ከዛሬ 124 ዓመታት በፊት የአድዋ ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ በነበሩት ዓመታትና ወራት የኢትዮጵያውያን የውስጥ ሁኔታ አንድነት የራቀውን መግባባት ያልሰፈነበት ነበር፡፡ በርካታ የሀገረ ግዛት አስተዳዳሪዎች በተለይም የትግራይ፤የጎጃምና የቤጌምድር አስተዳዳሪዎች ከአጼ ምኒልክ ጋር ተኳርፈው ጎራ ከለዩ ሰነባብተዋል፡፡ ሆኖም ግን ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የቃጣቸውን የቅኝ ግዛት መስፋፋት ፍላጎትን ለመግታት ንጉሱ ክተት ሰራዊት ባወጁበት ጊዜ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ለሀገራቸው ዳርድንበር ለመዋደቅ በግንባር ቀደምትነት ዘምተው ድል ነስተው ተመልሰዋል፡፡
በቅርቡም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተካሄደውም ጦርነት በተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ተለያይተው የነበሩ አካላት በሙሉ ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር በአንድነት ተነስተዋል፡፡ እነዚህና መሰል አኩሪ ታሪኮቻችን የሚነግሩን ሀቅ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ፈተና በሚያጋጥማቸው ወቅት አንድነታቸው እንደሚጠናከርና የተጋረጠባቸውንም ችግር በጋራ ለመፍታት በአንድነት እንደሚቆሙ ነው፡፡
ከሰሞኑም በህዳሴ ግድብ ላይ ከታዛቢነት ወደ አሸማጋይነት በራሳቸው ውሳኔ የመጡት አሜሪካኖች የኢትዮጵያውያንን ሉአላዊነት በሚጋፋ መልኩ እያወጡት ያለው መግለጫና አድሏዊ አሰራር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወደ አንድነት መንፈስ እያሰባሰበው ነው፡፡ 124ኛው የአድዋ በዓል በትግራይ በተከበረበትም ወቅት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ያስተላለፉትም መልዕክት የዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ዶክተር ደብረጽዮን እንዳሉትም ‹‹ በአድዋ የተሰራው አንፀባራቂ የድል ታሪክ የብዙ ትምህርቶች ምንጭ የሆነ፤ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ድል ነው። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ለአገራቸው ክብር፣ ብሄራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ልዕልና ማስከበርና ማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ፤ ከፍተኛ ስልጠናና ዝግጅት ካለው የጣሊያን ሰራዊት የማጠቃለያ ውጊያ በአድዋ በመግጠም ጦርነቱን በማሸነፋቸው ደካማ ተብለው የሚፈረጁ ህዝቦች ሳይለያዩ በጋራ ለጋራ ተራማጅ ህዝባዊ ዓላማ ከተነሱ ሊገመት የማይችል ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ አድዋ ህያው ምስክር ነች ›› የሚል የአንድነትን ጠቃሚነት የሚያሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ እያሳዩት ያለው ሀገራዊ የአንድነት ስሜት ተመሳሳይ መልክ ያለው ነው፡፡ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር መሆኗ እየታወቀ የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ስነልቦና በማይመጥን መልኩ በቅኝ ገዢዎች ውል እንድትገዛና ሀገራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንድትሰጥ በግብጽና በግብረ አበሮቿ እየተደረገ ያለውን ጫና በተባበረ ሀገራዊ አንድነት ልናወግዘው የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ይህ ትውልድም እንደ አባቶቹና አያቶቹ በሀገሪቱ ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን በተባበረ ክንድ መመከትና ከኢትዮጵያ በፊት የሚያስቀድመው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ዛሬ የተከፋፈልንና የተራራቅን የሚመስላቸው የውጭ ጣልቃ ገቦች የመልማት መብታችንንና ሉዓላዊነታችንን ሊነጥቁን ቆርጠው ተነስተዋልና እኛም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ መሆናችንን የምናሳይበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡በመሆኑም በዚህ ወሳኝ ወቅት ልዩነታችንን አጥብበን አንድነታችን አጉልተን ልናሳይ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ ም