የአድዋን ድል በተለያዩ መነፅሮች ተመልክቶ አንዳች ማጠቃለያ ላይ መድረስ ከባድ ነው። ሰሞኑን የተከበረውን 124ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል አስመ ልክቶ ከተከናወኑ ደማቅና አስደሳች ክንውኖች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ በተቆፈረ ቁጥር አዳዲስ መረጃዎች እየመጡ መሆናቸው ነው።
እንደተመለከትነው የዘንድሮው በዓል ልዩ ድባብ ነበረው። በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፤ ዜጎች በነቂስ ለመባል ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ወጥተው ታድመዋል (በተለይ አዲስ አበባ)።
ይህ ሁሉ ሲሆን ዋናው ማጀቢያና ማድመቂያዎቹ ደግሞ የኪነጥበብ ሥራዎች መሆናቸው ግልፅ ነው። በዓሉ ዋናውን፤ የአድዋውን ውሎ እንዲመስል የተደረገው ጥረት በእውነቱ የሚደንቅና የሚያስመሰግንም ነው። በተለይ ወጣቱን (ጠጠር ቢነካቸው የሚፈነዱ የሚመሳስሉ የልጃገረዶች እግሮች ሁሉ ባዷቸውን ሲሄዱ ላየ) አለማድነቅ ስለእውነት ለመናገር ታሪካዊ ንፍገት ይሆናል።
በኪነጥበቡ በኩል ለበዓሉ ሲባል ሥራ ላይ ያልዋሉ ሥራዎች አሉ ለማለት አያስደፍርም። ቴአትሩ፣ የስእል አውደ ርእዩ፣ ግጥሙ፣ ሽለላው፣ ቀረርቶው፣ ፉከራው … ሁሉ ለበዓሉ ከፍተኛ መስዋእትነትን ከፍለዋል።
ምንም እንኳን ያኔ “ኪነጥበብ” አንበለው እንጂ አዝማሪዎች ለአፍታም ከውጊያው አልተለዩም። የትም ይሁኑ የትም በሙያቸው ከአርበኞቻችን ጎን ነበሩ። በሙያቸው ተዋግተዋል፤ ስለ ውጊያው በድል መጠናቀቅ አዚመዋል፤ ስለ አርበኛና በጥቅሉም ስለ ጥቁር ጀግንነት አቀንቅነዋል፤ የፋሺስትን እኩይ ተግባር አውግዘዋል፤ አጋልጠዋልም። ለጀግና ፎክረዋል፤ በባንዳ ተሳልቀዋል።
ወደ አድዋ ሲዘመት የነበረው ፕሮቶኮል የዛሬው አይነት እንዳልሆነ ይታወቃል። በነጋሪት ጉሰማ የታጀበ አዋጅ ነው ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሰው። ምኒ ልክም ይህንኑ ነው ያደረጉትና ደብረብርሃን ሲደርሱ 600 ሰው ቀድሞ የጠበቃቸው። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ በየደረሱበት የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ እስከ አድዋ፤ ድሉ ፍፃሜ ድረስ የቀጠለው።
ልክ እንደ አፄ ምኒልክ ሁሉ እቴጌ ጣይቱም በራሳቸው መንገድ “ተከተሉኝ” ብለው ነበርና በዚሁ መልክ በሳቸው አቅጣጫ ያለውም ህዝብ ተከትሏቸው ወደ አድዋ አቅንቷል። ተጣይቱን ከምኒልክ ለየት የሚያደርጋቸው ግን አንድ ነገር አለ። እቴጌይቷን ከተከተሏቸው መካከል 100ዎቹ አዝማሪዎች መሆናቸው ነው። ይህ ነው የጣይቱን ተከታይ ከምኒልክ ተከታይ የሚለየው።
ዛሬ ላይ ሆነን ከመቶ ምናምን ሚሊዮን ህዝብ አንፃር አንድ መቶ ሰውን ካወዳደርነው እጅግ ያንስብናል፤ 100 ሰውን ከዛን ጊዜው ህዝብ ቁጥር ጋር ካስተያየነው ግን እጅጉን ይደንቀናልና ጣይቱ ያገኙት ምላሽ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑንም እንረዳለን።
የአዝማሪዎችን ጉዳይ ካነሳን ከምኒልክ ጋርም እንዲሁ የሚያያዝ ነገር አለ። ከድል (ዕለተ ሰንበት፣ የካቲት 23 1888 ዓ.ም) በኋላ ነው። ከድል በኋላ ወደ አዲስ አበባ በሚደረግ የመልስ ጉዞ። አዝማሪዎችም የትግሉም የድሉም አካል ናቸውና በመልስ ጉዞውም ወቅት አብረው ነበሩ። እናም ወደ መሃል አገር የሚደረገውን ድህረ-ጦርነት እንቅስቃሴ ወይም የድል ማግስት ጉዞ በአስፈላጊው የአዝማሪነት ተግባራችን ካላጀብነው ሞተን እንገኛለን በማለት ለጃንሆይ ጥያቄ ያቀርባሉ። ጃንሆይ ግን አልፈቀዱም። እንዴት ይህን የሚያክል ድል ተገኝቶ ዝም ተብሎ ወደ ህዝብ ይኬዳል? ሲሉም አዝማሪዎች ይጠይቃሉ። “አይ ምንም እንኳን እኛን ሊወጉ የመጡ ጠላቶቻችንም ቢሆኑ ሰው ናቸውና ’ሰው ገደልን’ ብለን መፎከር የለብንም። ይሄን እግዚአብሄር አይወደውምና ለጊዜው ተውት።” በማለት ከለከሏቸው ተብሎ ተከትቧል።
ከድል በኋላ ያለው የአፄ ምኒልክ ታሪክ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሌላም አለ። እሱም የአድዋ ድል በመጀመ ሪያዎቹ ሰባት ዓመታት አለመከበሩ ነው። እጅግ የሚገርም ነው። ምክንያታቸውም ያውና ተመሳሳይ ነው። “ጠላቶቻችንም ቢሆኑና ሊገሉን የመጡ ቢሆኑም ሰዎች ናቸውና የእነሱ ሰዎች እምባ ሳይደርቅ እኛ ድል አገኘን ብለን አናከብርም፤ አንደሰትም።” የሚል ነበር። አድናቂዎቻቸው “የሚገርሙ ሰው ናቸው” የሚሏቸውም አንዱ ምክንያታቸው ይሄው ነው። (ይህን የሰባት ዓመት ጉዳይ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች አኳያ ስንመለከተውና አንድ ሰው ከሞተ እስከ ሰባተኛ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ስናስብ አንዳች የሚነግረን ቁም ነገር መኖሩን ልብ ይሏል።)
ወደ አሁኑ ዘመን የኪነጥበብ ሥራዎች ስንመጣም፤ ሁሉም በደረሰበት ጊዜ ነውና ኃላፊነቱን የሚወጣው፤ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ ስለመሆናቸው አያከራክርም (ሁሉም አላልንም)።
ከዘመናዊ ሙዚቃዎቻችን እንኳን ብንጀምር ከሁሉም ከፍ ብሎ የሚሰማውን፤ እንደ ህዝባዊ መዝሙርም እየተቆጠረ ያለ የሚመስለው የ(ጂጂ) እጅጋየሁ ሽባባውን “አድዋ” እናገኛለን። በነገራችን ላይ የጂጂን አድዋ ዋናውን አግኝቶ የተመለከተ ሰው ከዚህ አሁን እየሰማነው ካለው የሚለይ መሆኑን ይገነዘባል። ምክንያቱ ደግሞ ጂጂ ሙዚቃውን በመድረክ ስትጫወተው አስፈላጊውን ማብራሪያና የጥቁር ህዝቦችን ድል አድራጊነት በሚገባ ከገለፀች (በእንግሊዝኛ) በኋላ ነው ወደ ማዜሙ የምትገባው። (ምናልባት እሱ እንዳለ የማይቀርበው ለዲፕሎማሲያዊ ጣጣዎች አልመች ስለሚል ሊሆን ይችል ይሆናል ብለን እንለፈው።)
ከአሁኑ ትውልድም አድዋና ድሉን ከነ ባለድሉ አሳምሮ የገለፀው ቴዲ አፍሮ ሲሆን ቀዳሚ ተጠቃሹም “ጥቁር ሰው” ሥራው ነው። ከአፍሪካም ቦብ ማርሌይን ጨምሮ በርካቶች ድህረ አድዋ ያፈራቸው መሆናቸው ይታወቃል።
ተሾመ አሰግድም «…መቅደላ አፋፉ ላይ ጎበዝ ወንድ ሆነበት/በመተማም ጎራ ጀግኖች አንድ ሆኑበት/እንዳይሞት ሆነ እንጂ ስሙን እንዳይቀብሩት/የመቅደላን መንደር የዶጋሊን ሜዳ/የማይጨው ዓድዋን የመተማን ሜዳ/ተዳኘበት እንጂ መች ዋኘበት ባዳ/አፄ ቴዎድሮስ አባ ታጠቅ ካሳ/እምዬ ምኒልክ ጥራኝ የእኔ አንበሳ/ በደም ታዋጋለህ በአካል ባትነሳ …” ሲል ያንቆረቆረው ከዚሁ ከአርበኛ አዝማሪዎች ጎራ የሚያስመድበው ነው።
ጥላሁን ገሰሰ፣ ራሄል ዮሐንስ፣ መሀሙድ አህመድ፣ እሱባለው፣ አብነት አጎናፍር ቆጥረን የማንጨርሳቸው ወጣትና አንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች ስለ አድዋና ድሉ፤ አርበኞቻችንና የከፈሉት መስዋእትነት፤ ስለአሁኑ ትውልድ ግዴታና ኃላፊነት፤ ስለአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ጀግንነት ወዘተ አዚመዋል። በፊልሙ (ባይበዛም) ፣በሥነ ጽሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በቴአትሩ፣ በታሪክና ምርምር ሥራዎች ወዘተ ብዙ ብዙ ተብሏል፤ ተሰርቷልም፤ አባይን በማንኪያ ቢሆንም።
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።” ተብሏል። (ከድል በኋላም “በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ/ተፈጠመ ጣሊያን ካበሻ ላይደርስ” እንደዛው።)
የፀጋዬ «ዋ! … ያቺ ዓድዋ»ም የተዘለለ እንዳይ መስለን ጠቅሰን፤ እሱንም ዘክረን እንለፍ። የ”ጉዞ አድዋ” አባላትንም እንደዛው።
ወደ ስነቃልም ስንሄድ ከኪነጥበቡ በገዘፈና ጠለቀ ደረጃ ስለአድዋና ድሉ ተነግሮ ነው የምናገኘው።
ለምሳሌ «እስኪ ለጣሊያኖች መድኃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው።» የሚለው ተዘወትሮ ተጠቃሽ ነው።
“ያ ጎራው ገበየሁ ምን አሉ ምን አሉ፣
ያ ትንታግ ታፈሰ ምን አሉ ምን አሉ፣
እነ ደጃች ጫጫ ምን አሉ ምን አሉ፣
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ፣
አገሩን አቅንተው አደዋ ላይ ቀሩ።” የሚል እንጉርጉሮም ታሪካዊ ቦታው ከፍ ያለ ነው።
ድል ለአባትና እናት አርበኞቻችን!!!!
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ግርማ መንግሥቴ