ ስፖርቶች የሚያደርጉትን ዝግጅት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ታላቅ የስፖርት መድረክ በተለይም በአትሌቲክስ ረጅምና መካከለኛ ርቀቶች ውጤታማ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ በማዋቀር የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ሰንብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውጤት በሚጠበቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የተመረጡ አትሌቶች ከመጋቢት ሦስት ጀምሮ ወደ ሆቴል ገብተው ዝግጅት እንዲጀምሩ ውሳኔ ላይ መድረሱን ያሳወቀ ሲሆን፣ አትሌቶችና አሰልጣኞች ከትናንት ጀምሮ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ፅሕፈት ቤት በአካል በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሁለት ሳምንት በፊት በኦሊምፒኩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችና አሰልጣኞችን መልምሎ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን በመካከለኛ ርቀት፣ ሦስት ሺ ሜትር መሰናክል፣ ረጅም ርቀት፣ ማራቶንና ርምጃ ውድድሮች አሰልጣኞችና አትሌቶች መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት በመካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ብርሃኑ መኮንን፣ ሃብታሙ ግርማ፣ ኢሳ ሽቦ እና ጉዲሳ ታሱ በአሰልጣኝነት ተመርጠዋል፡፡ አሰልጣኝ አብርሃም ኃይለማሪያም እና ስንታየሁ ካሳሁን ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዘዋል፡፡ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ እና ዶክተር ብዙአየሁ ታረቀኝ ሲመረጡ አሰልጣን ከፍያለው አለሙ ተጠባባቂ ሆነዋል፡፡
አገሪቷ በኦሊምፒክ መድረክ በተለይ ውጤታማ በሆነችባቸው የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶችም አራት አሰልጣኞች ተመራጭ ሆነዋል፡፡ አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ፣ ቶሌራ ዲንቃ፣ ንጋቱ ወርቁ እና ኃይሌ እያሱ ሲመረጡ፤ አሰልጣኝ ተፈሪ መኮንን እና በሪሁን ተስፋይ ደግሞ የተጠባባቂነት ስፍራን ይዘዋል፡፡ በረጅሙ የአትሌቲክስ ውድድር ማራቶን በማናጀር አሰልጣኝነት ስኬታማ የሆኑት አሰልጣኝ ሃጂ አደሎ ከሌላው ስኬታማ አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ጋር በመሆን የርቀቱን እንዲመሩም ተመርጠዋል፡፡ አሰልጣኝ ጌታነህ ተሰማ እና ይረፉ ብርሃኑ ደግሞ ተጠባባቂ ሆነው ተይዘዋል፡፡ የእርምጃ ቡድኑም በሻለቃ ባየ አሰፋ አሰልጣኝነት የሚያመራ ይሆናል፡፡
ውጤት በሚጠበቅበትና ታሪካዊ ሊሆን እንደሚችል በሚታሰበው የወንዶች ማራቶን ውድድር የ5ና 10ሺ ሜትር የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑና የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ባለፈው መስከረም በበርሊን ማራቶን ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓት መሰረት በዋናነት መመረጡ የሚታወስ ሲሆን ማራቶንን ጨምሮ በሌሎች ርቀትም ጠንካራ አትሌቶች በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል ወደ ዝግጅት ይገባሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በዶሃው ቻምፒዮና ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ሞስነት ገረመው 2፡02፡55 የሆነ ሰዓት ባለፈው ለንደን ማራቶን ላይ በማስመዝገቡ በማራቶን ቡድኑ ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ተመራጭ ሆኗል፡፡ ብርሃኑ ለገሰ በ2፡02፡48 በሁለተኛነት ሲመረጥ የዓለም ሻምፒዮኑ አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ከሌሎች አትሌቶች አኳያ ያለው የቅርብ ጊዜ ፈጣን ሰዓት በቡድኑ ሊያካትተው እንደማይችል ይፋ ከተደረገው የእጩዎቹ ዝርዝር መረዳት ተችሏል፡፡ በሴቶች ማራቶን የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ ወርቅነሽ ደገፋ 2፡17፡41 ሰዓት በመያዝ በቀዳሚነት ስሟ ሲቀመጥ ሮዛ ደረጄ 2፡18፡30ና በ2፡18፡34 ሰዓት ሩቲ አጋ በቀዳሚነት ታጭተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሚጠበቁበት የአስር ሺ ሜትር ውድድር የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ዮሚፍ ቀጄልቻ 26፡49፡34 በሆነ ሰዓት ሲመረጥ አንዱአምላክ በልሁ 26፡53፡15ና በ26፡54፡34 ጀማል ይመር በቀዳሚነት ተመርጠዋል፡፡ በሴቶች የኦሊምፒክ ቻምፒዮኗ አልማዝ አያና ከዓመት በላይ በጉዳት ላይ የቆየች ቢሆንም ቀዳሚዋ ተመራጭ መሆን ችላለች፡፡የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ለተሰንበት ግደይና ነፃነት ጉደታም ከቀዳሚዎቹ እጩዎች መካከል ተካተዋል፡፡
በወንዶች አምስት ሺ ሜትር በዶሃው የዓለም ሻምፒዮና የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያጠለቁት ሙክታር ኢድሪስና ሰለሞን ባረጋ እንዲሁም ሃጎስ ገብረህይወትና ጥላሁን ሃይሌ በቀዳሚነት ሊመረጡ ችለዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ ጸሐይ ገመቹ፣ ሐዊ ፈይሳና ፋንቱ ወርቁ ባስመዘገቡት ሰዓት መሰረት ሊመረጡ ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ከአትሌቲክስ ውድድሮች በተጨማሪ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ተሳታፊ መሆኗን ከሁለት ሳምንት በፊት ማረጋገጥ ችላለች፡፡ በሞሮኮ ራባት ተካሂዶ በነበረው የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ማስተር ሰለሞን ቱፋ በኦሎምፒክ እንደሚወዳደር ማረጋገጡ አይዘነጋም፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
ቦጋለ አበበ