አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስገነባቸው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንግ) በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ አለመሆናቸው ተገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ በሦስት ቦታዎች የሕንፃና የመሬት ላይ ቋሚ ፓርኪንጎችን ቢያስገነባም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንዱ ብቻ ነው።
በትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት የፓርኪንግ ማስፋፊያና ፈቃድ አገልግሎት ቡድን መሪ ወይዘሪት መአርነት ገብረጻድቅ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት መርካቶ አነዋር መስኪድ አካባቢ የተሠራው የሕንፃ ላይ መኪና ማቆሚያ መብራትና ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በመኖራቸውና የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያውም ከሳምንት በፊት ወደሥራ የገባ ቢሆንም መንገዱ ስላልተስተካከለ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም። እነዚህ ማቆሚያዎች በአንድ ጊዜ 185 ተሽከር ካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በመሬት ላይ ማቋሚያው ብቻ ጥቂት ተሽከርካሪዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ በወሎ ሰፈር አካባቢ በመሬት ላይ የተዘጋጀውና 50 ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግደው ማቆሚያም ከዋናው መንገድ ገባ ያለ በመሆኑና ምቹ መንገድ ባለመኖሩ በተገቢው መንገድ እየሠራ አይደለም። እስከአሁን ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀውና በታቀደው መሰረት እየሠራ ያለው በመገናኛ ዘፍመሽ አካባቢ ያለው 150 ተሽከርካሪዎች የሚይዘው የሕንፃና የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያ ሲሆን፤ ከዚህም በየቀኑ በአማካይ ስድስት ሺ ብር ገቢ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በከተማዋ በጊዜያዊነት በመሬት ላይ የተዘጋጁት አምስት ማቆሚያዎች 780 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችሉ ሲሆን፤ ሁሉም ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ160 በላይ ለሚሆኑ በማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚከፈቱም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የመሰረተ ልማት የሥራ ክፍል ተወካይ አቶ ትንሳኤ ወልደገብርኤል በበኩላቸው በከተማዋ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታ በሦስት ክፍል እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
አቶ ትንሳኤ እንደሚያብራሩት እስከአሁን 86 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በመመደብ ወደ ሥራ ከገቡት ጋር የስድስት ቋሚ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል። ሙሉ ለሙሉ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ብቻ የሚያገለግልና አንድ ሺ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ ሕንፃ ሾላ ገበያ አካባቢ በሰባት ሺ ካሬ ሜትር ላይ በ 530 ሚሊየን ብር ግንባታው መጀመሩን ጠቅሰዋል። በቅርቡም ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ በ10 ሺ ካሬ ሜትር ላይ አንድ ሺ ሰባ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል የመሬት ውስጥ ማቆሚያ ለማሠራት ጨረታ ተጠናቆ ወደ ግንባታ እየተገባ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 548 ጊዜያዊና 381 ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠሩም ተናግረዋል።
«በከተማዋ ያለው የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታ ችግር ከቀን ወደ ቀን አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል»ያሉት አቶ ትንሳኤ በመሆኑም በመንግሥት በጀትና ሥራ ብቻ ችግሩን መፈታት እንደማይቻል ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተጠና ጥናት መንግሥት ብቻውን ችግሩን መቅረፍ ስለማይችል አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው የግል ባለሀብቶች መግባት እንደሚኖርባቸውም አመላክቷል። በዚህም መሰረት ባለሀብቶች ምን ዓይነት ድጋፍ ሊደርግላቸው እንደሚገባ ለማወቅ በዘርፉ መሳተፍ ከሚፈልጉት ባለ ሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጎ ግብአት በመውሰድና መመሪያ በማዘጋጀት ለከተማዋ አስተዳደር ካቢኔ መቅረቡን ተናግረዋል። መመሪያው በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ትንሳኤ ይህም ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ በማስቻል ችግሩን ለመቅረፍ የሚረዳ ይሆናል።
በተጨማሪም ለመኪና ማቆሚያ ታስበው በየሕንፃው የተሠሩት ቦታዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች መዋላቸው አንዱ የችግሩ ምክንያት ነው። በመሆኑም ከከተማዋ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን ለታሰቡለት ዓላማ እንዲውሉ የማድረግ የቁጥጥር ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ