ኢትዮጵያ ከ124 ዓመታት በፊት ያካሄደችው የአድዋ ጦርነት ከተፋላሚው ወገን በመነጨ የተዛባ የጥቅም ፍላጎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዘመኑ ወራሪው የጣልያን ጦር በርካታ ኪሎሜትሮችን ተጉዞና ውቅያኖስ አቋርጦ፣ የመጣው ጉልበቱን በመተማመን ኢትዮጵያን በሃይል ለማንበርከክ ነው፡፡ ለግጭቱ መንስኤ የነበረውም የውጫሌ ውል ነው፡፡ ይህም በአገራት መካከል የሚፈጸሙ ውሎች በጥንቃቄ ሊካሄዱ እንደሚገባ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡
ዛሬም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ አደራዳሪነት እየተካሄደ ያለው የሶስትዮሽ ውይይት ጥንቃቄን የሚፈልግና የአድዋ ጦርነት መንስኤ የሚያስታውሰን ድርድር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ እንደ ትላንቱ አይደለም፡፡ በቃላት ጨዋታ ወይም በጥቂት ቡድኖች በተለይም በአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊዎች ግፊት የተሳሳተ ውሳኔ የምታስተላፍበት ወቅት አ ይደለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ከራስ አልፎ ለሌሎች አገራትም የሚተርፍ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላምን ለማምጣት አንድም በሸምጋይነት፣ በሌላም በኩል ሰላምን በማስከበር ስታካሂድ የነበረው እቅስቃሴ ዓለም የሚያውቀው ትልቅ ስራ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ለኖቤል ተሸላሚነት ካበቃቸው ተግባራት ውስጥም አንዱ ይኸው ለሰላም የተደረገ ጥረትና ስኬት ነው፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ ግምጃ ቤት አማካይነት ሲካሄድ የነበረው ሸምጋይነትና በሂደትም መልኩን እየለወጠ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ያለመው ሴራም ተገቢ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ይህንን ድርድር በርጋታና በሰከነ መንፈስ ማየት ይጠበቅባታል፡፡ የውጫሌ ውል አይነት ተንኮል ዳግም እንዳይፈፀም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም በቅርቡ ሊካሄድ ከነበረው ድርድር ላይ ከመሳተፏ በፊት በአገር ቤት ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ለጊዜው ወደስፍራው ሳትጓዝ መቅረቷ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡
ይህ ውሳኔ አንድም ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ ለመመልክትና የሁሉንም አካላት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ጉዳዩን ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አደራዳሪዎቹ አካላትም ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ እንዲመለከቱት እድል የሚሰጥ ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ የወሰደችውን አቋም ተከትሎም የአሜሪካው ግምጃ ቤት አካሄድ ከወዲሁ አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ችግሮች እንዳሉበት እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ ለዚህም በራስዋ በአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት እየቀረቡ ያሉ የተቃውሞ ድምጾች ትልቅ ማሳያ ናቸው። ሰሞኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን እና ኔቫዳን የወከሉት የምክር ቤት አባል ስቴቨን ሆርስፎርድ የግምጃ ቤቱን አካሄድ በግልጽ ተቃውመዋል፡፡
ዴቪድ ሺን እንደገለጹት፤ የአሜሪካ ግምጃ ቤት እየተከተለ ያለው አካሄድ ወገንተኝነት የሚታይበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማሻከር በዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በሌላም በኩል አካሄዱ ኢትዮጵያና ግብጽ ወደ ግጭት እንዲገቡ የሚያነሳሳ ነው፡፡ አካሄዱ የኢትዮጵያን ጥቅም ለግብጽ በገጸ በረከትነት በማቅረብ የራስ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረግ ፖለቲካዊ ሩጫ በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡
የምክር ቤት አባል ስቴቨን ሆርስፎርድ በበኩላቸው ከትላንት በስቲያ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ድርድሩን የሚመሩትን የግምጃ ቤት ሚኒስትር ሙንቺንን በጥያቄዎች ሲያጣድፉ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ሙንቺን የእንደራሴውን ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸው ጊዜዬን እየወሰድክብኝ ነው በሚል ሰበብ ጥለው መሄዳቸው ምን ያህል ለግብጽ ወግነው እየሰሩ መሆኑን ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ 56 ከመቶ የሚሆኑ ዜጎቿ ለኤሌክትሪክ ሃይል ባዳ የሆኑባት፣ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩባት፣ 11 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎቿ ስራ አጥ የሆኑባትና እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት በየዘርፉ የልማት ሩጫ ላይ ያለች አገር ናት፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታም የዚህ የልማት ሩጫው አንዱ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሩጫ እንዳይሳካ ለማድረግ የሚደረጉ ማናቸውም ጥረቶች ከቅኝ ግዛት አካሄዶች የተለዩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
እንዲህ አይነት ተግባራት መላ ኢትዮጵያውያንን የሚያበረታና አንድነታችንን የሚያጠናከር ከመሆኑም ባሻገር ግድቡን በአንድ ልብ ለመጨረስ ብርታት የሚሰጠን ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬም እንደተለመደው ግድባችንን ለመጨረስ የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን እድንቀጥል ከወዲሁ እንትጋ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም