የአድዋ ድል በዓል በድምቀት መከበር የጀመረው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ነው። 2008 ላይ ደመቅ ማለት ጀመረ፤ 2009 ላይ ግን በከፍተኛ ድምቀት ተከበረ። ከአድዋና ከአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ የቀጥታ ሥርጭትና ሠፊ የዘገባ ሽፋን አገኘ። ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት በተለመደው መንገድ እየተከበረ ቆየ።
የዘንድሮው ግን ለየት አለ። አዲስ አበባ ውስጥ ምኒልክ አደባባይ ብቻ ይደምቅ የነበረው በሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎችም ተከበረ። ለምሳሌ እኔ እንኳን በአይኔ ያየሁት መገናኛ፣ ካዛንቺስ እና ብሔራዊ አካባቢ ወጣቶች የአድዋን ድል የሚገልጹ የተለያዩ ቲሸርቶችን እየለበሱ አክብረዋል። አራት ኪሎ ለፒያሳ ቅርብ ስለሆነ ነው እንበል፤ ዳሩ ግን በሌሎች አካባቢዎችም በየታክሲው ውስጥ የአድዋ ጀግኖች ያሉበትን ቲሸርት የለበሱ ሰዎች ብዙ ነበሩ።
ምኒልክ አደባባይ የነበረው ድምቀትም ብዙ የተባለለት ነው። አዲስ ሚዲያ ኔቶርክ (አዲስ ቲቪ) በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ ነበር። በተወርዋሪ ካሜራ የተቀረጹ ምስሎች እንደሚያሳዩት ከአራቱም አቅጣጫ ያለው የሰው ብዛት ጠጠር ቢወረወር መሬት የሚያሳርፍ አይመስልም። ይሄ ብቻም አይደለም፤ እዚህም እዚያም ፉከራና ሽለላዎች ይበዙ ነበር።
ይሄው ድምቀት እስከ አራት ኪሎ ድረስ ቀጥሏል። ወጣቶች ያለምንም ድካም እየጨፈሩ እስከ አድዋ ድልድይ ድረስ ሲሄዱ ነበር። በጭፈራዎቻቸውና ፉከራዎቻቸው ውስጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስም ተደጋግሞ ይነሳል። በዚያው በምኒልክ አደባባይም የህዳሴው ግድም ስም በወጣቶች ሲነሳ ነበር።
ለምን እንደደመቀ አሁን ግልጽ ነው። የአድዋ ድል የፈጠረው የአሸናፊነት መንፈስ የቀሰቀሰው ወኔ ነው። ይሄ መሆኑን የምንረዳው በወጣቶች የአድዋ በዓል አከባበር ላይ በታየው ትርዒት ብቻ አይደለም። ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ያደረጓቸው ንግግሮችም የህዳሴውን ግድብ ስም እያነሱ ነበር። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በዚያው በአድዋ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተናገሩት ነገር ይህንኑ የአድዋን ድል ወኔ ለህዳሴው ግድብም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ነው።
በዚያው በአድዋ በዓል ዕለት በብሄራዊ ቴአትር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ያደረጉት ንግግርም ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ነበር። ‹‹ጣሊያን የተሸነፈው ክፉ ቀን መጥቶበት አይደለም›› ያሉት አቶ ልደቱ፤ ጣሊያን የተሸነፈው በመሪዎች ብልህነትና በህዝቡ አንድነት ነው። አስተያየታቸውን ሲቀጥሉም፤ አድዋ ኢትዮጵያን አልፈጠረም፤ ኢትዮጵያ ከዚያም በፊት ነበረች። አድዋ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ወኔና አንድነት ነው ያጠናከረ። አድዋ ህዝቡን አንድ አድርጎ የነበረውን ወኔ እንዲጠቀም ነው ያደረገው።
በአድዋ በዓል ዕለት የነበሩ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችም ከህዳሴው ግድብ ጋር የተገናኙ ናቸው። አስተያየት ሰጪዎችና ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እንግዶች ሁሉ ከህዳሴው ግድብ ጋር አያይዘው ነው የሚናገሩት።
ይሄ ሁሉ የሆነው እንግዲህ በአድዋ የድል በዓል ሰሞን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አሜሪካ በተናገረችው ነገር ነው። በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ አለመሳተፏን ተከትሎ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያወጣው ጽሑፍ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው ነበር። ይህን ተከትሎ ነው የህዝቡ ስሜት ወደ አንድ የመጣው።
እዚህ ላይ አንድ ያስተዋልኩትን ነገር ልጨምር። ብዙ ተከታይ ያላቸው በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን በማህበራዊ ገጾቻቸው ላይ የሚሰጡ ግብረ መልሶች አንድነትን የሚያሳዩ ነበሩ። ይህን ለማለት ያስቻለኝ ከዚህ በፊት በገጾቻቸው ላይ ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶችንም ስለማውቅ ነው። ‹‹ሌቦች፣ ውሸታሞች፣ አጨብጫቢዎች…›› የሚሉ ስድቦች አይጠፉም ነበር። በትክክል በአይን የሚታይ እውነተኛ ዘገባ ሰርተው ከሥር ስድብ አይጠፋም ነበር። በሌላ በኩል ብዛት ያለው ‹‹ላይክ›› እና አስተያየትም አይታይም ነበር።
ሰሞኑን ግን እንደዚያ አይደለም። 8100A በድጋሚ አገልግሎት ሊሰጥ ነው የሚለው ዜና በ10 ደቂቃ ውስጥ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ‹‹ላይክ›› ነበረው። አስተያየቶቹ በብዛት የወኔ እና የድጋፍ ነበሩ። በህዳሴው ግድብ ላይ መንግስት መግለጫ ሲሰጥ በደቂቃ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰው ወዶታል። የህዳሴውን ግድብ የተመለከተ አንድ ምሁር እንዲህ አለ ከተባለ ወዲያውኑ ብዙ ሰዎች ይጋሩታል። ከዚህ ሁሉ የምንረዳው በእንዲህ አይነቱ ወቅት ህዝቡ አንድ እንደሚሆን ነው።
እዚህ ላይ አድዋን እናስታውስ። የአድዋን ድል እንዴት አገኘን የሚለውን እናስተውል። አቶ ልደቱ አያሌው እንዳሉት፤ ጣሊያን የተሸነፈው አስማት ተደርጎበት ወይም የ40 ቀን ዕድሉ ፈርዶበት አይደለም። በነበረው ኢትዮጵያው ወኔ እና አንድነት ነው። በወቅቱ የአገሪቱ ንጉሥ የነበሩት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው። በአጼ ምኒልክ ሥርዓት አኩርፈው ጫካ የገቡ ነበሩ። ከእነዚህም የየጁው ደጃዝማች ዘገየ፣ ከትግራይ ራስ ስብሃት እና ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሰዎች በወቅቱ የአጼ ምኒልክ ደጋፊዎች አልነበሩም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ ከውጭ በኩል ሆነው አጼ ምኒልክን የሚቀናቀኑ ነበሩ።
ዳሩ ግን የአገር ጉዳይ ነውና የቁርጥ ቀን ሲሆን ‹‹ከአገሬ በላይ ምንም የለብኝም›› አሉ። የጣሊያን መምጣት ቁርጥ ሲሆን በየጫካው አኩርፎ የነበረው ሁሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ ይቅር ይበሉኝ›› አለ፤ አጼ ምኒልክም ያስቀየምኩህ ሁሉ እባክህ ናልኝ አሉ፤ የአገር ጉዳይ ነዋ! ከአጼ ምኒልክ አዋጅ አንዷን አረፍተ ነገር እንውሰድ። ‹‹…ያገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም ያስቀየምኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም…›› አሉ። ልብ በሉ፤ ምናልባት ያስቀየምኩት ሰው ሊኖር ይችላል በሚል ይመስላል በራሳቸው እርግጠኛ አይደሉም፤ ህዝቡ እንዳላስቀየማቸው ግን እርግጠኛ ሆነው ተናገሩ። ያም ሆነ ይህ ይቅር እንባባል አሉና አዋጅ አወጁ፤ ከሥርዓታቸው አፈንግጦ የነበረው ሁሉ ወደ እርሳቸው ሄደ። በዚህ አገራዊ ፍቅርና አንድነት ነው የአድዋን ድል ማግኘት የተቻለው።
ከሰሞኑ ተቃዋሚ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ከመንግስት ጎን እንቆማለን›› ሲሉ ተሰምቷል። መንግስት የሆነ መግለጫ ሲያወጣ መገናኛ ብዙኃን ሮጠው የሚጠይቁት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ነበር። የተለመደው መልስም መቃወም ነበር። በህዳሴው ግድብ ላይ ግን የመንግስትን አቋም አድንቀው በአቋሙ መጽናት እንዳለበት ሲናገሩ ነበር፤ አንዳንዶቹም እንደግፋለን የሚል መግለጫ አውጥተዋል።
በትንሽ ትልቁ ጭቅጭቅና መሰዳደብ የሚበዛበት ፌስቡክ እንኳን አንድ ሲሆን አየን። አበበ ‹‹የህዳሴው ግድብ ያገባኛል›› ብሎ ጽፎ ከሆነ፤ ጫላም ሐጎስም የሚሰጡት አስተያየት የድጋፍና የአድናቆት ነው። መሐመድ ‹‹የህዳሴው ግድብ የኔ ነው›› ብሎ ሲጽፍ ገብረማርያምም ገብረሚካኤልም የሚሰጡት የአድናቆትና የድጋፍ አስተያየት ነው።
አገራዊ አንድነት ማለት የግድ የጦር መሳሪያ ይዞ መሰለፍ ማለት አይደለም። በተለይም በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጥይት ጦርነት ቀርቷል። የዘመኑ ጦርነት ስነ ልቦናዊ አንድነት ነው። አገራትን ደካማ ጎን አይተው ነው የሚያስፈራሩ። ያ ደካማ ጎን የሚሉት ተወግዶ ካዩት ይተውታል። አገራዊ መከፋፈል ለእንዲህ አይነት ነገር ያጋልጣል፤ አገራዊ አንድነት ግን መፈራትና መከበርን ይፈጥራል። የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ይህን የህዝቡን አንድነት ሲያስተጋቡ ከታየ በሌሎች አገራት መከበርን ይፈጥራል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሁላችንም አንድ ነን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
ዋለልኝ አየለ