‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በፅኑ የተሳሰረ ነው››  – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የውጭ ግንኙነት እና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል

አዲስ አበባ፡የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በፅኑ የተሳሰረ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገው ጥረትም ሰጥቶ በመቀበል እንዲሁም ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ በመሥራት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ በየጊዜው የወጪ እና የገቢ ንግዷ እያደገ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳም በአንድ ወደብ ብቻ መጠቀም የሚቻልበት ጊዜ አልፏል፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት በላይ ስትጠቀምበት ከነበረው ጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ ሌሎች ወደቦችን መጠቀም የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

ሌሎች ወደቦችን ለማግኘት ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ በሂደት ስምምነቱ ይተገበራል፡፡ በዚህ ስምምነት ደግሞ ሶማሌ ላንድ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአካባቢው ሀገሮችም ተጠቃሚ መሆናቸው አይቀርም ብለዋል፡፡

የባሕር በር ዕድልን ለማስፋት ከሶማሌ ላንድ ጋር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የባሕር በር ካላቸው የአካባቢው ሀገሮች ጋር አብሮ በመሥራት፣ በመገናኘት እና በመጠቃቀም የባሕር በር ሊገኝ የሚችልበት ሁኔታ ላይም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ውስጥም ወደብ የማግኘት መብት እንዳላት የተደነገገ መሆኑና የባሕር በር ማግኘት ሕጋዊ መብቷ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህንን መብቷን ለማረጋገጥ የምትጥረው በሠላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሠላም ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ በብሩንዲ በሩዋንዳ ከፍተኛ ሥራ ስትሠራ የነበረች ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ የኢትዮጵያን ሠላም አስከባሪነት ምዕራባውያኑም የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሶማሊያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያ የምታደርገው የሠላም ማስከበር እንቅስቃሴ ሲደነቅ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ለምሥራቅ አፍሪካ ሠላም መስፈን ኢትዮጵያ ያላት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ አልሸባብን በመዋጋት እና በማዳከም ከፍተኛ ሚና መጫወቷ እንደተመሰከረላት አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሌለችበት የሠላም ማስከበር ሂደት አዋጭ እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ዲና እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሠላም የምትፈልገው እንደራሷ ሠላም ስለምታየው ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደምታምነው፤ የጎረቤት ሀገሮች ሠላም የኢትዮጵያም ሠላም ነው፡፡ እነርሱ ችግር ላይ ከወደቁ ሀገሪቱም ችግር ላይ ትወድቃለች፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ሠላም ከሌለ እና ሀገሪቱ ችግር ላይ ከወደቀች ሶማሊያን ጨምሮ ሌሎች የጎረቤት ሀገሮችም በተመሳሳይ መልኩ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የጋራ ጥቅም በመኖሩ የኢትዮጵያ በቀጣናው የሚኖራት የሠላም ሚና ወደ ፊትም ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You