በቻይና ከወር በፊት የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ይህ ገዳይ ወረርሽኝ በዓለም ስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ተጋኖ አይነገር እንጂ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ኩነቶች ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ የባሰ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ በርካታ ማሳያዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ ቫይረስ ምክኒያት ቻይናን ጨምሮ በበርካታ አገራት ዓለማቀፋዊ ውድድሮች የተሰረዙ ቢሆንም የዓለም ህዝብ ትኩረት ከአምስት ወር በኋላ በቶኪዮ የሚካሄደው የ2020 ኦሊምፒክ ላይ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ውድድሩን በበላይነት የሚመሩት አካላት ግን ታላቁን የስፖርት መድረክ መሰረዝ ወይም የሚካሄድበትን ጊዜ ማራዘም የማይታሰብ መሆኑን ከሳምንታት በፊት ሲናገሩ ነበር፡፡ በቫይረሱ ስጋት ምክኒያት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ምንም አይነት አደጋ እንዳላንዣበበት አፅኖት ሰጥተው መግለጫ ሲያወጡም ከርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቫይረሱ ስርጭት ከመቀነስ ይልቅ በበርካታ አገራት እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ የኦሊምፒክ አዘጋጆቹ ስጋት ውስጥ እንደገቡ የሚጠቁሙ መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡
የቀድሞው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ዲክ ፖንድ በኮሮና ቫይረስ ስጋት የቶኪዮ ኦሊምፒክ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ እርግጠኛ ሆኖ ለመወሰን ዓለም አቀፍ ኮሚቴው እስከ መጪው ሰኔ ድረስ እንደሚታገስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ አሁንም ድረስ የኮሚቴው አባል የሆኑት የቀድሞ የውሃ ዋና ተወዳዳሪ ፖንድ በቫይረሱ ሳቢያ ብዙ መጥፎ ነገሮች እየተፈጠሩ እንደሚገኙ በማስታወስ ዓለም አቀፍ ኮሚቴው ውድድሩ ሁለት ወር እስኪቀረው ድረስ ስጋት እንደማይኖርበትና አስፈላጊው ነገር ሁሉ መሟላቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ቶኪዮ ውድድሩን እንደምታካሂድ ወይም እንደሚሰረዝ፣ ካልሆነም እንደሚራዘም ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚቻል ፖንድ ገልፀዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ከጃፓናዊቷ የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ተጫዋች ናኦሚ ኦሳካ ጋር በመሆን ‹‹በስሜት አንድ እንሁን›› የሚለውን የውድድሩን መሪ ቃል በተንቀሳቃሽ ምስል ለዓለም ሲያስተዋውቁ ታይተዋል፡፡ በዚህ ወቅት የዓለምን ህዝብ በስሜት አንድ ያደረገው ጉዳይ ግን ከኦሊምፒኩ ይልቅ የኮሮና ቫይረስ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ የቅርብ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ 75 ሺ ሰዎች ተጠቅተዋል፡፡ ከሁለት ሺ በላይ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈም ሲሆን ቫይረሱ በሃምሳ የዓለም አገራት ተሰራጭቷል፡፡ የዚሁ ወረርሽኝ መነሻና ክፉኛ ተጎጂ የሆነችው ቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ‹‹ሰይጣኑ ቫይረስ›› ብለው እንደጠሩት ሁሉ የቫይረሱ ስርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ የዓለም ተመራማሪዎችም ፈውሱን የማግኘት ጥረት ተጨባጭ ተስፋ እንዳላመጣ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡
ይህም የዓለምን ምጣኔ ሀብት በተያዘው 2020 ሩብ ዓመት ብቻ 280 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ እንደሚያደርስ በጥናት ተጠቁሟል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ ከ2009 ወዲህ የመጀመሪያ ይሆናል፡፡ በቫይረሱ ስርጭት ከቻይና ቀጥላ በሁለተኛነት የተቀመጠችው ጃፓን ውስጥ ከሰባት መቶ ያላነሰ ሰው በቫይረሱ መጠቃቱ ተዘግቧል፡፡ የቅርብ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን 3700 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና የኦሊምፒክ ውድድሩ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች ዋነኛ ከሆነው ዮኮሃማ ቤዝ ቦል ስቴድየም ከሦስት ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ ላይ በመገለል እንደተቀመጡ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ጃፓን በቀጣዩ ወር በአርባ ሰባት ግዛቶቿ ለ121 ቀናት የሚዞረውን የኦሊምፒክ ችቦ ለመለኮስ ተዘጋጅታለች፡፡ የኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው መሪ ቶሺሮ ሙቶ የኦሊምፒክ ውድድሩን ለማስተናገድ ምንም ስጋት እንደሌለ ቀደም ብለው ቢፎክሩም አሁን አሁን ስጋት ውስጥ እንደገቡ በግልፅ በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ተናግረዋል፡፡ በግልፅ የቫይረሱ ስጋት ውድድሩን ያስቀረዋል ባይሉም በኦሊምፒኩ የሞቀ ዝግጅት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሊከልስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በቫይረሱ ስጋት የተነሳ ቶኪዮ የኦሊምፒክ ውድድሩን የመሰረዝ አዝማሚያ ባይታይባትም ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ከአትሌቶች በስተቀር ሕዝብ እንዳይሳተፍ አድርጋለች፡፡ ከሁለት ቀናት በፊትም የጃፓን የኦሊምፒክ ሚኒስትሯ ሴኮ ሃሺማቶ በአገሪቱ ፓርላማ በጉዳዩ ዙሪያ በቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ቶኪዮ ውድድሩን በ2020 ለማካሄድ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ውል እንደገባ በማስታወስ በውሉ መሰረት ውድድሩን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የማራዘም እድል እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
የኦሊምፒኩ አዘጋጅ ኮሚቴ ውድድሩን ለማካሄድ የልብ ልብ የተሰማቸው ወቅቱ በጋ እና ከፍተኛ ሙቀት የሚኖርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ልክ እኤአ 2003 ላይ የሳርስ ወረርሽኝ በበጋ ወራት ሊጠፋ እንደሚችል ተስፋ አድርገው መሆኑን መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሳርስ ወረርሽ ለምን በበጋ ወራት እንደሚጠፋ አሁንም ድረስ በህክምናው ዓለም ግልፅ ማስረጃ እንደሌለ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የህክምና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሚካኤል ኦስተርሆልም አንዳንድ የኮሮና ቫይረስ አይነቶች ከክረምት ወራት ይልቅ በበጋ እንደሚስፋፉ በመጠቆም የኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው ባዶ ተስፋ መሆኑን ከታይም መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አረጋግጠዋል፡፡
ጃፓን ለዓመታት የለፋችበት የኦሊምፒክ ዝግጅት ከንቱ ከሚቀርና ቫይረሱ ይዞ ከሚመጣው አደጋ አንዱን መምረጥ ያለባት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ የኦሊምፒክ ውድድሩ ቢሰረዝ ወይም የቦታ ለውጥ ቢደረግበት ጃፓን የሚገጥማትን ኪሳራ ያሰሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ለውድድሩ 25 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚሆን የታሰበ ሲሆን የመሰረዝ ወይም የቦታ ለውጥ የሚደረግበት ከሆነ ቀድሞ ከታሰበው በአራት እጥፍ ሊያስወጣ እንደሚችል ቢቢሲ ሰሞኑን ባስነበበው ዘገባ አትቷል፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ በዘለቀው የዘመናዊው ኦሊምፒክ ታሪክ ታላቁ የስፖርት መድረክ በጦርነት ካልሆነ በስተቀር በሌላ ምክኒያት ተራዝሞ ወይም ተሰርዞ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ኦሊምፒክ የአሁኑን ያህል ከባድ ፈተና ገጥሞት ያውቃል ለማለትም አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ቦጋለ አበበ