ወጣትነትና ፍልስፍና የሚመሳሰሉበት አንድ ባሕርይ አላቸው። ፍልስፍና እውነትን ለማወቅ ያለመታከት ይሰራል። ሁሉንም ነገር ለመፈተሽ በተለያየ አቅጣጫ ይቧጥጣል፤ ይቆፍራል። በባሕርይው ጠያቂ፤ ምክንያታዊና ሂሳዊ ነው። አሳማኝ ውጤት ካላገኘ ፍተሻውን አያቆምም።ወጣትነትም የማያውቀውን ለማወቅ፤ ያላገኘውን ለማግኘት፤ ካልደረሰበት ለመድረስ ያለ መታከት ይጥራል።በባህርይው አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመስራት፤ ለመፍጠር ወይም ለማግኘት፤ ፈትሾና አረጋግጦ ለማሳየት ይጓጓል።በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ወጣቶች ላይ የሚያተኩር ፍልስፍናዊ ቅኝት እናደርጋለን።ወጣትነት ፀጋዎች አሉት፤ በፀጋዎቹ ምክንያት ለአደጋም የተጋለጠ ነው።በተለይ ያልዳበረ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሥርዓት፤ ያልበለፀገ ግብረገባዊና ሥነ-ምግባራዊ ባሕል በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ወጣትነት ፈተናው እጅግ ብዙ ነው።ከዚህ አንፃር ስለ ወጣትነት ብዙ መማርና ማስተማር፤ ማወቅና ማሳወቅ፤ መምከርና መመካከር፤ መስራትና ማልማት ያስፈልጋል፡፡
የወደፊቱ ዓለምና የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ያለው በአዋቂዎች እጅ ሳይሆን ባብዛኛው በወጣቶች አእምሮ ውስጥ ነው።ዛሬ ያልተኮተኮተና ያልታረመ ማሳ ነገ በአረምና በአራሙቻ ይወረራል።ከዚህ የሚጠበቀውን ፍሬ ማምረት አይቻልም።የወጣቶች አእምሮም በዚሁ መልክ መታየት የሚችል ነው።አእምሮአቸው መልካምነት የሚዘራበት፤ ዕውቀትና ጥበብ የሚተከልበት፤ ሰላምና ፍቅር የሚታነፁበት መሆን አለበት።በእውን እየሆነ ያለው ግን ይኸ አይደለም።ማንኛውም ሐሳብና እምነት ጠቃሚነቱና ጎጂነቱ ሳይለይ ወደ ወጣቱ አእምሮ ይወረወራል።አይደለም ሌላ እናትና አባት ራሳቸው በልጆቻቸው ፊት ለሚያስቡትና ለሚናገሩት፤ ለሚሰሩትና ለሚፈጥሩት ነገር አስፈላጊውን ጥንቃቄ አያደርጉም።ዓለም የወጣቶችዋን አእምሮ ከቆሻሻ ነገሮች መጠበቅ አልቻለችም።ይልቁንም ይበልጥ የሚያቆሽሹና የሚያበላሹ ነገሮችን አምርታ ያለምንም የኃላፊነት ስሜት ለገበያ ታቀርባለች።ዛሬ ወጣቱንም ሆነ ዓለምን በሚፈለገው መንገድ ከጥፋት የሚታደግ ኃይል ወይም ሥርዓት የለም።ይህ በእጅጉ ያሳስባል።
ይህ በወጣትነት ላይ የሚያተኩር ጽሑፍ በሁለት ተከፍሎ የሚቀርብ ነው።ክፍል አንድ ይኸው ራሱ ሲሆን ክፍል ሁለት በሚቀጥለው እትም ላይ ይቀርባል።ክፍል አንድ የሚያተኩረው በአጠቃላይ ወጣቶችና ወጣትነት ላይ ነው።ክፍል ሁለት በኢትዮጵያ ወጣቶች ውስብስብ ተግዳሮቶችና ፀጋዎች ላይ ነው።
ስለወጣቶችና ወጣትነት በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል።ወጣት ማነው? ከየት መጣ? ወዴት ይሄዳል? መነሻውንና መድረሻውን በትክክል ያውቃል? ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን የጉዞ ውጣ-ውረድ በትክክል ይረዳል? ስለራሱና ስለ ሌሎች ምን ያህል ያውቃል? ስለሚያውቀው ነገር ምን ያህል እርግጠኛ ነው? የሆነውን እንዲሆን ያደረገው ወይም ማንነቱን የቀረጸው ማነው? ወጣትነት በሚኖርበት ጊዜ የሚለካ ብቻ ነው? ወጣት በወጣትነት ዘመኑ ምን መስራትና ማን መሆን አለበት? ማንና ምን ሆኖ፤ እንዴትና በምን ሰርቶ ከተመኘው ይደርሳል? ዓለም ምን እንድታደርግለት ወይም ምን እንድትሆንለት ይፈልጋል? ስላለበት ቤተሰብ፤ ማሕበረሰብ፤ አካባቢና ሀገር ያለው ግንዛቤ ምን ያህል ምክንያታዊ ነው ወይም ምን ያህል ጥልቀት አለው? እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት ያስፈለገው መነሳትና መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው ለማለት እንጂ በዚህ ዝግጅት ምላሽ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ናቸው ለማለት አይደለም።
አመለካከቶች፤ እሴቶች፤ ልምዶችና ዝንባሌዎች በየዕድሜ ደረጃ ሊለዋወጡ ይችላሉ።ለወጣቶች ደምቆ የሚታያቸው ነገር ለአዋቂዎች የሚደበዝዝ ሊሆን ይችላል።አዋቂዎች ዋጋ የሚያሳጡአቸውን ነገሮች ወጣቶች ዋጋ ይሰጡአቸው ይሆናል። አዋቂዎች የሚያናንቁአቸውን ወጣቶች ሊያደንቁአቸው ይችላሉ። አዋቂዎች ወጣቶችን በራሳቸው መስፈርት ይለኩአቸዋል። ወጣቶች አዋቂዎችን በራሳቸው ደረጃ ይገመግሙአቸዋል። አንዱ ሌላውን ባለበት ቦታ መረዳት ስለማይችል ወይም መረዳት ስለማይፈልግ በሁለቱ መካከል ርቀት ይፈጠራል። በሁለቱ ትውልዶች መካከል የሚፈጠረው የአስተሳሰብ ክፍተት ወይም ርቀት አንዱ ሌላውን በአግባቡ እንዳይረዳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የልማት እንቅፋት ይሆናል።አንድ ሰው ሌላውን ሰው፤ አንድ ትውልድ ሌላውን ትውልድ በራሴ መስፈርት መስፈሬ ትክክል ነው ወይ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት።ሁልጊዜ ነገሮችን ከራስ መለኪያ አንጻር መለካት ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡
ወጣትነት በራሱ ማንነት ነው።ማንነቱ የሶስት ጊዜያት ክንውኖች ጠቅላላ ድምር ነው።ውጤቱ ቀደም ሲል የሆነው፤ አሁን በመሆን ያለውና ለወደፊት መሆን የሚፈልገው ነው።ስለዚህ የወጣትነት ማንነት በዛሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትላንትና በነገ ውስጥ ይገኛል።ይህ ማለት ወጣትነት የሚለማ፤ የሚገነባ ወይም የሚታነፅ ማንነት ነው።ያለቀለት ሳይሆን በመሆን ሂደት ውስጥ ያለ ማንነት ነው።የሚታነፀው በራሱና በሌሎች ነው።ሌሎች ሲባል ወላጅን ወይም ቤተሰብን፤ ጎረቤትን፤ ሕብረተሰብን፤ መንግሥትን፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የመሳሰሉትን ለማለት ነው።ይህ ማንነት በእውን ያለው በሆነና መሆን በሚፈልገው፤ በያዘውና ማግኘት በሚመኘው መካከል ነው።የመጀመሪያው ከመድረሻው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ ማንነት ነው።ሁለተኛው ገና የሚደርስበት ወይም ከርቀት የሚታይ ማንነት ነው።ሽግግሩን ለማሳካት ያለውን አቀበትና ቁልቁለት መውጣትና መውረድ፤ መውደቅና መነሳት የግድ ይላል።ወጣትነት እንደ ውበቱና ድምቀቱ፤ እንደ ብሩህ ተስፋውና ትኩስ ጉልበቱ ሁሉ አደጋው የበዛ ነው።እንደ ተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
በሀገራችን እረፍት የሚነሱ ብዙ ችግሮች አሉ።እነዚህን ችግሮች በሕይወታችንና በግንኙነታችን፤ በአኗኗራችንና በአሰራራችን፤ በአስተሳሰባችንና በአነጋገራችን ውስጥ ተንሰራፍተው እናገኛቸዋለን።ወጣቶች በእነዚህ ችግሮች ውስጥ የተፈጠሩ፤ የሚኖሩና የሚሰሩ ናቸው።ሕይወት በችግሮች ስትወረር ለምን ብሎ መጠየቅ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው።እረፍት የሚነሳ ነገር ሲያጋጥም ከመተኛት መንፈራገጥ ይሻላል ብሎ መወሰን ያስፈልጋል።ችግሮቻችንን በምን ዓይን እንያቸው? በምን አእምሮ እንረዳቸው? ለምንድነው ስኬት የሚታጣው? ለምንድነው ብሶትና እሮሮ የሚበዛው? ለምንድነው ባንድ በኩል ሀገርን የሚገነቡ በሌላ በኩል ሀገርን የሚያፈርሱ የሀገር ልጆች የሚፈጠሩት? መፈጠራቸውና መኖራቸው የግድ ነው? የሚገነባው ነገር ዘላቂና መሠረታዊ ፋይዳ አለው ወይ? የሚፈርሰውስ የማያስፈልግ ሆኖ ነው? በማለት ምክንያታዊ መነሳሳት ማድረግ ያስፈልጋል።
ችግሮች እየተወሳሰቡ የሚሄዱት ባንድ በኩል ደረጃ በደረጃ የማንፈታቸው በመሆናቸው በሌላ በኩል አፈጣጠራቸውንና አወጋገዳቸውን ባለማወቃችን ነው።ወጣቶች ትኩስ ጉልበትና አእምሮ አላቸው።ካልተሰራባቸው ግን ትኩስነታቸው ትርጉም ያጣል።መመራመርና መፈተሽ፤ መፈላሰፍና መፍጠር አለባቸው።ያለማወቅ ካልሆነ በቀር ሁሉም ነገር የራሱ በጎና መጥፎ ገጽታ አለው።በውበት ውስጥ አስቀያሚነት፤ በአስቀያሚነት ውስጥ ውበት ሊኖር ይችላል።ሰው መመራመር የሚኖርበት የሚኖርባትን ዓለም በጥልቀት ለማወቅ ነው።የሚመራመር ከሩቅ የሚፈለገው መድኃኒት ከዚሁ ከቅርብ ሊያገኝ ይችላል።አለማወቅ በእኛና በምንፈልገው ነገር መካከል ጥቁር መጋረጃ ይሰራል።
የአንድ ነገርን የዛሬ ምንነት እንጂ ነገ ስለሚሰጠው ዋጋ አናስብም።ሰው ወርቅን በወርቅነት ሳያውቀው ለረጅም ጊዜ ኖሮአል።የሚጠቅም ማዕድን ሆኖ ከመታወቁ በፊት የማይጠቅም የድንጋይ ክምችት ሆኖ ሲታይ ቆይቷል።ብዙ መልካም ነገሮች በራሳችን ውስጥ አሉ።ባለማወቅ ግን ከውጭ እንፈልጋቸዋለን።ከውጭ የምንፈልገውን መልካም ነገር ማግኘት የሚያስችል አቅም በውስጣችን ያለው መልካም ነገር ነው።ሁሉም ሰው አእምሮአዊ፤ መንፈሳዊና አካላዊ አቅሙን በአግባቡ ከተጠቀመ ብዙ ችግር አይፈጠርም፤ ቢፈጠርም በቀላሉ መፍትሔ ያገኛል።በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር መጠቀም ስንችል ከውጭ ያለውን ማግኘት አይከብድም።ከውስጥ ያለውን ሳንጠቀም ከውጭ ማግኘቱ ግን ቀላል አይሆንም።ወጣቶች ይህን እውነት መረዳት አለባቸው፡፡
በመጀመሪያ ራስን ጠንቅቆ ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።ሰው ድንጋይ ወይም ፈረስ፤ ዝንጀሮ ወይም ቀበሮ አለመሆኑን ማወቁ እርግጥ ነው።ይህ ግን በቂ አይደለም።እኔ በሁሉም ውስጥ መሆኔን፤ ሁሉም በሆነ መልክ በእኔ ውስጥ መሆኑን መረዳት ከቻልኩ ራሴን አውቃለሁ ማለት ነው።ወጣች “እናወቃለን” በማለት አእምሮአቸውን መዝጋት የለባቸውም።ቢያውቁም በማወቅ ውስጥ አለማወቅ መኖሩን መዘንጋት ስሕተት ነው።አለማወቅን ያወቀ አእምሮ ብቻ ነው መማር እስከ መቃብር መሆኑን መረዳት የሚችለው።ስለዚህ ሰዎች በተለይ ወጣቶች ምንጊዜም አእምሮአቸውን ለመማርና ለመመራመር ክፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።አእምሮአችሁ የሚያስቡበት፤ የሚማሩበትና የሚመራመሩበት ብቻ ሳይሆን መልካምነትን የሚያንፁበት ነው።አእምሮአቸውን መጠበቅ አለባቸው – የክፋትና የቆሻሻ ነገሮች ማጠራቀሚያ ሊያደርጉት አይገባም።
ወጣቶች አካላችሁን ከጉዳት አእምሮአችሁን ከእኩይ ጥቃት መጠበቅ ነው።በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች በርካቶች ናቸው።በተለያዩ ሱሶች መጠመድ አካልን ለጉዳት ከሚዳርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።ማጨስ፤ የአልኮል መጠጦችን ማዘውተር፤ በአደንዛዥ እፅና በልቅ ወሲብ መጠመድ ለአካላዊ አደጋዎች ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።እነዚህ ከገንዘብና ከተለያዩ ጥቅሞች ጋር በመወሳሰብ በበሽታ መለከፍን፤ አቅመ-ቢስነትን፤ የመንፈስ ስብራትንና ያለጊዜ መቀጨትን ያስከትላሉ።በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጤናማ ጠንካራ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው።አእምሮአቸው በስንፍና በተንኮል ቁጥጥር ሥር እንዳይወድቅ መጠበቅ ግብረገባዊና ሥነ-ምግባራዊ ግዴታቸው ነው።ወጣቶች የሚያስብ ብቻ ሳይሆን የሚጠይቅና የሚያውቅ፤ ያወቀውን አምቆ የሚይዝ ብቻ ሳይሆን አውጥቶ የሚጠቀምበት አእምሮ ሊኖራቸው ይገባል።አስተሳሰባቸው አእምሮን የሚያሰፋ እንጂ የሚያጠብ፤ የማገናዘብ አቅማቸውን የሚያዳብር እንጂ የሚገድብ መሆን የለበትም።
በዚች ዓለም ውስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመኖር ራስን ማጠናከርም ሆነ ማዳከም የሚፈጠረው በአእምሮ አጠቃቀም ጉድለት ነው።ያለውን አቅም በአግባቡ የማይጠቀም ሰው ደካማ ነው ሊባል ይችላል።የሚሆነውንና የሚችለውን ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ደካማ ሆኖ የተፈጠረ ሰው የለም።ወጣቶች ይህን በውል መረዳት አለባቸው።ተስፋ መሰነቅ ለወጣቶች ትልቅ ጉልበት ይሆናል።ጉልበት የሚሆንለት ግን በዕውቀት ሲመራ ነው።አንድ ወጣት ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል።#ምንድነው የምችለው? ምንድነው የማልችለው?$ ብሎ አቅሙን መለካት አለበት።
ተስፋን ስንቁ የሚያደርግና የማያደርግ ሰው አለ።በአእምሮ ተስፋን ያልሰነቀ ሰው አቅም የለውም።ከመጠቃቱ በፊት ራሱ ይወድቃል።ድጋፍ ቢሰጠውም አይቋቋምም።ተስፋን የሰነቀ አእምሮ ያለው ሰው ግን ለድል ይበቃል።ተስፋ ግን ባዶ ሀሳብ መሆን የለበትም።“ጠንካራ ነኝ” በሚል እምነትና “ጥንካሬዬን ለዓለም ማሳየት አለብኝ” በሚል መንፈስ መታገዝ አለበት።ስለዚህ ማንም ደካም ነኝ ማለት አይኖርበትም።ደካማ ነኝ በሚል መንፈስ የራሱን ሕይወትና ደም በስንፍና መበከል የለበትም።ራስን ለመሆን ራስህን ፈልገህ ማግኘት አለብህ።ተስፋ ፍሬ ማፍራት የሚችለው በጥረት ሲታገዝ ነው።
አንድ የወጣቶች በርቱ ድክመት የራስን ዋጋ ማሳነስ ነው።ራስን ለማምጣት በመጀመሪያ ተገቢውን ዋጋ ወይም እሴት ለራስ መስጠት ያስፈልጋል።ሰው ክቡር ፍጡር ነው።ወጣቶች ይህን መረዳት ብቻ ሳይሆን የሚመሩበት እምነት ማድረግ አለባቸው።እንደ ሰብአዊ ፍጡር ክቡር ነኝ ብሎ ማመን ያስፈልጋል።ሰብአዊ ፍጡርነት የተሰጠ ብቻ ሳይሆን ያለማቋረጥ የሚታነፅ ወይም የሚሰራ ነው።በማፍቀርና በመፈቀር፤ በመጥላትና በመጠላት፤ በማክበርና በመከበር፤ በመሆንና ባለመሆን፤ በመስጠትና በመቀበል፤ በማግኘትና በማጣት ውስጥ ሰብአዊ ማንነት የሚሰራው።የወጣት ማንነት በዋናነት በራሱ፤ በከፊል ደግሞ በሌሎች ይሰራል።የሌላው እገዛ እንዳለ ሆኖ ለማንነቱ ግንባታ ዋናው መሐንዲስ ራሱ መሆን አለበት።የጥገኝነት መንፈስን ማስወገድ አለበት።ስብእናውን ማነፅ የሚኖርበት ራሱን ችሎና በእግሩ ቆሞ ነው።
ለራሱ ዋጋ የሚሰጥ ሰው ራሱን ማነጽና ማብቃት ይጠበቅበታል።ራስን ማክበር ማለት ለራስ ዋጋ መስጠት ማለት ነው።የተጋነነ ሳይሆን የሚመጥን ወይም የሚገባ ክብር ነው ለራስ መስጠት የሚገባቸው።ራሱን የሚያከብር ሰው መጥፎ ከመሆንና ከማድረግ ይታቀባል።ለራሳቸው ክብር የማይሰጡ ሰዎች መጥፎ ነገሮችን ከማሰብ፤ ከመናገር፤ ከመሆንና ከመስራት እምብዛም አይታቀቡም።ሰው በእርግጥ ሰው በመሆኑ ብቻ ሊከበር ይገባል።ሀብታም ወይም ደሃ፤ ቆንጆ ወይም አስቀያሚ፤ ባለሥልጣን ወይም ሥልጣን-አልባ ስለሆነ አይደለም።ይህ ብቻ አይደለም።ለራሳችን የመከበር ፍላጎት ካለን ሌሎችን ማክበር አለብን።ለራሱ የሚገባውን ክብር እየሰጠ ለሌላው የሚገባውን የሚነፍግ ግን ራሱን ማክበርና ማስከበር የሚችል አይደለም።ወጣቶች ለስብእናቸውና ለማንነታቸው፤ ባሕርያቸውና ድርጊታቸው፤ ለመብታቸውና ነፃነታቸው፤ ለፍላጎታቸውና ጥቅማቸው ተገቢውን ክብር መስጠት አለብን።ባሕርያቸውና ድርጊታቸው የማያስከብር እንኳ ቢሆን ሰብአዊ ፍጡር ናቸውና መከበር አለባቸው፡፡
ብዙ ወጣቶች ዘንድ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ የነገሮችን ውስብስብ ትስስርና ቁርኝት መረዳት አለመቻል።የብዙ ሰዎች ዓይን ባብዛኛው የሚያየው ነጠላውን እንጂ ጥንዱን አይደለም።አእምሮአቸውም የሚያስበው ስለ አንዱ እንጂ ስለሌላው አይደለም።መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ከዚህ ይለያል።ማንኛውም ነገር የተለያዩ ገጽታዎች አሉት።ባንድ ወጥነት የሚታወቅ ነገር የለም – በሐሳብ የተፈጠረ ካልሆነ በቀር።አንድን ነገር ስናይ በዚያ ነገር ውስጥ ድርብ ድርብርብ ነገሮች መኖራቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል።የሰው ሕይወትና ግንኙነት በብዙ ድርና ማጎች የተሰናሰለ ነው።“ለኛ የሚገባን የግል እንጂ የጋራ ዕድገት ወይም ልማት አይደለም ” የሚሉ ወገኖች አሉ።እነዚህ በልማት ውስጥ መስጠትም ሆነ መቀበል መኖራቸውን ማየት ይሳናቸዋል።በእውን የሚኖሩት ግን በመስጠትና በመቀበል ነው።ፍራንሲስ ባኮን እንዳለው አንዳንዶቻችን ዛፉን እንጂ ደኑን፤ ሌሎቻችን ደግሞ ደኑን እንጂ ዛፉን አናይም።የጋራ በሆነ ነገር ውስጥ የግል፤ የግል በሆነ ነገር ውስጥ የጋራ ጉዳይ መኖሩን መረዳት አለብን።አንድን ነገር በሌላው ውስጥ ማየት የማይችል አእምሮ እውነትን በትክክል መረዳት ይቸገራል።ሕዝብ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሰብአዊ ግለሰብን፤ ሰብአዊ ግለሰብ በሌለበት ቦታ ሕዝብን ማግኘት ያስቸግራል።ወጣትነት የሰው ልጆችንና የዓለምን ውስብስብነት ከተረዱ ሕይወታቸውን ለማቃናት አይቸገሩም።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ጠና ደዎ (ፒኤችዲ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ