ዲሞክራሲ እንደማንኛውም ፅንሰ ሀሳብ አንድ እራሱን የቻለ ክስተት ነው። አያት ቅድመ አያቶቻችን ባላቸው የማመዛዘን ብቃትና ማስተዋል አማካኝነት ለዛሬ ህልውናው የበቃ አንድ የመንግስት ቅርፅ ነው። ከ1874 ወዲህ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለለትና ግሪክን ጠቅሶ የዲሞክራሲን ከ-እስከ አይን ከሰበከት እያገላበጠ ያሳየው የጆን ኬን “The Life and Death of Democracy” (2009) መጽሐፍም የሚለው ይህንኑ ነው።
ዲሞክራሲ እንደማንኛውም አይነት የመንግስት አስተዳደር ፍልስፍናም ሆነ ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ የራሱ የእድሜም ይሁን የአገልግሎት የጊዜ ገደብ የለውም ማለት አይደለም፤ አለው። ከሌላው ጋር የሚለየው መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ከተቻለ በተሻለ ሁኔታ ዘላቂነት ያለው መሆኑ ነው። ያ ሳይሆን ቀርቶ ዲሞክራሲ መሰረታዊ መርሆቹን ከሳተ፣ የህዝብ፣ በህዝብ፣ ለህዝብ አስተዳደር መሆኑ ቀርቶ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ብዛት፣ የእርስ በርስ ፍጥጫና በጠላትነት የመተያየት ሁኔታ ሰፍኖ ፍርሀት ጥላውን ሲያጠላ፤ ስርአቱ ወደ አገዛዝና የመጨቆኛ መሳሪያነት (Necropolitics) ከተቀየረ ዲሞክራሲ እራሱን ማጥፋቱ (Suicidal democracy) አይቀርም፤ ምሁራኑም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። ለዚህ ደግሞ የት ይደርሳል የተባለውን የምእራብ አፍሪካዊቷን ቤኒን ተሞክሮ የሚገልፁ አሉ። ቤኒን በአፍሪካ ሞዴል ተደርጋ የተወሰደችውን ያህል ባለፈው (ኤፕሪል 28 2019) በእንከን የተሞላው ምርጫዋ ምክንያት ዲሞክራሲዋ እራሱ ወደሚያጠፋው ምድብ እየወረደ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው።
የካሜሩኑ ፈላስፋና የፖለቲካ ንድፈሀሳብ ቀማሪ አቺሌ ምቤምቤ በ”On the Postcolony” ስብስብ ስራው “Necropolitics”ን በጥልቀት በመፈተሽና በማብራራት የመጀመሪያው መሆኑ የተነገረለት ሲሆን ፅንሰ-ሀሳቡ አምባገነን መንግስታት ዜጎችን ለመቆጣጠርና ረግጦ ለመግዛት የሚጠቀሙበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስልጣን (for the use of social and political power to control people’s lives) መሆኑንም ይናገራል። ይህ አይነቱ አምባገነናዊ ስርአት ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ ዲሞክራሲ ራሱን ለማጥፋት ገፊ ምክንያት ተፈጠረለት ማለት ነው። “The Death of Democracy: Hitler’s Rise to Power and the Downfall of the Weimar Republic”ን ማንበብ ለተጨማሪ ግንዛቤ ያግዛል።
በጉዳዩ ላይ ጠጠር ያለ ሀሳባቸውን በቀዳሚነት የሰነዘሩት ሁለተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን አዳምስ ሲሆኑ እንደ እሳቸው አስተያየት ዲሞክራሲ እንደ ዘውዳዊና አምባገነናዊ የአገዛዝ ስርአቶች እድሜው ረዥም ሆኖ አያውቅም፤ ሊሆንም አይችልም። እድሜው ያልቃል። የሱ እድሜ ማለቅ ሳይሆን አሳሳቢው ጉዳይ ሲያልቅ የከፋ ደም አፋሳሽ ሆኖ ማለፉ ነው። ከዛ በፍጥነት ይባክናል፣ ተሟጦ ያልቃል፣ በመጨረሻም እራሱን ይገድላል። እስከ ዛሬም እራሱን በራሱ የማያጠፋ ዲሞክራሲ በፍፁም ኖሮ አያውቅም (Democracy has never been and never can be so durable as aristocracy or monarchy; but while it lasts, it is more bloody than either. Remember, democracy never lasts long. It soon wastes, exhausts, and murders itself. There never was a democracy yet that did not commit suicide.)።
ዲሞክራሲ በተለይ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጥልቅ ሀሳብ መሆኑን የሚያሰምሩበት በርካቶች ሲሆኑ በትራምፕ ምርጫ ወቅት ሀሳባቸውን “Will U.S. democracy commit suicide?” በሚል ርእስ ለንባብ ያበቁት ፍሪዳ ጊስትስ አንዷ ናቸው። እንደ እሳቸው (የአሁን ወቅት አቋማቸውም ነው) ከሆነ በትራምፕ መመረጥ ምክንያት ነባሩ የአሜሪካ ዲሞክራሲ ራሱን አጥፍቷል ባይ ናቸው፤ በሌላ መልክ እንደገና ካልተፈጠረ በስተቀር። ያ ደግሞ ለአሜሪካ አይጠቅማትም።
ይህ እንዳይሆን፤ ዲሞክራሲም እራሱን በራሱ ከማጥፋት/መግደል እንዲድን ማድረግ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሲሆን እንደተመራማሪዎች ምክረ ሀሳብ ከሆነ መልሱ “አዎ ይቻላል” ነው። ሮበርት ኤች ሊ እንደሚሉት ዴሞክራሲን ከዚህ አይነቱ ራስን ማጥፋት አደጋ መታደግ ይቻላል። ከሚቻልባቸው መንገዶችም አንዱ የዲሞክራሲን መሰረታዊያን በሚገባ ማወቅ፣ ችግሮቹን ለይቶ መረዳትና በአግባቡ መፍታት እና የመሳሰሉትን ስራ ላይ ማዋል ነው። በተለይ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያሉት ሁኔታዎችና አሰራሮች ልዩ ጥንቃቄን የሚሹ ከመሆናቸው አኳያ በአግባቡ ሊታሰብባቸው ይገባል ባይ ናቸው።
በ”Suicidal democracy” ስር እንደተገለፀው ካርል ማርክስ “ዲሞክራሲ ገና በምርጫ ሳጥን ውስጥ እያለ ሊዘረፍ እና በቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል፤ ይህም የሚሆነው ገና ለገና ’ኮሚኒዝም በማርክሲስት የመደብ ትግል አማካኝነት ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ጦርነት ሊያሸንፍ ይችላል’ ከሚል እምነት በመነሳት ነው” (a Democracy can be corrupted and conquered at the ballot box, believing that Communism could “win the battle of democracy” through Marxist class struggle.) የሚል እምነትና ስጋት ነበረው፤ በአስተምህሮቱም አካቶታል። ይህ ማለት ኮሚኒዝም የብዙሀን ተቀባይነት ስላለውና አላማውም የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በመሆኑ ሊመረጥና ሊያሸንፍ ይችላል ከሚል ስጋት በመነሳት ገና ከወዲሁ ምርጫው በሂደት ላይ እያለ ዲሞክራሲን የማጥቃት ተግባር ነው። ምናልባትም እኮ ይህ ገና በምርጫ ሳጥን ውስጥ ያለውን ዲሞክራሲ የሚያመክነው አካል አሸናፊው እሱ ሆኖ ሊሆን መቻሉ ነው።
ሌላውና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ፍተሻን ያደረጉትና በ2018 “How Democracies Die” በሚል ርእስ መጽሐፍ ያሳተሙት የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ሳይንቲስቶቹ ስቴቨን ሌቪትስኪ እና ዳንኤል ዚብላት እንደሚሉት ለዲሞክራሲ ህልፈተ ህይወት ዋነኛው ምክንያት በዲሞክራሲ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ ኖረው ስልጣን እጃቸው ከገባች በኋላ ስላጣናቸው ለማቆየት ሲሉ ሀይል መጠቀምና ዜጎችን ማፈን ሲጀምሩ ነው። ያኔ ዲሞክራሲ ጉዞዋን ወደ መቃብር አፋፋ ታደርጋለች ነው የሚሉት።
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ጄምስ እንደሚሉት ከሆነ “ዲሞክራሲ ሀሰብን ከመግለፅ አንፃር ብዙም አስጊ አይደለም፣ ሰፊ እድልን ይሰጣል፣ ራስ ወዳድም አይደለም፣ ስሜታዊነት የለበትም፣ ለሁሉም እድል ይሰጣል፣ እንደ ከበርቴአዊም ሆነ ልኡላዊ ስርአታት ገብጋባ አይደለም …” ብሎ በማሰብ በዲሞክራሲ መቀለድና መዘናጋት የዋህነት ነው። በመሆኑም አለመዘናጋትና ለእነዚህ አይነቶቹ ገራገር አመለካከቶች ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ የዳበረ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት ፍቱን መድሀኒቶች ናቸው።
ባጠቃላይ በተለይ በታዳጊ አገራት ይህ ችግር በከፍተኛ ደረጃ እያስፈራ በመምጣት ላይ መሆኑ በብዙዎች እየተተነበየ ሲሆን የዛኑ ያህልም አስፈላጊው ጥንቃቄ ከተደረገ ከችግሩ ነፃ መሆንና የዳበረ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት እደሚቻል ይገለፃል።
በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታም ይህንን ጉዳይ በአትኩሮት እንድናጤነው የሚያስገነዝብ እውነታ ይዟል። በተለይ ለውጡን ተከትሎ የሰፋው የዴሞክራሲ ምህዳር በአንድ በኩል ለእድገታችንንና ለአንድነታችን ጠቃሚ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን በዚህ ምህዳር በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር በርካታ ውስንነቶች ይስተዋላሉ። ስለዚህ ዴሞክራሲ ሰጥቶ የመቀበል እንጂ “ሁሉንም ወደአፍ” ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም አቅቶን አንዴ ከእጃችን ካመለጠ ግን የሚመጣውን መሸከም ሊከብድ ይችላል። ይህም አለ ለማለት ያህል ይህን ካልን የሰማነውን በልቦናችን ያሳድር ዘንድ በመመኘት ጽሑፋችንን እናጠናቅቃለን። መልካም የምርጫ ዘመን!!!
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ግርማ መንግሥቴ